እንደ ኢያሪኮ ግንብ
ሴቶችን ይዞራል
ከመካከላቸው
የአንዷ ልብ ይወድቃል፤
አብረው ይተኙና
ብቻውን ይነሣል፡፡
ደግሞ ሌላ ግዳይ
ደግሞ ሌላ ምርኮ
ልብና ዓይኑን ልኮ
እንደ ገና
ሴቶችን ይከባል፤
መላልሶ ሲያንኳኳ
የአንዷ ልብ ይፈርሳል፡፡
እንዲህ እያደረገ
በምድር እየኖረ
አልጋ ላይ አደገ፡፡
ምን ይሻላል!
አንድ ሰው ለአንድ ነው
ቢሉትም እነርሱ፣
አንድን ሰው አንዴ ነው
ትለዋለች ነፍሱ፡፡
(ዳዊት ጸጋዬ፤ አርነት የወጡ ሐሳቦች፣2003)
* * *
‹‹የሚሌኒየሙ ምርጥ አባባሎች››
- ሥራ የፈታ አዕምሮ የሰይጣን ፋብሪካ ነው
(ረቂቅ አሻራ)
- ሕይወት የግዴታዎች ሰንሰለት ናት፡፡ (ኦሮማይ)
- ቅናት ከፍቅር ጋር አብሮ ይወለዳል፣ ነገር ግን አብሮት አይሞትም፡፡
(የቅናት ዘር)
- አስቀድሞ የበሰለ ፍሬ አስቀድሞ ይጠፋል፡፡
(ጣምራ ጦር)
- እግዚአብሔር ይመስገን ፍቅርም ሀዘንም በቶሎ ያልፋሉ፡፡
(በርትል)
- አፍንጫ ሥር ያለውን ነገር ለመመልከት ዘላቂ ትግል ያስፈልጋል፡፡
- ነፃነት ማለት ኃላፊነት ነው፡፡ ስለዚህም ነው ብዙ ሰዎች የሚፈሩት፡፡
(ቤንጃሚን ፍራንክሊን)
- እያንዳንዱ ትውልድ በአባቶች ላይ ያምፃል ከአያቶች ጋር ያብራል፡፡ ከፈለጉ እሺ ካልፈለጉ አልፈልግም ይበሉ እንጁ ተፈቀርኩ ብለው አይመጻደቁ፡፡
(የንስር ዓይን)
- የሞኝ ሰው ልቡ አፉ ነው፡፡ የብልህ ሰው አፉ ግን ልቡ ነው፡፡
(ፍራንክሊን)
(ምርጥነህ ታምራት፤ጣዝማ፣2000)
* * *
እንቆቅልህ
እንቆቅልህ ወይም እንቆቅልሽ ማለት ከቀን ብዛት አነጋገሩ ተለውጦ ነው እንጂ ዕንቁላል አለህ ወይም እንቁላል አለሽ ማለት ነው፡፡ ዕንቁላል ድፍን በመሆኑ በውስጡ ያለው ጫጩት ወንድ ይሁን ወይም ሴት ትሁን ከቅፍቀፋው ወይም ከፍልፈላው በፊት ሊታወቅ ባለመቻሉ የተሰወረና የተደበቀ ምስጢር መጠያየቂያና መፈታተኛ ሆኖ ሲያፋትን ይኖራል፡፡
(ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ፤ ከሥራ በኋላ ሥራ ስትፈቱ እንቆቅልሽ ተጫወቱ፣1943)
* * *
ይሞክሩት
ሰውየው ሲሞት ያሉትን 17 ፈረሶች ሦስት ልጆቹ እንዲካፈሉዋቸው ተናዘዘ፡፡ ሲናዘዝም፣ ‹‹የመጀመሪያው ልጅ ከፈረሶቼ ግማሾቹን ይውሰድ፣ ሁለተኛው ልጄ ደግሞ ከፈረሶቼ ሲሶውን /አንድ ሦስተኛውን/ ይውሰድ፣ ሦስተኛው ትንሹ ልጄ ደግሞ ከፈረሶቼ ከዘጠኝ አንዱን ይውሰድ›› ብሎ ተናዝዞ ሞተ፡፡ ልጆቹ ፈረሶቹን ሊካፈሉ ፈለጉ፡፡ ገና የመጀመሪያው ልጅ ‹‹ግማሼን ላንሣ›› ብሎ ሲነሣ ስምንት ፈረሶች ተኩል የሚደርሰው ሆነና ነገሩ ተበላሸ፡፡ የሁሉም ልጆች ድርሻ እንዲሁ ፈረስ የሚያስገድል ሆነ፡፡ እነዚህ ልጆች ፈረሶቹን እንዴት አድርገው ነው መካፈል የሚችሉት?
