Thursday, Jun 20th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ኔቶ የሊቢያ አማፅያንን አስጠነቀቀ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

ኔቶ የሊቢያ አማፅያን በንጹኅን ዜጎች ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት እንዳያደርሱ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን የዘገበው ኒው ዮርክ ታይምስ ነው፡፡ ኔቶ የሊቢያን የአየር ላይ ጥቃት ተረክቦ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከሁሉም በላይ ዜጎችን ከጥቃት መጠበቅ ዋነኛ ዓላማው መሆኑን አስታውቋል፡፡ ተቃዋሚዎች በሕዝቡ ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያቆሙም አሳስቧል፡፡ የሙአመር ጋዳፊ ደጋፊ ቢሆኑም ባይሆኑም ሊቢያውያን ምንም ዓይነት ጥቃት ሊሰነዘርባቸው እንደማይገባ ጠቅሶ፣ ጥቃት የሚያደርሱትን ግን ቸል እንደማይላቸው ገልጿል፡፡ በተለይ እንደ ቤንጋዚ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ከፀረ ጋዳፊ ኃይሎች በሚደርስባቸው የኃይል ጥቃት ሳቢያ ውጥረት ውስጥ እንደሚገኙ ዘገባው አመልክቷል፡፡

*      *         *
በግሪክ፣ በስዊዘርላንድና በጣሊያን ፍንዳታዎች ደረሱ
በግሪክ፣ በስዊዘርላንድና በጣሊያን በደብዳቤ አማካይነት በደረሱ ተመሳሳይ ጥቃቶች በሦስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ችሶኒልቦ የተባለ ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡ ዘገባው የስዊዘርላንድን ፖሊስ ጠቅሶ እንዳመለከተው በስዊዝ ኑክሌር ኃይል ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ ሁለት ሠራተኞች የተላከላቸውን የፖስታ መልዕክት ሲከፍቱ ሊፈነዳ ችሏል፡፡ በሁለቱም ሠራተኞች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ በአስቸኳይ ወደ ሆስፒታል  ተወስደዋል፡፡ በስዊዘርላንድ አደጋው ከደረሰ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በጣሊያንም ተመሳሳይ አደጋ እንደደረሰ ያመለከተው ዘገባው፣ ለአንድ የጦር ኃይሉ አባል በተላከ ደብዳቤ ውስጥ የነበረ ፈንጂ ፈንድቶ ወታሩ ሁሉንም ጣቶቹን አጥቷል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሁለቱ አደጋዎች በደረሱበት ቀን በግሪክ እስር ቤት ቦምብ የያዘ ደብዳቤ የተላከ ቢሆንም በአካባቢው በነበረው ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ ምክንያት እስር ቤቱ ውስጥ ሳይፈነዳ ቀርቷል፡፡ ሦስቱም የቦምብ ጥቃቶች ከአንድ ቦታ የተላኩ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ መስጠት ባይቻልም፣ ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ በስዊዘርላንድ፣ በቺሊና በግሪክ ኤምባሲዎች ላይ ጥቃት ያደረሰው ‹‹ሥርዓት አልባው›› የሚባለው ቡድን ሊሆን እንደሚችል ተጠርጥሯል፡፡ ነገር ግን ቡድኑ ‹‹ግሪን ፒስ›› በተባለ ድረ ገጽ ላይ አሁን ስለደረሱት ፍንዳታዎች የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አስታውቋል፡፡

*      *         *

የሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲመረመሩ ተጠየቀ
የሊቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሳ ኩሳ ከድተው እንግሊዝ መግባታቸውን ተከትሎ በሎከርቢ አውሮፕላን ፍንዳታ ያለቁ መንገደኞች ቤተሰቦች ይመርመሩልን የሚል ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ኩሳ ከአጐራባቿ ቱኒዚያ ተነስተው ለንደን ከገቡ በኋላ በሰጡት አጭር መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርነት ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ እሳቸው እ.ኤ.አ በ1988 በቦምብ ፍንዳታ ላለቁ 270 መንገደኞች ዕልቂት አቀናባሪ ናቸው ተብሏል፡፡ ጋዳፊን ለመክዳት የተገደዱት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሰላማዊ ሕዝብ ላይ በሚፈጽሙት ጥቃት ምክንያት እንደሆነ መግለጻቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ሙሳ ኩሳ ከሙአመር ጋዳፊ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል አንዱ እንደነበሩ ተጠቁሞ አገሪቱ ከምዕራባውያን ጋር ያላት ግንኙነት እንዲሻሻል በማድረግ በኩል በግንባር ቀደምነት ተጠቃሽ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ ግለሰቡ የጋዳፊ የቅርብ ሰው የነበሩ ሲሆኑ፣ ለአሥራ አምስት ዓመታት የአገሪቱ የደኅንነት ኃላፊ በመሆን መሥራታቸውም ታውቋል፡፡

*      *         *

ሦስት የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከአገር እንዳይወጡ ታገዱ
በቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ አገዛዝ ወቅት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የነበሩ ሦስት ግለሰቦች በአገሪቱ ፍትሕ ሚኒስቴር አማካይነት ከአገር እንዳይወጡ መታገዳቸውን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ ነው፡፡ ሦስቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሙባረክ ከወረዱ ከአምስት ሳምንታት በኋላ ከአገር እንዳይወጡ የታገዱት በሙስና ተጠርጥረው የምርመራ ሥራ እየተሠራ ያለበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ የታገዱት ባለሥልጣናት የፓርላማ አፈ ጉባዔ፣ የገዢው ፓርቲ ባለሥልጣንና የፕሬዚዳንቱ ሠራተኞች የበላይ ኃላፊ እንደነበሩ ታውቋል፡፡ ምርመራው ተጣርቶ እስኪያበቃ ድረስም የትም እንዳይንቀሳቀሱ እገዳው መጣሉን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