[ላለፉት ስድስት ወራት ቀጠሮ እንዲሰጡት ከጨቀጨቀ በኋላ እንዲገባ ፈቀዱለትና ሰውዬው ገባ]
እሺ ምን ዓይነት የግል ችግር ቢያጋጥምህ ነው እንደዚህ የጨቀጨከኝ?
ክቡር ሚኒስትር እኔ የጨቀጨኩዎት የግል ችግር አጋጥሞኝ አይደለም፡፡
ታዲያ ምን አድርጌህ ነው ስድስት ወር ሙሉ እንደዚህ የጨቀጨከኝ?
የአገርና የሕዝብ ችግር ስላየሁ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
አልገባኝም!
ክቡር ሚኒስትር እኔ በዚህ መሥርያ ቤት ብዙ ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ ደስ የማይልና አገርን የሚጎዳ ነገር ሲሠራም አይቻለሁ፤ አዝኛለሁ፡፡ በቅርቡ እያየሁት ያለው ሙስና ግን ዘግናኝና እንቅልፍ የሚነሣ ተግባር ነው፡፡
እስቲ በደንብ ዘርዘር አድርገህ ንገረኝ፡፡
ክቡር ሚኒስትር በቃል ብቻ ሳይሆን ይኸው - ደብዳቤውን ያንብቡት፤ ማስረጃ ዶክመንቶቹንም ይመርምሩት፡፡ መሥርያ ቤታችን አጫርቻለሁ ብሎ እየሠራ ያለው ሥራ አንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን ብር ተዘርፎበታል፡፡
እንዴት?
ለሥራው የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎች ግዢ የተባለውና ለባለሙያዎችም ወጪ ተደርጓል የተባለው መጠን ሁሉ ውሸት ነው፡፡
እንዴት ውሸት?
ክቡር ሚኒስትር በሁለት መቶ ሰማንያ ሚሊዮን ብር መጠናቀቅ የሚችል ሥራ አራት መቶ ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡
ማስረጃ አለህ?
ይኸው ሁሉንም አያይዤዋለሁ፡፡
እስቲ አንድ ሁለቱን አስረዳኝ፡፡
ይኸው ክቡር ሚኒስትር በማንኛውም የዕቃ ግዢ ሕግ አንድ ዕቃ ሲገዛ የተገዛበት አገር በግልጽ መነገር አለበት ይላል፡፡ እዚህ እንደሚያዩት ግን እስያ ይላል እንጂ የየትኛው የእስያ አገር ስም እንደሆነ አይገልጽም፡፡ እስያ ብሎ ነገር የለም፡፡
እ. . .ህ. . . .ም
እዚህ ደግሞ ይመልከቱ፤ እስያ ይልና ኢንቮይሱ ግን በስፓኒሽ ቋንቋ የተጻፈ ነው፡፡ እስያ ብሎ ስፓኒሽ የለም፡፡
የሚገርም ነው፡፡
ክቡር ሚኒስትር ወደ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከመውሰድ ይልቅ እርስዎ ይዩት ብዬ ነው፡፡ እንደሚገድሉኝ ወይም እንደሚያስገድሉኝ አውቃለሁ፡፡ ግን የፈለጉትን ያድርጉ ብዬ ነው፡፡ በዛ. . .
እንዴ እስከማስገደል ይሔዳሉ?
አውሬዎች ናቸው ክቡር ሚኒስትር፡፡
ታዲያ ወደእኔ የመጣኸው እኔን ለማስገደል ነው?
ለምን ለፖሊስ ወይም ለፀረ ሙስና በቀጥታ አትሰጣቸውም፡፡
እርስዎ ይህ ሁሉ ሙስና ሲካሔድ አያውቁም፡፡ ባላወቁት ጉዳይ ተጠያቂ ከሚሆኑ ጠያቂ ቢሆኑ ይሻላል ብዬ ነው፡፡ የእርስዎ እጅ በዚህ ሙስና ውስጥ እንደሌለበት አውቃለሁ፡፡ ምናልባት ባለመቆጣጠርዎና የሚነገርዎትን በማመንዎ ይጠየቁ ይሆናል፡፡ በስርቆቱ ግን እጅ አላስገቡም ተጠያቂም አልሆኑም፡፡ ይህን አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በማጋለጡ ተሳታፊ ሆነው ታሪክ ይሥሩ ብዬ ነው፡፡
አመሰግናለሁ ልየውና እጠራሃለሁ፡፡
እሺ ቻው፡፡
[ሙሰኞቹ ሰውዬው እንዳጋለጣቸው ወሬውን ሰምተዋል፡፡ የራሳቸውን ቀጣይ ዕቅድ እየነደፉ ሳሉ ክቡር ሚኒስትሩ በቢሯቸው ስብሰባ ጠሯቸው]
መሥርያ ቤቱ በሚያሠራቸውና በሚገዛቸው ዕቃዎችና ንብረቶች ዙርያ የገንዘብ ብክነት አለ የሚል ቅሬታና ቁጭት በመሥርያ ቤቱ ሠራተኞች እየታየና እየተሰማ ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አውቃችኋል?
