Sunday, May 19th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የለማጅ ነገር

E-mail Print PDF
User Rating: / 3
PoorBest 

በሥራም ሆነ በትምህርት ምክንያት በቀን ቢያንስ አንድ ጊዜ ታክሲ ውስጥ ገባ ብሎ መውረድ አይቀርም፡፡ ይህ ዓረፍተ ነገር የሚመለከተው መኪና የሌላቸውን ብቻ ነው፡፡ ታዲያ በታክሲ ሲሄዱ አፌ ቁርጥ ይበልላችሁ የሚባሉ፣ ወይም ደግሞ አፋችሁ ይቆረጥ መባል የሚገባቸው ወያላና ሾፌር ሊያጋጥሙን ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ ሥርዓተ አልባ ወያላዎች የተማረሩ ሰዎች፣ ‹‹እግዜር ይይላችሁ›› ብለው ተራግመው ሲወርዱ፤ ሌሎች ደግሞ ለመብቴ መንግሥትንም ሆነ እግዜርን መጥራት አይጠበቅብኝም በሚመስል ስሜት የአፍ ጦርነት ይማዘዛሉ፤ ይጨቃጨቃሉ፤ የሚቧቀሱም አይጠፉም፡፡ እነሱ እንደሚሉት መብታቸውን ያስከብራሉ ማለት ነው፡፡

ብዙ ጊዜ ወያላዎች፣ ‹‹መብቴ ነው!›› የሚላቸው ሰው ጠላታቸው ነው ሊባል ይችላል፡፡ ‹‹መብታችሁ ታክሲ ውስጥ ትዝ አይበላችሁ›› በማለት ታክሲያቸው ውስጥ በሰቀሉት ጥቅስ ይከራከራሉ፡፡ ከዚህም አልፈው ተርፈው ካሳፈሩት ሰው ጋር ይጨቃጨቃሉ፤ ይወዛገባሉ፡፡ በአንድ በትንሽዬ አጋጣሚ ሳይሆን በርስት ወይም በሌላ ንብረት የሚከራከሩ ነው የሚመስሉት፡፡ አንድ ሰው፣ ‹‹ወገኖቼ ኧረ በደህና ነገር እንጨቃጨቅ! ማን ይሙት አሁን ደህና ውይይት የሚሻ አገራዊ ጉዳይ ጠፍቶ ነው እንደዚህ በረባ ባልረባው የምንነታረከው?›› አለ፡፡ ሌላኛው ሰው ደግሞ፣ ‹‹አየህ ሰው በርካታ ብሶቶች ሳይኖሩበት አይቀርም፡፡ ስለዚህ ትንሽ ነካ ስታደርገው በሆዱ ውስጥ አፍኖ ያቆየውን ሁሉ ይዘረግፈዋል፤ ወዶ አይደለም፤ በሰው አትፍረድ፤›› አለው፡፡

የሁለቱ ሰዎች ክርክር ታክሲዋን በከፊል ተቆጣጠራት፡፡ የመጀመሪያው ወጣት እንዲህ አለ፤ ‹‹ቢሆንም ለአገርም ለሕዝብም በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ መከራከር ያዋጣል፤ በማይረቡ ጉዳዮች ጊዜያችንን እያጠፋን አዕምሮአችንን ከምናደንዘው ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ መነጋገሩ ይበጀናል፤›› ሲል፣ አንዲት ወጣት፣ ‹‹እውነት ነው! ለምን ስለዓባይ ጉዳይ አናወራም? ለምን ስለኤርትራስ አናወራም? ኧረ እንዲያውም ወሳኝ ስለሆነው ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ላይ ለምን አንነጋገርም?›› በማለት አስተያየቷን ሰነዘረች፡፡ ወሬውም እየጦፈ ሄደ፡፡ ወጣቱና ወጣቷ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የራሳቸውን ወግ ቀጠሉ፡፡ ሌሎች ተሳፋሪዎች አፌን በዳቦ ያሉ ይመስል ጭጭ አሉ፡፡ አንድ ጎልማሳ በታፈነ ድምፅ፣ ‹‹አሁን ፖለቲካ ምን ያደርጋል? ክፉ እያናገሩ ለክፉ ይዳርጉናል፤›› አለ፡፡

