በዓለም ላይ ብዙ ችግር እየተከሠተ ነው፡፡ የተፈጥሮ ችግርም እንደ መሬት መንቀጥቀጥና ሱናሚ፣ የሰው ሠራሽ ችግርም እንደ የኢኮኖሚ ቀውስና የኒኩሌር ጣጣ፡፡
ሆኖም ግን ሁሉም አገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በጋራ ቢሠሩና ለመፍትሔው ቢረባረቡ የሚፈታና በቀላል ጉዳት ልንወጣው የምንችል እንጂ ህልውናችንን የሚያጠፋ አይሆንም፡፡
በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ዓረብ አገሮች እየታየ ያለው ችግርም ዓለምም፣ የዓረብ አገሮችም፣ አፍሪካም በጋራ ለመፍታት ከቆረጡና ከተንቀሳቀሱ በቀላሉ የሚፈታ ነው፡፡ መፍትሔው ግልጽና ግልጽ ነውና፡፡ ዴሞክራሲን ማስፈንና የኢኮኖሚ ችግርን መፍታት ነውና፡፡
በአገራችን በኢትዮጵያም በአጠቃላይ የዓለም፣ እንዲሁም በዓረብ አገሮች ሁኔታ ጫና እየተፈጠረ ነው፡፡ ያለው ችግር ግን በእነሱ ጫና ምክንያት ብቻ ሳይሆን ራሳችን በራሳችን ላይ እየፈጠርነው ያለ ችግርም አለ፡፡
ተደማምጠንና ተግባብተን በቀላሉ የምንፈታውን ችግር፣ እየተገታተርንና እየተፋጠጥን ችግሩንም እያባባስነው እንገኛለን፡፡
በመሬት አወሳሰድ ላይ የነበረው ችግር ከመጀመርያውም መንግሥትና ባለሀብቶች ተግባብተው ሊፈቱት ይችሉ ነበር፡፡ መፋጠጡና መገታተሩ ስለተመረጠ ግን ወደ አላስፈላጊ ደረጃ ደርሶ ትዝብትና ድንጋጤን አስከተለ፤ ተባባሰ፤ ተጯጯኸ፡፡ በኋላም መንገዱ የመግባባት መንገድ መሆን እንዳለበት ተመረጠ፡፡ ትክክል ነው፡፡ የመጀመርያው የመገታተር መንገድ ግን ችግሩን አባባሰው፡፡
በዋጋ ተመን ዙርያም መጀመርያውኑ በቀላሉ በመግባባት ይፈቱ የነበሩ ችግሮች በመገታተር እየተባባሱ ሲመጡ ታይተዋል፡፡ ከመጀመርያው ምክክሩ ስላልነበረም ተመኑን ደጋግሞ እስከመቀያየር አድርሷል፡፡ አላስፈላጊ መጠራጠርና መራራቅም አስከትሏል፡፡ አሁን ደግሞ ዘይት በመንግሥት ስለሚሸጥ አስረክቡን ሲባል ‹‹እንዴት ነው ነገሩ?›› አስብሏል፡፡
በታላላቅ ፕሮጀክቶች እንዲጠመድ የምንፈልገው መንግሥት፣ ስለዘይት ግዢና ሽያጭ እያሰላ ሊውል ነው እንዴ? የማይል የለም፡፡ የመንግሥት ኃይልና ጉልበት ስለ ባቡር መንገድ ዝርጋታና ስለ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ስኬታማነት እንዲከታተልና እንዲያተኩር ይመረጣልና፡፡ ብንግባባ ኖሮ፣ ይፈታ የነበረው የዘይቱም ሆነ የስኳሩ ሁኔታ፣ እየተገታተርን እንዳይባባስ እያስፈራን ነው፡፡
ብርሃንና ሰላም፣ በግል ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ እስከ ሃምሳ በመቶ ድረስ ዋጋ እጨምራለሁ ብሎ ሲገልጽ፣ የጋዜጣና የመጽሔት አዘጋጆች ነገሩን ወደ አላስፈላጊ ትርጉምና ደረጃ ከማድረስ ይልቅ፣ በቀላሉ ተግባብቶ መፍታት ይቻላል ብለው በማመን በጋራ ተሰባስበውና አስተባባሪ አካል ፈጥረው ተወያይተውበታል፡፡ ሁሉም በፊርማና በማሕተም በተረጋገጠ ሰነድ፣ ለብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ደብዳቤ ጽፈዋል፡፡ ያልሆነ ውሳኔ ከመወሰናችን በፊት የጭማሪው ፍትሐዊነት ለማጥናትና አቋም ለመውሰድ አስፈላጊውን መረጃ ስጡንና እሱን መርምረን አቋማችንን እስክንገልጽላችሁ ድረስ ጭማሪውን አቆዩልን ብለውም ጠይቀው ነበር፡፡ ለሦስት ወራት አራዝሙልን ብለውም ነበር፡፡
