ጣሊያን በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በተነሳው ብጥብጥ ሳቢያ የስደተኞች ቁጥር ከአቅሟ በላይ ስለሆነባት ወደቧን መዝጋቷን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡
‹‹በቃ፤ ቦታው ሞልቷል፤›› የሚል መፈክር የተሸከሙ ሁለት ሰዎችም በአካባቢው ቁመው እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡ ላምፔዱሳ የተባለችው የወደብ ከተማ በብዙ ሺዎች በሚቆጠሩ ስደተኞች ተጨናንቃ ትገኛለች፡፡ ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ ብቻ ከሦስት ሺሕ በላይ ስደተኞች ወደ ወደቡ እንደገቡ ተጠቁሟል፡፡ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ከሊቢያና ከቱኒዚያ የሚወጡ ስደተኞች እንደሆኑ ያመለከተው ዘገባው፣ የጣሊያን መንግሥትም የወደቡን መጨናነቅ ለመቀነስ ስደተኞቹን ወደሌላ የማቆያ ማዕከሎች ለማዘዋወር ቃል ገብቷል፡፡
* * *
ሙባረክ የቤት ውስጥ እስረኛ መሆናቸው ተገለጸ
የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከነቤተሰባቸው የቤት ውስጥ እስረኛ መሆናቸውን የአገሪቱን የጦር ኃይል ጠቅሶ አልጄዚራ ዘግቧል፡፡ ከጦር ኃይሉ የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንትና ቤተሰባቸው ከአገር እንዳይወጡ መደረጉንና ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ አቅንተዋል የሚባለውም ሀሰት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሙባረክንና የቤተሰባቸውን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ መሸሽ የተለያዩ ሚዲያዎች ሲያወሩት የቆዩ ቢሆንም፣ አሁን የወጣው መግለጫ ግን ሰውዬው በቤት ውስጥ እስረኛነት እንዲቀመጡ መደረጉን የሚገልጽ ነው፡፡ ሙባረክ በሕዝብ አመፅ ከወረዱ በኋላ፣ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጪው መስከረም ወር ፓርላሜንታዊ ምርጫ ሊደረግ መሆኑን ዘገባው አስታውሷል፡፡
* * *
በየመን የጥይት ፋብሪካ ላይ በደረሰ ፍንዳታ 121 ሰዎች ሞቱ
በየመን የጥይት ፋብሪካ ላይ በደረሰ ፍንዳታ በጥቂቱ 121 ሰዎች ሲሞቱ ከ45 በላይ ደግሞ መቁሰላቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ አደጋው የደረሰው አቢያን በተባለች ግዛት ውስጥ ሲሆን፣ የግዛቷን ሪፐብሊካን ሆስፒታል ጠቅሶ ዘገባው እንዳመለከተው፣ የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ የጥይት ፋብሪካው ባለፈው እሑድ በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ውሎ እንደነበር ያመለከተው ዘገባው፣ ከሟቾቹም መካከል አብዛኛዎቹ በአካባቢው የነበሩ የፋብሪካው ጠባቂዎች ናቸው፡፡ ለወራት የቆየው የአገሪቱ ሕዝባዊ አመፅ አሁንም እልባት እንዳላገኘ ያመለከተው ዘገባው፣ በተለይ ባለፈው እሑድ በመንግሥት ኃይሎችና በአገሪቱ ውስጥ በሚገኘው የአልቃይዳ ክንፍ መካከል ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሯል፡፡
* * *
የሶማሊያ መንግሥት ጦር በርካታ ሥፍራዎችን ከአልሸባብ አስለቀቀ
የሶማሊያ ጊዜያዊ መንግሥት ጦር ኃይል በሞቃዲሾና በሌሎች አንዳንድ ሥፍራዎች በአልሸባብ ላይ በመውሰድ ላይ ባለው የማጥቃት ዕርምጃ ድል እየተቀዳጀ መሆኑን ዥንዋ ዘግቧል፡፡ የሶማሊያ የመከላከያ ሚኒስቴር ከአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ጋር በመተባበር በሞቃዲሾና በአገሪቱ ደቡባዊ ክፍሎች በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች በአልሸባብ ላይ በከፈተው ጥቃት፣ ቁልፍ ሥፍራዎችን ለመያዝ መቻሉ ተመልክቷል፡፡ ሰሞኑን በተወሰዱት ዕርምጃዎች ሆዳን፣ ሆውልዋደግና ቦንዳሌ የተባሉትን ወረዳዎች ጦሩ እንደገና መቆጣጠሩን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል፡፡


