Sunday, May 26th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ታላቁ የሚሌኒየም ግድብ ፕሮጀክት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያደንቀው፣ የሚያበረታታውና በቦንድ ግዢም የሚሳተፍበት ነው

E-mail Print PDF
User Rating: / 15
PoorBest 

መንግሥት ታላቁን የሚሌኒየም ግድብ ፕሮጀክት መርቆ አስጀምሯል፡፡ ትናንት፡፡ ይህ የኃይል ማመንጫ ግድብ በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አጠገብ በቤኒሻንጉል ጉምዝ የሚገነባ ነው፡፡ ከ70 እስከ 80 ቢሊዮን ብር በጀት ይጠይቃል፡፡ 5250 ሜጋ ዋት ያመነጫል፡፡ 62 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ይይዛል፤ ይህ ማለትም የጣና ሐይቅ እጥፍ ያህል ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ጥያቄም በከፍተኛ ደረጃ ይመልሳል፡፡

ይህን ፕሮጀክት መንግሥት ሲጀምርና ሲያቅድ በቂ ገንዘብ ኖሮትና ይዞ አይደለም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብም የፕሮጀክቱ ባለቤት እንዲሆንና ቦንድ እንዲገዛም በማመቻቸት ነው፡፡ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ሒሳብ በመክፈል የሚሳተፍበት ሥራ ሳይሆን ባለቤት በመሆንም የሚረባረብበት ነው፡፡

በርግጥ ከፍተኛ በጀት ስለሚጠይቅ ለማሰባሰቡም ቀላል አይሆንም፡፡ በርግጥ ፕሮጀክቱ እንዳይሳካ የሚሞክሩና የሚሸርቡ ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ትልቅና ቆራጥ ውሳኔ የሚጠይቅ ነው፡፡ የሚያኮራ ነው፡፡ የሚደገፍ ነው፡፡ ሕዝብም ቦንድ ይገዛል ብለን እናምናለን፡፡ አሳማኝ የልማት ፕሮጀክት ነውና፡፡

ይህን ፕሮጀክት እውን ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ግን እንቅፋት አያጋጥመውም ማለት አይደለም፡፡ ያጋጥመዋል ብቻ ሳይሆን አሁንም ሥራው እንዳይጀመርና እንዳይሳካ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

በፖለቲካ ለመቃወም ያመቸናል የሚሉ የተሳሳቱ አካላትና ውኃው ከተገደበ ይጎዳናል የሚሉ የተፋሰሱ አገሮች አባላት ተቃውሞ እያሰሙ ናቸው፡፡

የተቃውሞ ነጥባቸው ሦስት ዓይነት ነው፡፡ አንደኛው ገበሬን ያፈናቅላል የሚል ነው፡፡ በእርግጥም ያፈናቅላል፡፡ ነገር ግን የኃይል ማመንጫው እንዳይገነባ የሚያደርግ በቂ ምክንያት አይሆንም፡፡ የተፈናቀለው አርሶ አደር በቂና ብቁ ተለዋጭ ቦታ ከተሰጠውና ማቋቋሚያ በጀትም ከተመደበለት፤ የተፈናቀለውን አቋቁሞ ግንባታውንም አሳክቶ አገርና ሕዝብ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፡፡ 

ሁለተኛው እንደምክንያት ተደምሮ የሚቀርበው ደግሞ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በተለይ በዛፎች፣ በተክሎችና እንሰሳት ላይ አደጋ ያስከትላል የሚል ነው፡፡ አዎን፤ በዚህም አያስከትልም ማለት አይደለም፡፡ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ነገር ግን ጉዳቱን መቀነስና ጉዳቱን በተሻለ ደረጃ መተካትና ማካካስ ይቻላል፡፡

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኃይል ማመንጫ ዙርያ በተካሔደው ኮንፈረንስ ባደረጉት ንግግርም፣ እውነትም መፈናቀልና በአካባቢ ጥበቃ ላይ አደጋ ሊከሠት ይችላል፤ ነገር ግን መቋቋምና ማቋቋም በበለጠ የአካባቢውን ሁኔታ ለመፍጠር መንቀሳቀስ ይቻላል ብለዋል፡፡ በዚህ ዙርያ መንግሥት ያዘጋጃቸው መፍትሔዎችና ፕሮግራሞች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

ከትዝብት ላይ የሚከተው ጉዳይ ግን፣ በዓለም ደረጃ የኒኩሊየር አደጋ የአየር ሁኔታ መበከል ሲያስከትል ያልተቆረቆሩ አካላትና የኢንዱስትሪው ጢስ ዓለምን ሲያፍናት ምንም የማይሉ አካላት፣ በኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫ ይገነባልን ሲሰሙ የአየር ጠባይ ሲሉ ስንሰማ ይገርመናል፤ ያሳዝነናል፤ ያስቀናልም፡፡