ወያላው በተጀመረው ውይይት ብዙ የተመሰጠ አይመስልም፡፡ ለሾፌሩ የድሮ ታሪኩን ይተርክለት ጀመረ፤ ‹‹ድሮ ልጅ እያለሁ ጫማ የሚባል ነገር ጠላቴ ነበር፤›› አለ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹እግር ኳስ እንኳን ታኬታ ካደረጉ ልጆች ጋር በባዶ እግሬ ነበር የምጫወተው፡፡ የመጫወቻ ሥፍራዬ ተከላካይ ነበር፤›› አለ፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹እሺ እባክህ እስቲ በደንብ አጫውተኝ፤›› በማለት ለታክሲዋ ነዳጅ እየሰጠ ወያላውም እንዲያወራ ቆሰቆሰው፡፡ ወያላው ቀጠለ፣ ‹‹የቅጥል ስሜ ‘ቀልጥመው’ ነበር፡፡ እያቆላመጡ ‘ከቀልጥም ኳስ ቢያልፍ እግር አያልፍም’ ሲሉኝ በቃ! እንኳን በታኬታ በታንክ ቢመጣ ማንንም አላሳልፍም ነበር፡፡ ኳሱን አታሎኝ ቢያሳልፍ ሰውዬውን ግን ተአምር ቢፈጠር አላሳልፈውም፤›› እያለ ተረከለት፡፡

በዚያ እንደብረት በሚከተክተው እግሩ የስንቱን ቅልጥም እንደሰበረ ሲናገር የጦር ሜዳ ውሎ የሚተርክ ይመስል ነበር፡፡ ሾፌሩ ብስጭት እያለ፣ ‹‹በእናትህ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንተን አሰልፈውህ ቢሆን ኖሮ በሰላሳ አምስተኛው ሰከንድ ፈጣኗ ጐል ባልተመዘገበችብን ነበር፤›› አለው፡፡ ይኼኔ ወያላው፣ ‹‹እባክህ ተዋቸው እንኳን የአፍሪካ ዋንጫን ይቅርና የበረኪና ዋንጫ አያነሱም፤አልሰማህም እንዴ? ናይጄሪያን ነጥብ እናስጥላለን ሲሉ በጎል መአት ሲደበደቡ?›› አለ፡፡ ወያላው ቀጥሎ፣ ‹‹እኔን ግን ሰፈር ውስጥ በጣም የሚያማርሩኝ ልጆች ነበሩ፤›› በማለት የጥንቱን እያስታወሰ ይስቅ ጀመር፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ለምንድን ነው የሚያማርሩህ? አታነክታቸውም እንዴ?›› አለው፡፡ እሱም፣ ‹‹ያላነከትኩት ሰው የለም፤ ግን ትችታቸውን አያቆሙም፡፡ አንዴ ምን እንዳሉኝ ታውቃለህ?›› አለው፡፡  ሾፌሩም፣ ምን ብለው እንደተቹት ለመስማት እየጓጓ፣ ‹‹ደግሞ ምን አሉህ?›› አለው፡፡ ወያላው ከመናገሩ በፊት ሒሳብ መሰብሰብ ጀመረ፡፡ ይኼኔ ቅድም የተጀመረውን ወሬ ለመስማት ፋታ አገኘሁኝ፡፡ የመጀመሪያው ወጣት አንድ ነገር ሲናገር ጆሮዬ ውስጥ ጥልቅ አለ፡፡

