አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባልና የፋይናንስና የበጀት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር
በቅርቡ የተዘጋጀው የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ ረቂቅ አዋጅ ሰሞኑን ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ ጉዳዩ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተልኳል፡፡
በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ እንደተደነገገው ከሆነ ማንኛውም የግል ድርጅት የተቀጣሪውን ሠራተኛ ደመወዝ 11 በመቶ፣ ሠራተኛው ደግሞ 7 በመቶ የጡረታ መዋጮ ማዋጣት አለባቸው፡፡ ከአሥር ዓመት በታች ያገለገለ የግል ድርጅት ሠራተኛ ሥራ ሲለቅ ምንም ዓይነት ክፍያ እንደማያገኝ፣ ከሃያ ዓመት በታች ያገለገለ የግል ድርጅት ሠራተኛ ደግሞ ሥራ ሲለቅ ራሱ ያጠራቀመውን ገንዘብ ብቻ እንደሚወስድም ረቂቅ አዋጁ ይደነግጋል፡፡ ሰሞኑን አነጋጋሪ በሆነው በዚህ ረቂቅ አዋጅና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ኃይሌ ሙሉ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባልና የፓርላማው የበጀትና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ ግርማ ሰይፉን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን የግል ድርጅቶች ጡረታ ፈንድ ረቂቅ አዋጅ እንዴት ተመለከቱት?
አቶ ግርማ፡- ረቂቅ አዋጁ የራሱ የሆነ ጥሩ ጎን አለው፡፡ በግል ድርጅት ውስጥ የሚሠራ ማንኛውም ተቀጣሪ ማኅበራዊ ዋስትና ስለሚኖረው በረቂቅ ሕጉ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ የማኅበራዊ ዋስትና የምንለው ነገር እኛ አገር የተለመደ አይደለም፡፡ ብዙ ሰው የመንግሥት ሥራ የሚወደውና ግለሰብ ዘንድ ተቀጥሮ መሥራት የማይፈልገው እንደዚህ ዓይነት ማኅበራዊ ዋስትና ስለሌለው ነው፡፡ ይህ ጥሩ ጅምር ነው፡፡ ነገር ግን ረቂቅ አዋጁ ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ አንደኛውና ዋናው ችግር የመውረስ ነገር አለበት፡፡ አንድ ሰው ዘጠኝ ዓመት ያህል የግል ድርጅት ውስጥ ሠርቶ ሥራ የሚለቅ ከሆነ ያስቀመጠውን ገንዘብ አያገኝም ይላል፡፡ ይኼ ድርቅና ነው፡፡ ሌላው ከአሥር ዓመትም በላይ ሠርተህ ሥራ የምትለቅ ከሆነ የራስህን ድርሻ ነው እንጂ ይዘህ የምትወጣው አሠሪው ያስቀመጠልህን አትወስድም ይላል፡፡ ይህ ልክ አይደለም፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤትም ቢሆን ይህ ትርጉም አለው፡፡ መንግሥት እኔ ዘንድ ከቆየህ ብቻ ነው ይህንን ነገር የምሰጥህ ብሎ የሚያስቀምጠው ገንዘብ አለ፡፡ የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲን የሚያስተዳድረው መንግሥት ስለሆነ ያ ገንዘብ ተመልሶ ለራሱ ለመንግሥት ነው የሚቀረው፡፡ በግለሰብ ከሆነ ግን ትርጉም አይሰጥም፡፡ ለምሳሌ እኔ ለሠራተኞች ገንዘብ አስቀምጣለሁ፣ ለሠራተኞች ነው ያስቀመጥኩት፡፡ ከዚያ በኋላ ሠራተኞቹ ሥራ ሲለቁ ሠራተኞቹ ናቸው እንጂ ገንዘቡን መውሰድ ያለባቸው መንግሥት የሚወርስበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የግል ድርጅቶች አሉ፡፡ ስድስት ወር ካልቆየህ እኔ መሥርያ ቤት ውስጥ የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ አትሆንም የሚሉት ምንድነው ምክንያቱ? መሥርያ ቤቱ ውስጥ የምትቆይበትን ሁኔታ ለማራዘም ነው፡፡ አምስት ዓመት ከቆየህ መኪና እገዛልሃለሁ የሚል ድርጅት አለ፡፡ አንተ ትመርጣለህ፡፡ አምስት ዓመት ቆይተህ መኪና ከሚገዛልህ፣ ስድስት ወር ቆይተህ ፕሮቪደንት ፈንድ ከሚሰጥህ ወይም ሥራውን ከምትለቅ? ምርጫው የአንተ ነው፡፡ ይህ ሠራተኛን የማቆያ ዘዴ ነው፡፡ መንግሥት አሥር ዓመት እንዲያገለግሉት ወይም ሃያ ዓመት እንዲያገለግሉት ከፈለገ ይህንን የማቆያ ዘዴ ሊጠቀም ይችላል፡፡ መንግሥት ቤት እቀጠራለሁ ብለህ ስታስብ ይህ ሊገጥምህ ይችላል፡፡ የግል ድርጅት ውስጥ ከተቀጠርክ ግን ሁኔታው የተለየ ነው መሆን ያለበት፡፡ ሪፖርተር ያጠራቀመልህን ገንዘብ ‹‹አይ እኛ እንወስደዋለን›› ማለት ምንም ትርጉም አይሰጥም፡፡ ምንም ዓይነት ምክንያታዊ መነሻ የለውም፡፡
ሪፖርተር፡- በፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚ የነበሩ የግል ድርጅት ሠራተኞች በዚህ ሕግ ምክንያት የሚያጡት ነገር አለ?
