በምዕራፍ ብርሃኔ
የባልና ሚስት ፍቺ፤ በሕግ ሳይሆን በተግባር አብረዋቸው ለሚኖሩ ልጆቻቸው እንጂ ለጎረቤቶቻቸውና ዘመዶቻቸው ሊጠረጠር የማይችልና በቀላል የማይፈታ ለዓመታት የሚዘልቅ ጥብቅ ምሥጢር ነው፡፡
እንዲህ ያሉ ጥንዶች አብረው ጨፍረው እልል ብለው ልጆቻቸውን ይድራሉ፡፡ ለቅሶም ይሁን ሰርግ ሲኖርባቸው በአንድ ላይ በመሔድ ፕሮግራሙን ይታደማሉ፡፡ እንዲሁም ማንኛውንም ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ሳያውኩ መገኘት ባለባቸው ቦታ ሁሉ ይገኛሉ፡፡ በትዳር ላይ እንደሆኑ አስመስለው ወደቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ ሚስት ቀድማ እቤት ከገባች ሳሎኑን በመቆጣጠር ቡናና ራት በማስቀረብ ከልጆቿ ጋር ቤት ያፈራውን ትቋደሳለች፡፡ ሳሎኑን የተቀደመው ባልም ቀጥታ ወደ መኝታ ቤቱ በማምራት ራቱን ከመኝታ ቤት እንዲመጣለት በማድረግ፣ ከገባበት ሰዓት ጀምሮ ወደሳሎን ብቅ ሳይል እዛው ያድራል፡፡ ሚስትም ሳሎን መቆየቱ ሲበቃት ወደ መኝታ ቤቷ ትሔዳለች፡፡ ወደራሷ መኝታ ቤት፡፡ ባልም ሳሎን ቀድሞ የሚገባበት አጋጣሚ ካለ እርሱም እንደ ሚስቱ ያደርጋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ባልና ሚስት የሚባሉት ወረቀት ስላልቀደዱ እንጂ እውነት ባልና ሚስትነቱን ኖሯቸው አይደለም፡፡ እንደእነዚህ አይነት ጥንዶች ጧት ወደሥራ ሲሔዱና ማታ ሲመለሱ ሰዓታቸው እንዳይገናኝ ስለሚጠነቀቁ፣ ማንም ሰው ትዳራቸው መሃል ችግር እንዳለ አይገምትም፡፡
በእንደዚህ አይነት ትዳር ውስጥ ካደጉ ልጆች መሃል አንዱ የ20 ዓመቱ ሳሙኤል ተካ ነው፡፡ ሳሙኤል የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፣ ከፍተኛ ተቋም በመግቢያው ዕድሜ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በመሆኑ ቤተሰቦቹን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡
‹‹ወላጆቼ በተገኘው ክፍተትና አጋጣሚ፤ መጣላት፣ መጨቃጨቅ ሲላቸው ደግሞ መደባደብ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ነው፡፡ በየትኛው ጊዜያቸው እኔንና ሁለት ወንድሞቼን ይከታተሉ?›› ሲል ወላጆቹ መሃል ሰላም ባለመኖሩ ለሁለት ዓመታት ትምህርቱን አቋርጦ እንደነበር ይናገራል፡፡
ከዓመታት ወዲህ ባልና ሚስቶች መሀል በሚኖሩ ግጭቶች አማካይነት፣ ጥንዶቹ በሕግ ባይፋቱም አንድ ግቢ እየኖሩና መኝታ ክፍሎቻቸውን እየለዩ፣ ለብዙ ዓመታት እንደሚኖሩ እየታየ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ወላጆች ንብረትን ላለመበተን፣ ልጆቻቸውን ለእንጀራ አባት ወይም ደግሞ የእንጀራ እናት ላለመዳረግና ከኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት አኳያ ፍቺ ላለመፈጸማቸው ምክንያት ሆነው እንደሚጠቀሱም ይሰማል፡፡
