Wednesday, May 22nd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ተኩስ አቁም በሊቢያ እውን ይሆናል?

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

ዓርብ እለት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዦን ፒንግ በሊቢያ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ጠርተዋል፡፡

ተኩስ አቁሙ እንዲደረግ የሚፈለገው በጋዳፊ መንግሥትና በአማፅያን መካከል ቢሆንም፣ የአማፅያኑ ተወካይ በኮንፈረንሱ ላይ ሳይገኙ መቅረታቸውን የአሜሪካ ድምፅ ዘግቧል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ባንኪሙን የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ሁሉም አባላት ተወክለው ነበር፡፡ በሰሜን አፍሪካ የሊቢያ ጎረቤቶችና በሊቢያ ምንም ዓይነት በረራ እንዳይደረግ ስምምነት ላይ የተደረሰበትን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰኑ አገሮችም በኮንፈረንሱ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ እነዚህ ሁሉ አካላት ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል የሚያሰጋው የሊቢያ ግጭት ላይ ለመወያየትና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ለውይይት ቢገኙም፣ የሊቢያ አማፅያን በውይይቱ ላይ አለመሳተፍ ትልቅ ኪሳራ ሆኖ ታይቷል፡፡ ማንነታቸው እንዲታወቅ ያልፈለጉ አንድ የአፍሪካ ዲፕሎማት የአማፅያኑ መሪ በውይይቱ ላይ ለመሳተፍ የጋዳፊን ሥልጣን መልቀቅ እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል፡፡

ከተወሰኑ ቀናት በፊት በአዲስ አበባ በተደረገው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በሊቢያ የተከሰተውን ቀውስ በመፍታት ረገድ ኅብረቱ ቀዳሚ ሚና ሊኖረው እንደሚያስፈልግ ተጠቁሞ ነበር፡፡

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ልዩነቶቹን አስታርቆ በሊቢያ የተቀጣጠለውን እሳት ለማጥፋትና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በአንድ ላይ እንዲሠራ ጥሪ በማቅረብ፣ ለሚፈለገው ውጤት የተኩስ አቁም የመጀመሪያው ዕርምጃ መሆን እንዳለበት ፒንግ ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የሊቢያን ቀውስ ለማረጋጋት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የተኩስ አቁም የመጀመሪያውና ወሳኙ ዕርምጃ መሆን እንደሚገባውም አመልክተዋል፡፡

የተኩስ አቁሙ ዕርዳታ የሚፈልጉትን ሊረዱ ለሚችሉ የዕርዳታ ድርጅቶች፣ የውጭ አገር ዜጎችን ከአደጋ ለመጠበቅ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚኖረውን ጠቀሜታ በማጉላት መሠረታዊውን የአገሪቱ ቀውስ መንስዔ ለማግኘትም እንደሚጠቅም ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲልም የአፍሪካ ኅብረት አምስት የአፍሪካ አገሮች መሪዎች የያዘ ቡድን በጋዳፊና በአማፅያን መካከል ያለውን አለመግባባት በሽምግልና እንዲፈታ፣ ቡድኑም የሊቢያ መዲና ትሪፖሊን እንዲሁም ቤንጋዚን እንዲጎበኝ ውሳኔ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን በሊቢያ ምንም ዓይነት በረራ እንዳይደረግ በተመድ በመወሰኑ ነገሩ ከንቱ ሆኗል፡፡ ቡድኑ አሁንም ለሥራ ዝግጁ ሲሆን፣ የአፍሪካ ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ጋዳፊን ለድርድር በማመቻቸት ረገድ ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል፡፡

ባለፈው ሐሙስ የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን በሊቢያ ያለው ሁኔታ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚቻልበትን ሁኔታ የሚያመላክት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህም የንፁኃን ዜጎች ደኀንነት አደጋ ላይ መውደቁን የሰብዓዊ መብትና የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎች ጥሰትም እንዳይካሔድ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ባን ኪሙን ባለፈው ሳምንት መጀመርያ ላይ ግብፅንና ቱኒዝያን የጎበኙ ሲሆን፣ በመቶ ሺሕዎች የሚሆኑ ሊቢያውያን ወደ እነዚህ አገሮች መሰደዳቸው በሊቢያ ያለው ሁኔታ ምን ያህል ከባድ መሆኑን እንደሚያሳይ ለፀጥታው ምክር ቤት አባላት ግልጽ አድርገዋል፡፡ የሊቢያ ባለሥልጣናት የተኩስ አቁም ማድረጋቸውን በተደጋጋሚ ቢገልጹም፣ ዋና ጸሐፊው የሊቢያ መንግሥት እያለ እንዳለው የተኩስ አቁም ማድረጉን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ማስረጃ አለመኖሩንም ገልጸዋል፡፡ ‹‹በተቃራኒው እንደ አጅዳቢያ፣ ሚስራታህና ዚታን በመሳሰሉ ከተሞች ከባድ የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