Wednesday, Jun 19th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ለዓባይ ግድብ ግንባታ ይሁንታችንን እንግለጽ

E-mail Print PDF
User Rating: / 24
PoorBest 

በመለስ ዓለም

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እደግመዋለሁ በገባር ወንዞች ላይ ሳይሆን በራሱ በዓባይ ወንዝ ላይ በ80 ቢሊዮን ብር ግድብ ልትገነባ ነው የሚለው ሰበር ዜና ከተበሰረና ኢትዮጵያውያንም የዜግነት ድርሻቸውን ይወጡ የሚል ደውል ከተሰማ በኋላ አናታቸውን የተመቱ ያህል የነዘራቸው ግብፆች ናቸው፡፡

ለመንግሥት የሚወግነውና በዓባይ ጉዳይ የሰላ ሂስ በመሰንዘር የሚታወቀው አልሚሰሪ አል አልዮም፣ ይህ ‹‹በእሳት የመጫወት›› ያህል ነው በማለት ነው የዘገበው፡፡ ግብፅ ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ ልታዋቅር ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ በኦሞ ወንዝ ላይ እያካሄደች ያለችው የጊቤ ሦስት ግድብ ጉዳይ ላይ ዘመቻ የከፈቱት የአካባቢ ደህንነት ተንከባካቢ ነን ባዮች፣ የዓለም የውኃ ቀንን አስታከው ግድቡን በመቃወም ፊርማ በማሰባሰብ ሥራ በዝቶባቸው ሰንብተዋል፡፡ ሳራ ሼንክር የተባለች የዚህ ፀረ ጊቤ ዘመቻ ፊት አውራሪ 400 ድርጅቶች አውሮፓና አሜሪካ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አቤት ማለታቸውን ተናግራለች፡፡ ከእነዚሁ ድርጅቶች ጀርባ ያለችው በዓባይ ውኃ ሱስ የምትጀነጅነው ግብፅ ነች፡፡ የግብፅም ሆነ የሌሎቹ ድርጅቶች ስጋቶች መንስዔ ኢትዮጵያውያን በጨለማ እንዲኖሩ ከመፈለግ የመነጨ ነው ከማለት ውጪ ሌላ ትርጉም የለም፡፡ በጊቤ ጉዳይ የኬንያ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ተባብሮ እየሠራ ባለበት ወቅት የሲቪክ ተቋማቱ ክስ ከጀርባው እንዲታይ ያስገድዳል፡፡ ናታሊን ሮትቻ ይልድ የተባለች ጋዜጠኛ ሰሞኑን ባቀረበችው መጣጥፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በእርግጥም ለአፍሪካውያን የሚጨነቁ ከሆነ ኢትዮጵያ ለማደግ የምታደርገውን ጥረት መደገፍ አለባቸው ብላለች፡፡ ለኢትዮጵያውያን የዓባይም ሆነ የጊቤ ጉዳይ የአገር ጥቅምን የማረጋገጥ ነው፡፡ የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይም ነው፡፡ ስለሆነም ብዙ ሆነው እንደ አንድ ሆነው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ደጉ ነገር ከዓባይ በላይ አብይ ነገር ምን ሊኖር ይችላል? በማስታወቂያው ዓለም ጥሩ ዕቃ አስተዋዋቂ አያስፈልገውም ይባላል፡፡ በዓባይ ጉዳይ ለዜጎች የቀረበው ጥሪ የዛኑ ያህል ነው፡፡ በዓባይ ላይ መዝፈን፣ መቃኘት ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ መንግሥትም ሁሉንም ኢትዮጵያ በዚህ ዙሪያ የማሰለፍ ግዴታ አለበት፡፡ ሁሉንም ጎራ የሚሰብር የአመለካከት ለውጥ ግድ ይላል፡፡

