በጦርነት እጅግ አስገራሚና አኩሪ ታሪክ አስመዝግበናል፡፡ ታሪክ ሠርተናል፡፡ ሐውልት አቁመናል፡፡ ጀግኖች መሆናችንን፣ የቅኝ አገዛዝን የምንቃወምና ለነፃነታችን ቀናኒ መሆናችንን የሚያሳይ ሐውልት ተክለናል፡፡
በቅኝ ግዛት ያልተገዛ ሕዝብም ተብለናል፡፡
የላሊበላ፣ የፋሲል፣ የአክሱም ግንቦችና ሐውልቶችም ጥንታዊና ታሪካዊ ሕዝብ መሆናችንን አሳይተውልናል፡፡ መስክረውልናል፡፡
መስጊዶቻችንና ቤተ ክርስቲያኖቻችንም፣ ከተሞቻችንና ገጠሮቻችንም አለባበሳችንና ባህላዊ ዘፈኖቻችንም፣ ሕብረ ብሔርና ሕብረታውያን ስለመሆናችን መስክረዋል፡፡ ክርስቲያኑም፣ እስላሙም፣ ፈላሻውም፣ ሁሉም ብሔር ብሔረሰብም በሰላም ካለግጭትና ፍጅት በሰላም የሚኖር አርአያ ሕዝብ መሆኑን መስክረዋል፡፡
በሁሉም ዘርፍ ሐውልት እየተከተልንና ታሪክ እየሠራን ስንመጣ ግን በልማት በኩል ግን ሐውልት የለንም፡፡ ታሪክም አልሠራንም፡፡
አሁን ዕድል አለ፡፡ እንዳያመልጠን፡፡ በሕዝብ ገንዘብ፣ በሕዝብ ትብብር፣ በሕዝብ ፍላጐትና ዓላማ ሊሠራ የሚችል የኃይል ማመንጫ ግድብ ለመሥራት በሩ ተከፍቷል፡፡ የሚሌኒየሙ ግድብ፡፡
ሊያበድሩ የሚችሉ ባንኮች አናበድርም እያሉ ናቸው፡፡ ዕርዳታ የሚሰጡትም ለዚህ አንሰጥም እያሉ ናቸው፡፡ ኃላፊነቱ በኢትዮጵያውያን ላይ እየወደቀ ነው፡፡
እንሥራው ወይስ አንሥራው?
የመሥራቱና የመገንባቱ ጉዳይ አማራጭ የሌለው ነው፡፡ የኃይል ማመንጫ ጉዳይ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ጉዳይ ነው፡፡ የእርሻ ጉዳይ ነው፡፡ የጤና ጉዳይ ነው፡፡ የትምህርት ጉዳይ ነው፡፡ የትራንስፖርት ጉዳይ ነው፡፡ የኮሚዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ጉዳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ የልማት ጉዳይ ነው፡፡ ይዋል ይደር የማይባል የልማት ጉዳይ ስለሆነም የግድ ልንሠራው ይገባል፡፡
ከልማት ጐን ለጐን ያለው ደግሞ ታሪክ የምንሠራበት ጉዳይ ነው፡፡ ሊያመልጠን የማይገባ ታሪካዊ ጉዳይ፡፡ ኢትዮጵያውያን በጋራ እጅ ለእጅ ተያይዘው አንድ ብርና አሥር ብር አዋጥተው፣ የኃይል ማመንጫ ሠሩ የሚልና ለቀጣዩ ትውልድ የልማት ሐውልት ተከሉ፤ አስረከቡ የሚያሰኝ ልዩ ታሪካዊ መድረክ ነው፡፡
የጦርነት ሐውልት፣ የድል ሐውልት፣ የውበት ሐውልት፣ የታሪካዊነትና ጥንታዊነት ሐውልት አለን፡፡ የልማት ሐውልቱን ግን አሁን እንገንባ፡፡
ያውም አቶ እከሌና መሪ እከሌ ተከሉት፤ ገነቡት፤ ሳይባል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ገነባው፤ ተከለው፤ አስቆመው፤ የሚባል ሐውልት፣ ለቀጣዩ ትውልድ በኩራት የምናስተላልፈውና መጪው ትውልድም የሚኮራበት ሐውልት ይሆናል፡፡
እዚህ ጋ አንድ በግልጽና በድፍረት የምንነጋገርበት ጉዳይ አለ፡፡ መነሣቱ አይቀርምና ደፍረን እናንሣው፡፡
የሚሌኒየም ግድብ ግንባታን መደገፍ፣ ቦንድ መግዛትና ማስተባበር የኢሕአዴግ ደጋፊዎች አጀንዳ ነውን? የፖለቲካ አቋም ተመሳሳይነት ያላቸው ሰዎች ብቻ የሚደግፉት ነውን? የኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችስ የግድቡን ግንባታ ሊደግፉት ይችላሉን?
