አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ናቸው፡፡ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን እንዲሁም ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ ደረጃዎች የሠሩ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 12 ዓመት ያህሉን በስዊድንና በአሜሪካ በተለይም በዋሽንግተንና ሎስአንጀለስ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች አገልግለዋል፡፡
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በሚባልበት ጊዜ የፖለቲካል ሳይንስና ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ትምህርታቸውን ጀምረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ከተቀየረ በኋላ በዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ በእንግሊዝ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ላንጋስተር በዲፕሎማሲና በስትራቴጂክ ስተዲስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በመጪው ሳምንት በአሜሪካና ካናዳ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ውይይት ለማድረግ ታቅዷል፡፡ በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርቡ በአሜሪካና ካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ስለሚኖረው ውይይት ቢገልጹልን?
አምባሳደር ታዬ፡- በመጪው ቅዳሜና እሑድ ሚያዝያ 1 እና 2 ቀን 2003 ዓ.ም. በአሜሪካና ካናዳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በልማት ጉዳይ ለመወያየት ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በአሜሪካ በሚገኙ 13 እንዲሁም በካናዳ በሁለት ግዛቶች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት የሚያካሒዱት ከ40 በላይ የሚሆኑ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ በአሜሪካ ከተሞች ዋሽንግተን፣ አትላንታ፣ ኮሎምበስ/ኦሃዩ፣ ሚኒያፖሊስ/ሚኒሶታ፣ ዳላስ፣ ቦስተን፣ ዴንቨር፣ ሲያትል፣ ሎስአንጀለስ፣ ላስቬጋዝ፣ ሳንሆዜና ኒውዮርክ እንዲሁም በካናዳ፤ ኦታዋና ቶሮንቶ ውይይቱ የሚካሔድባቸው ግዛቶች ናቸው፡፡ በሳምንቱ ሚያዝያ 8 ቀን 2003 ዓ.ም. ደግሞ በእንግሊዝ ለንደንና በጀርመን ፍራንክፈርት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይቱ ይቀጥላል፡፡
ሪፖርተር፡- የስብሰባው ዓላማ ምንድን ነው? ምን ያህል ተሳታፊስ ይጠበቃል?
አምባሳደር ታዬ፡- ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ለሚካሔደው ልማት የራሱ ድርሻ አለው፡፡ ተሳትፎው ያልተከፋፈለና ያልተናጠበ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ እስካሁን ባለን ተሞክሮ በየትኛውም አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ያለው ስሜት ብርቱ ነው፡፡ ይህን ብርታቱን ትርጉም ወዳለው የልማት እንቅስቃሴ መቀየር አለብን፡፡ በመሆኑም ዓላማው ኢትዮጵያ ለጀመረችው ልማትና እድገት ኢትዮጵያውያኑ በግብርና፣ በኢንዱስትሪው፣ በምርት፣ በእውቀት ሽግግርና በአገልግሎት መስጠት ዘርፍ እንዲሰማሩ ማወያየት ነው፡፡ በውይይቱ ላይም ከ15ሺሕ እስከ 20 ሺሕ በግዛቶቹ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሪፖርተር፡- የዲያስፖራውን የልማት ተሳትፎ እንዴት ያዩታል?
አምባሳደር ታዬ፡- የዲያስፖራው የልማት ተሳትፎ በትንሹ የሚታይ አይደለም፡፡ ከውጭ ገንዘብ በማስገባት (በሬሚታንስ) እና በእውቀት ሽግግር ያላቸው ተሳትፎ የጐላ ነው፡፡ ከሌሎች አገሮች ሲነጻጸር አነስተኛ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ ግን ካለፉት 10 ዓመታት ጀምሮ ዕድገቱ እየጨመረ ነው፡፡ ሬሚታንስና ብቻ ብናይ ባለፈው ዓመት ከኤክስፖርት ከምናገኘው ገቢ በተመጣጣኝ አግኝተንበታል፡፡ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶችም የተሠማሩ አሉ፡፡ ምናልባት በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት በልማቱ ያልተሳተፉ ዲያስፖራዎች የልማቱ አጋር እንዲሆኑ በሚኖረው ስብሰባ እናነጋግራለን፡፡ የልማትና የትራንስፎርሜሽን እቅዱ ላይም ገለጻ ይደረግላቸዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ አባላት በውይይቱ በሚሳተፉበት ጊዜ ገለጻ መስጠት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንዳቅሙ ሊሳተፍበት የሚችለውን ፕሮጀክት ይዘው ይሔዳሉ፡፡ መድረኩ የውይይት ብቻ ሳይሆን የሥራም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቤንሻንጉል ጉምዝ አካባቢ ይገነባል ለተባለው ግድብ ተሳታፊ እንዲሆኑ የመቀስቀስ ዓላማ ይኖረዋል?