የመጽሔትና ጋዜጦችን ጥያቄ በተገቢ መንፈስና መንገድ ተገንዝበው ቀን ማራዘም፣ አስፈላጊ ካልሆነም በተገቢ የደብዳቤ ምላሽ አናራዝምም ብለው መልስ ከመስጠት ይልቅ፣ ጨምረናል ጨምረናል፤ ጭማሪውን አናቆይም፤ አናራዝምም ብሎ ደንበኞችን አጣጥሎ መመለስ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ፖለቲካው ይቆይና በቢዝነስ አንፃር ሲታይም የደንበኛ አያያዝ እንዲህ መሆን አልነበረበትም፡፡
ይህም በቀላሉ ተግባብቶ የሚፈታን ችግር ተገታትሮ ማባባስን ያሳያል፡፡
በኪራይ ቤቶች ዙርያ እጅግ አሳዛኝና አስተዛዛቢ ነገሮች በስፋትና በጥልቀት እየተስተዋሉ ነው፡፡ ከሕዝብ ጋር ተግባብቶና ተረዳድቶ በቀላሉ የሚፈታውን ችግር ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ በኃይል ማስወገድና ማባረር ችግሩን በእጅጉ እያባባሰው ነው፡፡ ያውም፣ በተለይም አንዱን አላግባብ ውጣ ብሎ ማባረር፣ ሌላውን ተቀመጥ ችግር የለም እያሉ ማንቀባረር ሲታይና አንዱን ግለሰብ እያባረሩ፣ ለሌላው ግን ተጨማሪ ቤት ለምን አትወስድም እያሉ መልፈስፈሱ፣ በእጅጉ ሕዝብና መንግሥትን እያራራቀ ያለ ሁኔታ ሆኗል፡፡
ሕዝብ ችግር አለብኝና አቤት ልበል ሲል፣ ሕዝብ ለበላይ አካል ለመናገር ቀጠሮ ይያዝልኝ ሲል፣ ሕዝብ አቤት የሚባለው የት ነው? እያለ ሲጮህና ሲያለቅስ፣ ናና እኔ ላዳምጥህ እያሉ ከማስታገስና አዳምጦ ይሁንም አይሁንም ብሎ ከማለት ይልቅ፣ ከመጀመርያውም አላዳምጥም፤ ጥሪ አልቀበልም በማለት በቀላሉ ሊፈታ የሚችለውን ችግር በመገታተር እያባባሰው ይገኛል፡፡
ሁሉንም ችግር ልንፈታው አንችልም፡፡ ብንተባበርም በእኛ አቅም በኢትዮጵያ ደረጃ ብቻ ልንፈታው የማንችለው ችግር ይኖራል፡፡ ስለሆነም፣ መንግሥት ለምን ሁሉንም ችግር አልፈታም ተብሎ አይወቀስም፡፡
መንግሥት ሊወቀስ የሚችለው፣ በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን፣ በማዳመጥና በመግባባት ከመፍታት ይልቅ፣ አላዳምጥም፣ አልግባባም በማለት ብቻ ችግሩ እንዲባባስ ሲያደርግ ነው፡፡ ባለሀብቱም ቢሆን በቀላሉ ሊያርመውና ሊያስተካክለው የሚችለውን ችግር በመገታተር፣ ለመፍታት ዝግጁ ሳይሆን ሲቀር ነው፡፡
ተወቃሹ መንግሥት ብቻ ባይሆንም በኃላፊነት ላይ ያለ አካል የወቀሳን የላቀ ድርሻ እንዲቀበል ማድረግም የተለመደ ነው፡፡ ሕግና አሠራርን የማስተካከል ሥልጣን አለውና፡፡
ስለሆነም፣ ያለፉትን ለማስተካከል ሌሎች ችግሮች ሲከሠቱም ለመፍታት መንግሥት ያዳምጥ፡፡ ይወያይ፤ ይመካከር፤ በሩን ክፍት ያድርግ፡፡ አቤት ብትልም መንግሥት ችግርህን አይፈታም ብሎ ሕዝብ ቅር ከሚለው ይልቅ፣ መንግሥት እያዳመጠ ውሳኔ ቢሰጥ ይመረጣል፡፡
ጉዟችን ችግርን ሁሉ የመፍታት እንጂ፤ ችግርን የማባባስ መሆን የለበትም፡፡
ተግባብተን በቀላሉ የምንፈታውን ችግር ተገታትረን አናባብሰው!!