የግብፅ ዲፕሎማሲ
ለግብፅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መነሻና መድረሻው የናይል ውኃ ነው በሚለው ብዙ ወገኖች ይስማማሉ፡፡ በካይሮ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ሃሰን ናፋ ደግሞ የግብፅ የውጭ ግንኙነትን የሚወስኑት አገሪቱ ያላት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥና ታሪካዊ የውኃ ፍላጎት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ አስተያየት፣ የግብፅ ሕልውና ከድንበሯ በስተደቡብ ከሚኖሩ ወንዞች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ከጆኦግራፊያዊ አቀማመጥም አንፃር ግብፅ በታሪክ ወረራ የተፈፀመባት ከሶሪያና ፍልስጥኤም አቅጣጫ ነው፡፡ ማንም ሥልጣን ላይ ወጣ የፖሊሲው አስኳል ሆኖ ለዓመታት ቀጥሏል፡፡ ለግብፃውያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አርቃቂዎች የሰሜን ግንባርና የደቡብ ግንባር ብለው የሚከፍሉት ለዚህ ነው፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይና የፀጥታ ተቋማት  አሁን በሁለቱም ግንባሮች አደጋ ተጋርጦብናል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ በደቡብ ግንባር ነው የምትሰለፈው፡፡ በዚህም ሳቢያ የናይል ውኃ እንዲጠበቅ በተፋሰሱ አገሮች የሚደረግን ምንም ዓይነት ለውጥ በጥንቃቄ ይመለከታሉ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በፍልስጤም ራስ ገዝና ሶሪያ የሚኖሩ አካሄዶችንም በዓይነ ቁራኛ ይከታተላሉ፡፡

አብዛኛዎቹ ግብፃውያን ምሁራንም ቢሆኑ በሰሜን በኩል የተቃጣ ወረራ ባይኖርም በደቡብም በኩል የናይል ውኃ መፍሰሱን ይቀጥል እንጂ መንግሥት በሁለቱ አካባቢዎች ያሉ ለውጦችን መቆጣጠር አልቻለም ሲሉ ይነሳሉ፡፡ ይህንንም በምሳሌ ሲያስረዱ፣ የናይል ተፋሰስ አገሮች በኢትዮጵያ መንግሥት ስምምነት ፈርመዋል፡፡ አገሮቹ በናይል ጉዳይ የይገባኛል ጥያቄ እያነሱት ያለውም በእስራኤል በኩል በተደረገባቸው ጫና ሳቢያ ወይም ግብፅን ሆን ብሎ ለመጉዳት በማሰብ ሊሆን ይችላል ሲሉ የተሳከረ ትንተና ይሰጣሉ፡፡ እንደ ምሁሩ እምነት በመካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ሂደት ላይ እንድትለሳለስ ለማድረግ እስራኤል የእጅ አዙር ጫና የማድረግ ፍላጎት አላት፡፡ ምሁራኑ ይሁን ሲሉ ዋናው ዓላማቸው የላይኛውን የተፋሰስ አገሮች ከውኃው የመጋራት ሕጋዊ መብት አቅጣጫ ለማንሳት ለሕዝባቸው የሚግቱት ሐሺሽ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ግብፃውያን ወደ ውስጣቸው እንዳያዩ ሆነዋል፡፡ እስራኤል የዓባይ ትሩፋት ተቃማሽ እንድትሆን ሐሳብ በማቅረብ ረገድ የግብፅ መንግሥት በግንባር ቀደም ይጠቀሳል፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት አንዋር ሳዳት ለወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜናሂም ቤጊን ‹‹የናይል ውኃ በስዊዝ ካናል በኩል ኔጌቭ ወደተሰኘች የእስራኤል ከተማ በማድረግ የሱንም ሐውልት መትከል እንፈልጋለን፤›› በማለት በገፀ በረከትነት አቅርበዋል፡፡ ይሄ ነው ታሪኩ፡፡ የላይኛው የተፋሰሱ አገሮች በናይል የመጣ በዓይኔ መጣ የምትለው ግብፅ፣ ለእስራኤል ሁለት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ልስጥ ማለቷ ሳያንስ ዛሬ ደርሳ ሌላ ሴራ አለ ባይ ነች፡፡ ይህ ውኃ ሱስ የወለደው መቀባዠር ነው፡፡ ግብፃውያን በዚህ የተሻለ ከደቡብ አንፃር የፖሊሲ ለውጥ ይደረግ ማለቷ ባልከፋ፣ ነገር ግን ግብፃውያን ከጥልቅ እንቅልፋቸው ሲነቁ ያስተዋሉት የሁኔታዎች መለዋወጥን አምኖ መቀበል ነው፡፡