አቶ ግርማ፡- እነሱ ባሉበት መቀጠል ይችላሉ፡፡ ቀደም ሲል ፕሮቪደንት ፈንድ የነበራቸው ባሉበት ይቀጥላሉ ይላል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ወደ ግል ጡረታ ፈንድ የሚመጡት ከፈለጉ ነው፡፡ ‹‹ይህ አዋጅ ከመጽደቁ በፊት በተቋቋሙ የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ዕቅድ ወይም ፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ያላቸው ሠራተኞች በነበራቸው ዕቅድ ወይም ፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚነታቸውን ለመቀጠል ሊወስኑ ወይም በዚህ አዋጅ ስለሚሸፈኑበት ሁኔታ ሊስማሙ ይችላሉ›› ይላል ረቂቅ አዋጁ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ድርጅቶች ዱሮ በነበሩት ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ሕጉ ለሁሉም ተመሳሳይ መሆን የለበትም? ለምሳሌ አንድ ድርጅት ነገ ተነስቶ ‹‹አይ ጡረታ ፈንድ ውስጥ መግባት የለብኝም ከዚያ ይልቅ ሕጉ ከመጽደቁ በፊት ፕሮቪደንት ፈንድ ባቋቁም እችላለሁ›› ቢል ችግር አይኖረውም?
አቶ ግርማ፡- ምንም ችግር አይኖረውም፡፡ አሁን የእኔ ድርጅት ላይ እንደዛ ነው ያደረግኩት፡፡ ቀደም ሲል ፕሮቪደንት ፈንድ አልነበረኝም፡፡
ሪፖርተር፡- እንደዚያ ከሆነ መንግሥት ከግል ድርጅቶችና ከተቀጣሪ ሠራተኞች በጡረታ ፈንድ አማካኝነት ሊያገኝ የሚችለውን ገንዘብ ሊያሳጣው አይችልም?
አቶ ግርማ፡- መንግሥት ገንዘብ የሚፈልግ ከሆነ እሱ የሚፈልገውም ቦታ ይቀመጥ፣ የትም ይቀመጥ ገንዘቡን እኮ ያገኛል፡፡ ፕሮቪደንት ፈንድ የማስቀምጠው እኮ ባንክ ውስጥ ነው፡፡ ኪሴ ውስጥ ማስቀመጥ አልችልም ያው ነው፡፡ ገንዘቡ ይገኛል ማለት ነው፡፡ ያንን ገንዘብ ማንቀሳቀስ የመንግሥት ድርሻ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ነገር ግን መንግሥት በጡረታ አበል መዋጮ ለረጅም ጊዜ የሚጠቀምበትን ገንዘብ የማግኘት ዕድል የሚያጠበው ይመስላል፡፡
አቶ ግርማ፡- ምን መሰለህ መንግሥት (miss calculate) የተሳሳተ ስሌት ውስጥ የገባ ይመስለኛል፡፡ እስካሁን ድረስ የጡረታ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የጡረታ አበል ያዋጣሉ፡፡ ያ የጡረታ ገንዘባቸው ግን አይቀመጥላቸውም፡፡ መንግሥት ያጠፋዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ሁልጊዜ መንግሥት በጀት ነው የሚመድበው፡፡ ከጊዜ በኋላ መንግሥት ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ ሌላው አገር ግን እንደዚያ አይደለም የሚደረገው፡፡ ‹‹Actually System›› የሚባል አለ፡፡ የተዋጣ የጡረታ ገንዘብ ጡረታ ፈንድ ውስጥ ይቀመጣል፡፡ ያን ገንዘብ ያን የጡረታ አበል የሚያስተዳድረው ድርጅት ኢንቨስት ያደርገዋል፡፡ ይሠራበታል፤ አክሲዮን ይገዛበታል፡፡ ያተርፍበታል፤ ይነግድበታል፡፡ ያ ገንዘብ እየጨመረ ይመጣል፡፡ ይህንን የጡረታ አበል የሚያንቀሳቅሰው ድርጅት ትርፋማ ሲሆን ለጡረተኞችም የሚከፍለውን ገንዘብ ይጨምራል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ለጡረተኞች ደመወዝ የሚጨምረው መንግሥት ነው እንጂ የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ አይደለም፡፡ መጀመርያ ላይ ሠራተኛው ያወጣል፤ መንግሥትም ያንን መዋጮ ዝም ብሎ ይወስዳል፡፡ አሁን ለምሳሌ ልክ የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ እንደተቋቋመ ጡረታ የሚወጡ ሰዎች ገንዘብ አይወስዱም፡፡ አሥር ዓመትና ከዚያ በላይ እስከሚሆናቸው ድረስ ይቆያሉ፡፡ መንግሥት መጀመርያ ላይ ብዙ ገንዘብ ያገኛል፡፡ ያንን ያጠፋ ያጠፋና ኋላ ላይ ለጡረተኞቹ ገንዘብ መክፈል ሲጀምር ይቸገራል፡፡ አሁን እያደረገ ያለው ከአንዱ የሚሰበስበውን ለሌላ መስጠት ነው፡፡ መንግሥት በዚህ መልኩ ነው ገንዘቡን የሚያሽከረክረው፡፡ የጡረታ ኤጀንሲው የሚዋጣውን ገንዘብ በአግባቡ ኢንቨስት አድርጎ እያዋለው አይደለም፡፡ አሁንም ማድረግ የተፈለገው የግል ድርጅቶችን የጡረታ መዋጮዎችን ለመጠቀም ነው፡፡ ሁሉም ያዋጣውን አንድ ላይ ይሰበስብና ያስቀምጣል፡፡ መንግሥት ያንን ያጠፋል፡፡ ከዛሬ አሥር ዓመት በኋላ ነው እንግዲህ ከመንግሥት ጋር ስለጡረታ የምናወራው ማለት ነው፡፡ ይህ አካሄድ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ያውቅልኛል የሚል እንጂ ኃላፊነት የተሞላበት ዕርምጃ አይደለም፡፡ የሚቋቋመው ኤጀንሲ የሚዋጣውን ገንዘብ ኢንቨስት እንዲያደርግበትና በኋላም ጡረታ የሚወጡ ሰዎች የተሻለ ጥቅም የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ሰው አማካይ የዕድሜ ዘመን ከአርባ አምስት ዓመት አይበልጥም፡፡ በአዲሱ የግል ድርጅቶች የጡረታ ረቂቅ አዋጅ አንድ ሃያ ዓመት ያገለገለ ሠራተኛ የጡረታ አበል እንዲወስድ የሚፈቀድለት 60 ዓመት ሲሞላው መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህንን እንዴት ያዩታል?
አቶ ግርማ፡- አሁን ለምሳሌ በወጣትነት ዕድሜው ከዩኒቨርሲቲ በ21 እና በ22 ዓመቱ እንደወጣ ሥራ የሚጀምር ሰው 38 እና 40 ዓመት አገልግሎ ነው ጡረታ የሚወጣው፡፡ ከዚያ በኋላ እንግዲህ በአገሪቱ ካለው የዕድሜ ቆይታ አንፃር ስንት ሰው ነው ከስልሳ ዓመት በላይ የሚኖረው ብለህ ስታስብ የጡረተኞቹ ቁጥር በጣም ያንስብሀል፡፡ እንደ ጃፓን ባሉ ያደጉ አገሮች ቢሆን እንቀበለዋለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የጡረታ ጊዜው መርዘሙ ጡረታ ለሚከፍለው ኤጀንሲ ትርፍ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አሥር ዓመት ያገለገለ የግል ድርጅት ሠራተኛ ራሱ ያዋጣውን ገንዘብ ብቻ ወለድን ሳይጨምር ይወስዳል የሚለውስ ጉዳይ አግባብ ነው?
