በኃይሌ ሙሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትናንት በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የመንግሥታቸውን የስምነት ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ በበርካታ የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ቢሆንም፣ በዕለቱ የአብዛኛዎቹን የፓርላማ አባላት ትኩረት የሳበው ጉዳይ ግን ሰሞኑን ለሕዝብ ይፋ የሆነው የዓባይ ግድብ ግንባታና ከግንባታው ጋር ተያይዞ የሚነሳው ስጋት ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥታቸውን የስምንት ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማ ያቀረቡት የዓባይ ግድብ የመሠረት ድንጋይ በተጣለ ማግስት መሆኑ የፕሮጀክቱ ጉዳይ የምክር ቤቱ የመወያያ አጀንዳ እንደሚሆን በብዙዎች ዘንድ ተጠብቆ ነበር፡፡ እንደተጠበቀውም ጉዳዩ የዕለቱ ዋና አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል፡፡
ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው በሚፈልጓቸው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ጥያቄ እንዲያቀርቡ ዕድል የተሰጣቸው አብዛኛዎቹ የፓርላማ አባላት የዓባይን ግድብ ጉዳይ ሳያነሱት አላለፉም፡፡ ለዚህም ይመስላል አቶ መለስ በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት፡፡ ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለግብፅና ሱዳን ያለውን ጠቀሜታ፣ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ገድባ ተጠቃሚ እንዳትሆን ለማድረግ የግብፅ መሪዎች ለዘመናት ሲያካሂዱት የነበረውን ሸፍጥና ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ ያሉትን ስጋቶች በሰፊው ቃኝተዋል፡፡
የግብፅ ቅኝ ገዢ የነበረችው እንግሊዝ ግብፅ ውስጥ በመስኖ ይመረት የነበረውን ጥጥ በአስተማማኝ መልኩ ለማግች ስትል የዓባይ ወንዝ እንዳይገደብ ከፍተኛ ጥረት አድርጋ እንደነበር ያስታወሱት አቶ መለስ፣ ግብፅ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች በኋላም ሥልጣን ላይ የወጡት የአገሪቱ መሪዎች ይህንኑ የእንግሊዝ አቋም በመያዝ በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት ግድብ እንዳይገነባ ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ መለስ ገለጻ፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ግድብ እንዳትገነባ ለማድረግ ግብፅ ሦስት ስትራቴጂዎችን ነድፋ ለበርካታ ዓመታት ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡ እነዚህ ስትራቴጂዎችም፡-
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ለምትሠራው ግድብ የምትፈልገውን ብድርና ዕርዳታ እንዳታገኝ ማደናቀፍ፣ ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ማተራመስና በጣም ግዙፍ ወታደራዊ ኃይል በመፍጠር ኢትዮጵያ አደጋውን በስጋት እንድታየው ማድረግ የሚሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የግብፅ መሪዎች አገራቸው ያላትን ጂኦ ፖለቲካል ተፅዕኖ በመጠቀም ኢትዮጵያ ለግብድ ግንባታ የምትፈልገውን ዕርዳታ እንዳታገኝ ሲያካሂዱት የነበው የማደናቀፍ ሥራ ሲሳካላቸው የቆየ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መለስ፣ ከስምንት ወር በፊት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ግለሰብ ‹‹[ለዓባይ ወንዝ ግድብ መሥሪያ የሚውል] ብድርና ዕርዳታ እንዳትሰጡ፤ ብድር የምትሰጡ ከሆነ ከግብፅ ጋር ነው የምትጣሉት፤ ከግብፅ ጋር መጣላት ደግሞ ከዓረቡ ዓለም ጋር መጣላት ነው፤›› በማለት ዕርዳታና ብድር ለሚሰጡ አገሮችና ተቋማት ደብዳቤ መጻፋቸውን ግብፅ ስታካሂደው ለነበረው የማደናቀፍ ሥራ እንደአንድ ምሳሌ አድርገው ጠቅሰውታል፡፡
አቶ መለስ እንደሚሉት ሁለተኛውን ስትራቴጂ ማለትም ኢትዮጵያን በእጅ አዙር የማተራማስ ስትራቴጂ ግብፅ ስትከተል የነበረው ኢትዮጵያ ግጭትና ትርምስ ውስጥ ከገባች ዜጐቿ በልማት ሥራ ላይ ለመሰማራት ጊዜውም አቅሙም አይኖራቸውም የሚል ግምት በመያዝ ነበር፡፡ ግብፅ ይህንን ስትራቴጂዋን ለመተግበርም አልሸባብን፣ ኦብነግና ኦነግ የመሳሰሉትን የአገሪቱን ፀረ ሰላም ኃይሎች እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በነጭ ለባሽነት የተሰለፈውን የኤርትራ መንግሥት በመጠቀም ኢትዮጵያን ለማተራመስ ሥትሠራ መቆየቷን፣ ይህንን የማተራመስ ስትራቴጂን ሲመሩ የነበሩትም የቀድሞው የግብፅ የደኅንነት ኃላፊ አሕመድ ሱሌማን (ሙባረክ ሥልጣን ከመውረዳቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ምክትል ፕሬዚዳንት አድርገው የሾሟቸው) እንደነበሩም አብራርተዋል፡፡