ሌላው የግብፃውያን ስጋት እንደ ደቡቡ ሁሉ በሰሜንም ስትራቴጂካዊ አደጋ አለ የሚል ነው፡፡ ከእስራኤል ጋር የካምፕ ዴቪድ ስምምንት ከተፈረመ ከ30 ዓመት በላይ ይሁን እንጂ የግብፅ ሰላም አስተማማኝ አይደለም፡፡ በአካባቢውም ሰላም የለም፡፡ ከአረፋት ሞት በኋላ የፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት (ፒ.ኤል.ኦ) ተሽመድምዷል፡፡ በተቃራኒው የግብፅ መንግሥት የሙስሊም ወንድማማቾች አጋር ነው የሚለው ሃማስ የበለጠ ተጠናክሯል፡፡ የፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር መንግሥትም የለም፡፡ ግብፅ በደቡብም ሆነ በሰሜን አካባቢው ከቅኝቷ ውጭ በመሆኑ አገሪቱ በአፍሪካ፣ ዓረቡና ሙስሊሙ ዓለም የምትደመጥ አይደለችም፡፡ ፕሮፌሰር ሀሰን ናፋ ለዚህ ተጠያቂ የሚያደርጉት የቀድሞውን የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክን ነው፡፡ ሙባረክ አፍሪካን ችላ በማለታቸው ግብፅ በአህጉሪቱ የነበራት ሚና ሞተ ሲሉ ምሁሩ ይናገራሉ፡፡ ግብፃውያን የአገራቸውን ሚና ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያና አልጄሪያ ወስደዋል በሚል ይብሰከሰካሉ፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ ሌሎችን ታሳድማለች ሲሉ ይከሳሉ፡፡ በዚህ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሐሙስ በዓባይ ወንዝ ላይ 5200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል ግድብ ለመገንባት ዝግጅት ማጠናቀቁን ሲገልጽ የሚፈጠርባትን ስሜት መገመት ይቻላል፡፡

ግብፅ በዓረቡ ዓለም አድራጊ ፈጣሪ ሆና ቆይታለች፡፡ የግብፅ መንግሥታት ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት መጀመር እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ በነበራት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሠረት የዓረብ ሊግን በመመሥረትና ዋና መቀመጫው ካይሮ በማድረግ ተፅዕኖዋን ስታሳርፍበት ነበር፡፡ ከካፒታሊስቱና ሶሻሊስቱ ጎራ ውጭ የገለልተኛ አገሮች ማኅበር በማቋቋም ተደማጭነትን ለማግኘት ሞክራለች፡፡ የካምፕ ዴቪዱ የሰላም ስምምነት እስኪፈረም ድረስም የፀረ አይሁድነት ግንባር መሪ ነበረች፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያና ሶሪያን እንደ አስፈላጊነታቸው በማፈራረቅ ተፅዕኖዋን ማሳረፍ ብትችልም፣ አሁን ቦታዋን ለሳዑዲና ኳታር አስረክባለች፡፡ ሌላ ራስ ምታት፡፡ በሙስሊሙ ዓለምም ከግብፅ ይልቅ ቀይ ምንጣፍ የሚዘረጋላቸው ቱርክና ኢራን ናቸው፡፡

እነዚህ ሁኔታዎች ተደራርበው ቀደም ሲል በሆስኒ ሙባረክ ጊዜም ሆነ አሁን ባለው ወታደራዊ አስተዳደር የግብፅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መፈተሽ አለበት የሚሉ ወገኖች በዝተዋል፡፡ አገሪቱ ካላት ጂኦስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ጋር የሚመጥን ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ሙከራዎች አለ፡፡ በዚህ ረገድ ዋነኛው ትኩረት አሁንም ናይል ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይና አገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ልዑላዊነታችን ዋስትና የአገር ውስጥ ጥንካሬያችን እንደሆነ በማያወላዳ መልኩ የሚገልጽ ሲሆን፣ ለዚህ የሚመጥን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ ሕዝቡም ደህንነቱ የሚጠበቅበት፣ ድህነቱን የሚዎገድበት ብቸኛው መንገድ በመሆኑ ሊረባረብ ይገባል፡፡

የፓን-አፍሪካ ዲፕሎማሲ
የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን በተባረሩ ወቅት የተመሠረተው መንግሥት የላይኛው የተፋሰሱ ስድስት አገሮች ስምምነት (Comprehensive Framework Agreement) ከፈረሙ በኋላ የደቡብ ግንባሩን ዲፕሎማሲያዊ መልፈስፈስ ይፈታልኛል ያለውን ጥረት ጀምሯል፡፡ የአል አህራም ጋዜጠኛ የሆነው ጋማል ንክሩማ (በአባቱ የጋና መስራች አባት ኩዋሚ ንኩሩማ ልጅ ሲሆን፣ በእናቱ ግብፃዊ ነው) ይህ ጥረት የፓን አፍሪካ ዲፕሎማሲ ሲል ሰይሞታል፡፡