አቶ ግርማ፡- እኔ ወለድ መኖር አለበት ነው የምለው፡፡ ከሥራ እወጣለሁ ብዬ ከወሰንኩኝ ያዋጣሁት ገንዘብ ከነወለዱ ነው ሊሰጠኝ የሚገባው፡፡ እንዲያውም ወለድ ብቻ ሳይሆን የጡረታ አበል የሚሰበስበው ኤጀንሲ ኢንቨስት አድርጎ ካተረፈ ትርፉንም ሊያካፍለኝ ይገባ ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ግን ወለድ ሊሰጠኝ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የግል ፕሮቪደንት ፈንድ ሲቀመጥልህ ከነወለዱ ነው የምታገኘው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ የግል ድርጅቶች ጡረታ ፈንድ ረቂቅ አዋጅ ከእንግሊዝ በተወሰደ ተሞክሮ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንዴት ነው?
አቶ ግርማ፡- የሌላው አገር መንግሥት የሰው ገንዘብ አይነካም፡፡ እንግሊዝ አገር ብትሄድ የጡረታ ፈንድን የሚያስተዳድረው ኤጀንሲ ነው፡፡ ይህ ኤጀንሲ ከመንግሥት በጀት የሚደጎምለት አይደለም፡፡ ቅድም ያልኩህ ነው በ‹‹Actually system›› ኢንቨስት ያደርጋሉ፡፡ ብዙ ነገር ይሠራሉ፡፡ ለምሳሌ የመንግሥት ቦንድ የሚገዙት እነሱ ናቸው፡፡ ከዚያ ያተርፋሉ፡፡ ይህንን ገንዘብ ነው ለጡረተኞች የሚከፍሉት፡፡ የእኛን የጡረታ አበል እኮ መንግሥት በሙሉ አጥፍቶታል፡፡ የለውም፡፡ ስለዚህ በየዓመቱ በጀት እየበጀተ ነው ገንዘብ የሚከፍለው፡፡
ሪፖርተር፡- ከጡረታ ፈንድ ጋር ሲነጻጸር ፕሮቪደንት ፈንድ የሚያስገኘው የተለየ ጥቅም አለ? በፕሮቪደንት ፈንድ ያጠራቀምነውን ገንዘብ ተጠቅመን ቤት ሠርተናል፣ መኪና ገዝተናል የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡
አቶ ግርማ፡- መኪና መግዛት፣ ቤት መሥራት በራሱ አንድ ነገር ነው፡፡ ከጡረታ ገንዘብ ወስዶ መኪና የገዛ ሰው አናውቅም፡፡ በግል ድርጅት ተቀጥሮ ሲሰራ የነበረ ሰው ግን ፕሮቪደንት ፈንድ አውጥቶ ቤት ይሠራል፤ መኪና ይገዛል፡፡ ይህ በጣም የተለመደ ነገር ነው፡፡ ይህንን ነው እንግዲህ ይህ ሕግ የሚገድለው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ሥራ የሚፈጥሩ ሰዎች አሉ፡፡ በአብዛኛው ሃያ ሰማንያ፣ ዘጠና አሥር የሚባሉ አሉ፡፡ በዓለም ላይ እነዚህ ሃያ በመቶ አስር በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ተቀጣሪ ሆኖ ከመሥራት ይልቅ በሥራ ፈጣሪነት መሠማራት ይመርጣሉ፡፡ እኛ አገር ይህ ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያ የተሠማራ ሠራተኛ የራሱን የህትመት ድርጅት ይከፍታል? አይከፍትም፡፡ ግማሽ ዋስትና እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ አርፎ ሪፖርተር ወይም አዘጋጅ ሆኖ መቆየት ይፈልጋል፡፡ አንዳንዱ ግን ገና ሥራ እንደጀመረ ተነሳሽነቱ ጨምሮ ማተሚያ ቤት መክፈት የሚፈልግ አለ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ከ20 ወይም ከ10 በመቶ አይበልጡም፡፡ እኛ አገር ውስጥ ከ10 በመቶ የሚበልጥ አይመስለኝም፡፡ ይኼ የግል ድርጅቶች የጡረታ ፈንድ ሕግ እንግዲህ እነዚህን ሰዎች ነው የሚገድለው፡፡ ተቀጣሪ ሠራተኛ ሆነህ ስትሠራ ካልሰረቅህ በስተቀር ገንዘብ ማጠራቀሚያ መንገድህ ፕሮቪደንት ፈንድ ነው፡፡ ይኼ ጠርቀም ሲልልህ ነው አንድ ነገር የምታስበው፡፡ ኢንቨስት የምታደርገው፡፡ ስለዚህ ይኼ ሕግ እነዚህን ሰዎች በጣም ይጎዳቸዋል፡፡ እነዚያኞቹ ዋስትና