ሦስተኛው የመቃወሚያ ምክንያት የኃይል ማመንጫ ግድብ ከተሠራ ሱዳንና ግብፅ የሚያገኙት ውኃ ይቀንስና ይጎዳሉ የሚል ነው፡፡ መልሳችን አይጎዱም ነው፡፡ ውኃውም መጓዙ ይቀጥላል፡፡ የኃይል ማመንጫዎች ውኃን አያስቀሩም፤ ለማሽከርከር ይጠቀሙበታል እንጂ፡፡ የኃይል ማመንጨቱ ተጠቃሚ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን እነሱዳንም ይሆናሉ፡፡ የትም ይባክን የነበረ ውኃ ተገድቦ ስለማይሔድ መጠኑ አይቀንስም፡፡ አፈሩ ይቀንስ እንደሆነ እንጂ፡፡

በዚህ አንፃር ሲታይም ግብፅና ሱዳን ፕሮጀክቱን ሊደግፉትና በጋራ እንሥራው ሊሉ ይገባል እንጂ ሊያዙበትና ሊተክዙበት አይገባም እንላለን፡፡

ስለዚህ፣ አሁንም ደግመን ደጋግመን የምንለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፕሮጀክቱን ይደግፍ፤ ያበረታታ፤ ቦንዱንም ይግዛ ነው፡፡

አፍሪካ ካላት የውኃ አቅርቦት ከ5 እስከ 7 በመቶ ብቻ ተጠቅማለች፡፡ አውሮፓ 75 በመቶ ተጠቅማለች፡፡ አሜሪካ 69 በመቶ ተጠቅማለች፡፡ አውሮፓና አሜሪካ ይህን ያህል አቅም ሲጠቀሙ ያልተጮኸ፣ አፍሪካ ይህን አቅም ልትጠቀም ስትል መቃወምና ማደናቀፍ ተገቢ አይደለም እንላለን፡፡

ከአፍሪካ አገሮችም የውኃ አገር የምትባለው አገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡ መጠቀሟን ትቀጥል እንላለን፡፡ ግድቦች በብዛት ይሠሩ እንላለን፡፡ ተፈናቃይ እንዳይባል ተጠንቅቀን፣ አካባቢው እንዳይወድም ተዘጋጅተን፣ ሌሎች አገሮችም ተጠቃሚነታቸው እንዳይቋረጥ አስበንና አቅደን ኃይል ማመንጨቱን እንቀጥል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ ኃይል ማመንጨት የምንቀጥለው ከውኃ ብቻ ሳይሆን ከጂኦተርማል፣ ከባዮ ጋዝና ከነፋስም ይሆናል ብለዋል፡፡ ጥሩ፤ ተግባሩ ግን ይቀጥል፡፡ አካባቢው እንዳይበላሽ ግን ለደን ልማቱ ከፍተኛ እቅድ ይዘናል ብለዋል፡፡ ጥሩ፤ ተግባሩ ግን ይቀጥል፡፡ እቅዱ 15 ሚሊዮን ሔክታር በደን እንሸፍናለን ይላል፡፡ ጥሩ፡፡

የኃይል ማመንጨቱ ግን ለሁሉም የልማት ዘርፍና ለኑሮ አስፈላጊ ነውና በታሰበው ደረጃና ፍጥነት የሕዝብ ተሳትፎ ባለበት ይቀጥል፤ ይበረታታ፤ ይደገፍ እንላለን፡፡

እግረ መንገዳችንን አንድ ትዝብት እንግለጽ፤ በአንድ በኩል የኢሕአዴግ መንግሥት እንደዚህ ዓይነቱ ትልቅ አገራዊና ሕዝባዊ ሐሳብና ፕሮጀክት ነድፎ ተንቀሳቅሶ ስናየው ጎሽ ያስብለናል፡፡ ትልቅ ሥራ ነው፤ ከጎናችሁ ነን ያሰኘናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከትናንሽና አላስፈላጊ ሥራዎች ውስጥ ገብቶ ከሕዝብ ጋር እየተጋጨ ሲውልና ሲያንስ፣ ሲሽመደመድም እናየውና ምን ሆነ ደግሞ፣ ምንነካው ደግሞ፣ ማን ነው የሚያሳስተው? እንላለን፡፡ አነሰ ስንል ይተልቅብናል፡፡ ተለቀ ስንል ያንስብናል፡፡

አሁንም የምንለው፣ መንግሥት እንደአሁኑ ሁሌም ትልቅ ነገር አስቡ፣ ሁሌም አገራዊና ሕዝባዊ ፕሮጀክት ንደፉ፣ አገርና ሕዝብን አኩሩ እንላለን፡፡

የአሁኑ ታላቁ የሚሌኒየም ግድብ የሚያኮራ ነው፡፡ የፈለገው ቢባል በርቱ ቀጥሉ እንላለን፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ስለሆነ ሕዝብ ይደግፈዋል፡፡ ያደንቀዋል፡፡ ያበረታታዋል፡፡ ቦንድም ይገዛል፡፡

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያውያን፣ ለኢትዮጵያውያን የሆነ ናሙና ፕሮጀክት ይሆናል፡፡ ይቻላልም፡፡