በምዕራፍ ብርሃኔ
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የኤች አይ ቪን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ፕሮግራም በመዘርጋት ተግባራዊ ለማድረግ ከ 24 የመንግሥት ልማታዊ ድርጅቶች ጋር ባለፈው ሐሙስ ተወያየ፡፡
ሚኒስቴሩ በሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ማስጠበቂያ ዳይሬክቶሬቱ አማካይነት በዘረጋው የሥራ ቦታ ኤች አይ ቪ/ኤድስን የመከላከልና የመቆጣጠር ፕሮግራም መሠረት፣ በአንድ የሥራ ቦታ የሚደራጀው የኤች አይቪ ኤድስ የመከላከልና የመቆጣጠር እንቅስቃሴ ፕሮግራም፣ ድርጅቱ ኤች አይ ቪ ኤድስን የሥራ ቦታ ችግር ብሎም በድርጅቱ ተልእኮ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያስከትል በመገንዘብ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል እንቅስቃሴ ማካሔድ እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡
ሚኒስቴሩ በ2001 ዓ.ም. ባወጣው የሥራ ቦታዎች የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕቀፍ ላይ በመመርኮዝ፣ ወረርሺኙን ለመከላከል የሚያስችል በሥራ ቦታ የሚገኙ ግለሰቦች፣ በማኅበረሰብና በቤተሰብ ዙርያ ራሳቸውን የሚያውቁበት መንገድ በአሠሪዎች ሊመቻች እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡ እንዲሁም በምርመራ አማካይነት ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው ወገኖች፣ በሚሠሩበት ቦታ በባልደረቦቻቸው መገለልና መድልዎ እንዳይከሠትባቸው፣ በማስተማርና ተገቢ መረጃዎችን በመስጠት፣ በሽታውን በተመለከተ ያለውን አስተሳሰብ ለመለወጥ እንዲረዳ፣ የምርመራና የምክር አገልግሎት ሠራተኛው የሚያገኝበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚገባቸው አቶ ዘርይሁን ገዛኸኝ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ልዩ ረዳት ተናግረዋል፡፡
ይህ ሠራተኞች ላይ በማተኮር እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ወደ ግል ተቋማትና ወደተቀሩት የመንግሥት ልማታዊ ድርጅቶች እንደሚስፋፋም አቶ መስፍን ይልማ የሰላማዊ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ማስጠበቂያ ዳይሬክቶሬት የሙያ፣ ጤንነትና ደኅንነት እንዲሁም የሥራ ሁኔታዎች ቁጥጥር አስተባባሪ ገልጸዋል፡፡
በሥራ ቦታ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ፖሊሲና ሕጎች አተገባበር ከፖሊሲው ጋር ሊያያዝ የሚገባ ሲሆን፣ ማንኛውም ከቫይረሱ ጋር የሚኖር ሠራተኛ በዚህ በኩል ከሚደርስበት አድልዎና ሌሎች ጉዳዮች ከሚያስከትሉበት ወከባና ጥቃት የሚከላከልለት ጥበቃ ያለው መሆኑንና ኤች አይ ቪ በደሙ ውስጥ በመኖሩ ወይም በበሽታው በመጠርጠሩ ምክንያት የሥራ ዕድልና ቅጥር ያለመከልከል ወይም ከሥራ ያለመባረር መብት እንዳለው ተገልጿል፡፡
እንዲሁም አስገዳጅ የሆነ የቅድመ ቅጥር የሕክምና ምርመራ በሕግ የተከለከለ ወይም ሕገወጥ ድርጊት መሆኑን፣ የሕክምና ምርመራ ሁሉ የሚከናወነው በዓለም ሥራ ድርጅት የኤች አይ ቪ/ኤድስ በሥራ ቦታ የተግባር መመርያም ሆነ ሌሎች ሰብዓዊ መብት የተመለከቱ ድንጋጌዎች መርሆችን በተከተለ መንገድ መሆን እንደሚገባውና ይኸውም ከምርመራ በፊትና በኋላ ደረጃውን የጠበቀ የምክር አገልግሎት በተደራጀበት፣ ሠራተኛው በቅድሚያ ስለጉዳዩ አውቆና መረጃ አግኝቶ፣ እንዲሁም የምርመራው ውጤት ምንም ይሁን ምን ምሥጢራዊነቱን ባሟላና ክሥተቱን ተከትለው የሚፈጠሩትን በተመለከተም ሠራተኛው አስፈላጊ ድጋፍ የሚያገኝበት መንገድ መኖር እንደሚገባውም ተጠቅሷል፡፡
በፖሊሲው መሠረት በሥራ ቦታ ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመቆጣጠር የድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎት ማደራጀትና ተግባራዊ ማድረግ ዋነኛው የፕሮግራሙ አካል ነው፡፡
በመሆኑም ማንኛውም “የድጋፍና የእንክብካቤ የሥራ ቦታ ኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር አገልግሎት” ቢቻል በድርጅቱ ውስጥ ቢከናወን ይመረጣል፡፡ አለዚያ ግን አገልግሎቱ ከድርጅቱ ውጪ እንኳን ቢሆን፣ አገልግሎቱን ከማደራጀትና ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ የአሠሪና የድርጅት ባለቤቶች ግዴታ ሊሆን የሚገባው ሲሆን ለድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎቶች ዋና ዋና ክፍሎች ምን ምን እንደሆኑ በግልጽ ማሳየትም እንደሚኖርበት ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም በሥራ ቦታ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሠራተኞችን ከሚያገለግል የድጋፍና እንክብካቤ አገለግሎት ከሚሰጥ ክፍል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግም አኳያ፣ አሠሪዎችና የድርጅት ባለቤቶች ከፍተኛ ኃላፊነትና ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ የተጠናው ጥናት አመልክቷል፡፡
የጥናታዊው ጽሑፍ አቅራቢ አቶ ዘርይሁን እንዳሉት ከሆነ፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ዕድሜአቸው ከ15-49 ከሆናቸው መካከል 1ሚሊዮን 38ሺሕ 892 ወገኖች ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ አያይዘውም ወላጆቻቸውን በኤድስ ሳቢያ ያጡ ወደ 885 ሺሕ 720 የሚገመቱ ሕፃናት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ግምታዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ጠቅሰዋል፡፡