(አዲስ ዘመን፤ኅዳር 10 ቀን 1987 ዓ.ም.)
መልስ
ልጆቹ እንዳይጣሉ ወደ ሽማግሌ ዘንድ ሔደው ምክር እንዲሰጧቸው ጠየቁ፡፡ ሽማግሌውም በነገሩ አሰቡበትና ልጆቹን በሰላም ለመለያየት ብለው ከራሳቸው አንድ ፈረስ ጨምረው ለመጀመሪያው ልጅ ግማሹን ዘጠኝ ፈረስ በኑዛዜ መሠረት ሰጡት፡፡ ለሁለተኛው ልጅም በኑዛዜው መሠረት የአስራ ስምንቱን ፈረሶች ሲሶ ስድስት ፈረሶች ሰጡና ለሦስተኛ ልጅ በኑዛዜው መሠረት ከዘጠኝ አንድ የሚደርሰውን ሁለት ፈረሶች ሰጡት፡፡ አሁን በመጨረሻ አንድ ፈረስ ስለቀረ ሽማግሌው የቀረውን አንድ ፈረስ የእሳቸው ነበርና ይዘው ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡ /ቋንቋው ጋዜጣው ላይ እንደተጻፈው ነው፡፡
(አዲስ ዘመን፤ታኅሣሥ 25 ቀን 1987 ዓ.ም.)
* * *
በምልልስ የሚቀርብ እንቆቅልሽ
ጥያቄ /ሴት?/
ከሎሚ ላይ ጠርሙስ፣ ከጠርሙስ ላይ ባላ፣
ከባላ ላይ ጐታ፣ ከጐታ ላይ ሳንቃ፣
ከሳንቃ ላይ ሽጉጥ፣ ከሽጉጥ ላይ መንቀል፣
ከመንቀል ላይ በረድ፣ ከበረድ ላይ ኩስኩስት
ከኩስኩስት ላይ ኮከብ፣ ከኮከብ ላይ ዘንዶ
ከዘንዶ ላይ ሜዳ፣ ከሜዳ ላይ ቅል፣
ከቅሉ ላይ ሐር፣ ከሐሩ ላይ ጤዛ፣
ከጤዛው ላይ ብር፣
ይህንን የፈታ ከእኔ ጋር ይደር፡፡
መልስ /ወንድ?/
ሎሚው ተረከዝሽ፣ ጠርሙሱ ባትሽ ነው፣
ባላውም ጭንሽ ነው፣ ጐታውም ሆድሽ ነው
ሳንቃው ደረትሽ ነው፣ ሽጉጡም ጡትሽ
መንቀል አንገትሽ ነው፣ በረዶው ጥርስሽ
ኩስኩስቱ አፍንጫሽ ነው፣ ኰከቡም ዓይንሽ፣
ዘንዶው ቅንድብሽ ነው፣ ሜዳው ግንባርሽ፣
ቅሉም ራስሽ ነው፣ ጤዛውም ወዝሽ፣
ሐሩም ነው ጠጉርሽ
ብሩም ሳዱላሽ ነው
ይህንን ፈታሁኝ ይዤሽ ማደሬ ነው፡፡
(ጌታቸው ወልዴ፤‹‹እንቆቅልሽ?››የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤ ታኅሣሥ 22 ቀን 1987)
* * *
‹‹ዘንዶ››
ዘንዶ (አርዌ) በቅድመ ክርስትና ዘመን በኢትዮጵያ ይመለክ ነበር፡፡ በአፈ ታሪክ አባባል ይህ ዘንዶ ባንድ ወገኑ የሰው ዘር ነበረ፡፡ ቁመቱ 70 ክንድ፣ ጥርሱም 70 ሆኖ ሰውን እየበላ ስላስቸገረ፣ ሕዝቡ በእህቱ አማካይነት ድርድር ጀምሮ ለዘንዶው በቀን 10 በሬ፣ 10 ላም፣ 50 ፍየል፣ 50 በግ እንዲሁም ማርና ወተት አንዲት ልጃገረድ ሊገብሩለት፣ እርሱ ሰውን እያሳደደ መብላት እንዲተው ተስማምተው 40 ዓመት ዘንዶው ግብሩን እየተቀበለ ገዛ ይባላል፡፡ በመጨረሻ አንድ ሰው ከሐማሴን ስሙ ገብገቦ የሚባል መጥቶ ‹‹ለምን ይህን ሁሉ ግብር ለዘንዶ ትገብራላችሁ ብትገሉት አይሻልምን?