ጋማል ንኩርማ ሰሞኑን እንደጻፈው፣ ሙባረክ አፍሪካን ችላ በማለት የአንደኛ ደረጃ ተማሪ የማይፈጽመውን ስህተት ሠርተዋል ብሏል፡፡ በዚህም ሳቢያ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች ስምምነቱን ሲፈርሙ የግብፅ-አፍሪካ ግንኙነትም ተጎድቷል ሲል ይሞግታል፡፡ ግብፅ ጀርባዋን ስትሰጥ አፍሪካውያን በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ የቱርክ፣ የኢራንና የቻይና ይዞታ ሆነዋል የሚል ግምገማም አለው፡፡

የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሳም ሻሪፍ የአዲሲ የዲፕሎማሲ ጥረትን ሱዳንን (ደቡብም ሰሜንም) መነሻ በማድረግ በሌሎች ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ግብፅ በኢኮኖሚና ፖለቲካው መስክ የበላይነቷን እንድታረጋግጥ ከሱዳንና ሌላ የአፍሪካ አገሮች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ሊኖራት ይገባል ባይ ናቸው፡፡

ሮናልድ ብሌየር በኒውዮርክ የብሩክሊን ኮሌጅ አማካሪ ሲሆኑ፣ ግብፅ በናይል ላይ ያላት ተፅዕኖ ከሶስት ምክንያቶች እንደሚመነጭ ይናገራሉ፡፡ እነዚህም በቅኝ ግዛት ሳቢያ የተፈረሙ ስምምነቶች፣ ከዓለም ልዕለ ኃያል አገሮችና ዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ያላት ድጋፍ (በርካታ ዜጎቿ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ይሠራሉ) ከሁሉም በላይ ደግሞ የላይኛው የተፋሰስ አገሮች ሰላምና መረጋጋት የራቃቸው መሆናቸው ነው፡፡ የግብፅ መንግሥታት የተፋሰሱን አገሮች ከውስጥ የሚጠምዳቸው ቀውስ ውስጥ በመክተት፣ በመደለል ብሎም የስነ ልቦና ጦርነት በማድረግ የናይልን ውኃ ለብቻቸው ሲጠቀሙ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ የግብፅ አካሄዶች ይለወጣሉ ተብለው ባይጠበቅም አዲሱ የዲፕሎማሲ መስክ ከተፋሰሱ አገሮች ጋር በንግድ ኢንቨስትመንት መተሳሰር የልማት እርዳት ድጋፍ መስጠት (ፅድቁ ቀርቶ. . .) በግብርናና አግሪ ቢዝነስ መስክ መሳተፍ የሚል ፓኬጅ አለው፡፡ ጋማል ንኩሩማ እንደጻፈው፣ ግብፅ የአፍሪካ ጉዳዮችን ብቻ የሚከታተል ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ሁሉ የመክፈት ፍላጎት አላት፡፡

ግብፅ አዲሱ ፖሊሲዋን በአፍሪካ ተግባራዊ ስታደርግ ተግባራዊነቱ የተጀመረው ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ውስጥ ነው፡፡ ግብፅ የደቡብ ሱዳን መገንጠልን አጥብቃ ስታወግዝ ብትቆይም፣ አሁን ተሯሩጣ ዕውቅና ሰጥታለች፡፡ ግብፅ የደቡብ መገንጠል ከተፋሰሱ ሌላ 10 አገር መፍጠር ነው፤ ሱዳንንም ያዳክማል የሚለው ስጋቷን ይዛ ነው ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ የጀመረችው፡፡  ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ባቀረበው ሪፖርት ግብፅ ከደቡብ ሱዳን ያላትን ተፅዕኖ ለመጠበቅ ከካርቱም በላይ ትሰራለች ይላል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ግብፅ በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳል ቫኬር ተቃዋሚዎች ናቸው የሚባሉትን የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ላም አኮልና በቅርቡ ነፍጥ ያነሱትን ጄኔራል ጆርጅ አቶር ትጠቀማለች፡፡