(አንዱ) በቅርቡ አንድ ድራማ መሳይ እያየን ነው፡፡ አንዱ የመሥርያ ቤታችን ባልደረባ፣ ማለትም ኢንጂነር ነኝ የሚል የኢንጂነሪንግ ዲግሪህ የውሸት ነው ይባላል፤ እናጣራዋለን ስላልነው ዶኩሜንት ሰብስቦ ለእርስዎ እንደሰጠ ሰምተናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
አሁን የቀረበው ዶኩሜንት ትክክል ነው ትክክል አይደለም በሚለው ላይ እናተኩር፡፡ ሰውዬው ኢንጂነር ነው ኢንጂነር አይደለም የሚለው ለጊዜው አንገብጋቢ ጉዳይ አይደለም፡፡
ውሸታሞች ሐቀኛ ለመምሰል እንዴት እንደሚሞክሩ ለማሳየትና ለማጋለጥ ያመቻል ብለን ነው፡፡
እንደ አጋጣሚ ሰውዬው በኢንጂነሪንግ ዲግሪ ሲመረቅ ወንድሜም ይመረቅ ስለነበርና በአንድ ዩኒቨርሲቲም ስለተመረቁ ለምርቃቱ ሔጄ ስለነበር ከዓይኔ በላይ ሌላ ምስክርነት ስለማያስፈልገኝ አሁን ወደ ዶኩሜንቶቹ እንመለስ፡፡
[ሌላ] እኛ ዛሬ፣ ነገ ሽልማት ይሰጠናል ብለን የምንጠብቅ እንጂ የምንወቀስ አይደለንም፡፡
ጥሩ ነገሩን በሚገባ ለማጣራትና ሐቀኛውንና ቀጣፊውን ለመለየት እንድንችል አንድ አጣሪ ኮሚቴ ለማቋቋም ወስኛለሁ፡፡
አስፈላጊ አይመስለኝም ክቡር ሚኒስትር፡፡
ለምን አስፈላጊ አይሆንም?
እንዲህ ከተደረገና እንዲህ ማድረግ ከተለመደማ ነገም በእርስዎ ላይ ጥቆማ መስጠት ሊጀመር ነው፡፡ መጠቆም ፋሽን ሊሆን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
ችግር የለም ቅሬታ ያለው ይጠቁም፡፡ ጥቆማዎች ዳግም ይጣራሉ፡፡
[ሌላው ሰው] ለመሆኑ የአጣሪ ኮሚቴው አባላት እነማን ናቸው?
ይኸው እነዚህ ናቸው ዝርዝራቸውን እዩት፡፡
[ዝርዝሩን ሲያዩት ሙሰኞቹ ደስ አላላቸውም፡፡ የማይፈልጉትን አስወጥተው የሚፈልጉትን ለማስገባት ፈለጉ]
[አንዱ] ዝርዝሩን አየሁት ክቡር ሚኒስትር፤ ግን ከሕዳሴው መንፈስ ጋር የሚሔድ ኮሚቴ ብናደርገው አይሻልም ወይ?
አልገባኝም ምን ማለትህ ነው?
ወንዶችም ሴቶችም እኩል የሚገኙበት ኮሚቴ ቢሆን ማለቴ ነው፡፡ ‹‹የማርች 8›› ስሜት የሚያስተጋባ ኮሚቴ ይሁን ማለቴ ነው፡፡ የኢሕአዴግ አመለካከት አይንፀባረቅ ማለቴ ነው፡፡
ችግር የለም ከአምስቱ ሁለቱን ልሰርዝና ሴቶች ይግቡ፡፡ ይኸው አስተካክዬዋለሁ፡፡
[አሁንም ያልረካ ሌላ ሰው] ጥሩ ነው ክቡር ሚኒስትር፤ ግን የፌዴራሊዝም በዓል አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ስለነበርክ ነው ወይ እንዳይሉኝ እንጂ፣ በእኔ በኩል ከየክልሉ አንድ አንድ ሰው በኮሚቴ ቢኖርበት ብዬ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
ችግር የለም እሱንም ማስተካከል ይቻላል፡፡ (አስተካከሉት)
(በአንድ አባል ብቻ ቅር ያለው አንዱ ሌላ ሰው) ሁሉም ጥሩ ነው ግን በጾታም በብሔር ብሔረሰብም ብቻ ሳይሆን በሃይማኖትም ጥሩ አስተዋጽኦ እንዲኖር እንትና ወጥቶ እንትና ቢገባስ ክቡር ሚኒስትር፡፡
እሺ ችግር የለም፡፡ ይኸው እንትና ወጥቶ እንትና ገብቷል፡፡ አሁንስ ተስማማችሁ?
