በጌታሁን ወርቁ
የዚህን ሰሞን ጋዜጦች ያጨናነቀው የጅማ ጉዳይ ነው፡፡ በጅማ ወደ 59 የሚሆኑ የፕሮቴስታንት አቢያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸው፣ በክርስቲያኖችና በሙስሊሞች መካከል ለተፈጠረው ግጭት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸው፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት የሰላምና የምክክር የጋራ ጉባኤ የተፈፀመውን አፀያፊ ተግባር በፅኑ አውግዘው መንግስት እየወሰደው ያለውን ጥረት ማድነቃቸው፣ ወ.ዘ.ተ. የተዘገበው ባለፉት ሁለት ሳምንታት ነው፡፡
ዜናውን ያነበበ ሁሉ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን በታሪክ በአገራችን መኖሩ የሚነገርለት የሃይማኖት መቻቻል ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ ድርጊቶች መከሰታቸውን መመስከሩ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በሃይማኖቶች መካከል የሚኖሩ አለመግባባቶች አንዱ ምንጭ የሃሐይማኖት ነፃነት መብትና ገደቡን፤ ሃይማኖቶች አስተምሮአቸውን የሚያስተምሩበትን /የሚያስፋፉበትን/ መንገድ በአግባቡ ካለመረዳት ሊሆን ስለሚችል በዚህ ጽሑፍ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችና በአገራችን ሕጎች የሃይማኖት ነፃነት መብትንና አፈፃፀሙን ለመዳሰስ ይሞከራል፡፡ በጽሑፉ በአገራችን ያሉ የተለያዩ እምነት አማኞችና ተከታዮች አምልኮታቸውንና አስተምሮአቸውን በሕግ አግባብ እንዲያደርጉ እንደሚረዳ ጸሐፊው ያምናል፡፡
የሃይማኖት ትርጉም
ቀደም ሲል ሃይማኖትን “በአንድ የበላይ ኃይል ወይም አምላክ ማመን” በሚል የሚሰጠው ትርጉም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥመውታል፡፡ ምክንያቱም በአንድ መንፈሳዊ ኃይል ማመንን የማይቀበሉ እምነቶች በመምጣታቸው ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ለሃይማኖት የሚሰጡት ትርጉም ሁሉን አቀፍ ሆኖ መቅረብ እንደሚገባው ይታመናል፡፡ ስለ መሠረታዊ መብቶች ትንታኔ የጻፈው ዮሴፍ ፓርቲሽ ሃይማኖትን “አንድ ግለሰብ መንፈሳዊ አካልም ይሁን በኃያል ማንነት ወይም በምክንያት ወይም በምክንያታዊነት ወይም በለውጥ ይመን ለዓአለም፣ ለኅብረተሰቡና የእርሱንና የዓለምን እጣ ፈንታ ስለሚወሰንበት ሁኔታ ያለው አመለካከት” በሚል ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ በሁሉም ተቀባይነት ያለው የሃይማኖት ትርጉም መፈለግ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ፈጽሞ የማይቻል ባለመሆኑ ለዚህ ጽሑፍ ፓርቲሽ የገለጸውን መጠቀም እንችላለን፡፡ ይህ ትርጉም ብላክስ ሎው የሕግ መዝገበ ቃላት ለሃይማኖት ከሚሰጠው ፍቺ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ የሃይማኖት ነፃነትን መብት ለመተንተን መነሻ እንደሚሆን ይታሰባል፡፡
የሃይማኖት ነፃነት ትርጉምና ወሰን
ብላክስ ሎው የሃይማኖትን ነፃነት /Freedom of religion/ “the right to adhere to any form of religion or none, to practice or abstain from practicing religious beliefs, and to be free from governmental interference with or promotion of religion as guaranteed by a fundamental law” በሚል ይተረጉመዋል፡፡ በዚህ መሠረት የሃይማኖት ነፃነት የተወሰኑ መብቶች ድምር መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ የሃይማኖት ነፃነት ስንል አንድ ሰው የመረጠውን እምነት የመያዝ /አለማመንን ጨምሮ/ የእምነቱን ስርዓት የመከተል፣ እምነቱን የማስፋፋት እንዲሁም ከመንግስት ያለአግባብ ጣልቃ ገብነት የመጠበቅ መብትን ያካትታል፡፡