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ባይሆንልን ነው እንጂ ወደን ነው፣ አንተ ብትገድለው ገዣችን እናደርግሃለን›› ሲሉ ቃል ገቡለት፡፡ በዚህም ገብገቦ ስለተስማማ ዘንዶውን ለመግደል እቅድ አወጣ፡፡ ዘንዶው በሚኖርበት ዙርያ 7 ዙር አጥር ከቅጠልና ከሳር አሳጠረ፡፡ ይህን ካደረገ በኋላ በአራት ማዕዘን እሳት ለኰሰበት፡፡ በሙቀቱና በጭሱ ስለተቸገረ ዘንዶው ለመውጣት ሲታገል ገላው በእሳት ተለብልቦ ተዳክሞ ከዳር ሲደርስ ገብገቦ በሰይፍ አንገቱን በመቁረጥ ጨረሰው፡፡
ተመሳሳይ ታሪክ በአቬስታ የፋርሶች (ኢራን) ቅዱስ መጽሐፍ ይገኛል፡፡ ከስሞቹ መለዋወጥ በስተቀር የታሪኩ ይዘት አንድ ነው፡፡ ምናልባት በንግድ ግንኙነት አማካይነት ይህ የዘንዶ አምልኮት ከፋርስ ወደ ኢትዮጵያ ተሻግሮ ይሆናል፡፡
የእባብ መመለክ በሰሜን ኢትዮጵያ ተስፋፍቶ እንደነበር የሚያመለክት አንድ መረጃ በአክሱም ከወደቁት ሐውልቶች አንዱ፣ የእባብ ሥዕል ተቀርጾበታል፡፡ ይህ ዓይነቱ አምልኮት ምናልባት እስከ 6ኛው ምእት ድረስ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሳይቆይ አልቀረም፡፡
በዚህን ዘመን ዘጠኙ ቅዱሳን ከእያሉበት ተሰማርተው ወንጌልን በማስተማር የዘንዶን አምልኮን አጥፍተዋል፡፡ በዚህ በኩል ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ አቡነ አረጋዊ የደብረ ዳሞ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ይመለክ የነበረውን ዘንዶ አጥፍተው ቤተ እግዚአብሔር አንጸውበታል፡፡ ስላደረጉትም ተጋድሎ እስከ ዛሬ ድረስ ወደ ገዳሙ የሚወጣው በዘንዶ ቅርጽ ከጠፍር በተሠራ ገመድ ነው፡፡ ስሙም ዘንዶ ይባላል፡፡
(ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፤ የአማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት፣ 1979)
* * *
ገራገር
40 እባቦች ከአውሮፕላን ውስጥ ሊገቡ ሲሉ ተያዙ
ሁለት ግለሰቦች 40 እባቦችን በሻንጣቸው ውስጥ አድርገው ከኢንዶኔዢያ ወደ ዱባይ ይዘው ሊሄዱ ሲሉ በኢንዶኔዢያ አየር መንገድ ሠራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