ጥሩ ኮሚቴ ነው ክቡር ሚኒስትር ተስማምቶናል፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ሳይታወቃቸው ያቋቋሙት ኮሚቴ የሙሰኞቹ ደጋፊና ተባባሪ አካል ነው፡፡ ኮሚቴው ያቀረበው የመጀመርያው ሪፖርትም አጠራጠራቸው፡፡]
የተከበራችሁ የኮሚቴ አባላት እስቲ እስካሁን የሔዳችሁበትን ሪፖርት አቅርቡልኝ፡፡
እ. . . እ. . . .እ. . ክቡር ሚኒስትር እኛ ገና አልጨረስንም ግን ብዙ አላገኘንም፡፡ ከእስያ የተገዙት ዕቃዎች በደህና ካገር ውስጥ መግባታቸውን አረጋግጠናል፡፡
ሌላስ?
ኢንቮይሶቹንም አስተርጉመን መርምረናል፡፡
ሌላስ?
አሁን ያለውን ዋጋ ቼክ ስናደርግም አራት መቶ ሚሊዮን ብር ነው፡፡
እና?
እናማ ክቡር ሚኒስትር ጤናማ ነው፡፡
ለመሆኑ መመርያውና ፖሊሲውን ካጣራችሁ በኋላ ነው ምርመራ የጀመራችሁት?
አዎን ክቡር ሚኒስትር፤ እያንዳንዱን አንቀጽ ያጠናነው በነቂስ ነው፡፡
እና እስያ የሚባል አገር አለ?
እ. . . .እ . . . .
እ. . . ከእስያ የመጣ የስፓኒሽ ቋንቋ ኢንቮይስ አላስገረማችሁም?
እ. . . .እ
እና አሁን ያለው ዋጋ አራት መቶ ሚሊዮን ሲመጣና ዕቃው የተገዛው ግን አንድ ዶላር ዘጠኝ ብር በነበረበት ጊዜ መሆኑን ስታውቁ አልደነገጣችሁም?
እ. . . .እ
በቃ ኮሚቴው ተበትኗል፤ በሌላ መንገድ አጣራዋለሁ፡፡ ፖሊስና ፀረ ሙስና ኮሚሽንም እንዲገቡበት አደርጋለሁ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡ ቻው፡፡
እንዴ ክቡር ሚኒስትር!
ቻው. . .ቻው
[ክቡር ሚኒስትሩ በጉዳዩ ተናደውና አዝነው ሙስናውን ለማጋለጥ በቆራጥ መንፈስ ተነሥተው ሳለ ወንድማቸው የመኪና አደጋ እንዳጋጠማቸው ተደወለላቸው]
መቼ ነው እንዲህ ያጋጠመው?
ከግማሽ ሰዓት በፊት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
አሁን የት ነው ያላችሁት?
እዛው ባለፈው ጊዜ የሔድንበት ሆስፒታል ውስጥ፡፡
አደገኛ ሁኔታ ነው?
በጣም አስጊ ነው ብሏል ዶክተሩ፡፡
እሺ አሁን መጣሁ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ሆስፒታሉ ሔዱና ዶክተሩን አነጋገሩት]
ክቡር ሚኒስትር አሁን ኮማ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ከኮማው ሲወጣና ትንሽ ነፍስ ሲዘራ ባንኮክ ወይም ሌላ አገር ቢሔድ ጥሩ ነው፡፡
ማን ይልከዋል ብለህ ነው፡፡ እኔ ገንዘብ የለኝም፡፡
ስለሱ ወዳጅ ዘመድ ተነጋገሩበት፤ እዚህ በቂ ሕክምና አያገኝም ማለቴ ነው፡፡
[በቢሮ በተከሠተው ሙስናና በወንድማቸው ላይ ባጋጠመው አደጋ ተረብሸው እንቅልፍ ሳይወስዳቸው ተነሥተው በጧት ቢሮ ሔዱ፡፡ ጸሐፊያቸው መጣች]
አንድ ሰው እየደወለ አገናኚኝ እያለ ነዘነዘኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
ሲደውል አገናኚኝ፡፡
(ደወለና አገናኘቻቸው) አቤት፤
የተከበሩ ሚኒስትር ነዎት?
ምን ነበር?
ሙስና እያጣሩ ነዎት ሰማን፡፡
ይመለከትሃል?