ለጽሑፋችን መግቢያነት የተጠቀምንበት ሳሙኤል፣ ወላጆቹ መስማማትና ተቻችለው መኖር የማይችሉ ከሆነ ለምን እንደማይፋቱ ግራ እንደሚገባው ይናገራል፡፡
‹‹ቀን ቆርጦልኝ ከወላጆቼ ቤት የምወጣበት ይናፍቀኛል፡፡ በእነርሱ የዕለት ተዕለት ግጭት ምክንያት፣ አንድም ቀን በራስ የመተማመን ስሜት ኖሮኝ አያውቅም፡፡ በጣም የሚያሳዝነኝ ደግሞ ወላጆቼ ስለማይንከባከቡኝና ስለኔ ስለማይጨነቁ፣ ሰው ለእኔ የሚያስብ ፍጡር ነው ብዬ አለማመኔ ነው፡፡ እናም ስለ ሰዎች ጥሩ ስሜት እንዳያድርብኝ ሳያደርግ አይቀርም፡፡ ሲል በራሱም እንደማይተማመንና ማኅበራዊ ግንኙነቱም ክፍተት ያለበት እንደሆነ ይናገራል፡፡
በወጣቱ ህልውና ውስጥ የተጠራቀሙት አስተሳሰቦችና ማንነት፣ ከስምንት ዓመቱ ጀምሮ ያዳበራቸው ስለሆኑ፣ መቅረፍ እንደሚቸገርም አክሏል፡፡ ሳሙኤል በውኃ ቀጠነ ከሚነሣው የወላጆቹ ግጭት ለመሸሽና ለመገላገል ወታደር ለመሆን አቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ዕቅዱን የሰሙት የጓደኛው አባት ሐሳቡን እንዳስቀየሩት ያስታውሳል፡፡ ቢሆንም ግን ‹‹ወይ ከትምህርቴ አልሆንኩ ወይ ደግሞ ቤተሰቤ አልተመቸኝ፤›› የሚለው ሳሙኤል፣ የወታደርነት አጋጣሚውን ቢጠቀምበት የተሻለ እንደነበር ይናገራል፡፡
ሳሙኤል፣ እንኳን ሚስት አግብቶ ልጆች ሊወልድ ይቅርና፣ እህትና ወንድሙን እንኳን ከመጤፍ እንደማይቆጥራቸው ይገልጻል፡፡ ‹‹እንደ አባቴ ዓይነት ባልና አባት መሆን አልፈልግም፡፡ ስለዚህ ትዳር ለምኔ፣›› ያለው ይህ ወጣት የተለመደውን ዓይነት የሕይወት ጎዳናን እንደማይከተል ይናገራል፡፡
የሳሙኤል ወላጆች የሚተኙት አንድ መኝታ ክፍል ቢሆንም፣ አልጋቸው ግን የተለያየ ነው፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ከሆነ ወላጆቹ የማይስማሙ ከሆነና የኢኮኖሚ ጥገኝነት ከሌለባቸው፤ አብረው እየኖሩ የራሳቸውን ሰላም ከመንሳት አልፈው የልጆቻቸውን ሕይወት ሊበጠብጡ አይገባም፡፡
‹‹እናቴ ለምን አየኸኝ፣ አየር ለምን ቀለም የለውም? ብላ ጠብ ትጭራለች፡፡ አባቴም ደግሞ አጸፋውን በዱላ ይመልስላታል፡፡ እሷም ሆነች እሱ ኢኮኖሚያዊ ጥገኝነት የለባቸውም›› ሲል የወላጆቹ እስከዛሬ ድረስ በትዳር መቆየት እንቆቅልሽ ሆኖበታል፡፡
በወላጆቹ መካከል ስድብ፣ ጭቅጭቅና ድብድቡ በመበርከቱና ወጣቱ፣ ስላሰለቹትም የወሰደው መፍትሔ በመኖርያ ቤታቸው አካባቢ ወደሚገኘው የፖሊስ መምርያ ሔዶ አባቱን መክሰስ ነበር፡፡ ክሱን አዳምጠው የልጆቹን መሰቃየት የተረዱት የፖሊስ መምሪያው አዛዥም፣ ወደ ሳሙኤል አባት ስልክ ደውለው ከዚህ በኋላ በቤታቸው ውስጥ ጭቅጭቅና ድብድብ የማይቆም ከሆነ፣ እርሳቸው ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድባቸው በማስጠንቀቃቸው ቤታቸው ውስጥ ሰላም መስፈኑን ሳሙኤል ይናገራል፡፡
