በታደሰ ገብረ ማርያም
የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ባይቋቋም ኖሮ የሙስናው እንቅስቃሴ ምን ሊሆን ይችል ነበር? እስካዛሬ ድረስስ ምን ሠርቷል? የሚለውን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል ሁለተኛ ጥናት በመካሔድ ላይ መሆኑን አቶ አሊ ሱሌማን የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አስታወቁ፡፡
በተለያዩ ደረጃ ለሚገኙ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅን አስመልክቶ መጋቢት 21 ቀን 2003 ዓ.ም. በተካሔደው የግንዛቤ ማስጨበጫና መድረክ ላይ ኮሚሽነሩ እንዳመለከቱት፣ ቅኝቱን የሚያካሒደው መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው አንድ የታንዛኒያ አማካሪ ቡድን ነው፡፡
ከዚህም ሌላ ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተፈራረመው የመግባቢያ ሰነድ መሠረት እስካሁን የተከናወነው ሥራ ያስገኘው ጥቅም ምን ይመስላል በሚለው ዙርያ ያተኮረ ጥናት በመከናወን ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በስምንት ዘርፎች ላይ ምርመራና ጥናት መሠራቱንና በዚህም ጥናት ላይ የጎላ የሙስና እንቅስቃሴ ያለው በየትኛው ዘርፍ ነው የሚለውን ለማወቅ ሙከራ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የዚህ ዓይነቱም ጥናት ውጤት ኮሚሽኑ ካመጣው ውጤት ጋር መዛመዱን ጠቁመዋል፡፡
ይህም ማለት በመሬት አስተዳደርና በቴሌ አካባቢ ከዕቃ ግዢ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ችግሮች እንዳሉና በሌሎች ዘርፎች ያለው ችግር ግን ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ሆኖ እንደተገኘ ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
አቶ አሊ እንዳብራሩት፣ ኮሚሽኑ የተቋቋመው በአገሪቱ የተንሰራፋው ሙስና ምን ይመስላል? ምን ያህል አደጋ አለው? በሚለው ዙርያ ትኩረት ያደረገው የመጀመርያው ጥናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ከተከናወነ በኋላ ነው፡፡ አመሠራረቱም የተባበሩት መንግሥታት የፀረ ሙስና ኮንቬንሽንንም መሠረት ባደረገ መልኩ ነው፡፡
ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ ሙስናና ብልሹ አሠራርን የማይቀበል፣ የማያስተናግድና የሚጠየፍ ኅብረተሰብን ለመፍጠር የተንቀሳቀሰው በብዙ አገሮች ተሞክሮ ውጤታማ የሆኑ ሦስት ዓይነት አካሔዶችን በመከተል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በማስተማር፣ በመከላከልና በሕጋዊ አፈጻጸም ላይ ያተኮረው አካሔድም ጠቃሚ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል፡፡ የኮሚሽኑ ትልቁ ሥራ ግን በትምህርት ላይ ያተኮረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹መከላከልን በተመለከተ በአንዳንድ የመንግሥት መሥርያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ከብልሹና ከሙስና አሠራር አኳያ ክፍተት አለ ብለን ባመን ጊዜ እያጠናን ክፍተቱ የታየበትን አካሔድ እንዲያስተካክሉ እንመክራቸዋለን፡፡ ሕጋዊ መንገዱን መከተል ደግሞ የመጨረሻው አማራጫችን ነው፡፡ ከተከሰሱት 100 ሰዎች መካከልም 85 ከመቶ ያህሉ ይቀጣሉ፡፡ ይህም በማንኛውም መለኪያ ትልቅ ተግባር ነው›› ብለዋል፡፡