አምባሳደር ታዬ፡- እንደ አገራችን ልጆች፤ እንደ ኢትዮጵያዊነታቸው በዚህ ዙርያ እንዲሳተፉ በጣም ይጠበቃል፡፡ አሁን የሚሠራው ግድብ በአብዛኛው በአገር ውስጥ ሀብት ነው፡፡ ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ቦንድ በመግዛት እንዲሳተፉ እንፈልጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- የስብሰባው ዓላማ ልማት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያዊውና ትውልደ ኢትዮጵያዊው ከተመዘገቡ ከ2 ሺሕ በላይ ፕሮጀክቶች ትግበራ ላይ ያሉት እንደሚነገረው ከሁለት መቶ እስከ ሦስት መቶ ቢሆኑ ነው፡፡ በርካታ ዲያስፖራ ኢንቨስተሮችን መያዝ ሌሎችን ለማበረታታት፣ ለማሳያነት ይጠቅማል፡፡ ወደሥራው ላለመግባታቸው ከመሬት፣ ከአፈጻጸምና ከሌሎችም የተያያዙ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ በልማት ላይ ለመወያየት ሲኬድ ለእነዚህ ምን መፍትሔ ተይዟል?
አምባሳደር ታዬ፡- ከአሜሪካ የመጡት ኢትዮጵያውያን በኢንቨስትመንት የተሰማሩባቸው ዘርፎች በርካታ ናቸው፡፡ በጥቅል በገንዘብ መጠኑ ሳይሆን በዓይነቱ ቢነገር ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ አሜሪካ የኖረ ሲባል ሰው የሚጠብቀው እጁ የለሰለሰ ቆዳው ያማረ ነው፡፡ ይህ በአብዛኛው ትክክል አይደለም፡፡ የሆነ ሆኖ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ሰቲት ሁመራ፣ አፋር ሔዶ ኦርሶ ሰሊጥ፣ ጥጥ በማምረት መሠማራቱ ገንዘቡ ሳይሆን ፈር ቀዳጅነቱ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ በግብርና ከምዕራብ አሜሪካ በንጽጽር በሰሊጥ፣ በጥጥ፣ በበቆሎና ማሽላ ምረት የተሠማሩ አሉ፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ውስን ቢሆንም በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዙርያ አሉ፡፡ ለምሳሌ አጐዋ በሰጠው እድል ተጠቃሚነታችን አናሳ ነው፡፡ ትንሽም ቢሆን አስተዋጽኦ እያደረጉ የሚገኙት ከአሜሪካ የመጡ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ በሌላ በኩል አገልግሎት በመስጠት በሆቴል፣ በቱሪዝም፣ በኬክ ቤት በመሳሰሉት የተሠማሩ አሉ፡፡ በዚህ ዘርፍ መሠማራት ዋነኛ ባይሆንም ለብዙ አዳጊ አገሮች የኢኮኖሚ ዋልታ የአገልግሎት ዘርፍ ኢንዱስትሪው ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ግን የግብርናውና የኢንዱስትሪው ዘርፍ መሠረት መሆናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ አሜሪካን ብንወስድ አገልግሎት ሰጪ እንዱስትሪው 42 በመቶ ያህል ይሸፍናል፡፡ በራስ አቅም የሚሠራ በመሆኑም እያንዳንዱ ሰው የራሱ ቢዝነስ እንዲኖረው ያስችላል፡፡ ሌላውና በአሜሪካም እያለን ብዙ የደከምንበት የእውቀት ሽግግር ነው፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ ውስጥ ስመጥር በሆኑ ኩባንያዎችና ዩኒቨርሲቲዎች ሲሠሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እዚህ መጥተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በምግብ ጥራት ላቦራቶሪ በማቋቋም አገርና ተቋማትን በመርዳት የጐላ ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡ በሌሎች መስኮችም አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው፡፡ በመንገድ ግንባታ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ብዙም