Sunday, May 19th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

አየር መንገድ የ40 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተፈቀደለት

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በጋዜጣው ሪፖርተር

የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የ40 ሚሊዮን ዶላር ብድር መፍቀዱ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ፣ ብድሩ በቅርቡ ለተገዛው ቦይንግ 777-200LRs አውሮፕላን ተጨማሪ ፈንድ እንደሆነ አስታውቋል፡፡ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተጨማሪም የሰሜን አፍሪካው ሲቲ ባንክ፣ አፍሪካን ፋይናንስ ኮርፖሬሽን፣ የምሥራቅና የደቡባዊ አፍሪካ ንግድና ልማት ባንክም ብድር መስጠታቸው ታውቋል፡፡

አየር መንገዱ አቅሙን ለማሳደግ ካለው ፍላጐትና የበረራ መዳረሻዎቹንም ከማስፋፋት አኳያ ዘመናዊ አውሮፕላን አምራቾችን እንዳዘዘ አስታውቆ እነዚህ አውሮፕላኖች ለደንበኞች ምቾትና ለአካባቢ ተስማሚ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት ለማስመጣት ማቀዱን ገልጿል፡፡

ከታዘዙት አውሮፕላኖች መካከል አስር 787 ድሪም ላይነር እና አስር 737-800s ከቦይንግ ኩባንያ፣ A-350-900s የተባሉት ደግሞ ከኤርባስ ኩባንያ እንደሚመጡ ይጠበቃል፡፡

እስካሁን ሦስት ቦይንግ 777-200LRs አውሮፕላኖችን ከቦይንግ ኩባንያ የተረከበ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ሚያዝያና ሐምሌ ውስጥም ተጨማሪ ሁለት አውሮፕላኖችን ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

አየር መንገዱ 46 ያህል አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 60 ያህል ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችም ላይ እየበረረ ይገኛል፡፡ 40 ያህሉን በአፍሪካ ውስጥ ያከናውናል፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ደግሞ ሁለት ተጨማሪ የበረራ መዳረሻዎች ይኖሩታል፡፡ እኒህም ወደ ጣሊያኗ ሚላንና ወደ ቻይናይቱ ሃንዡ የሚዘረጉ መስመሮች ሆነው በእያንዳንዳቸው ላይ በሳምንት አምስት ጊዜ በረራ ይካሔድባቸዋል፡፡