ሌላዋ ዝም ባለ ፍቺ መሃል ያደገችው የ26 ዓመት ወጣቷ ትዕግስት ታምሩ ናት፡፡ ትዳር እንዲኖራት በፍጹም ተመኝታ እንደማታውቅ ትናገራለች፡፡ ይህች የገበያ ጥናት ባለሙያ፣ ወንዶች የአባቷ ዓይነት ባሕሪና ለትዳር የማይመች ክፉ ማንነት አላቸው ብላ ብላ ስለምታስብ፣ ስለምን የሕይወቴ አጋር እንዲሆን እፈቅዳለሁ በሚል ምክንያት ትዳር እንደማይኖራት ትገልጻለች፡፡
ትዕግስት ከሰማችውና ነገሮችን ማስተዋል ከጀመረችበት ጊዜ አንሥቶ፣ ወላጆቿ ሰላም እንዳልነበራቸው ትናገራለች፡፡ ትዳርን የማትቀላቀለው ትዕግስት ብቻ ሳትሆን ሦስት ታናናሾች እህቶቿም ጭምር እንደሆኑና ምክንያታቸውም ‹‹አባታቸው እናታቸውን ስለሚበድል›› በሚል እሳቤም እንደሆነ ወጣቶቹ ይናገራሉ፡፡
የትዕግስት ወላጆች በሕግ ባይፋቱም መኝታ ቤታቸውን ከለዩ ግን ሦስት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ ወላጆቿ ለመፋታት ያቀዱት ከዓመታት በፊት ቢሆንም፣ እርሷም ሦስት ጊዜ በቤተሰብ ሽምግልና ላይ እንዲፋቱና የየራሳቸውን ሕይወት እንዲመሩ ሐሳብ ብታቀርብም፣ የትኛውም መንገድ ግን በወቅቱ ተግባራዊ ሊሆን እንዳልቻለ ታስታውሳለች፡፡
ትዕግስት እንደምትለው ከሆነ፣ በወላጆቿ መሃል ጭቅጭቅ፣ ጥላቻ፣ መናናቅና አለመተጋገዝ እጅግ ተንሰራፍቶ ነበር፡፡ አባቷ ከእናቷ በገቢም ይሁን በእውቀት ዝቅ ማለታቸው የጠባቸው ዋነኛ መንስኤ እንደሆነ፣ በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ጠቦችም መግዘፋቸው ሌላው ምክንያት ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ወላጆቿ በቅርቡ ቢፋቱም ይህንን ውሳኔያቸውን ግን ቀደም ብለው ቢያደርጉት ኖሮ፣ በእነርሱ ላይ የተፈጠረው አለመረጋጋት ባልተከሰተም ነበር በማለትም ተናግራለች፡፡
የ45 ዓመቷ የትዕግስት እናት ወ/ሮ ሸዋን ገረመውም እንደሚሉት ከሆነ፣ ትዳር የያዙት በ19 ዓመታቸው ነበር፡፡ ያኔ ይፈጠሩም ለነበሩት ችግሮችም ‹‹እኔ ልጅ ስለነበርኩና በአስተሳሰብም ስላልበሰልኩ ይሆናል ብዬ አስብ ስለነበር፣ ለሚፈጠሩት ችግሮች በሙሉ ራሴን ተጠያቂ አደርግ ነበር፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ያኔውኑ ትዳሬን ብፈታ ኖሮ ሌላ ማግባቴ ስለማይቀር፣ ልጆቼን ለእንጀራ አባት መዳረግ አለመፈለጌም ጭምር ነበር›› ሲሉ ጠብ በጀመሩበት ጊዜ ወዲያውኑ ለምን እንዳልተፋቱ ገልጸዋል፡፡
ይህንን የምትቃወመው ትዕግስት፣ ‹‹ሳይተዋወቁ የተጋቡ ሰዎች ሲተዋወቁ ይፋታሉ፡፡ ስለዚህ ወላጆቼ መስማማት ካቃታቸው ተለያይተው እውነቱን ለልጆቻቸው አስረድተው በሰላም ቢያሳድጉን ይሻል ነበር፤›› ባይ ነች፡፡