ባይሆኑ እውቀት ያላቸው አሉ፡፡ እነሱን እስካሁን አልተጠቀምንባቸውም፡፡ በአሁኑ ውይይት ከሚታዩት ዘርፎች አንዱ ይሆናል፡፡ በገንዘብ ሲሰላ ውሱን ሊሆን ቢችልም በዓይነት ሲታይ በተለይ ከአሜሪካ የሚመጣ ኢንቨስትመንት ትርጉም አለው፡፡ በሽርክናም የሚያመጧቸው ኢንቨስትመንቶች አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በእውቀት ሽግግር ላይ በተለይ በጤናውና በትምህርት ዘርፍ ይመጣሉ፡፡ ሆኖም ከመጡ በኋላ ‘እንደምንፈልገው የእውቀት ሽግግር እንድናደርግ በተቀናጀ መልኩ የሚያግዝ አካል የለም’ ይላሉ፤
አምባሳደር ታዬ፡- ብዙ ጊዜ ፍላጐት ይኖርና የዝግጅት ጉድለት ይኖራል፡፡ ለምሳሌ በሕክምናና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚመጡ አሉ፡፡ በቡድን ብቻ ሳይሆን በግልም የሚመጡ ይኖራሉ፡፡ የዚህ አገር ፍላጐት በመገንባትና በመሥራት ላይ ያለ አገር በመሆኑ እጅግ ሰፊ ነው፡፡ የተፈለገውን ያህል የሕክምና ቡድን፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ባለሙያ ቢመጣ ለፍላጐቱ የሚረጥብ/የሚበቃ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን የተወሰኑ ይመጣሉ፣ ዝግጅት አይኖርም፡፡ አንዳንዴ በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በሌላ አገር ዜጐችም ድጋፍ ለመስጠት መጥተው ክፍተት ያጋጥማቸዋል፡፡ ሕግን ጠንቅቆ ካለማወቅ የሚመጣም ችግር አለ፡፡ ከበጐ አድራጊነት መንፈስ የሚመጡም ስለሆነ ተቀባዩ የምንሰጠውን ሁሉ ይቀበል የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ ዕርዳታ ሲሰጥ ተቀባዩ የሚፈልገው መሆኑን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ሕጎችንም ማወቅ ግድ ነው፡፡ እንደተባለው ከዝግጅት ማነስ እንደተፈለገው ላይሟላ ይችላል፡፡ ይህንን ለማቃናት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዋና ዳይሬክቶሬት አለ፡፡ ሥራው ድጋፍና ዕርዳታ ለማድረግ እንዲሁም ኢንቨስትመንት ላይ ለመሳተፍ ከሚመጡት ጋር አብሮ በመራመድ ማመቻቸት ነው፡፡ ክፍተቱን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡
ሪፖርተር፡- ዲያስፖራውን በልማት ለማሳተፍ ሲባል ከዚህ ቀደምም ከየክልሉ የተውጣጡ ባለሥልጣናት በየአገራቱ ሔደው ያወያዩ ነበር፡፡ ግን ተከታታይነት የለውም፡፡ የአሁኑም ዘግይቶ ነው የመጣው፤
አምባሳደር ታዬ፡- ሁል ጊዜ በመሔድ ብቻ መሥራት አይቻልም፡፡ አዳዲስ ዘዴዎችንም መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ባልሳሳት በአሜሪካ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሌለው ጥቂት ነው፡፡ ስለአገሩ ግንዛቤውን እያገኘ ነው፡፡ እንደዱሮው በአፍ የሚራገብ ነገር አይኖርም፡፡ ሰው በየቤቱ የኢትዮጵያን ልማት የሚያይበት እድል ተፈጥሮለታል፡፡ ወደጥያቄው ለመመለስ ያዝ ለቀቅ ዓይነት አካሔድ አለ፡፡ ግን ሔዶ ማወያየት ዋነኛው መንገድ ስለመሆኑ ማየት ይጠይቃል፡፡ የልዑካን ቡድን መላክ አንዱ መንገድ ነው፡፡ መላክ ብቻ ሳይሆን ፕሮጀክትም ማቅረብ አንድ ነገር ነው፡፡ አንድ ዕርምጃ ሔዷል፡፡ ነገር ግን ጋዜጦችን፣ ድረ ገጾችን፣ ሬዲዮ ጣቢያዎችን በመጠቀምም መሥራት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- አሜሪካ ተሔዶ የልማት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ጥያቄም መነሣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ተቀራርበን እንሥራ የምትሉበት አካሔድ ይኖራል?
