Sunday, May 26th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ማለቂያ የሌለው ማመልከቻ?

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በአሰፋ እንዳሻው (ዶ/ር የሕግ ለንደን፣ ኢንግላንድ)

በነሐሴ ወር 2001 ዓ.ም. በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይድረስ ተብሎ የተላከውንና ወደ 600 የሚጠጉ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ለአገሪቱ ያስፈልጋሉ የሚለውን ዝርዝር ተመልክቼ ወዲያውኑ ፈቃደኝነቴን ገልጬ ነበር፡፡ ወሬው እንደተሰማ ዝርዝሩን ለማየት ብዬ አጠያይቄ ከሳምንታት ውጣ ውረድ በኋላ ሳገኘው አንድም ለምን በምስጢር እንደተያዘ ገርሞኝ ነበር፡፡ ሁለተኛም ይህን ያህል የሰው ኃይል ሳይኖር እንዴት ተብሎ ዩኒቨርሲቲዎቹ በራቸውን ከፍተው ሥራ እንደጀመሩ ሊገባኝ አልቻለም ነበር፡፡ መልሶም የምልመላው አጣዳፊነት ስላልተጠቆመ በተለይም የቀነ ገደብ ስላልተሰጠው ከአዲሱ የትምህርት ዓመት በፊት መምህራኑ መፈለጋቸውን ወይም አለመፈለጋቸውን የሚጠቅስ ስላልነበረ ይህ ተግባር በማን እጅ ይሆን የሚለው ይቆረቁረኝ ነበር፡፡

ቀደም ሲል ትምህርቴን በ1985 ዓ.ም. በለንደን ዩኒቨርሲቲ ካጠናቀቅሁ ጀምሮ በተደጋጋሚ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ለማስተማር ሞክሬ መግቢያ ቀዳዳ ሳላገኝ በመቅረቴ፣ በባዕዳን አገሮች ተሰማርቼ ስለቆየሁ ይህ ከላይ የተጠቀሰው ሰፊ የምልመላ ሥራ እውነትነት ያለው መስሎኝ ነበር፡፡ በ2002 ዓ.ም. እንኳን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድኅረ ምረቃ ዘርፉን አስፋፍቶ ባጭር ጊዜ 5000 ዶክትሬት ያላቸውን ተማሪዎች አመርታለሁ ባለበት ወቅት፣ እኔም ድርሻዬን ላበረክት በማለት በድረ ገጻቸው የተገኘውን መረጃ በመያዝ ማመልከቻ ልኬ መልስ በማጣቴ አርፌ አልተቀመጥኩም፡፡

አገሪቱን ከኖረችበት አዘቅት ማውጣት የሚቻለው የትምህርት ዘርፎችን በጥራትና በብዛት አጠናክሮ በመገኘት መሆኑን የአያሌ አገሮች ታሪክ ስለሚያስረዳና እኔም የዚያው አስተሳሰብ ተካፋይ ስለሆንኩ፣ ባለመታከት እንደገና ነሐሴ ላይ ማመልከቻዬን ለንደን በሚገኘው ኤምባሲ አማካይነት ለሚመለከተው ክፍል እንዲደርስልኝ አስገባሁ፡፡ የሕይወቴን ታሪክም ባጭሩ ገልጬ በተለይ በሐዋሳና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ከአንድ ዓመት ያላነሰ አገልግሎት ለመስጠት መፍቀዴን አስታውቄያለሁ፡፡

