Friday, May 24th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የማኅበረሰብ ወግና ሕግ ለወጣቱ ምኑ?

E-mail Print PDF
User Rating: / 1
PoorBest 

በምሕረት አስቻለው

ጧት ከቢሮ ገብቶ ጥቂት እንደቆየ ሞባይል ስልኩ ጮኸ፡፡ የደወለችለት አብራው ዩኒቨርሲቲ የተማረችው፣ አሁንም የቅርብ ጓደኛው የሆነችው ናት፡፡ ማኅደር ታዬ በአንድ የመንግሥት መሥርያ ቤት ውስጥ የሰው ኃይል አደረጃጀት ኤክስፐርት ሆኖ በመሥራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ስልክ የደወለችለት ጓደኛው ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪዋን ካጠናቀቀች ጥቂት ወራት ሆኗታል፡፡ ሥራ በመፈለግ ላይ ብትሆንም የተለያዩ የአጭር ጊዜ ሥራዎችን ትሠራለች፡፡ ጓደኛዋ ጋ የደወለችው ለአንድ ድርጅት ውሂብ (ዳታ)የማሰባሰብ ሥራ በመሥራት ላይ በመሆኗ ነበር፡፡ ነገር ግን ለማኅደር የደወለችለት ውሂብ ለማሰባሰብ የሚረዳውን መጠይቅ እንዲሞላ አይደለም፡፡

‹‹ለአንድ ድርጅት መረጃ እያሰባሰበች እንደሆነ ከነገረችኝ በኋላ በቀጥታ የጠየቀችኝ የቤት ቁጥሬን ነበር፡፡ ለምን ስላት እኔ መሙላት የሚገባኝን መጠይቅ ራሷ ሞልታ የቀራት የቤት ቁጥሬ ብቻ እንደሆነ ነገረችኝ፡፡ ተገረምኩኝ፣ ደነገጥኩኝ፡፡›› በማለት ቆየት ብሎ ለምን እንደዚያ ማድረግ እንደመረጠች ሲጠይቃት መጠይቁ በጣም ብዙ ገጽ ያለው በመሆኑ ያንን ማንም ፈቃደኛ ሆኖ አይሞላልኝም ከሚል ፍራቻ በመነሣት መሆኑን እንደነገረችው ገልጾልናል፡፡

ምንም እንኳ መጠይቆችን አብዛኛውን ጊዜ በቁም ነገር የመሙላት ፍላጎት በብዙዎች ላይ ባይመለከትም፣ የመጠይቆቹ ገጽ መብዛትም በተወሰነ መልኩ መረጃውን በማሰባሰብ ላይ ለሚገኘው ሰው ቢከብድም ጓደኛው የመረጠችው አካሔድ በፍጹም ተቀባይነት ይኖረዋል ብሎ አያምንም፡፡ የተለያዩ ትልልቅ አገራዊ የጤናና የትምህርት፣ የመሳሰሉትም ጉዳዮች ላይ ለሚሠሩ ሥራዎች መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ የመረጃ ማሰባሰብም ሥራዎች በዚህ መልኩ የሚሠሩበት ሁኔታ መኖሩን ማወቅ ትልቅ ሥጋት እንዳሳደረበት አጫውቶናል፡፡ ‹‹ጥናት፣ ግኝት ተብለው የሚቀርቡ ጽሑፎችን እንዴት ማመንና መቀበል ይቻላል? በአመለካከት የተሻሉ፣ በዕውቀት ደረጃቸውም እንደዚያው ከፍ ያሉና ለኅብረተሰቡ ብዙ ይሠራሉ ከሚባሉ የተማሩ ወጣቶች የሚጠበቀው ይኼ ነው?›› ሲልም ጠይቋል፡፡

ሰው ሥራውን ሊያከብርና በአግባቡ ሊሠራ የግድ ሕግና ደንብ መቀመጥ የለበትም፡፡ ሕግ፣ ደንብና አሠራር በሥራዎች ክንዋኔ ላይ ትልቅ ሚና ቢኖራቸውም፣ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ፣ በየትኛውም የሥራ ልምድ ደረጃ የሚገኝ ሠራተኛ ሥነ ምግባር ሊኖረው በእያንዳንዱ ሁኔታ ውስጥ የሞራል ጥያቄም በኅሊናው ሊመላለስ እንደሚገባ  ማኅደር ይሰማዋል፡፡ 