አምባሳደር ታዬ፡- እንደአጋጣሚ ሆኖ ከልዑካን ቡድኑ ጋር አልሔድም፡፡ የሆነ ሆኖ የፖለቲካና አገራዊ ጥያቄዎች መነሣታቸው አይቀርም፡፡ ይጠበቃልም፡፡ ዋናው የሚፈለገው ምንም ይሁን፤ ጥያቄም ሆነ አስተያየት ይቅረብ፤ የምንፈልገው አስተያየት ሰጥቶ መቀበል ነው፡፡ በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ሲባል በአንድ እንቅብ ማየት ትክክል አይመስለኝም፡፡ በፊት የነበረው አስተሳሰብ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሲባል ሁሉም ፖለቲከኛ፣ መንግሥትን የሚጠላና የሚቃወም ተደርጐ ነበር፡፡ ይህ ዱሮም ትክክል አልነበረም፡፡ አሁንም ትክክል አይደለም፡፡ እንደማኅበራዊ ጥንቅሩ እንደ አካሔዱ እና እንደሔደበት ምክንያት አስተሳሰቡና አመለካከቱ የተለያየ ነው፡፡ ግን የተለያየ አስተሳሰብና አስተያየት ቢኖረውም ሁሉም የሚጋራው የአገሩ ፍቅር አለው፡፡ ይህ ሲባል ከዚህ አጠቃላይ ድምዳሜ ፈንጠር ብሎ የወጣ የለም ማለት አይደለም፡፡ እንደመንግሥት ሁሉንም ማስተናገድ አለብን፡፡ በመሆኑም ጥቂት የሚባሉ ከራሳቸው በመነጨ ምክንያት ወይም ደግሞ ከፖለቲካ አስተሳሰባቸው በመነሣት ምንም ይሁን ምን የማይስማማቸው ይኖራሉ፡፡ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ መገለጫ ባሕሪው ግን አገሩን የሚወድና የሚያፈቅር መሆኑ ነው፡፡ ድጋፍ መስጠት ብቻ ሳይሆን በአካል ተገኝቶ ተሳትፎ ማድረግ የሚፈልግ ነው፡፡ ችግሩ የአቅም ጉዳይ ነው፡፡ ቢሆንም ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡ ሊወያዩበትም ይችላሉ፡፡ ለሁሉም ክፍት ነው፡፡ አስተያየቶች ሁሉ ይምረሩም ይጣሙም ፋይዳ አላቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በልማት ለመሳተፍ ከሚመጡት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከአሜሪካ የሚመጡት ይበዛሉ፡፡ በናንተ በኩል በተሠራው ሥራ ነው?
አምባሳደር ታዬ፡- በኛ ሳይሆን በዋነኛነት በመስክ ላይ ባሉት ነው፡፡ የኛ ደጋፊ ሥራ ነው፡፡ እዛ ያሉ ሚሲዮኖች በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እንቁ ሊባል የሚችል፣ የመንግሥት ሳይሆን የአገር ሀብት በመሆኑ እንደመንግሥት ኢትዮጵያዊውን በተለይ ራሱ ሠርቶ ሊረካባቸው በሚችልበት፣ ቤተሰቡንና አገሩን በሚያኮራበት መስክ እንዲሰማራ የመንግሥት ፍላጐት ነው፡፡ በመሆኑም በየኤምባሲዎች በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳያቸውን የሚቀበል፣ የሚያበረታታ፣ የሚያመቻች አለ፡፡ ይህ ሲባል ችግር የለም ማለት አይደለም፡፡