ወዲያውኑም ምናልባት የተጠቀሱት ዩኒቨርሲቲዎች በተለይ የሚፈልጉት የሕግ መምህር ምን ዓይነት ትምህርት እንዲሰጥ እንደሆነ ለማወቅ በኢንተርኔት አማካይነት ጥያቄዬን ሰደድኩ፡፡ የጎንደርና የመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁ የሚፈልጉት የሰው ኃይል ስለነበር ለእነሱም መልእክቴንና ጥያቄዎቼን ጫርኩ፡፡ እነዚህኞቹ ግን አንዳችም መልስ ሳይሰጡኝ ቀሩ፡፡ የሐዋሳው ዩኒቨርሲቲ ትንሽ መንቀሳቀስ አሳይቶ እገሌ ይህን ተመልክተህ መልስ ስጥ የሚል መመሪያ ማሰራጨቱን በግልባጩ አሳውቆኝ ወዲያው ዝምታው ሰፈነ፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ባስደነቀኝ ሁኔታ የተቀላጠፈና የተሟላ መልስ ሰጥተውኝ ጉዳዩን አጣድፈው ወደ ውሳኔ ለማድረስ ተራወጡ፡፡ ድሬዳዋ ርቀት ስላለውና አዲስ በመሆኑ ሲያስከትል የሚችለውን ልፋትና ቧጠጣ ሳልፈራ አስተዋጽኦ ላድርግ ካልኩ እነዚህንም መቀበል ይገባኛል ብዬ ወስኜ እየተጠባበቅሁ እያለሁ መጀመሪያ ሙሉ የአዎንታ ቃል ተሰጠኝ፡፡ ትንሽ ቆይቶ አንድ ሌላ ባለሥልጣን ስሙን እንኳን ሳያሳውቅ በፕሬዚዳንቱ ስም ቅጥ አምባሩ የጠፋ ደብዳቤ ላከልኝ፡፡ ፍሬ ነገሩ ለአገሪቱ ማኅበረሰብ አስተዋጽኦ ያላደረገ ሰው ፕሮፌሰር አይሆንም የሚል ነበር፡፡ በውስጤ ምናልባት ስሜ ቤንጃሚን ፍራንክሊን ቢሆን ኖሮ እጄን ስሞ ይቀበል ነበር ብዬ ማመልከቻዬን እንደሰረዝኩ አሳወቅሁ፡፡

አገር ለማየትና ዘመድ ለመጠየቅ በታኅሣሥ 2002 ዓ.ም. ኢትዮጵያ እስከመጣሁ ድረስ በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል የተላከው ማመልከቻ ፍጻሜ አላገኘም ነበር፡፡ በድፍኑ ወደ ኢትዮጵያ ስለተላከ ጠብቅ የሚል መልስ ግን በቃል ተሰጥቶኛል፡፡ ከዚያም ወዲህ በሰው በሰው ምን እንደደረሰ ስሰማ ምንም የተደረገ ነገር እንደሌለ አውቄያለሁ፡፡ ለካስ እንደኔው በዩኒቨርሲቲዎች ለማስተማር ፈቃደኛ የነበሩ ሌሎችም ምሁራን ስለነበሩ አንድ በኤምባሲው በተጠራ ስብሰባ ላይ መልስ ሳይሰጥ መቆየቱን እየተማረሩ መናገራቸውን ሰምቻለሁ፡፡

የዚህ ሁሉ ፍቺ ምን እንደሆነ የተለያዩ ሰዎች የሚሰነዝሯቸው ነገሮች አሉ፡፡ አንዳንዶች አንተን የመሰለ ብዙ ልምድና ከፍተኛ ደረጃ ያለው ሰው ከመቀበል ከናይጄሪያና ከህንድ የታዘዙትን ሊፈጽሙ የሚራወጡ ‹‹ዱዳዎችን›› መቅጠር ይመርጣሉ ይላሉ፡፡ በእርግጥም አገሪቱ ውስጥ ስለትምህርትና እውቀት ያለው ግንዛቤ አሁንም ቢሆን በአብዛኛው ወረቀት የያዘ ሰውን የሥራ ልምዱ ከግምት ሳይገባ በእኩል ዓይን ማየት ስለሆነ ይህ አባባል ፈጽሞ ከእውነት የራቀ አይደለም፡፡ የእኔ የሥራ ልምድና ትምህርት አዲስ ከተመረቀ የዶክትሬት ተማሪ የሚሻልበትን መንገድ ለተማሩትም ገና ግልጽ የሆነ አይመስልም፡፡ ከአንድ ሰው ጋር በቅርቡ ስናወራ እንግሊዝ አገር ስላሉ የእኛ ሰዎች ማለትም በመምህርነት ያሉትን ሲጠቅስ ዶ/ር እገሌ ይለኛል፡፡ እኔ ደግሞ ‹‹ያሉት በጣም ጥቂት ናቸው፤ ይህን ስም አልሰማሁም፤›› እላለሁ፡፡ ለነገሩ በብሪታንያ ከኢትዮጵያውያን መካከል በሕግ (ምናልባትም በሁሉም መስኮች) ከፍተኛው ማዕረግ ላይ ያለሁት እኔ ነኝ፡፡ በርከት ያሉ ጀማሪ መምህራን ብቅ ብቅ ማለታቸውም እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ወረቀትን ከወረቀት በማወዳደር ካልሆነ በስተቀር ያውም የተመረቅንበትን ዘመንና ከዚያ ወዲህ ያሳለፍነውን ሳይጨምር ያንዱ ስም በተጠራበት አፍ የሌላውን መድገም የማያስኬድ ነው፡፡