የቢሯችሁ ሳይበቃ በእዚህ አገር ያለውን የውጪዎቹ ወኪል ማን ነው ብላችሁም እያጣራችሁ በፖሊስና በፀረ ሙስና ልታስይዙን ነው አሉ፡፡
ማን ነህ አንተ?
ስማ ክቡር ሚኒስትር ‹‹አንቱ›› ልልህ አትጠብቅ፣ መቼስ . . . ሙስና የምትለውን ቀልድ ተውና ትናንት የመኪና አደጋ ያጋጠመውን ወንድምህን ውጭ ልከህ አሳክም፡፡
ያገባሃል ወይ?
አያገባኝም ወንድምነቱ ለአንተ ነው፡፡ ነገር ግን ገንዘብ ያስፈልግሃል እንስጥህ ማለቴ ነው፡፡
አልገባኝም፡፡
አንተ የሙስናውን ጉዳይ አስቁም፤ እኛ የአየር ቲኬት፣ የሆቴልና የሕክምና ሙሉ ወጪ በገንዘብ እንሸፍንልሃለን፡፡ ቶሎ ገንዘቡን ውሰድ፣ ቶሎ አስቁም፣ ቻው፡፡ እደውልልሃለሁ ቻው፡፡
[ስልኩ ተዘጋ፤ ክቡር ሚኒስትሩም ሆን ብለው ገጭተውታል የሚል ጥርጣሬም አደረባቸው፡፡ ሙስናው አሳሰባቸው፤ የወንድማቸው ጤናም አሳሰባቸው፡፡ የትኛውን ይመርጡ ይሆን?]
ሀሎ!
ማን ልበል?
እኔ ነኝ ክቡር ሚኒስትር የመሥርያ ቤትዎ ባልደረባ ነኝ፡፡
እሺ. .
ባለፈው ጊዜ ሁሉንም ዶኩሜንት አሟልቼ ሰጥቼ አጣሪ ኮሚቴ አቋቁመው ጥሩ ይዘው ነበር፤ ፖሊስና ፀረ ሙስናም ገብቶበት ጥሩ ሔዶ ነበር፤ አሁን ግን እርስዎ ምርመራው እንዲቋረጥ አድርገዋል መባሉን ሰማሁ፡፡
እ. . .
እንጃ ወንድሜ ታሞብኝ ባንኮክ ሔጄ ነበር፡፡ ያለበትን ሁኔታ ስላላወቅኩ አጣርቼ እደውልልሃለሁ፡፡
በባንኮክ ምክንያት መዘጋቱን ሰማሁ፡፡
ወንድሜ ታሞብኝ እኔም እየተሰቃየሁ ነው፤ አሁን ምንም ልልህ አልችልም፡፡
ኢትዮጵያም ታማ እየተሰቃየች ናትኮ!
ይቅርታ . . . . ቻው፡፡
[ጆሮው ላይ ስልኩን ዘጉበት፡፡ ልክ በእሱ ላይ እንደዘጉ ሌላ ስልክ ተደወለላቸው]
ሀሎ!
ክቡር ሚኒስትር ውሳኔህ ጥሩ ነው፡፡ ወንድምህም ተሽሎታል፡፡ ጉዳዩ ይቋረጥ እንዳልክም አረጋግጠናል፡፡ ግን. . .
ግን ምን?
አንተ ጋ ያለውን መጀመርያ ጥቆማ የሰጠህ ኢንጂነር ማን ነው የሚባለው ሰው፣ ከሥራ ካላባረርከው በየሦስት ወሩ ወንድምህ ባንኮክ እየሔደ ምርመራ ማድረግ ይቸግረዋል፡፡
ምን አድርግ እያልከኝ ነው?
አባረው፡፡
ምን?
ሰውዬውን አባረው፡፡ የመጨረሻ ቀን ነገ! ቻው፡፡
[ከሥራ በመባረሩና የሙስና ምርመራው በመቋረጡ እጅግ ያዘነው ሰውዬና ክቡር ሚኒስትሩ በመስቀለኛ መንገድ ላይ መብራት አስቆማቸውና ፊት ለፊት ተፋጠጡ፡፡ ይተያያሉ፡፡ ሰውዬው ስልክ ደወለላቸው፡፡ እሳቸውም እንደሚደውል ገብቷቸዋል፡፡]
ጢ. . . . .ጥ. . . ..
‹‹እየተነጋገሩበት ስለሆነ ትንሽ ቆይተው ይሞክሩ››
ጢ. . . . . ጥ. . . .
‹‹መስመሩን እየተነጋገሩበት ስለሆነ ትንሽ ቆይተው ይሞክሩ››
ጢ. . . . . ጥ. . . .
‹‹ጥሪ . . . .አይቀበልም››
ጢ. . . . . ¬ጥ. . . . .
‹‹ጥሪ አይቀበልም››


