Wednesday, Jun 19th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

በወርቅ ኢዮቤልዩ ማግስትም የተነሣው አበበ ቢቂላ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በሔኖክ ያሬድ

‹‹ጀግናው ሻምበል አበበ ቢቂላ በ17ኛው የሮም ኦሊምፒክ ጌምስ ከባዱን የማራቶን ውድድር በባዶ እግሩ ሮጦ ለአገሩና ለአፍሪካ የመጀመርያ የሆነውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘበትን 50ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ምክንያት በማድረግ በተካሔደው የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር በመሳተፍዎ ይህ የምስክር ወረቀት ከታላቅ ምስጋና ጋር ተሰጥቶዎታል፡፡

መጋቢት 18 ቀን 2003 ዓ.ም.፤ አዘጋጅ ኮሚቴ››

ባለፈው እሑድ የአበበ ቢቂላ የሮም ኦሊምፒክ የማራቶን ድል 50ኛ ዓመት መታሰቢያ ሩጫን ውድድር ላጠናቀቁ ሯጮች የተሰጠ የምስክር ወረቀት ነው፡፡ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ (ከአዋቂ እስከ ሕፃን) በተካፈሉበት ውድድር የጎዳና 10 ኪሎ ሜትር ሩጫ ነበር፡፡ ተወዳዳሪዎች ስላልነበሩም ታስቦ የነበረው የአካል ጉዳተኞች የዊልቸር ሩጫም ሳይካሔድ ቀርቷል፡፡

መጋቢት 18 ቀን 2003 ዓ.ም. ዕለተ ሰንበት በተዘከረበት ዕለት ማለዳ፣ መስቀል አደባባይ ስደርስ ከአደባባዩ ላይ ያጋጠመኝ ሰሌዳ፣ ‹‹የሻምበል አበበ ቢቂላ 50ኛው ዓመት የሮም ኦሊምፒክ ድል መታሰቢያ ሩጫ ውድድርን ይሩጡ! ይዝናኑ! ድልን ይቀዳጁ›› የሚል ጽሑፍና የአበበ ቢቂላ ፎቶ ግራፍ የያዘ ነበር፡፡

የአበበ ቢቂላ ምስልም ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም. በሮም ጎዳናዎች በባዶ እግሩ በድል ፈረስ እየጋለበ ያለፈበትን 11 ቁጥር መለያውን የያዘ ነበር፡፡

በሺሕ የሚቆጠሩ ወንድና ሴት ሯጮችም ሁሉም የለበሱት መለያ፣ የሮሙን አበበ የሚያስታውሰው 11 ቁጥር ነበር፡፡

የክለብ አትሌቶችና የግል ተወዳዳሪዎች በተገኙበት ውድድር ዕድሜያቸው ከስምንት ዓመት አንሥቶ እስከ አሥራዎቹ ድረስ የሚሆናቸው ሕፃናትና ታዳጊዎች የአበበን መንፈስ ለመሰነቅ፣ አርአያነቱንና ታሪኩን ለማክበር ሮጠው ነበር፡፡

ዕለቱ ዓመታዊው የሰንበት ደብረ ዘይት በዓል ነበርና የበዓሉ የተለየ ምግብን የዳግም መነሣት ምልክት የኾነውን በቆልት እየተመገብን፣ የውድድሩን ፍጻሜ ጠበቅን፡፡ መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ አልፋ ኢንጂነሪንግና የጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከል ክለቦች በተሳተፉበት ውድድር የአሸናፊነቱን አክሊል፣ ‹‹የአበበ ቢቂላ ድል መታሰቢያ የወርቅ ሜዳሊያ›› ያጠለቀው በግል የተወዳደረው አፀዱ ጸጋዬ ነው፡፡ የፈጀበት ጊዜ 31 ደቂቃ ከ13 ነጥብ 58 ሰከንድ ሲሆን፣ 2ኛና 3ኛ ሆነው የብርና ነሐሱን ሜዳሊያ የተሸለሙት የአልፋ ኢንጂነሪንግ አሰፋ መንግሥቱና የጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጠኛ ማዕከሉ ተወዳዳሪ ገመቹ አዲስ ናቸው፡፡

በሁለቱም ጾታ የተካሔደው ውድድር በአንድነት በመጀመር የመጀመርያ በሆነው የእሑዱ ሩጫ፣ በሴቶች የፌዴራል ፖሊሷ ሌሊሴ ታደሰ በ35 ደቂቃ 29 ሰከንድ 1ኛ ሆና ወርቁን ስታገኝ፣ የአልፋ ኢንጂነሪንግ አትሌቷ የብርጓል በለጠ እና የመከላከያዋ አልማዝ ዓለሙ የብርና የነሐስ ሜዳሊያን ያስጠለቀቻቸውን የ2ኛና 3ኛነት ውጤትን አግኝተዋል፡፡