ከቀን ተቀን የማስተማር ግዴታቸው ውጭ የትርፍ ሰዓት ሥራ ሲያባርሩ ውለው ሲመሻሽ በተለያዩ ግላዊ አመሎች ተክነው ዓመታት ያስቆጠሩ ሰዎች ምናልባት የተመረቁበትንም ሙያ አጣርተው ላያውቁ እንደሚችል ገሃድ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዕድሜ ስንት ሰው የሕግ ፕሮፌሰር፣ ስንቱ ተባባሪ ነበር ቢባል ለዚህ ከፊል ምላሽ ይሆናል፡፡ በአንድ ወቅት በሕግ ትምህርት ቤት ንግግር ላድርግ ብዬ ስጠይቅ ‹‹እገሌን ለምነው›› መባሌን መቼም የማልረሳው ነው፡፡ ሰዎቹ ትዝ ቢላቸው ከሌላ አገር የመጣ ሰው ልምዱንና የምርምር ሥራውን ለማካፈል ፈቃደኛ ቢሆን እንወያይ ማለት የሚገባቸው እነሱ ነበሩ፡፡ ኋላቀርነታቸውን በማየት ደግሞ ፍንጩ ሲሰጣቸው ዘለው መያዝ የነሱ ፋንታ ነበር፡፡ ነገር ግን አስተሳሰባቸው የሚመራው ያው ፊታውራሪና ፊታውራሪ እኩል ነው ዓይነት ስለሆነ ተያይዞ ማዝገም ሆኖ ቆይቷል፡፡

በቅርቡ የወሬ ወሬ አንዱ ከተመረቀ ገና ዓመት የሆነው የሕግ መምህር የ4ኛ ዓመት ተማሪዎችን እንዲያስተምር መደረጉን ስሰማ አልተደነቅሁም፡፡ ከእሱ ይልቅ የአካባቢው የልምድ ጠበቃ አሥር እጥፍ ችሎታ ሊኖረው እንደሚችል ኃላፊዎቹ ስለማይገነዘቡ የወረቀት ማወዳደሪያ እይታቸው ውስጥ ተሰንቅረው የመጪውን ትውልድ ዕድል ይሸብባሉ፡፡

ማናቸውም የትምህርት ተቋሟት እውነተኛና በተግባር የሚረጋገጥ የሙያ ብቃት ያለው ሰው ካልመራቸውና በአናታቸው ላይ በየትምህርት ዘርፉ አኳያ ካልተመደበ፣ የተመራቂዎቹ ደረጃና ለኅብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ቁልቁል እየወረደ እንደሚሄድ የታመነ ነው፡፡ ደርግ ሥልጣን ከተረከበ በኋላ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት ውስጥ ይህ መሠረታዊ እምነት እየተጣሰ የተማሩበትን ደብተር ሳይለውጡ መምህራን የሆኑና በዚያው የቀጠሉ ሰዎች ለቁልቁለቱ መፋጠን ቋሚ አለኝታ ሆነው ኖረዋል፡፡

ዛሬ በአገሪቱ እንዳሸን የፈላው በከፍተኛ ትምህርት ገበታ ላይ ስንቶች ብቃት እንዳላቸው ማጠያየቅ እንደማያሻ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ ነገር ግን በዋና ተጠያቂነት የሚያዘው መንግሥት በመሆኑ እያደር እየባሰ ለሚሄደው የትምህርት ሥርዓት መናጋትና የጥራት መውደቅ አፋጣኝ መፍትሔ ከተግባር ጋር ካላሰመረ አገሪቱ ወደባሰ አዘቅት መግባቷ አሌ የሚባል አይሆንም፡፡