የሚፈልጉት ዱሮም ከመንግሥት ቤት አይወጡም፡፡ ስለዚህ እነሱ እዚያው ይቆዩ፡፡ ትንሽ ይሻለኛል ያለ ደግሞ የግል ድርጅት ውስጥ ይገባል፡፡ ለሚገጥመው ችግር ኃላፊነት ይወስዳል፡፡ ያንን ኃላፊነት አመዛዝኖ ይጠቀማል፡፡ እነዚህን ኢንቨስተር የሚሆኑ ሰዎችን፣ ለውጥ የሚፈልጉ ሰዎችን ረቂቅ ሕጉ አያበረታታም፡፡ ዋስትና ለሚፈልጉ ሰዎች ብቻ ነው ከለላ የሚሰጠው፡፡ እስቲ አስበው በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ እንዴት ነው አሥር ዓመት የምትሠራው? ለምንድን ነው አንድ ሰው አሥር ዓመት እስኪሞላው ድረስ አንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚሠራው? በቃ ሪፖርተር ውስጥ መሥራት በቅቶኛል የራሴ ፕሬስ ሊኖረኝ ይገባል ካልክ ለምንድነው ገንዘብህን የምትቀማው? ለምንድነው ኤጀንሲ በሚል ስያሜ የሚቋቋም አንድ የመንግሥት ተቋም ገንዘብህን የሚወርሰው? እኔ ምክንያቱ አይታየኝም፡፡
ሪፖርተር፡- አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት የአገሪቱ ዜጎች ከተቀጣሪነት ሥነ ልቦና ወጥተው በሥራ ፈጠራ ላይ በመሠማራት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ አሁን የተዘጋጀው የግል ድርጅቶች የጡረታ ፈንድ ሕግ ከዚህ አባባል ጋር አይጋጭም?
አቶ ግርማ፡- በደንብ ነው እንጂ ልትም የሚለው፡፡ እንዴት ነው አንተ ሥራ የምትፈጥረው? በምንስ ትፈጥራለህ? አብዛኛው የመንግሥት ተቀጣሪ ጡረታዬን ላስከብር እያለ አይደል ታግቶ የቀረው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ዋስትና አንፈልግም ብለው አደጋ ለመጋፈጥ የተዘጋጁ ሰዎች ሊበረታቱ ይገባ ነበር፡፡ እኔ እንደማስበው አስበውበት ያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ አይመስለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት ይህንን ረቂቅ አዋጅ ያዘጋጀው በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ አሳካዋለሁ ላለው ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለመሰብሰብ አስቦ ይሆን?
አቶ ግርማ፡- አዎ! ለእሱ አስበው ያደረጉት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ግን ትርጉም የለውም፡፡ ትልቁ ችግር መንግሥት ሁሉንም ነገር እኔ እሠራዋለሁ ብሎ ማሰቡ ነው፡፡ እኔ እሠራዋለሁ ብሎ ሲያስብ ከሁላችንም ገንዘብ መውሰድ ይፈልጋል፡፡ ኢንቨስት ከሚያደርገውም ሰውዬ ገንዘብ ይወስዳል፤ ኢንቨስት ከሚያደርገው ሰው ገንዘብ ከወሰደበት ደግሞ ኢንቨስት ማድረግ ያቆማል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እንዴት ሆኖ የኢንቨስትሮች ቁጥር ይበዛል? እንዴት ሆኖ ብዙ ኢንተርፕረነሮች ይኖራሉ? መንግሥት ልማታዊ መንግሥት መሆን የለበትም ማለቴ አይደለም፡፡ መንግሥት መንገድ መሥራት የለበትም ማለቴ አይደለም፡፡ በመሠረቱ መንገድ የሚሠራ የግል ድርጅት የለም፡፡ መንግሥት መሠረተ ልማት መሥራት የለበትም ብሎ የሚከራከር የለም፡፡ መንግሥት መሠረተ ልማት ማስፋፋት አለበት፡፡ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግን ማቋቋም የለበትም፡፡ ትልቅ ኢንቨስትመንት ነው እያለ የሚያስፈራራን የሲሚንቶ ፋብሪካውን አይደል? እሱን ማቋቋም የለበትም፡፡ መንግሥት ስኳር ፋብሪካ ማቋቋም የለበትም፡፡ አያገባውም፡፡ መንግሥት አሁን ስኳር ፋብሪካ አቋቁምበታለሁ ብሎ ተንዳሆ ላይ እስካሁን ያወጣው ገንዘብ የግል ድርጅቶች ሁለት ሦስት ስኳር ፋብሪካ ይከፍቱበታል፡፡ ግን ማን ይጠይቀዋል? የሚጠይቀው የለም፡፡ ገንዘቡ ይባክናል፤ ይጠፋል፤ በአግባቡ ጥቅም ላይ አይውልም፡፡ ኅብር ስኳር አክሲዮን ማኅበር እንደዚህ የሚያደርግ ይመስልሃል? ሐበሻ ሲሚንቶ እንዲህ የሚያደርግ ይመስልሃል? ሰው ሆ ብሎ ወጥቶ ነው የሚበላው፡፡ ሐበሻ ሲሚንቶ ገንዘቡን እንደዚህ ሲጫወትበት ቢያይ አንድ ቀን ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ ነው ኢንጂነሩን የሚበላው፡፡ ግን የተንዳሆን ማን ይጠይቃል? የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ሥራ ገና ጫፉ አልተነካም፡፡ ግን መንግሥት ሁሉንም ነገር ራሱ መሥራት ይፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ኅብሮች ገንዘብ ለማሰባሰብ እየተሰቃዩ ነው ያሉት፡፡ መንግሥት ገንዘብ ካለው አቅም ካለው ለምንድነው ለእነሱ የማይሰጣቸው? ለምንድነው ለሐበሻ ሲሚንቶ ‹‹በሚቀጥለው ዓመት እፈልገዋለሁ ቶሎ ጨርሱ 30 በመቶ እኔ እገዛችኋለሁ ትከፍላላችሁ፤›› ብሎ የማይሰጣቸው? ለኅብር ሲሰጥ አክሲዮን ያለን ሰዎች እንጠቀማለን፡፡ ለሐበሻ ሲሰጥ አክሲዮን ያለን ሰዎች እንጠቀማለን፡፡ ዜጎች ይጠቀማሉ፡፡ መንግሥት ይህንን ሲያደርግ አይታይም፡፡ እንደማስበው ይኼ ትልቅ ምቀኝነት ነው፡፡ እንደ መንግሥት ዜጎች እንዲጠቀሙ የሚፈልግ ከሆነ ይኼንን በማድረግ ችግሩን መቅረፍ ይቻል ነበር፡፡ ዋናው መፈታት ያለበት የዚህች አገር ችግር የስኳር ችግር ነው፡፡ ዋናው ችግር የሲሚንቶ ችግር ነው፡፡ ይህንን ችግር በመርህ ደረጃ መፍታት ያለበት የግል ዘርፉ ነው፡፡ የግል ዘርፉ ለራሱ ሲል ለትርፍ ሲል አጠናቅቆ ይሠራና ይጨርሳል፡፡ የተንዳሆ ፕሮጀክት ግን አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሚገርም ሁኔታ ዘረፋ እየተካሄደበት ነው፡፡ የስኳር ፋብሪካው ገንዘብ ሜዳ ላይ ነው ያለው፡፡ ማሽነሪዎቹ ሜዳ ላይ ናቸው፡፡ የመንግሥት ትልቁ ችግር ሁሉንም ነገር እኔ እሠራለሁ ብሎ ገንዘብ ካለበት ቀዳዳ ሁሉ ሰብስቦ መያዝ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት የሚፈልገውን ገንዘብ ከጡረታ መዋጮ ሊያገኝ ይችላል ብለው ያስባሉ?
አቶ ግርማ፡- የሚፈልገውን ያህል ላያገኝ ይችላል፡፡ ግን ብዙ ገንዘብ ያስገኛል፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ሠራተኛ ከሚከፍለው የሥራ ግብር በተጨማሪ ለጡረታ መዋጮ በየወሩ ብዙ ገንዘብ ያዋጣል፡፡ ይኼ በተከታታይ ለአሥር ዓመት ለመንግሥት የሚገባ ገንዘብ ነው፡፡ መንግሥት ለጡረተኞች መክፈል እስከሚጀምር ድረስ እኮ መሰብሰብ ብቻ ነው፡፡ የሰበሰበውን ገንዘብ ደግሞ እያወጣ ይጠቀምበታል፡፡ ለጡረተኞች የሚከፈለው ገንዘብም ያን ያህል የሚጎዳው አይደለም፡፡ ወይ ደግሞ የሚመጣው መንግሥት ነው የሚጨነቅበት፡፡ ይኼ ደግሞ ኃላፊነት ይጠይቃል፡፡ ለመጪው ትውልድ የማሰብና የመጨነቅ ጉዳይ ይፈልጋል፡፡ የሚመጣውን መንግሥት ችግር ውስጥ ማስገባት አግባብ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ፕሮቪደንት ፈንድ ለሠራተኛው ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ በአንድ አገር ዕድገት ላይ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አይኖረውም?