በቡድን አጠቃላይ ውጤት በሴቶች መከላከያ፣ በወንዶች አልፋ ኢንጂነሪንግ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ብሔራዊ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የአበበ ቢቂላ ቤተሰብ በጋራ ባዘጋጁት ውድድር የብሔራዊ ኦሊምፒክ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ ኪዳነ ማርያም የተገኙ ሲሆን፣ የአበበ ቢቂላ ልጅ የትናየት አበበ ቢቂላ የዋንጫ ሽልማቱን ለአሸናፊዎች ሰጥቷል፡፡

ሩጫውን ከፈጸሙት ተወዳዳሪዎች መካከል የድል በትግል 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሆኑት የ8 እና 9 ዓመት ሕፃናቱ ተስፋዬ ፒተርና ወንዱ መልስ ናቸው፡፡ ሁለቱም የ2ኛና 3ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ በታሪክ የሚያውቁትን፣ በቴሌቪዥን መስኮት በስፖርት መክፈቻ ላይ የሚያዩትን አበበ ቢቂላ ባስታወሰው ውድድር ላይ መሳተፋቸው ደስ ብሏቸዋል፡፡

የሊትል ቮይስ ኢትዮጵያን አካዴሚ የ4ኛ ክፍል ተማሪና የ11 ዓመቷ ስንታየሁ ጠንክርም ውድድሩን ፈጽማለች፡፡ በጣም መደሰቷንም ገልጻልኛለች፡፡

በካዛንቺስ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ  አካባቢ በጎዳና ላይ እንደሚኖር የነገረኝ በአሥራዎቹ መጨረሻ ላይ የሚገኘው በረከት ተሾመ ውድድሩ ተጀምሮ እስከሚያበቃ ድረስ የሮጠው በባዶ እግሩ ነበር፡፡ የአበበን ታላቅነት እየደጋገመ ይናገራል፡፡ ሕፃናቱን ለማበረታታት አብሯቸው መሮጡን ጠቅሶ፣ ለሕፃናቱም ሽልማት ይገባቸው ነበር ብሏል፡፡ መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ባደረገው ውድድር ወጣት ተማሪዎች እየዘመሩና እየጨፈሩ ‹‹አበበ አበበ›› እያሉ ሲያዜሙ የታወሰኝ፣ አበበ የሮሙን ድሉ፣ ከአራት ዓመት በኋላ በቶኪዮ ሲደግም፣ ሕዝቡ ያኔ የዘፈነለት “አበበ ቢቂላ ያገባሻል ጥላሁን ገሠሠ ይድርሻል” ዜማ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የክብር ዘበኛ ባልደረባ የነበረው ሻምበል አበበ ቢቂላ፣ የክፍሉ የሙዚቃ ኦርኬስትራ ድምፃዊ ከነበረው ጥላሁን ገሠሠ ጋር ቁርኝት ነበራቸው፡፡ ሁለቱም በ1950ዎቹ እንቁ ነበሩ፡፡ አበበ ቶኪዮ ላይ ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም. አሸንፎ እንደመጣ ኦርኬስትራው ከዘፈነው ሌላ ኅብረተሰቡ ለሥነ ቃል የበቃውን መንቶ ገጥሞላቸዋል፡፡

‹‹ያገባሻል ያገባሻል
አበበ ቢቂላ ያገባሻል
ጥላሁን ገሠሠ ይድርሻል›› ብሎላቸዋል፡፡  
በሮምና በቶኪዮ በተከታታይ የኦሊምፒክ ሁለት ወርቆችን በማጥለቅ የዓለማችን የመጀመርያ ሰው የነበረው ሻምበል አበበ ቢቂላ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ለማሸነፍ በሜክሲኮ ኦሊምፒክ በ1961 ዓ.ም. ቢሮጥም፣ በመጎዳቱ አቋርጦ በመውጣቱ ማሞ ወልዴ አርማውን አንሥቶ ድልን መቀዳጀቱ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያም በተከታታይ የኦሊምፒክን ማራቶን ሦስት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ መሆኗም ይዘከራል፡፡

ከሜክሲኮው የድል መልስ አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴ ከልዑካኑ መሪ አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ጋር በተመለሱ ጊዜ የተዘፈነለቸው ዘፈንም ባለፈው እሑድ ትዝ ብሎኛል፡፡

‹‹ማራቶን ማራቶን ማራቶን ልዕልቷ
አበበና ማሞ ሆኑ ባለቤቷ››
አበበ ከተጎዳ በኋላ በዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ውድድርም ባለድል ነበር፡፡
አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ መሮጡ ብቻ ሳይሆን፣ የመጀመርያው ጥቁር አፍሪካዊ ባለወርቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በሁለቱ የሮሙና የቶኪዮው የ17ኛውና 18ኛው ኦሊምፒያዶች፣ የኦሊምፒክም የዓለምም ክብር ወሰን ባለቤት እንደነበር እዚህ ላይ ማንሣቱ ተገቢ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት፣ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል የነበሩት ነፍስ ኄር ይድነቃቸው ተሰማ ስለ አበበ ቢቂላ ባለ ክብረ ወሰንነት ከ46 ዓመት በፊት ከቶኪዮ መልስ እንዲህ ተቀኝተውለታል፡፡
‹‹ከበረዶ የነጣጡ ጥርሶችን አብቅሎ
ይቆረጥማል ሰዓት እንደቆሎ››