እምነትን በነፃነት ማራመድ ማለት ከሁሉም በላይ የማመን መብትን እንዲሁም ምንም አይነት የእምነት አስተምህሮም ቢሆን የፈለገውን የመቀበል መብት ማለት ነው፡፡ የእምነት ነፃነት መጀመሪያም የግለሰብን እምነት ማክበር ነው፡፡ ማመን በድርጊት ከመገለጹ በቀር ውሳጣዊ በመሆኑ ከመንግስት ጥበቃ ውጭ ነው፡፡ ማንም ሰው አንድ ሰው የያዘውን የእምነት አስተሳሰብ ሊያውክ አይችልም፡፡ ጀፈርሰን “Religious belief neither breaks my leg nor picks my pocket” እንዳለው፡፡
የእምነት ነፃነት የመምረጥ ነፃነትንም ያካትታል፡፡ አንድ ሰው ካሉት እምነቶች በነፃነት የፈለገውን እምነት የመምረጥ፣ አዲስ እምነት የመመስረት ወይም ሁሉንም እምነቶች ያለመቀበል መብት አለው፡፡ ከመምረጥ መብት ጋር በተያያዘ ማንም ሰው የሚከተለውን እምነት የመተውም ሆነ ወደ ሌላ እምነት የመለወጥ መብት አለው፡፡ በራሱ አምነት ባይሆንም “አለማመንም” ከምንም እምነት ነፃ የመሆን መብት በመሆኑ እኩል ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፡፡
እምነት አምነውት የሚቀመጡት ብቻ አይደለም፡፡ የሚተገብሩት፣ የሚገልጹት፣ አማኞች ሊያደርጓቸው የሚገቡ፣ ከማድረግ እንዲቆጠቡዋቸው የሚገደዱ ድርጊቶች አሉ፡፡ በዚህ መሠረት አማኞች እምነትን መሠረት ያደረጉ ድርጊቶች /የሃይማኖትን ስርዓትን ማክበር፣ ማስተማርና እምነታቸውን ለማስፋፋት/ ነፃነት አላቸው፡፡ የሃይማኖት ስርዓት ማክበር መፆም፣ መፀለይ፣ የተከለከሉ ምግቦችን አለመመገብ፣ የአለባበስ ሰርዓትን መከተል፣ ወ.ዘ.ተን ያጠቃልላል፡፡ በሌላ በኩል የሃይማኖት ትምህርት በቃል፣ በጽሑፍ ወይም በኤሌክትሮኒክ ሚዲያ ሊሰጥ ወይም ሊሰበክ ይችላል፡፡ ያለሃይማኖት ትምህርት የእምነት ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ እምነትን ማስፋፋት ደግሞ የእምነቱን አስተምህሮ ለማያምኑ ወይም ሌላ እምነት ላላቸው ሰዎች መስበክ /ማስተማርን/ ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ሃይማኖታዊ ድርጊቶች በመንግስት ቁጥጥር ወይም ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ ግለሰቦች እምነታቸውን ሲተገብሩ ለኅብረተሰቡና ለሌላው ሰው መብት ጥንቃቄ ማድረግ፣ መንግስትም ከተገቢው ያለፈ ቁጥጥር እንዳይኖር መታቀብ ይገባዋል፡፡
ለሃይማኖት ነፃነት ሌላው ወሳኝ ነገር የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት /Secularism/ ነው፡፡ በዚህ መርህ መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ተቋማት እንደመሆናቸው መንግስት በሃይማኖት፣ ሃይማኖትም በመንግስት የውስጥ ስራ ውስጥ ጣልቃ ሊገቡ አይገባም፡፡ የመንግስት ከሃይማኖት ጣልቃ አለመግባት በተለይ ለአናሳ አማኞችና ለማያምኑ ዜጎች እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ የመንግስትና የሃይማኖት መለያየት እርስ በርሳቸው እንዳይተጋገዙ ያደርጋቸዋል ማለት አይደለም፡፡ ሃይማኖት በኅብረተሰቡ ውስጥ የሕግ የበላይነትና ግዴታ እንዲሰርጽ የሚረዳ ሲሆን፣ መንግስት ደግሞ የሃይማኖት ተቋማትን የመጠበቅ ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ፡- መንግስት የሃይማኖት ተቋማት የአደባባይ የአምልኮ ስርዓት ሲፈፅሙ የፖሊስ ኃይል በመመደብ ጥበቃ ያደርጋል፡፡
የሃይማኖት ነፃነት በዓለም ዓቀፍ ሕጎች