‹‹በአንድ አገር ውስጥ የሕዝብ ንዴት በየትኛው ቅጽበት እንደሚነሳ ማወቅ አይቻልም፤›› በማለት የተወሰኑ ሰዎችን ጆሮዎች ሰበሰበ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹በቱኒዚያ በተነሳው አመፅ ራሱን አቃጥሎ በመግደል ለቱኒዝያውያን መነሳሳት ምክንያት የሆነው ሰው ይህን ያህል ቀውስ እንደሚያስከትል መንግሥት ቢያውቅ ኖሮ፣ እንኳን መንገድ ላይ አትክልት አትሽጥ ሊለው ይቅርና እባክህ ቤተ መንግሥት ውስጥ ገብተህ የፈለግከውን ሽጥ ብለው ሁኔታዎችን ያመቻችለት ነበር፤›› ሲል፣ አንድ ሌላ ሰው፣ ‹‹እኔ እንዲያውም የፕሬዚዳንቱ ገበታ ላይ በየቀኑ እንዲካፈል የሚያደርጉት ይመስለኛል፤ ፕሬዚዳንቱ እያባበሉና እያጎረሱት ያሞላቅቁት ነበር፤›› ሲል፣ የባሰ አታምጣ አልኩኝ በሆዴ፡፡ የመጀመሪያው ወጣት ከሰውዬው አፍ ተቀበለና፣ ‹‹ስለዚህ አመፅ የቱጋ በምን ቅጽበት እንደሚነሳ ማወቅ አይቻልም፡፡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፤›› አለ፡፡ ወጣቱን ምን እንደዚህ እንዳበሳጨው ባይታወቅም ከመናገር የሚገታው ጠፋ፤ ‹‹ውኃ ቀጠነ ብለን በመንግሥት ላይ መማረር አንፈልግም፤ ነገር ግን እንጀራችን ሲቀጥን፣ ዳቦዋችን ሲያር ዝም ብለን መቀመጥ አንችልም፤ ተገቢው ድጋፍና ማበረታቻ ሊደረግልን ይገባል፤›› አለ፡፡

የልጁ እንደዚያ መማረር ያስገረማቸው አንድ አባት ምክራቸውን ለገሱት፣ ‹‹ተው ልጄ አንተ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነህ፤›› ብለው ወሬያቸውን ሲጀምሩ ልጁ ተቆጣ፤ ‹‹ምኔ ነው አንድ ፍሬ? ተማርኩኝ! ተመረቅኩኝ! አሁን ሰላሳ ዓመት ሊሞላኝ ነው፤ ታዲያ ምኑ ነው አንድ ፍሬ ያሰኘኝ?›› ሲላቸው፣ አዛውንቱ አሁንም በሰከነ አንደበት፣ ‹‹ድሮ ወጣቱ በሰላም መኖር አይችልም ነበር፤ ልማት የሚባል ነገር አልነበረም፤ ዴሞክራሲም ቢሆን አልነበረም፤ ያ ጨቋኝ ሥርዓት በማለፉ ፈጣሪን ማመስገን ነው የሚገባህ፤›› ሲሉት የባሰ ተበሳጨ፤ ‹‹ለምንድነው ሁልጊዜ የዚህን መንግሥት ዴሞክራሲያዊነት ካለፈው መንግሥት ጋር ብቻ የምታወዳድሩት? ለምን ከአሜሪካ ዴሞክራሲ ወይም ከአውሮፓ ዴሞክራሲ ወይም ደግሞ ከእነ ደቡብ አፍሪካ ጋር አታወዳድሩትም? ድሮም የወደቀ ዛፍ ምንድን ይበዛበታል አሉ፤›› በማለት መቶ ሜትር የሮጠ ይመስል ቁና ቁና ተነፈሰ፡፡ የወጣቱ ነገር ያላማራቸው አዛውንት ዝም አሉ፡፡ ሌሎቹ ተሳፋሪዎች ልጁን በስጋት እያዩት አሁንም ዝም ብለዋል፡፡ የቅድሙ ጎልማሳ ልጁን በጥርጣሬ እያየው፣ ‹‹አንተ አስመሳይ ሳትሆን አትቀርም፤ እኛ ዝም ብለን አንተን የማያስለፈልፍህ ምንድነው?›› ሲለው ጥቂት ሰዎች ሳቁ፡፡ ወጣቱ ግን በንዴት እያየው ዝም አለ፡፡