ሱዳን ትሪቡን እንደዘገበው ይህ የግብፅ ዘመቻ የደቡብ ሱዳን ይሁንታ ያገኘ መስሏል፡፡ ደቡቦች ሱዳንና ግብፅ በናይል ላይ የፈረሙትን ስምምንት እናከብራለን ብለዋል፡፡ የሌሎች የላይኛው ተፋሰሱ አገሮች ጋር መልካም ግንኙነት ያላቸው ደቡብ ሱዳኖች እንዴት ከኡጋንዳ፣ ኬንያና ኢትዮጵያ የተለያ አቋም ሊይዙ ቻሉ? ዋናው ነገር ስድስት አገሮች እስከፈረሙ ድረስ ለውጥ  አያመጣም፡፡

የውኃ ደህንነት ፖለቲካ

ታላላቆቹ የዓለም ሥልጣኔዎች መሠረታቸው ከወንዞች ዳር ነው፡፡ ጤግሮስ፣ ኤፍራጠስ፣ ሚሶፖታምያ እንዲሁም ‹‹የናይል ስጦታ›› ተብላ ከምትታወቀው ግብፅ እስከ የዋንግ (ቢጫ ባህር) የዚህ ታሪካዊ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ጥንታዊ መንግሥታት ውኃን ጥቅም ላይ ለማዋል አዳዲስ ቴክኖሎጂን መጠቀም ብቻ ሳይሆን ውኃውን በብቸኝነት ለመቆጣጠር ተንቀሳቅሰዋል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኢትዮጵያ ወንዞቿ ከጥቅማቸው ይልቅ ጠላት ነው ያፈሩላት፡፡ የውኃ ማማ የሚል ስያሜ ብቻ ነው ያተረፈችው፡፡ በዓባይም ሆነ በጊቤ የታየው/የሚታየውም ይኸው ነው፡፡ ግብፅና አጋሮቿ እንዲሁም እሷ የምታሽከረክራቸው ኢንተርናሽናል ዎተርስ የመሰሉ የተሰኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተግባር የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡

በያዝነው ዘመን ውኃን የመሰሉ ሀብቶች ለአንድ አገር ፀጥታ አስተማማኝ መሆንና አለመሆን አስፈላጊ አንደሆነ ይናገራል፡፡ በካሮኒጌ የዓለም አቀፍ ሰላም ተቋም የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ጄ.ሲካ.ቲ. ማቲው “Redefining Security” በሚል ርዕስ በቅርቡ ባስነበቡት ጽሑፍ፣ በአንድ አገር ፖለቲካዊና ማኅበራዊ መረጋጋት እንዲኖር በዚህ ሀብትና የሕዝብ ቁጥጥር መካከል የተመጣጠነ ዕድገትና አጠቃቀም መኖር አለበት፡፡ የዓባይ ጉዳይም መታየት ያለበት በዚህ መነፀር ነው፡፡ ኢትዮጵያ መስማት ትፈልጋለች፡፡ ለዚሁ ደግሞ የኢኮኖሚ ዕድገቱን የሚመግብ አስተማማኝ ኃይል ያስፈልጋል፡፡

የግብፅ መንግሥት የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ከናይል ውኃ አጠቃቀም ጋር የተያያዘ እንደሆነ እየተናገረ ስለሌሎቹ አገሮች ብዙም ግድ የለውም፡፡ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ የአካባቢው አገሮች የሚያቀርቡት ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት መፍትሔም ቁብ የለውም፡፡ ይባስ ብሎ እኛ እንጥገብ እናንተ ተራቡ ይላል፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት የወጣው የአገሪቱ አራት የውኃ ሀብት አጠቃቀም ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ካቀረበችው አራት አማራጮች ውስጥ ሁለቱ የናይልን ውኃ በተገቢው መንገድ መጠቀምና ሌላ የውኃ አማራጮችን መፈለግ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ግብፃውያን ዘንድሮ የሚጠቀሙት የመስኖ ዘዴ ሳይቀር የፈርኦኖቹን ዘመን ነው፡፡ ተጨማሪ የውኃ አማራጮችን መፈለግ ቢልም በዚህ ደረጃ እዚህ ግባ የሚል ውጤት አልታየም፡፡  የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር መድኃኔ ታደሰ በአገሮች መካከል ሊከሰት የሚችልን ግጭትን ለማስወገድ አንድ አገር ከሌላው የሚያገኘው ጥቅም ማስተሳሰር አስፈላጊ እንደሆነ የሚናገሩት ለዚህ ነው፡፡