የተባበሩት መንግስታት የሃይማኖት ነፃነት እንዲከበር ከመጀመሪያው ስብሰባ ጀምሮ ብዙ ጥረት አድርጓል፡፡ በመጀመሪያቹ ስብሰባ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ አድሎአዊነት እንዲቀር የመከረ ሲሆን፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በፀደቁት መግለጫዎችና ስምምነቶች ላይ የሃይማኖት ነፃነት ተገቢ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡ ቀዳሚው የተባበሩት መንግስታት ሁሉን አቀፍ መግለጫ /Universal Declaration of Human Rights/ ሲሆን፣ ይህ ሰነድ መግቢያውን ጨምሮ በአንቀፅ 1፣ 2፣ 16፣ 18 እና 26 ላይ ለሃይማኖት ነፃነት ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ለአብነት ያህል አንቀፅ 18
“Every one has the right to freedom of thought, conscience and religion; this right includes freedom to change his religion or belief and freedom, either alone or in community with others and in public or private, to manifest his religion or belief in teaching, practice, worship and observance” በሚል ቀደም ሲል በዝርዝር የተመለከትናቸውን የሃይማኖት ነፃነት ዝርዝር መብቶች አካትቶ ደንግጓል፡፡ ተመሳሳይ ድንጋጌ በዓለም አቀፍ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ስምምነት /ICCPR/ አንቀጽ 18 ላይ ተደንግጓል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ሃይማኖትን ብቻ የሚመለከት ሰነድ ለማጽደቅ የነበረው ሐሳብ በተግባር ባይተረጎምም እ.ኤ.አ. በ1965 ማንኛውም ዓይነት የሃይማኖት አለመቻቻልን ለማስወገድ የተዘጋጀ ረቂቅ ስምምነት ዘርዘር ያሉ ድንጋጌዎችን እንዲይዝ ተደርጎ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ሰነዱ ያልፀደቀና በአባል አገሮች ላይ አስገዳጅነት ሰለሌለው ለዚህ ጽሑፍ ብዙ ረብ የለውም፡፡ በአህጉር አቀፍ ደረጃም በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ የሃይማኖት ነፃነትን በአግባቡ ዋስትና የሚሰጡ ድንጋጌዎች ተካተዋል፡፡
የሃይማኖት ነፃነት በኢትዮጵያ ሕግ
የሃይማኖት ነፃነት መብት የሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት ተካትቷል፡፡ ሕገ መንግስቱ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ሰነዶች የኢትዮጵያ ሕግ አካላት መሆናቸውን ከመደንገግ ባለፈ በሕገ መንግስቱ የተካተቱት ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ከዓለም አቀፍ ሰነዶች ጋር ተጣጥመው እንዲተረጎሙ ያስገድዳል፡፡ ስለዚህ ቀደም ሲል በጽንሠ ሐሳብ ደረጃና በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች በተካተተው መልኩ የሃይማኖት ነፃነት ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 27/1/ ደግሞ “የሃይማኖት፣ የእምነትና የአመለካከት ነፃነት” በሚል ርዕስ “ማንኛውም ሰው የማሰብ፣ የሕሊናና የሃይማኖት ነፃነት አለው፡፡ ይህ መብት ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል፣ ሃይማኖቱንና እምነቱን ለብቻ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በይፋ ወይም በግል የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን ያካተታል” ሲል ከዓለም አቀፉ የሲቪልና የፖለቲካ ቃል ኪዳን ስምምነት አንቀጽ 18 ጋር የሚመሳሰል ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡
ሕገ መንግስቱ የሃይማኖትን ነፃነት “ከማሰብና ከሕሊና ነፃነት” ጋር በማያያዝ የማያምኑ /Atheist and other non-believers/ ሰዎችን መብት እውቅና ሰጥቷል፡፡ ማመን ውሳጣዊ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ሕገ መንግስቱ በአንቀጽ 27/3/ ‘ማንኛውንም ሰው የሚፈልገውን እምነት ለመያዝ ያለውን ነፃነት በኃይል ወይም በሌላ ሁኔታ በማስገደድ መገደብ ወይም መከልከል አይቻልም’ በማለት ፍፁማዊ የእምነት /Belief/ መብትን ጥበቃ ሰጥቷል፡፡ ሕገ መንግስቱ ሃይማኖትን በተግባር የመግለፅ መብትን ለዜጎችም ሆነ ዜጋ ላልሆኑ ሰዎች የሰጠ ሲሆን፣ በግል ወይም በሕብረት የማምለክ፣ የመከተል፣ የመተግበር፣ የማስተማር ወይም የመግለጽ መብትን በአግባቡ በማካተት ደንግጓል፡፡
ሃይማኖት የማስፋፋት መብት በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 27/2/ የሃይማኖት ትምህርትና የአስተዳደር ተቋማት ማቋቋምን የሚጨምር እንደሆነ ቢገለጽም፣ ትምህርትን በተመለከተ በአንቀፅ 90/2/ የተወሰነ ገደብ ተጥሎበታል፡፡ ይህ ድንጋጌ “ትምህርት በማናቸውም ረገድ ከሃይማኖት…. ተፅዕኖዎች ነፃ በሆነ መንገድ መካሄድ አለበት” ስለሚል የሃይማኖት ተቋማት የእምነት ትምህርት ካልሆነ በቀር መደበኛ ትምህርት ቤት ሲያቋቁሙ ይህን ገደብ ግምት ውስጥ ሊያስገቡ ይገባል፡፡
ሕገ መንግስቱ በአንቀፅ 11 መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን፤ መንግስታዊ ሃይማኖት እንደማይኖር በመግለጽ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ፣ ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ይደነግጋል፡፡ ይህም ለሃይማኖት ነፃነት መብት አፈፃፀም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
ከሕገ መንግስቱ በተጨማሪ ሌሎች ሕጎችም ለሃይማኖት መብት ጥበቃ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ረገድ በሃይማኖት ሥርዓት መሠረት የሚፈፀም ጋብቻን እውቅና የሚሰጠው የቤተሰብ ሕግ፣ የሕገ መንግስቱን አንቀጽ 34/5/ ተከትሎ በሃይማኖት የመዳኘት መብትን እውቅና የሚሰጡ አዋጆች ለዓብነት ይጠቀሳሉ፡፡ የወንጀል ሕጉም በአንቀፅ 792 “የሃይማኖትን ሰላምና ስሜት መንካት” ወንጀል እንደሆነ በመግለጽ፣
“ማንም ሰው አስቦ በአደባባይ፡-
ሀ/ የተፈቀደውን ሃይማኖታዊ ሥርዓት፣ ሥነ በዓል ወይም ሃይማኖታዊ ተግባር እንዳይፈፀም የከለከለ፣ ያወከ ወይም ያስተሐቀረ እንደሆነ፤ ወይም
ለ/ ለሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የሚያገለግለውን ቦታ፣ ሥዕል ወይም ዕቃ ያረከሰ እንደሆነ
ከአንድ ሺሕ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከሁለት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ይቀጣል” ሲል ይደነግጋል፡፡
የሃይማኖት ነፃነት መብት ላይ የሚጣል ገደብ