ሁለት የኩዌት ዜግነት ያላቸው ሰዎች በያዙት የመንገደኛ ቦርሳ ውስጥ እባቦቹን ሞልተው ለማለፍ ሲሞክሩ በኤክስሬይ በተደረገ ፍተሻ መያዛቸውን የአየር መንገዱ ሠራተኞች ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ግለሰቦች ለመርማሪዎች እንደተናገሩት፣ እባቦቹን ወደ ተባበሩት ዓረብ ኤምሬት ወስደው ለመሸጥ መሆኑን ነው፡፡ የዱር እንስሳትን ይዞ መዘዋወር በሕግ ስለሚያስቀጣ፤ ክስ ከተመሠረተባቸው በሰባት ዓመት እስራትና በ3200 ዶላር ሊቀጡ እንደሚችሉ የአየር መንገዱ ሹም ሚስተር ሳላሁዲን ራፊ ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው እንደገለጹት፣ ባለፈው ታኅሣሥ ፖሊስ ወደ ኢንዶኔዢያ የመጣን የመንገደኞች አውሮፕላን ዱባይ ላይ ሲፈትሽ በሳጥን ውስጥ የተጫኑ አራት እባቦችን፣ ሁለት በቀቀንና አንድ አይጠ መጐጥ መያዙን አስታውሰዋል፡፡
* * *
ፈረንሳዊው ከትልቁ ማማ ሊወጣ ነው
ከፓሪሱ ኢፍል ማማ እና ከሒድሮው ኦፔራ ሃውስ በመውጣት ብቃቱን ያረጋገጠው ፈረንሳዊው ስፓይደርማን፣ አሁን ደግሞ ትኩረቱን የዓለም ረዥሙ ማማ ላይ አርፏል፡፡
የ48 ዓመቱ አላይን ሮበርት፣ በአሁኑ ወቅት ለመውጣት ያቀደው ከዱባዩ ቡርጅ ካሊፋ ማማ ሲሆን፣ “ድንበር አልባ ትምህርት” በሚል በሥሩ በሚገኘው አዳራሽ እየተካሔደ ያለውን ስብሰባ ምክንያት በማድረግ መሆኑን የፈረንሣይ የዜና ወኪል (ኤ.ኤፍ.ፒ) ዘግቧል፡፡
ሮበርት ከትልልቅ ሕንፃዎችና ማማዎች ላይ በመውጣት የሚታወቀው ምንም ዓይነት አጋዥ መሣርያ ሳይጠቀም ነው፡፡ ሰውየው በአሁኑ ወቅት ሊወጣው ያቀደው ማማ 828 ሜትር ርዝማኔ ያለው ሲሆን፣ ይህንን ለመውጣት ግን ገመድና አንዳንድ መሣርያ ለመጠቀም እንደሚገደድ ተጠቁሟል፡፡ ምክንያቱም ራሱ እንዳስታወቀው በዱባይ ያለው እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርሰው ከፍተኛ ሙቀት ነው፡፡
“የእኔ ጭንቀት ቢፎርድ ላይ ረዥም ግዜ ማጥፋት ነው፡፡ አንድ ነገር መውጣት ለእኔ እንደመብላትና መጠጣትም ነው፡፡ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች (ማማዎች) መውጣት የሕይወቴ ፍቅርና ዓላማ ነው” ብለዋል፡፡
ሮበርት እስከአሁን በአሜሪካና በቻይና የሚገኙትን ጨምሮ በርዝማኔያቸው የሚታወቁትን ከ100 በላይ ማማዎችና ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎችን በመውጣት ይታወቃል፡፡