በሌላ በኩል ይህንኑ ምስቅልቅል ሁኔታ የሚመለከቱ ሰዎች የከፍተኛ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ከበቂ የሰው ኃይል ጋር ባለመቆራኘቱ ችግሩ ወቅታዊ ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ለእኔ ግን ትክክለኛ አይመስለኝም፡፡ የተያዘው አሠራር በመሠረቱ ጉድለት የሌለው በመሆን ከጊዜ ጋራ ይስተካከል ማለት ይቻል ነበር፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለውጥ አመጣለሁ፤ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብሎ ሲፎክር ‹‹ምን ተይዞ ጉዞ›› የሚለውን ጥያቄ የመለሰ አይመስለኝም፡፡ ስልክ ተደውሎ ‹‹ከፕሬዚዳንቱ ጋር ለመነጋገር ቀጠሮ ማድረግ እፈልጋለሁ፤›› ሲባል፣ ‹‹ቀጠሮ የምትይዘው ልጅ አሁን የለችም፤ በኋላ ይደውሉ፤›› የሚለው መልስ ለለውጡ ሥርነቀልነት ምስክር ሳይሆን ይቀራል?

አንጋፋው ዩኒቨርሲቲ ምርምርንና ማስተማርን ጎን ለጎን ሳያስቀምጥ ኖሮ በቅጽበት 21ኛው ክፍለ ዘመን እገባለሁ ሲል ምንኛ የዕቅዱን ተፈጻሚነት ራሱ እንደሚያምንበት የሚጠቁም መረጃ የለም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ግቢውን ከዳር እስከዳር ለዞረ ሰው በጉልህ የሚታይ የለውጥ አየር የለም፡፡ ወረቀት ላይ በእርግጥ የሰፈረ፤ ለለጋሽ ድርጅቶችና መንግሥታት የቀረበ የተጠናቀረ ጽሑፍ ይኖር ይሆናል፡፡ እንደገና አንዲት ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ባለው የመጽሐፍ መደብር የእኔን መጽሐፍ ሽጡልኝ ለማለት ጎራ ብዬ ሳለሁ ‹‹ማመልከቻ ጻፍ›› ስባል ያለሁበት ቦታ ጠፍቶኝ ነበር፡፡ እነሱ ነጋዴዎች መሆናቸው ቀርቶ ሹሞች ሆነው ሲገኙና አገልግሎት መስጠት ጭራሽ ጠፍቶባቸው መጻሕፍቱን ሁሉ ገንዘውና በቁልፍ ጠፍረው ይዘው ሳለ የለውጡ አየር እንዴት እንደነፈሰ አልገባኝም፡፡

በመጨረሻም የተማረውንና ልምድ ያካበተውን የኢትዮጵያ ተወላጅ በአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት መስተካከልና መጠናከር ላይ ማሳተፍ ሳይቻል እንዴት አቅም እንደሚገነባ አጠያያቂ መሆኑ መጠቀስ አለበት፡፡ ተባራሪ ፈረንጆችና አገራቸው ላይ ሥራ ያላገኙ የናይጄሪያና የህንድ ተወላጆች የወረቀቱን ፋብሪካ ለማንቀሳቀስ ቢረዱም፣ እውቀትና ልምድን በአገሪቱ አቅምና ይዞታ ልክ መጥነው ማካፈላቸው ብሎም ለግንባታው ተጋድሎ መስዋእት መክፈላቸው ሙሉ በሙሉ የተረጋገጠ አይደለም፡፡ የውጭ ኃይል ጠቀሜታ ቢኖረውም በዋናነትና በባለቤትነት ከመቆርቆር ጋር ተግቶ የሚሠራ ትውልድ በየተቋማቱ ካልተሰገሰገ ማጣፊያው የሚያጥር ጉዞ ይሆናል፡፡ በቅን ልቦናና በወገን ፍቅር አስተዋጽኦ ሊያደርግ ለተሰናዳው ክፍል ምላሹ እሺ ነገ፣ በዚህና በዚያ ሆኖ ከቀጠለ እንደተጠቀሰው ቁልቁለት መውረዱ አይገታም፡፡ በዚህ ላይ የዓለም ኢኮኖሚ የተሻሉ አዕምሮና ልምድ ያላቸውን ላፍ እንዲያደርጉ የሚያስችለው እንደ ኢትዮጵያ መሰል አገሮችን አይደለም፡፡

(ጸሐፊውን በዚህ አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡- This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it )