ሳሙኤልና ትዕግስት ባደጉበት መንገድ አድጋ፣ ነገር ግን ትዳር የመሠረተችው የ33 ዓመቷ መስከረም ታዬ ናት፡፡ መስከረም የአንዲት ሴት ልጅ እናት ስትሆን፣ ዕድገቷ ጥላቻና ድብድብ በሰፈነበት የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ በመሆኑ፣ ያዳበረችው ባሕርይ ከባለቤቷ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአካባቢዋ ሰዎች ጋርም እንደሚያጋጫትና እንደሚያቃቅራት ትናገራለች፡፡ ‹‹እናቴ ነገሮችን ስለማታልፍ ከአባቴ ጋር ሁሌ ይጋጫሉ፡፡ እኔም የዛሬ ሦስት ዓመት አግብቼ እስከምወጣ ድረስ የኖርኩት እዛው በመሆኑ በትዳር ላይ ያለኝ አቋም ያደግኩበትን ዓይነት ነው፤›› ስትልም አክላለች፡፡ ባሕርይዋ በትዳሯ ላይ ችግር የሚፈጥር ቢሆንም፣ ባለቤቷም እሷ ባደገችበት ዓይነት የአኗኗር ዘይቤ ስላደገ በመሀከላቸው በሚፈጠሩት አለመስማማቶች ግፋ ቢል ቢደባደቡ እንጂ ለፍቺ እንደማይዳረሱም አውስታለች፡፡ ቢሆንም ግን እሷ የእናቷ ዓይነት እናት በመሆኗ የምታሳድጋት ልጇም የእርሷን የሚመስል ባሕርይ ይዛ እንዳታድግ ትሰጋለች፡፡
የመስከረምም እናትና አባት በሕግ ባይፋቱም መኝታቸውን ከለዩ ግን 10 ዓመታት እንዳለፋቸው ትናገራለች፡፡
በሕግ ያልተፋቱ ነገር ግን መኝታ ለይተው በአንድ ጣርያ ሥር እየኖሩ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ ወላጆች፤ አለመስማማታቸውን እያዩ የሚያድጉ ልጆች፣ ሊኖራቸው ስለሚችለው ሰብእናና አስተሳሰብ አስመልክቶ፣ የቤሪያ የጋብቻ ምክር አገልግሎትና ስልጠና ማእከል ሥራ አስኪያጅና የሥነ ልቦናና የጋብቻ አማካሪ የሆኑትን አቶ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስን አነጋግረናቸዋል፡፡ ባለሙያው እንደሚሉት ከሆነ፣ ወላጆች ልጆቻውን ሊያሳደጉ የሚገባው ለልጆቻቸው ጠቃሚ በሆነ መልኩ እንጂ እነርሱን በሚጠቅም መንገድ መሆን የለበትም፡፡ አቶ የማነ አክለውም፣ ክፍተት ያለበት፣ አለመግባባት የሰፈነበት፣ ጥላቻ፣ ጭቅጭቅና ድብድብ የሞላበት ቤት ውስጥ የሚያድጉ ልጆች ሱሰኛ፣ ተስፋ የቆረጡና ብሎም ወንጀለኛ የሚሆኑበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
‹‹ሁል ጊዜ በትዳር መኖር ላይቻል ይቻላል፡፡ ፍቺን ሳይፈጽሙ ልጆችን ግራ በተጋባና እቅድ በሌለው መንገድ ከማሳደግ ይልቅ፣ ትዳሩን መመለስ የሚቻል ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ አለዚያ ግን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ግልጽ በሆነ መንገድ ትዳሩን መቀጠል እንደማይችል ለልጆች አሳውቆ ፣ ልጆቹን ከአንዳቸው ጋር እንዲያድጉ በማድረግ፣ ባልና ሚስትነቱ የቀረባቸው ወላጆች፣ ወላጅነታቸውን ሳይተዉ በኃላፊነት ልጆቻቸውን የማሳደግ ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
ቢሆንም ግን የወላጆች ጠብ በልጆች ላይ የሚፈጥረው የሥነ ልቦና ቀውስ ትንሽ ነው ስለማይባል፣ ሥነ አዕምሮአዊ ሕክምና (ሳይኮቴራፒ) ሊሰጣቸው እንደሚገባም ባለሙያው ያሳስባሉ፡፡