አቶ ግርማ፡- በፕሮቪደንት ፈንድ ያደገ አገር አኔ አላውቅም፡፡ ፕሮቪደንት ፈንድን እንደ አንድ የገንዘብ ምንጭ ወስደህ ልትጠቀም ትችላለህ፡፡ ፕሮቪደንት ፈንዳችሁን ለመጠቀም እንድንችል የሆነ ቦታ አስቀምጡ ማለቱ ችግር የለውም፡፡ በየሦስት ወሩ ማውጣት ይቁም ቢል ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶችም ውስጥ እኮ ፕሮቪደንት ፈንድ ዝም ብሎ አይሰጥም፡፡ሥራ ስትለቅ ብቻ የሚሰጥህ ነገር ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. መንግሥት አካውንት ውስጥ የተሰበሰበውን ፈንድ እወስዳለሁ ሲል ሁሉም ሰው ገንዘቡን አወጣ፡፡ አሁንም ብዙ ሰው አውጥቷል፡፡ የብዙ ሰው አካውንት ዜሮ ነው፡፡ በወቅቱ እኔ የመከርኳቸው የተወሰኑ ሰዎች ፕሮቪደንት ፈንዳቸውን አውጥተው በጣም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ አክሲዮን ገዝተው፣ የራሳቸውን ቢዝነስ ከፍተው ከእጥፍ በላይ ያተረፉ ሰዎች አሉ፡፡ ከ100 ሺሕ እስከ 200 ሺሕ ብር የተጠራቀመ ፕሮቪደንት ነበራቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ጡረታ ሲወጡ ምን እናድርገው ብለው ሲጨነቁ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ኋላ ላይ ግን ኢንቨስት አድርገው የተለያዩ ባንኮች ውስጥ አክሲዮን ገዝተው ገንዘባቸውን መልሰዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ብሩን የትም አልወሰዱትም፡፡ እዚያው ነው ኢንቨስት ያደረጉት፡፡ የሚበደር ሰው እየሠራበት ነው፡፡ ኢንቨስትመንቱ ላይ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከደመወዙ እየቀነሰ በፕሮቪደንት ፈንድ የሚያዋጣ ሠራተኛ በድንገት እየተነሳ ያዋጣሁት ገንዘብ ይመለስልኝ ቢል፣ መንግሥት ያንን ገንዘብ ለኢንቨስትመንት አውሎት ከሆነ ችግር አይፈጥርም?
አቶ ግርማ፡- ባንክ ያስቀመጥከውን ገንዘብ ባንክ ቤት ስትሄድ አበድሬዋለሁ አልሰጥህም ብሎ ያውቃል? አያውቅም፡፡ አንዱ ሲያወጣ አንዱ ያስገባል፡፡ መንግሥት በምንም መልኩ ገንዘብ አያጥረውም፡፡ የኤጀንሲው ሥራ ይኼን መቆጣጠር አይደል እንዴ? ሰዎች ሥራ ሲለቁ ሊጠይቁ የሚችሉት አማካይ ገንዘብ ምን ያህል ነው? ብሎ የራሱን ሥራ መሥራት አለበት፡፡ ካለበለዚያ ደግሞ ‹‹Overdraft Facility›› (ሰነድ አስይዘህ የምትበደረው ብድር) ከባንኮች ጋር መያዝ አለበት፡፡ መንግሥትም እኮ እንዲሁ ዝም ብሎ ያንን ገንዘብ እየወሰደ የሚጠቀምበት አይመስለኝም፡፡ በብድር ቦንድ ገዝቶ ሊሆን ይችላል የሚወስደው፡፡ ስለዚህ የሚመልስበት ማዕቀፍ መኖር አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት የያዘው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አይሳካም የምትሉበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ግርማ፡- የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አይሳካም የምንለው ምቀኞች ስለሆንን አይደለም፡፡ አይሳካም የምንለው የማስፈጸም አቅማቸውን እያየን ነው፡፡ ከዚህ በፊት የጀመሩትን የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት እስከዛሬ ድረስ አልጨረሱትም፡፡ ከ25 እስከ 30 በመቶ ላይ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ ይህንን አፈጻጸም ይዘው ሌሎች ስኳር ፋብሪካዎችን እንገነባለን ሲሉ እንደማይሳካ መገመት አይከብድም፡፡ ሌላው የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ የሚባል አስማተኛ ኢንዱስትሪ ይቋቋማል ተብሏል፡፡ ጋዜጠኞች ናችሁ ሄዳችሁ ይኼ ኮርፖሬሽን ምን እየሠራ እንደሆነ ማየት አለባችሁ፡፡ ይኼ ኮርፖሬሽን አገሪቱ ውስጥ ይቋቋማሉ የሚባሉት የኢንዱስትሪ ዘርፎች የጨርቃ ጨርቅ፣ የሲሚንቶ፣ የስኳር ፋብሪካዎች ከ75 በመቶ በላይ የሚያስፈልጋቸውን የፋብሪካ መገንቢያ አመርታለሁ እያለ ነው፡፡ ይህ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ግን ማምረት ይቅርና ገዝቶ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ተቃዋሚዎች ድንጋይ እየደረደሩ ዕቅዱ እንዳይሳካ ይጥራሉ ብሎ ነው ኢሕአዴግ የሚያስበው፡፡ ይኼ ስህተት ነው፡፡ እኛ ግን ድጋፍ የሚሰጡት አገሮች ሲጠይቁን ‹‹ከፈለጋችሁ ባቡሩን እንዳለ ስፖንሰር አድርጓቸውና ሥሩት፡፡ ከተሠራ እኛንም ነው የሚጠቅመን፡፡ የምትሰጧቸው ዕርዳታዎች ግን የኢሕአዴግን ጡንቻ እያፈረጠሙ ሕዝብ መጨቆኛ እንዳይሆኑ ቁጥጥር መደረግ አለበት ነው፤›› እያልን ነው ያለነው፡፡ መንገዱን ቢሠሩልን፣ የባቡር ሀዲዱን ቢገነቡልን እንዲያውም ቢችሉ ስኳር ፋብሪካውንም፣ ሲሚንቶ ፋብሪካውንም ቢገነቡልን ደስ ነው የሚለን፡፡ እዚህ ላይ እኛ ምንም ተቃውሞ የለንም፡፡ ነገር ግን ወደ እውነታው ስንመለስ መንግሥት ይህንን የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለፕሮፓጋንዳ ሲል ያስቀምጠው እንጂ አቅም ኖሮት አይደለም፡፡ ገንዘቡን ኪሱ ቢያስቀምጡለት አይሠራውም፡፡ ምክንያቱም አቅም የለውም፡፡ አቅም ማለት ሕዝብ ነው፣ አቅም ማለት ሰው ነው፡፡ የተማረውን ሰው በሙሉ በካልቾ እየገፋ ይህንን ዓይነት ትልቅ ነገር እናሳካለን ማለት ውሸት ነው፡፡ መሠረታችን ገበሬ ላይ ነው እያሉ፣ ምንም ዓይነት ፊደል መቁጠር የማይችል፣ ምንም ዓይነት የኤክስቴንሽን ሥራዎችን መቀበል የማይችለውን አርሶ አደር ይዘን ነው የምናለማው እያሉ፣ ይህንን ለውጥ ያመጣሉ ማለት አይቻልም፡፡ አይሳካም ስንል በምክንያት ነው፡፡ አንዳንዶቹ የኢሕአዴግ ትልልቅ ካድሬዎች የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ሰነድ ነክተውት አያውቁም፡፡ እነሱ ናቸው እንግዲህ ዕቅዱን እንዲያስፈጽሙ የሚፈለገው፡፡ እነዚህን ሰዎች ብትሰማቸው ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ተግተን እንሠራለን ምናምን ይሉሃል፡፡ ነገር ግን ወረቀቱን በእጃቸው ነክተውት እንኳን አያውቁም፡፡ እስኪ አንድ ሁለት ካድሬ ፈልግና የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ላይ አንድ ሁለት ጥያቄ ጠይቀው፡፡ ያኔ ሰነዱን አንብቦት እንደማያውቅ ትረዳለህ፡፡ ብዙ ጥናት ማካሄድ አይጠይቅም፡፡
ሪፖርተር፡- የብረታ ብረት ኢንዱስትሪው ምንም መሥራት አይችልም ያሉበት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ግርማ፡- ኮርፖሬሽኑ ምንም አቅም የለውም፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አምስት መቶ አውቶቡሶች እንሠራለን ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን ሊሠሩ ይቅርና ገዝተው እንኳን ሊያመጡ አልቻሉም፡፡ አሁን ባለኝ መረጃ አራት አውቶቡሶችን አምጥተዋል፡፡ ሠርተው ሳይሆን ገዝተው ነው፡፡ ይኼንን ለማድረግ ደግሞ የብረታ ብረት ኮርፖሬሽን አያስፈልግም፡፡ ኢንዱስትሪው ተደራጅቷል ከተባለ የሚፈለገውን ነገር ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን ግን አይታይም፡፡ ፕሮፓጋንዳ መንዛት አይደለም የሚፈለገው፡፡