መልሳችን ግልጽና ግልጽ ነው፡፡ የሚሌኒየም ግድብን ማሳካት የአገር አጀንዳ፣ የሕዝብ አጀንዳ፣ የልማት አጀንዳ እንጂ የፖለቲካ አጀንዳ አይደለም፡፡ የኢሕአዴግ ደጋፊ የሚደግፈው የኢሕአዴግ ተቃዋሚ የሚቃወመው ጉዳይ አይደለም፡፡
በሰለጠኑ አገሮች የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦችና የፖለቲካ ፓርቲዎች በአየር መንገድም፣ በምድር ባቡርም፣ በዩኒቨርሲቲዎችም፣ በግድቦችም፣ በጠፈር ምርምርም እየተባሉና እየተናከሱ አይውሉም፡፡ የጋራ አጀንዳቸው አድርገው ይወስዳሉ እንጂ፡፡ በአተገባበሩ ላይ ልዩነት ካለ ይከራከራሉ እንጂ፤ ያኛው ይልማ ሌላኛው አይልማ እያሉ አይከራከሩም፤ አይጣሉም፤ አይለያዩም፡፡
እኛም ይህን ብስለት እናሳይ፡፡ እኛም ከፖለቲካ በፊት አገር እናስቀድም፡፡
በአፄ ምኒልክ ጊዜ መኪና ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቷል፡፡ አፄ ምኒልክን መደገፍና መቃወም ከመኪና መግባትና አለመግባት ጋር መያያዝ የለበትም፡፡ ደጋፊ መኪና ይግባ ብሎ፣ ተቃዋሚ አይግባ ካለ ድንቁርና ነው፡፡
በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጥቁር አንበሳ ተገንብቶ ከሆነ ወይም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተገነባ የሳቸው ደጋፊ ዩኒቨርሲቲ መቋቋሙን ወዶ፣ ተቃዋሚ ለምን ዩኒቨርሲቲ ይገነባል ካለ ድንቁርና ነው፡፡
በደርግ ጊዜ ሙገር ሲሚንቶ ከተገነባ ደጋፊዎች ወደውት፣ ተቃዋሚዎች ግን ለምን በደርግ ጊዜ የተገነባ የሲሚንቶ ፋብሪካ እንወዳለን ካሉ ድንቁርና ነው፡፡
በደርግ ጊዜ ቀለበት መንገድ ከተሠራና የኃይል ማመንጫ ከተገነባ ተቃዋሚዎች በኢሕአዴግ ከሚሠራ በቀረብን ይሻላል ካሉ የድንቁርናዎች ሁሉ ድንቁርና ይሆናል፡፡
አፄ ምኒልክም መኪናውን ይዘው አልሔዱም፤ ለአገር ተርፏል፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴም ዩኒቨርሲቲውን አልወሰዱትም፤ ለአገር ተርፏል፡፡ ደርግም ሲሚንቶ ፋብሪካውን አልወሰደውም፤ ለሕዝብ ተርፏል፡፡ ኢሕአዴግም የኃይል ማመንጫውን አይወስደውም፤ ሲያልፍ ለአገር የሚተርፍ ይሆናል፡፡
ስለዚህ፣ ከፖለቲካ ነፃ በሆነ አመለካከት ተቃዋሚም ደጋፊም፣ ሽማግሌና አሮጊትም፣ ወጣትም፣ ክርስቲያንና እስላሙም፣ በውጭ ያለውም በውስጥ ያለውም፣ የሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ በጋራ፣ በራሱ ገንዘብና እውቀት፣ ጉልበትም ግንባታውን እውን ያድርገው፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ለሚሌኒየም ግንባታ ድጋፍ ይቋቋም፡፡ ሁሉም ይተባበር፤ ይተጋገዝ፣ ሳንሠራ እንዳያመልጠን፡፡
ታሪክ እንሥራ! የሚሌኒየሙን ግድብ በሕዝብ ትብብር እውን እናድርገው! የልማት ሐውልት እንገንባ!!