ሦስተኛው የግብፅ ስትራቴጂ ነው ተብሎ በአቶ መለስ የተገለጸው በጣም ግዙፍ ወታደራዊ ኃይል በመፍጠር ሌሎች አደጋውን እንዲሰጉ ማድረግ ነው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት ይህንን ስጋት ለመፍጠር ግብፅ ስድስት ሚሊዮን የሚሆን ተጠባባቂ ጦር አዘጋጅታለች፡ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሰው የጦር ኃይል በቋሚነት የተሰለፈ ነው፡፡
በቅርቡ ግብፅ ውስጥ የተነሳው ሕዝባዊ አመፅ ከዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በመሪዎቹና በሕዝቡ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ያስከትላል የሚለው ጥያቄ ወደፊት የሚታይ መሆኑኑ የገለጹት አቶ መለስ፣ የግብፅ መሪዎች ይዘውት ከቆዩት የተሳሳተ አመለካከት እንዲወጡ ለማድረግ የግብፅን መንግሥት የጥፋት መንገድ እንደማያዋጣ ማስገንዘብ፣ ከግብፃውያን ጋር የሚገናኝ በማንኛውም ደረጃ የሚገኝ ኢትዮጵያዊም የግብፅ ሕዝብ በዓባይ ግድብ ከማንም በላይ ተጠቃሚ እንጂ ተጐጂ እንዳልሆነ፣ የግብፅ ሕዝብም የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት እንዳልሆነ በማስገንዘብ በኩል የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል፡፡
አቶ መለስ እንደሚሉት የግብፅ መንግሥት በዓባይ ወንዝ ግድብ ላይ ያለው የተሳሳተ አመለካከት እስከሚለወጥና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የግብፅ ጋዜጦችና ባለሥልጣኖች የማነገሩ ጥሩ ጥሩ ቃላቶች እስከሚያድጉ ድረስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊከሰት የሚችለውን ማንኛውንም ስጋት ለመከላከል ተዘጋጅቷል፡፡ ‹‹ግብፅ የምታካሂደውን የማስፈራራት ስትራቴጂ ለማስወገድ መንግሥት የሚከተለው ፖሊሲ አለመፍራት ነው፤›› ሲሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ካደረጋቸው ዝግጅቶች መካከል አንዱን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የፓርላማ አባላትን ፈገግ አሰኝቷል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ብትፈጽም ሊከሰት የሚችለው አደጋ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ‹‹በጣም ትንሽ ለሆነ አደጋ እንቅልፍ የምናጣበት ምክንያት የለም፡፡ አምስት በመቶ ትኩረት ሰጥቶ የመከላከል አቅማችንን መገንባት [በቂ] ነው፡፡ ስጋቱን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም አለን አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረግን ነው፤›› ብለዋል፡፡
በእርሳቸው እምነት ግብፅ ከምትፈጽመው ጥቃት ይልቅ በጣም ትልቁ አደጋ በነጭ ለባሾች አማካይነት የሚፈጸም ወረራ ነው፡፡ እርሳቸው ነጭ ለባሾች ናቸው ባሏቸው በኤርትራ መንግሥትና በአልሸባብ የሚፈጸመውን አደጋ ለመመከት የሚያስችል አቅጣጫ መንደፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ለመገደብ የሚያስችላትን ብድርና ዕርዳታ እንዳታገኝ ግብፅ የፈጠረችውን የማደናቀፍ ሥራ ተከትሎ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ግድቡን ለመገንባት የወሰነችበትን ምክንያት አቶ መለስ አብራርተዋል፡፡
እንደርሳቸው ገለጻ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም የሚጠይቀውንና 5250 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችለውን የዓባይን ግድብ ለመገንባት የወሰነችው አገሪቱ በራሷ አቅም ይህንን ግድብ መገንባት ከቻለች፣ ሌሎች አነስተኛ ግድቦችን የመገንባት አቅም ያላት መሆኑን ግብፆች እንዲረዱ ለማድረግና ግድቡ ሱዳንና ግብፅን የሚጠቅም መሆኑን ለማስገንዘብ ነው፡፡
የዓባይ ግድብ መሠረተ ድንጋይ ከተጣለ በኋላ በሕዝቡ ላይ የታየው ከፍተኛ መነሳሳት ከጠበቁት በላይ መሆኑን አቶ መለስ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ይህንን ትልቅ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ይረዳ ዘንድም ኅብረተሰቡ ቦንድ በመግዛት ለግንባታው የበኩሉን አስተዋጽ እንዲያደርግ የሚችልበትን ሥርዓት ከመዘርጋት በተጨማሪም፣ ገንዘብ በነፃ ማዋጣት የሚፈልገው የኅብረተሰብ ክፍል ገንዘብ የሚያዋጣበትን ሁኔታ ሥራ የሚያስተባብር ቡድንም እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል፡፡