ሕገ መንግስቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተፈረሙት የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች ጋር የተጣጣመ ገደብ በሃይማኖት መብት ላይ ይጥላል፡፡ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 25/5/ “ሃይማኖትንና እምነትን የመግለጽ መብት ሊገደብ የሚችለው የሕዝብን ደህንነት፣ ሰላምን፣ ጤናን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታ፣ የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶች ነፃነቶችና መንግስት ከሃይማኖት ነፃ መሆኑን ለማረጋገጥ በሚወጡ ሕጎች ይሆናል” በማለት ደንግጓል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የሚገደበው የሃይማኖት መብት /የመረጡትን እምነት መያዝ/ ሳይሆን አገላለጹ ነው፡፡ የእምነት /አመለካከት/ መብት ፍፁማዊ በመሆኑ አይገደብም፤ መገደብም አይቻልም፡፡ አገላለጹን በተመለከተ ግን በሕግ በተዘረዘሩት ሰባት ምክንያቶች ሊገደብ ይችላል፡፡
ሃይማኖትን የመግለጽ መብት ለሕዝብ ሰላምና ደህንነት ሲባል ገደብ ሊጣልበት ይችላል፡፡ የአንድ እምነት የአምልኮ ስርዓቶች ኅብረተሰቡን የሚረብሹ፣ የሕዝቡን ስርዓትና ደህንነት የሚያናጉ፣ በኅብረተሰቡ ሕይወት፣ ህልውናና ንብረት ላይ ከባድ አደጋ የሚያደርሱ ሆነው ከተገኙ መንግስት ሕግ በማውጣትና ገደቡም በአግባቡ እንዲመራ በማድረግ ገደብ ሊጥል ይችላል፡፡ ገደቡ ግልጽና የማያሻማ ካልሆነ የግለሰቦች የሃይማኖት ነፃነት መብት ሊጣስ ስለሚችል በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ የሃይማኖት ዶግማ ወይም አፈፃፀሙ በአማኞቹ ጤናም ላይ ሆነ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ጎጅ ከሆነ መብቱ ሊገደብ ይችላል፡፡ “የሕዝብ ሞራል” የሚለው ቃል አከራካሪም ቢሆን የሃይማኖት ሥርዓቱ የኅብረተሰቡን መልካም እሴቶችን የሚቃረን መሆኑን መንግስት ካመነ ገደብ ሊጥል ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሕፃናት ለመስዋዕትነት እንዲቀርቡ የሚያስገድድ ሃይማኖት ቢኖር ገደብ መጣሉ አግባብ ነው፡፡ ምክንያቱም ድርጊቱ ወንጀል ከመሆን ባለፈ ኅብረተሰቡ ለሰው ልጅ ነፍስ ቅዱስነት ያለውን እሳቤ የሚሸረሽር ስለሆነ ነው፡፡ በተጨማሪም የሕፃናትን በሕይወት የመኖር መብት የሚጥስ ይሆናል፡፡ የሌሎች ሰዎችን መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች መጋፋት ለመብት ገደብ ምክንያት የሆነውም ለዚህ ነው፡፡ “አንድ ሰው እጁን የመዘርጋት መብቱ የሌላውን አፍንጫ እስካልነካ ድረስ ነው” የሚባለው አነጋገር ይህንኑ ለማጠየቅ ነው፡፡
በተግባር የሚስተዋሉ ችግሮች
ብዙሃ-ሃይማኖት የሃይማኖት ነፃነት ቀጥታ ውጤት ነው፡፡ ሆኖም ሃይማኖቶች “የእውነት ሞኖፖሊ” ጥያቄ ሲያቀርቡ ሌሎቹ እምነቶች ያላቸውን እኩል ክብር አለመቀበልን ያስከትላል፡፡ በሃይማኖቶች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች የሚመነጨው ከዚሁ ጥያቄ ነው፡፡ ብዙ ሃይማኖቶችና የሥነ ምግባር ትውፊቶች “ሌላው ሊያደርግብህ የማትፈልገውን አንተም እንዲሁ አታድርግበት” የሚለውን “ወርቃማው መርህ” ይቀበላሉ፡፡ አተገባበሩ ግን ከዚህ የራቀ ነው፡፡ በሃይማኖቶች መካከል ያለው መቻቻል ቀደም ሲል አገራችን በምትኮራበት ደረጃ ነው ለማለት የማያስችሉ ተሞክሮዎችን እያስተዋልን ነው፡፡
ይታክቱ ጥበቡ የተባሉ የሕግ ባለሙያ እ.ኤ.አ. በ2006 “Freedom of Religion and Propagation of Religious Precepts in Ethiopia” በሚል በሠሩት መመረቂያ ጽሑፋቸው፣ በአገራችን ሰፋ ያለ ተከታይ ያላቸውን የኦርቶዶክስ ክርስቲያን፣ የሙስሊምና የኢቫንጀሊካል እምነቶች ለዘመናት በመቻቻል የኖሩ መሆኑን በመግለጽ፣ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ግን በሃይማኖቶች መካከል አለመግባባቶች መስፋታቸውን ያትታሉ፡፡ የሕግ ባለሙያዋ በጽሑፋቸው በሃገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት በአማኞች መካከል የተነሱ ችግሮችን በማንሳት የችግሮችን መንስኤዎች ተንትነዋል፡፡ የችግሮቹ መንስኤ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ምክንያት ያላቸው መሆኑን በመጥቀስ በአብዛኛው የሚነሱ የፖለቲካም ሆነ የቡድን ወይም የብሔር ግምቶች አልፎ አልፎ የሃይማኖት ጉዳዮችም የተነሱበት አጋጣሚ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡
ይታክቱ በጥናታቸው በሃይማኖት መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች መነሻቸው ከእምነት ማስተማርና ማስፋፋት /Propagation/ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ክፍተቶች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ የድምጽ መሣሪያ /ማይክሮፎን/ አጠቃቀም በአግባቡ አለመገዛቱ፣ በመጽሐፍት መልክ የሚታተሙ ስብከቶች ወይም ትምህርቶች የእምነቱን ዶክትሪን ከመግለጽ ባለፈ በሌላው እምነት ላይ የጥላቻ መንፈስ የሚያጭሩ መሆናቸው፣ ተመሳስለው ወደ ሌላ የእምነት ተቋም በመሄድ ውስጥ ለውስጥ ሰበካ ማካሄድ፣ ማኅበራዊ አገልግሎቶች በሚሰጥባቸው የሕዝብ አደባባዮች፣ የአውቶብስ መቆሚያ አካባቢ፣ እንዲሁም አውቶብስ ውስጥ የሚደረጉ ‘የሰው ለሰው’ ወይም ‘የጎዳና’ ሰብከቶች ለግጭት መንስኤ እንደሆኑ በጥናታቸው ገልጸዋል፡፡ በጥናታቸው ማጠቃለያም መንግስት የሌላውን እምነት የሚሰድቡ ወይም የሚያዋርዱ የጽሑፍ የሃይማኖት ማስፋፊያዎችን /መጽሐፍት፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች/ በተመለከተ ገደብ ቢያደርግ፣ በሌላ የእምነት ተቋም ውስጥ የሚደረጉ የእምነት ማስፋፋት ዘዴዎች ቢታገዱ፣ የድምጽ ማጉያ ቮልዩም የሚገዛ ሕግ ቢወጣ፣ እንዲሁም የሕዝብ ሰላምን የሚረብሹ በሕዝብ ቦታዎች የሚደረጉ የሃይማኖት አስተምሮዎች እንዲከለከሉ ጠቁመዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምንመለከተታቸው እምነትን መሠረት ያደረጉ አለመግባባቶች አጥኚዋ ከደረሱበት መደምደሚያ ላይ የሚያደርስ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ አለመግባባቶች መነሳት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ያሉትን ጉዳዮች በአግባቡ በማጥናት፣ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት፣ ግልጽ ስትራቴጂ ማስቀመጥ ወቅታዊ መሆኑን ጸሐፊው ያምናል፡፡
በአጠቃላይ የሃይማኖት ነፃነት መብት መሠረታዊ ሕገ መንግስታዊ መብት ቢሆንም፣ በአፈፃፀሙ ገደብ የሚጣልባቸውን ሁኔታዎች በሕግ የተቀመጡ በመሆኑ መንግስት ከጊዜ ወደ ጊዜ ለሕዝብ ሰላም መታጣት መነሻ የሚሆኑ ግጭቶችን ለመቆጣጠር ዝርዝር ሕግ የማውጣቱ ጊዜ መድረሱን ያሳያል፡፡ በሌላ በኩል በማንኛውም ሁኔታ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሰዎችን መግደል፣ የአምልኮ ቤቶችን ማቃጠል ከሃይማኖት ነፃነት መብትን ከመጠቀም ጋር የማይያያዝና ሊወገዝ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ መንግስት የሚወስደው ሕጋዊ እርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ የእምነት ተቋማት ተከታዮቻቸው ሕጋዊ ሆነው በመቻቻል እንዲኖሩ ማስተማር ግዴታቸው ነው፡፡ “ሌላው ሊያደርግብህ የማትፈልገውን አንተም እንዲሁ አታድርግበት” የሚለው ወርቃማ መርህ በምድር ላይ ተፈጽሞ እናየው ይሆን?
ከአዘጋጁ፡- ፀሐፊውን በ
This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it
ማግኘት ትችላላችሁ፡፡