እኔም ወያላው ዘንድ ብመለስ ይሻለኛል፤ እንደዚህ ዓይነቱን ነገር እንኳን ማውራት መስማትም አንዳንዴ ሊያስጠይቅ ይችላል የሚሉ ጎረቤቴን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ከጀመርኩ ጥቂት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ጎረቤቴ አንዳንዱ ባልሆነ መንገድ ወሬ ይጀምርና ወይ ያስከስስሃል ወይ ያስጠይቅሃል ይላሉ፡፡ የጎረቤቴ ጥንቃቄ እኔ ዘንድ ተጋብቶ እኔም እንደሳቸው የጥርጣሬ ማርሼን ቀይሬአለሁ፡፡ ሾፌሩ፣ ‹‹በእናትህ ታሪክህን ቀጥልልኝ፤ ምን እያሉ ነበር የሚተቹህ?›› አለው፡፡ ወያላውም ሳያቅማማ ማውራት ጀመረ፤ ‹‹እንዳልኩህ ጫማ የሚባል ነገር አልወድም፤ እናም ሁልጊዜ በባዶ እግሬ ስሄድ ነበር ሰላም የሚሰማኝ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ቤተሰቦቼና እኔ የተጋበዝንበት አንድ የቅርብ ዘመድ ሠርግ ነበር፡፡ እዚያ ሠርግ ላይ ታዲያ ባዶ እግሬን መገኘት ለእኔም ሆነ ለቤተሰቦቼ ውርደት ነበር፡፡ ስለዚህ ቤተሰቦቼም እንደምንም ተጣጥረው አንድ አዲዳስ ጫማ ገዙልኝ፡፡ ያንን ጫማ አድርጌ ትንሽ ‘ወክ’ ለማድረግ ከቤት ወጣ ስል እነዚህ እርጉም የሆኑ የሰፈራችን ልጆች አጋጠሙኝ፤›› ብሎ ወሬውን አቋረጠው፤ ይኼኔ ልቡ የተሰቀለው ሾፌር፣ ‹‹ታዲያ ይዩሃ! አትዘንጥባቸውም ነበር? ግን ምን አሉህ?›› አለው፡፡ ወያላውም፣ ‹‹አካሄድ ጠፍቶብኝ ስሸነካከል አይተው ወደ እግሬ እየጠቆሙ፣ ‘ለማጅ’ አይሉኝ መሰለህ?›› ሲል፣ ሾፌሩ ራሱን መቆጣጠር አልቻለም፤ ታክሲዋን ወደዳር እንኳን አስጠግቶ ማቆም አቃተው፤ መሀል ላይ አቁሞ በሳቅ ተንከተከተ፡፡ መኪናዎች ማለፊያ ስላጡ በጥሩምባቸው አካባቢውን ድብልቅልቁን አወጡት፡፡ ሾፌሩ ግን መኪናዋን ማሽከርከር እስከሚያቅተው ድረስ ሳቀ፡፡ አንዳንድ መንገድ የተዘጋባቸው አሽከርካሪዎች በመስኮታቸው ብቅ እያሉ፣ ‹‹ለማጅ ነህ እንዴ? ሰው እንዳትጨርስ አውርዳቸው፤›› በማለት ተጯጯሁ፡፡ ሾፌሩን ‘ለማጅ’ ሲሉት የባሰ እያሳቀው እንደምንም ብሎ ታክሲዋን አስነሳት፡፡ አንዲት ተሳፋሪ ወያላውን፣ ‹‹ሾፌሩ ለማጅ ነው?›› ብላ ስትጠይቀው፡፡ እሱም እየሳቀ፣ ‹‹አዎ! ልምድም የለውም፤›› ሲል ታክሲዋ በጩኸት ታመሰች፡፡ ወያላው እንደገና በከፍተኛ ድምፅ፣ ‹‹ተሳፋሪዎች እባካችሁ ተረጋጉ፤ የሾፌሩ ልምድ ከማንም ጋር ሳይነጋገር መንዳት እንጂ፣ እየሳቁ መንዳት አይደለም፤›› ሲል ነፍሴ ተመለሰች፡፡ ‘ለማጅ’ የሚለውን ቃል አግዝፈው የሰሙት ግን ቆፈን እንደያዘው ሰው ይንዘፈዘፉ ነበር፡፡