ግብፆች ከዚህ ይልቅ የመረጡት አብዛኛውን ውኃ የምትሰጣቸው ኢትዮጵያ በውስጥም በውጪም መወጠር ነው፡፡ መንገዱ ቢለያይም ዓላማው ኢትየጵያን ማቆርቆዝ ነው፡፡ ይህ ሰይጣናዊ አስተሳሰብ  ቢሆንም ቢቻል ውኃው የትብብር ምንጭ መሆን በቻለ ነበር፡፡

የሚሊኒየም ግድብ

የአፍሪካ የደህንነት ጥናት ተቋም አፍሪካ በመጪዎቹ 40 ዓመት ያላትን ተስፋ በተመለከተ በቅርቡ ባሳተመው መጽሐፍ፣ በመጪዎቹ አሥርት ዓመታት ውስጥ በአገልግሎትና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ሽግግር ከሚያደርጉ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ዋነኛዎቹ ኢትዮጵያና ናይጄሪያ ናቸው ይላል፡፡ እንደ በርካታ የአኅጉሩ አገሮች ሁሉ ሊያስቡበት የሚገባው ደግሞ የኃይል አቅርቦት ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ባለፋት ጥቂት ዓመታት በዚህ ረገድ ያለውን ችግር ለመቅረፍ አዎንታዊ እንቅስቃሴ ማድረጓ ቢታወቅም ፍላጐቷን አላሟላችም፡፡ አሁንም መብራት የሌላቸው መንደሮች አሉን፡፡ የእነዚህን መንደሮች ብርሃን ያለብሳሉ ተብለው ከሚታሰቡ ፕሮጀክቶች አንጋፋው በዓባይ ወንዝ ላይ የሚሠራው ታላቁ የሚሌኒየም ግድብ ዋነኛ ነው፡፡ ልብ አርስ ዕቅድ ነው፡፡ ይህ ዕቅድ ስትራቴጂካዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡

ይህ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እስኪተነፍሱት ድረስ ጥብቅ ሚስጢር ሆኖ በመቆየቱ እንኳን ለግብፆችና ለኢትዮጵያውያንም ድብዕዳ ነው የሆነባቸው፡፡ የግድቡ መሥራት ታላቅ ፖለቲካዊ መልዕክት አለው፡፡ በገንዘብ ድጋፍ ሰበብ አታስሩንም እንደ ማለት ነው፡፡ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ እንዳሉት፣ የግድቡ ወጪ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፍነው መሆኑ ደግሞ ሌላው የኩራት ምንጭ ነው፡፡ መንግሥት በጣና በለስን ከሰባት ቢሊዮን፣ ተከዜን ደግሞ ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በራሱ አቅም ለመሥራት ያዳበረው አቅምና ተሞክሮ ለዚህ ሊጠቅመው ይችላል፡፡ በአብዛኛው በራስ የኢትዮጵያውያን ምሁራን የሚሰራ መሆኑ ትንግርት የሆነባቸው ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ ያም ሆኖ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የቀረበው ጥሪ ከባድ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ሁሉም የመንግሥት ጩኸት ሊጮህ ይገባል፡፡ ዓባይን ለመገደብ የማይውል ገንዘብ ለመቼ ይሆናል? ምንም ዓይነት ልዩነት ቢኖር በዓባይ ጉዳይ ኢትዮጵያዊ ለወዳጅም ለጠላትም አንድነቱን ማሳየት ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ የምታለማው ማንንም ለመጉዳት አይደለም፡፡ አገሪቱ ከድህነት መውጣት አለባት፤ በዓባይ ላይ የሚገነባው ይህ ግድብ ከኃይል ማመንጨቱ ጎን ለጎን ለግብፅና ሱዳን በመስኖ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገሩን እንደሚወድ ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንዴ በመንግሥትና አገር፣ በመንግሥትና ፓርቲ ወዘተ. ያለው ትርጉም የተዘበራረቀበት ዜጋ ቁጥር አነስተኛ ላይሆን ይችላል፡፡ ግብፆች አሁን ባሉበት ቀውጢ ወቅት ሳይቀር በናይል ጉዳይ አንድ ነው ቋንቋቸው፡፡ ኢትዮጵያውያንስ? በዓባይ ላይ ተዘፍኗል፣ ተገጥሟል፡፡ እሱ ይብቃን፡፡ ለሚሌኒየሙ ግድብ ተግባራዊነት ይሁንታ የመግለጽ የሞራል ግዴታ የሁሉም ዜጋ ነው፡፡ ዓባይ አብይ አጀንዳ ነው፡፡

