- የድንጋይ መፍጫ ገዝቶ ወደ ሥራ ሊገባ ነው
በዳዊት ታዬ
ሐበሻ ኮንስትራክሽንና ማቴሪያልስና ልማት አክሲዮን ማኅበር ከአንድ ወር በፊት አሸንፎ ሊረከብ የነበረው ቦታ ሲሰረዝበት፣ አንድ የግለሰብ ቦታና በመሥራት ላይ የሚገኝ የድንጋይ መፍጫ ድርጅት ገዝቶ ወደ ሥራ ሊገባ ነው፡፡
የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሊቀመንበር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቡልቡላ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ክፍለ ከተማው ባወጣው የሊዝ ጨረታ መሠረት 547 ካሬ ሜትር ቦታ በአንድ ካሬ 2759 ብር ከ55 ሳንቲም አሸናፊ መሆኑ ተገልጾለት ነበር፡፡
ሆኖም አክሲዮን ማኅበሩ ለቦታው የሰጠው ዋጋ በአካባቢው ካሉ ተመሳሳይ ቦታዎች ከተሰጠው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር የሚያንስ ነው በመባሉ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ሆኖም ግን አክሲዮን ማኅበሩ የዚህ ቦታ አሸናፊነቱ ቢሰረዝበትም፣ በግንቦት ወር ግንባታ ለመጀመር መሿለኪያ አካባቢ ከአንድ ግለሰብ 4540 ካሬ ሜትር ቦታ በ3.4 ሚሊዮን ብር መግዛቱን አቶ እስክንድር ገልጸዋል፡፡
በዚህ ቦታና ከሁለት ወር በፊት ሃያት አካባቢ በሊዝ በገዛው 1130 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ባለስምንትና ሰባት ፎቅ ሕንፃ ግንባታዎችን ለማካሔድ ዝግጅት ማጠናቀቁንም ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አክሲዮን ማኅበሩ በ7.3 ሚሊዮን ብር የድንጋይ መፍጫ መግዛቱን ገልጿል፡፡ የድንጋይ መፍጫው የተገዛው ከአዲስ አበባ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ገላን ከተማ ውስጥ ነው፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ የአክሲዮን ሽያጭ የጀመረው ጥቅምት 2003 ዓ.ም. ላይ ቢሆንም፣ በአክሲዮን ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ ያለ ሥራ እንዳይቀመጥና ኩባንያው የአክሲዮን ሽያጩ እየተካሄደ ቀደም ብሎ ሥራ መጀመሩ ጠቀሜታነት ያለው በመሆኑ ነው፡፡
በቀን 150 ቶን ጠጠር የማምረት አቅም ያለው ይህ ድንጋይ መፍጫ የአክሲዮን ኩባንያው አክሲዮን እየሸጠም ቢሆን ገቢ ምንጭ ያለው እንዲሆን ለማድረግ አስቧል፡፡ ለአንድ ቶን ሲሚንቶ ሦስት ቶን ጠጠር ያስፈልጋል ያሉት አቶ እስክንድር፣ በአሁኑ ጊዜ የኮንስትራክሽን ግብዓት ፍላጐት አንጻር አክሲዮን ኩባንያው የገዛው የድንጋይ መፍጫ ለራሱ ለግንባታዎችም ሆነ ለሌሎች ሽያጭ የሚያከናውን ይሆናል፡፡
በግንቦት በሁለቱ ቦታዎች ከሚያካሂደው ግንባታ ጐን ለጐንም የቤት ሽያጭን የሚጀምር መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ አክሲዮን መሸጡም ተገልጿል፡፡


