Tuesday, Jun 18th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

የባሰ ሳይመጣ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በናታን ዳዊት

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብቷ በአፍሪካ ቀዳሚውን ደረጃ በመያዝ የምትጠቀስ አገር ብትሆንም በዚህ ሀብት መጠቀም የምትችለውን ያህል ያልተጠቀመች መሆኑም እንዲሁ ሲወሳ ቆይቷል፡፡  ከእንስሳት ሀብት ጋር በቀጥታ ተያያዥ የሆነው የወተትና የወተት ተዋፅኦ ምርቶችም የአገሪቱን ሀብት በሚመጥን መልኩ እየተመረቱ አይደለም፡፡ በተለይ በከተሞች አካባቢ በቂ የሆነ የወተት አቅርቦት እንደሌለ ይታመናል፡፡ አቀርቦቱ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው እየታየ ያለው የዋጋ ዕድገት ለአብዛኛው ሸማች የተመቸ አልሆነም፡፡ 

በከብት ሀብቷ የምትታወቀው አገር በወተትና በወተት ተዋፅኦ ምርቶችን በበቂ ሁኔታ ማምረት አለመቻሏ የወተት ምርትን ሊተኩ ይችላሉ የሚባሉ የተለያዩ ስያሜ ያላቸው የዱቄት ወተቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡም እያስገደደ ነው፡፡

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከውጭ የሚገቡ የዱቄት ወተቶች ወይም ተመሳሳይ ምርቶች በዓመት በአማካይ ከ20 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ወጪ ያስወጣሉ፡፡ ይህ አሃዝ የሚያሳየን ባለን ሀብት በአግባቡ ያለመጠቀማችንና ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለን መሆኑን ነው፡፡

እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች በአሁኑ ወቅት አንድ ሊትር ወተት በአማካይ 10 ብር ይሸጣል፡፡ በወር ሲሰላ 300 ብር ይደርሳል፡፡ የታሸጉ የወተት ምርቶች ደግሞ የመሸጫ ዋጋቸው ከዚህ የሚበልጥ ስለመሆኑም ገበያው ይነግረናል፡፡

የወተት ዋጋ የዚህን ያህል ዋጋ ማውጣቱ እንዲሁም የዚህን ያህል ለመጨመሩ የተለያዩ ምክንያቶች የሚሰነዘሩ ቢሆንም፣ ሁሉም ምክንያት ትክክል ነው ወይም አይደለም ብሎ ለመደምደም የሚያስቸግር ይሆናል፡፡

የሆነ ሆኖ የወተት ዋጋ መጨመር በወተት ተዋጽኦ ምርቶችም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ሸማቹ በወተት ተዋጽኦ ምርቶች ላይ ሰምቶ የማያውቃቸውን ትልልቅ የዋጋ ቁልሎች እያዳመጠ ነው፡፡

በሰሞኑ ገበያ አንድ ኪሎ የምግብ ቅቤ 120 ብር ደርሷል፡፡ አንድ ኪሎ አይብ ደግሞ 30 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ የገበታ ቅቤም እንዲሁ ዋጋው እያደገ መጥቷል፡፡ ከሁለት ዓመታት ወዲህ ያለው የገበያ ልዩነት ብቻ ከ30 እስከ 40 በመቶ የዋጋ ጭማሪዎች ታይተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚታወቁ የወተት ማቀነባበሪያዎች ከአዲስ አበባ በጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙ እንደ ሠላሌ ያሉ ከተሞች በመሄድ አንድ ሊትር ወተት ከገበሬዎች በአምስት ብር በመግዛት አሽገው በእጥፍ ይሸጣሉ፡፡ በከተሞች አካባቢ በግለሰብ የወተት አቅራቢዎች በኩልም የሚሸጠው ወተት ቢሆን የወተት ማቀነባበሪያዎች አሽገው የሚሸጡበትን ያህል ዋጋ እየደረሰው ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወተትም ሆነ የወተት ተዋፅኦ ምርቶች ዋጋ የዚህን ያህል የተወደደበት፣ እንዲሁም ዋጋው በየጊዜው እየጨመረ የመጣበት ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው የመኖ ምርት ዋጋ መናርና የአቅርቦት እጥረት ነው፡፡ በተለይ በከተሞች አካባቢ ያሉ የወተት አቅራቢዎች ለሚያመርቱት ወተት ለከብቶቻቸው በመኖነት ከሚጠቀሙት ምርቶች መካከል ትልቁን እጅ የሚይዘው ፉርሽካ ነው፡፡ በሰሞኑ የገበያ ዋጋ አንድ ኩንታል ፉርሽካ ከ300 ብር በላይ ደርሷል፡፡ ሌሎች የመኖ ዓይነቶችም በተመሳሳይ መልኩ ዋጋ ጨምረዋል፡፡ ከዚህም በኋላም ቢሆን ይህ የዋጋ ጭማሪ እጥፍ መሆን፣ ለወተት አቅርቦትና ዋጋ መናር ምክንያት ይሆናልም እየተባለ ነው፡፡ የወተት አልሚዎች የሚያቀርቡት ምክንያት ትክክል ነው ሊባል ቢቻልም፣ የፉርሽካ ዋጋ የዚህን ያህል ዋጋ የማውጣቱ ጉዳይ ግን አጠያያቂ ነው፡፡