የፖለቲካ ቆረጣ

የግብፅ የመስኖ የውኃ ሀብት ሚኒስቴር ዶ/ር ሀሰን አልአጠፍ በዓባይ ግድብ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ማብራሪያ እንጠብቃለን ብለዋል፡፡ የምን ማብራሪያ? አንሰጥም ቢባሉስ ምን ስለሆኑ ነው ማብራሪያ የምንሰጣቸው ብንል፣ እብሪት ይመስልብን ይሆን?  ግብፅ በናይል ጉዳዩ የትኛውን ማብራሪያ ሰጥታን ታውቃለች፡፡ ይህ ግብፆች ለራሳቸው ካላቸው የተሳሳተ ግምትና ለሌሎች አገሮች ካላቸው ንቀት ይመነጫል፡፡ ሃቅ ያንቃል፡፡ ለግብፅ የሚበጃት ከዕውነታው ጋር መታረቅ ነው፡፡ የጥንትዋ ግብፅ ዛሬ ያ አቅም የላትም፡፡ ኢትዮጵያም እየተለወጠች ናት፡፡ ለግብፅ በዓባይ ላይ ተባብሮ በመሥራት ኢትዮጵያ የምታካሂዳቸው ግንባታ ተጠቃሚ መሆን የመጀመሪያ አማራጭ ነው፡፡ በዓለም የገንዘብ ተቋማትና አገሮች ላይ ተፅዕኖ ማድረግ እንደማያዋጣት ልትረዳ ይገባታል፡፡ ሌላኛው አማራጭ ጦርነት ነው፡፡ ጦርነት ለማንም ጠቃሚ አይደለም፡፡ ግብፅም ጦርነት እንደማያዋጣት ታውቃለች፡፡ ግብፅ ልታደርግ የምትችለው የእጅ አዙር ጦርነት ነው፡፡ የተለያዩ አሸባሪ ኃይሎችን መጠቀም የምትችለው ደግሞ በኢትዮጵያውያን መሀከል አለመግባባት ሲኖር ነው፡፡ ይህን ለማስወገዱ መንግስት ሆደ ሰፊ መሆንና አለመግባባቶቹን በመነጋገር መፍታት ይጠበቅበታል፡፡

ዶ/ር ካሊድ አሊ የተባሉ ፀሀፊ በአል አህራም ጋዜጣ ሰሞኑን ባቀረቡት ጽሁፍ፣ የግብፅ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ላይ ተፅዕኖ ከማሳደር በተጨማሪ ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ድጋፍ የሚሰጡ አገሮችን በጠላትነት መፈረጅ ይገባል ብሏል፡፡ ሰዎቹ ምን ነካቸው? የትኞቹን አገሮች? በተጨማሪም ግብፅ ኤርትራ ውስጥ የጦር ሠፈር በመመስረት ግድቦቹ ላይ ጥቃት በአውሮፕላን ለመፈፀም ያስችላታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራ ውስጥ ይህ ሲፈፀም እንዴት ዝም ብሎ ያያል?  የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሰፊር ሙንሃ ባኩም፣ ግብፅ በተፋሰሱ አገሮች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የልዑካን ቡድን ወደ ኡጋንዳ ለመላክ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡ የመጀመሪያ ነገር እንኳን ወደ ካምፓላ ገነትም ሆነ ጀሃነም ልኡክ ቢላክ ቢላክ ትርጉም የለውም፡፡ ምክንያቱም ግድቡ ከስምምነቱ ጋር ምንም አይያያዝም፡፡ ሁለቱ የተለያዩ ጨዋታዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ የሰራችው የግብፆች ትኩረት በላይኛው የተፋሰስ አገሮች ድርድር ላይ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ቆረጣ ይሆን? ምንም ተባለ ምን? ከአሁን በኋላ  ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት ግስጋሴ መቁልበስ አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያውያንም በድህነታቸው መኖር አይፈልጉም፡፡ በቃቸው፡፡ ተስፋቸው ዕውን ሆኖ ማየት ይፈልጋሉ፡፡
ሰላም!!  This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it