ስሙን መግለጽ ያልፈለገ ሌላ ያነጋገርነው ወጣት፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ሕግና ደንቦችን የማክበር ነገር ከፍተኛ እንደነበር፤ በአሁኑ ትውልድ በስመ ሥልጣኔ የማኅበረሰብ ሕግና ደንቦች እየተጣሱ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ‹‹በተለይም ወጣቱ ሕይወቱን በብርሃን ፍጥነት መለወጥ ስለሚፈልግ በሥራው ብዙም የሞራል ጥያቄ ያለበት አይመስልም፡፡ የማኅበረሰብ ሕግ፣ ወግና ባህል ብዙ የሚያስጨንቀው አይመስለኝም፡፡››

እንደ እሱ አባባል፣ የሞራል ጥያቄዎችን ወደ ጎን በማለት፣ የማኅበረሰብ ሕግ፣ ወግና የሞራል እሴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩ ሲሆን፣ በምክንያትነት በርካታ ነገሮች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ የአኗኗር ዘዬ መቀየር፣ ዘመናዊነት ያመጣቸው ቴክኖሎጂዎችና አዳዲስ ባህሎች በተለያየ ደረጃ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል፡፡ በመቶኛ ሲያስቀምጠው ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ለሞራል እሴት፣ ለማኅበረሰብ ሕግና ወግ አይጨነቅም፡፡ ከዚህ ውስጥ አብላጫዎቹ ደግሞ ወጣቶች ናቸው፡፡

ሞራል ወይም የሞራል እሴት የምንለው አንፃራዊ ነገር ነው፡፡ ከአንድ ማኅበረሰብ ባህል፣ የአኗኗር ዘዬ፣ የሥልጣኔ ደረጃ፣ እምነትና ፍልስፍና ጋር ተያያዥነት አለው፡፡ በዚህም ምክንያት ይኼ ልክ፣ ይኼ ስህተት ለማለት ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ከግንዛቤ መግባት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ወጣትም በሞራል አንፃራዊነት ይስማማል፡፡

ወደ ማኅበረሰባችን በንጽጽር ስንመለከት ከቀድሞ ጋር ሲነፃፀር ማኅበረሰቡ ከባህል፣ ከወግና ከእምነታችን አንፃር ሕግ ብሎ ያስቀመጣቸው ነገሮች እየተጣሱ፣ ትክክል ተብለው የተቀመጡ ነገሮች እየተሸረሸሩ መሆናቸውን ይናገራል፡፡  እንደ እሱ እምነት ለመሸርሸሩ ምክንያት የሆነው ጎጂና ጠቃሚ የሚሆነው ባለማመዛዘን፣ ሊገልጹ ባለመቻሉ እንዲሁ ባህልን የመተው አዝማሚያ መታየቱ ነው፡፡

‹‹ባህል በተጠየቅ (በሎጂክ) ላይበየን ይችላል፤ ይህ ማለት ግን ትክክል አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ አያደርስም፡፡ ሁሉንም ባህል ትክክል ነው ወይም አይደለም ብሎ ማስቀመጥም አይቻልም፡፡ የእኛ የሞራል እሴቶች የተገነቡት በኢትዮጵያዊ ወግና ባህላችን ላይ ነው፡፡ ባህላችንን መጣል፣ ወጋችንን መተው ደግሞ የሞራል እሴቶቻችን እንዲጠፉ፣ ሰዉም እንዲሁ እንደፈቀደው በፈለገው መንገድ የፈለገውን ነገር እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡ ሁሉም ወግና ባህላችን ትክክል ነው ማለት አይደለም፤ ሁሉም ትክክል አይደሉም ብሎ መተው ግን ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ወደፊት ሳይሆን ወደ ኋላ ያስኬዳል፡፡ አጓጉል የምንላቸው በጊዜው እየወደቁና እየቀሩ የሚሔዱበት ሽግግርም አለ፡፡››