ፉርሽካን የሚያቀርቡ ተቋማት፤ ፉርሽካ ላይ የዚህን ያህል ዋጋ ለመጨመራቸው የሚሰጡት ምክንያት የስንዴ ዋጋ ተወደደ፣ የምናመጣበት ቦታ ሩቅ ሆነ የሚልና የትራንስፖርት ዋጋ መጨመር ነው፡፡ ነገር ግን የስንዴ ዋጋ ተወደደ በተባለበት ወቅት እንኳን የፉርሽካ ዋጋ አሁን እየተሸጠበት ከሚገኘው ዋጋ ከግማሽ በላይ ያነሰ ነበር፡፡

አሁንም ቢሆን አንድ ኩንታል ስንዴ ከ600 እስከ 800 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በስንዴ አምራችነታቸው ከሚታወቁ አካባቢዎች አንዱ በሆነው አርሲ (አሳሳ) ደውዬ እንዳረጋገጥኩት ደግሞ አንድ ኩንታል ስንዴ ከ520 እስከ 540 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ የገበያ ዋጋው ይህ ከሆነ ፉርሽካ ብቻውን የጥሬ ስንዴውን ዋጋ ለመንጠቅ እሽቅድምድም የጀመረ እስኪመስል ድረስ የዚህን ያህል ዋጋ ማውጣቱ ተገቢ ነው ሊባል አይችልም፡፡

ጉዳዩ አነጋጋሪ ቢሆንም በስፋት እየተነገረ ያለው ግን በዱቄት ምርቶች ላይ የተጣለው የዱቄት የዋጋ ገደብ ለፉርሽካ ዋጋ እንዲጨምር ማድረጉን ነው፡፡ የዱቄት አምራቾች ዋጋ ገደቡ መጣል የትርፍ መጠናቸውን ስላጣበበው ቀረብን የሚሉትን ትርፍ በተዘዋዋሪ ለማግኘት የተጠቀሙበት አግባብ ያልሆነ መላ ተደርጎም ይወሰዳል፡፡

ይህ አመለካከት እውነት ስለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሆነውም በፉርሽካ ላይ ፈጣን የሆነ የዋጋ ለውጥ የታየው መንግሥት ዱቄት በዚህን ያህል ዋጋ መሸጥ አለበት ብሎ ካወጀበት ጊዜ ወዲህ ነው፡፡

የፉርሽካ ዋጋ መጨመር ብዙም ጉዳት የለውም በሚል ጉዳዩ ትኩረት ካልተሰጠው ደግሞ ይዞት የሚመጣው ጣጣ የወተትና የወተት ተዋፅኦ ምርቶች ላይ ዋጋ ለመጨመር ትልቅ ሰበብ ሊሆን የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ለጊዜው የፉርሽካን ብቻ አነሳን እንጂ በጥቅሉ የእንስሳት መኖ እጥረት ትኩረት ካልተሰጠው ትልቅ ችግር እየሆነ መምጣቱ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ አንዳንድ ጥናቶችም ይህንኑ ችግር እያመለከቱ ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ በቅርቡ የዶሮ አርቢዎች በቂ መኖ ማጣት፤ ቢያገኙም የዋጋው ውድነት ከሥራ እንዲወጡ እያደረጋቸው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት ዞሮ ዞሮ ለእንስሳትና ተዋጸኦ ምርቶች መመናመንና ከፍተኛ ለሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚመራ በመሆኑ፣ መንግሥት ጊዜ ሳይሰጥ ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን መጠቆሙ መልካም ነው፡፡