በመለስ ዓ.
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሚሊኒየሙ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የመጣል ሥነ ሥርዓት ላይ ያደረጉት ንግግር ስሜቱን ያልፈነቀለው፣ ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት የድርሻዬን እወጣለሁ ያላለ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡
ይህ ዕቅድ አነሰም በዛም የርዕዮት ክፍፍሉን ሳይቀር ዘልቆ አልፏል፡፡ ይሁን እንጂ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገም ጠቀም ከሚል አቋም በዘለለ ለግድቡ ያላቸውን ድጋፍ ምን ዓይነት አስተዋጽኦም እንደሚያደርጉም የመግለጽ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ብዙ ሆነው እንደ አንድ ለመቆም ከቆረጡባቸው ጥቂት የታሪክ አጋጣሚዎች የአሁኑ ዋነኛው ነው፡፡ ባለፉት 2ዐ ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ አንድ የሆኑበት ወቅት ቢኖር የኤርትራ ወረራ ነበር፡፡ መንግሥት ከጦርነቱ በኋላ ይህን አንድነት አሟጦ አልተጠቀመበትም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጦርነት በመለስ በአገራዊ ልማት ዙሪያ ልዩነታቸውን ወደ ጐን ያደረጉበት ጊዜ መቼ እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ማጣቀሻ መጻሕፍትን ማገላበጥ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ይበል የሚያሰኝ ጅምር በመሆኑ በዓባይ ጉዳይ በራሴና በቤተሰቤ ስም አይደለም በግመሌ ቦንድ እገዛለሁ ያለኝ ሰው አጋጥሞኛል፡፡ ዮሐንስ አበበ በአዲስ አበበ አስተዳድር ውስጥ የኢንጂነሪንግ ባለሙያ ሲሆን፣ ‹‹ከምበላው ቀንሼ በግድቡ ላይ አሻራዬን አኖራለሁ›› ሲል ለዚህ ፀሐፊ ገልጾለታል፡፡ መቱ ውስጥ በሆቴል ሥራ የሚተዳደረው ቴዎድሮስ ታደሰ በበኩሉ መንግሥት የኅብረተሰቡን የጋለ ስሜት በፍጥነት በመጠቀም መረባረብ ይገባዋል ሲል ተናግሯል፡፡ ይህ ፀሐፊ መጋቢት 25 ቀን 2003 ዓ.ም. በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ‹‹በዓባይ ግድብ ግንባታ ይሁንታችንን እንግለጽ›› የሚል ጽሑፍ ካቀረበ በኋላ በድረ ገጽ ላይ አስተያየት ከሰጡት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት ምን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ወንድሙ ፍስሐ ፈለገ የተባለ በውጭ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ የውኃ ሀብት ባለሙያ እንደሆነ በመግለጽ ‹‹ምን አስተዋጽኦ፣ እንዴት እንደምናደርግ ይገለጽልን›› ሲል ጠይቋል፡፡ የዓባይ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያውያንን ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንዲህ የፈነቀለበት ምክንያት ምን ይሆን?
ቁጭት
ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ነፃነቷን ጠብቃ የቆየች አገር መሆኗን በተመለከተ በየተገኘው አጋጣሚ ብዙ ሰው መናገር ይወዳል፡፡ ደግ ይሁን፡፡ ኢትዮጵያውያን የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ጐህ እንዲቀድ ጉልህ ወይም የማይተካ ሚና ነበራቸው፡፡ በዚህም እንስማማ:: ዋናው ጥያቄ ዛሬ የት ነን ያለነው የሚለው መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡ በድጋሚ የት ነን?
ትናንት እጃቸውን ይዘን የነፃነት ብርሃን እንዲያዩ አድርገናቸዋል ከምንላቸው አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሳይቀር ያነስን ነን፡፡ በጣም ያነስን:: አገራዊ ክብር እንድናጣ ያደረገን የማን እርግማን ነው? በሥራ ምክንያት የምናገኛቸው በርካታ የውጭ አገር ሰዎች ቀደም ሲል ከላይ በተጠቀሱት የኢትዮጵያ የነፃነት ፋና ወጊነት ይስማሙና ይህን የመሰለ የነፃነት ሀብት በመጠቀም አሁን ያለው ትውልድ ምን ሠራ የሚል ጥያቄ ነው የሚያስከትሉት፡፡ የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይና የአገራዊ የደኅንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ላይ እንደተገለጸው፣ አገራችን በአፍሪካ ነፃነቷን አስከብራ የኖረች ብቸኛዋ አገርና ረጅምና የሚያኮራ የሥልጣኔ ታሪክ ያላት አገር ብትሆንም፣ የአገሮች ሁሉ ጭራ ነች፡፡ ሀቁ ይህ ነው፡፡ ይህ ሰነድ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በዚህ መልኩ ሲያስቀምጥ ብዙ ሰዎችን ማስቆጣቱን አስታውሳለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ሊያሳፍረንና ሊያሸማቅቀን የሚገባን ገጽታችን ይኸው ነው፡፡ ውኃ ላይ ተኝተን እንራባለን፡፡ እንጠማለን፡፡ የዓባይ የሚሊኒየም ግድብ የመሠረት ድንጋይ ሲጣል የተሰማው የተስፋ ስሜት ከዚህ ቁጭት ይመነጫል፡፡ ዓባይ ላይ ከመቀኘትና ከማዜም በስተቀር ምን እዚህ ጠብ የሚል ሥራ ተሠራ? በቅርቡ በአልጄዚራ ቴሌቪዥን በተላለፈው ፕሮግራም ላይ ዓባይ ወንዝ አቅራቢያ አርሶ አደሩ በስንጥር እየቆፈረ ሲዘራ የግብፆችን ሜካናይዝድ እርሻ ነበር በንጽጽር ያቀረበው፡፡ በዚህ ልቡ የማይደማና መንፈሳዊ ቅናት የማይሰማው ዜጋ እንዴት ሊኖር ይችላል? ዓባይ ላይ እንኳን ግድብ እሠራለሁ ማለት ማሰብ የሚቻል የማይመስለው አያሌ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ የሰሞኑ የሚሊኒየም ግድብ ሁኔታ የገፈፈው ይህን የሥነ ልቦናና ማኅበራዊ /Socio-psychological fear/ ፍርኅት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዳሉት አዲስ ዘመን ተበስሯል፡፡ በመብታችንን ከመቀጠም የሚገታን ምንም ነገር እንደሌለ ለወዳጅም ለጠላትም ፖለቲካዊ መልዕክት መተላለፉ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ በመብቱ ለመጠቀም ሲፈልግ አቁም ቢባል አሻፈረኝ እንደሚል ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ በዚህም የግብፅ መንግሥት ኢትዮጵያ ብድርና ዕርዳታ እንዳታገኝ የሚያደርገውን ጥረት መተው እንዳለበት ሊገነዘብ ይገባል፡፡ የግብፅ መንግሥት በተላላኪዎቹ የሚያደርገው ጣልቃ ገብነት መጨናገፍና የወታደራዊ የሥነ ልቦና ጦርነት ፍሬቢስነት ጋር ተደማምሮ የግብፅ ሁሉም ስትራቴጂዎች መክነዋል ቢባልም፣ እስከመጨረሻ ድረስ ከመባዘን ግን አይታቀብም፡፡ የአሁኑ ትውልድ ይህን በማድረግ የተለየ ስሜት ይኖረዋል፡፡
አሁን ያለው ትውልድ በየአጋጣሚው የሚያነሳቸውና የሚኮራባቸው ያለፈው ትውልድ የሥራ ውጤቶች ናቸው፤ ይገባዋል፡፡ ይሁን እንጂ ራሳችንን እንኳ መመገብ አቅቶን አቁፋዳ ይዘን አደባባይ ከመውጣት በላይ ምን ውርደት አለ? የአሁኑ ትውልድ ለአዲስ ታሪክ መታደሙ እጅግ ዕድለኛ ያደርገዋል፡፡ እንደልቡ እየተገማሸረ ያለምንም ከልካይ የሚሄደው ዓባይ ለኃይል ማመንጫና ለመስኖ ጥቅም ላይ ውሎ ከማየት በላይ ምን መታደል ይኖራል? ግብፅ አገራችንን በዓባይ ጉዳይ ገንዘብ እንዳታገኝ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በማድረግ ፍላጐቷን ትጭን ከመሆኗ አንጻር እንዴት አይቆጭ? ለዚህም ነው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ከወዲሁ እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡
እኛና እነሱ
በዓባይ ጉዳይ ከአፄ ሚኒልክ ጊዜ ጀምሮ ለአንድ ወገን ያጋደለ የውኃ አጠቃቀምን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥታት ቅሬታ ከማቅረብ የተቆጠቡበት ወቅት እንዳልነበረ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ፡፡ ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. በ1902 በአፄ ሚኒልክና በእንግሊዝ መንግሥት አማካኝነት የሱዳን ድንበር ሲከለል በተፈረመው ስምምነት አንቀጽ 31 ንጉሡ ኢትዮጵያ ናይልን፣ ጣናንና ባሮን አታግድም (Arrest) የሚል አንቀጽ እንዲገባ ቢደረግም፣ ይህ በወንዙ ላይ ያለንን ጥቅም የሚከለክል አይደለም፡፡ እናግድ ብንልም አንችልም፡፡
ኢትዮጵያ በራሷና ከውጭ ሆን ብለው በተጫኑባት ተፅዕኖዎች ሳቢያ ዓባይን መጠቀም ነውር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ግብፆች በበኩላቸው ሱዳንን ከጐናቸው በማድረግ ኢትዮጵያና ሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ጐሮሮ ይዘው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ግብፃውያን ወደ ሰማያዊው ዓለም ሲሄዱ ከሚቀርብላቸው ጥያቄ ውስጥ ‹‹ናይልን ለመጠበቅ ምን አድርገሃል?›› የሚለው ዋነኛው እንደሆነ ሲነገረው ያደገ ሕዝብ ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ በዓባይ ጉዳይ በምንም ዓይነት ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት የመፍትሔ ሐሳብ እንዲኖር አይቀበሉም፡፡ ይህ የእነሱ ውኃ የወለደው ጭንቀት /Water stress phobia/ ሕመም ነው፡፡ ይህ ባይሆን የግብፅ ፖለቲከኞች፣ የውኃ ባለሙያዎች፣ ወዘተ የዓባይን ውኃ አጠቃቀም በተመለከተ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአካባቢው አገሮች ተግባብተው በሠሩ ነበር፡፡
የሚሊኒየሙ ግድብ መሠራት ከኢትዮጵያ ያልተናነሰ ጥቅም የሚያስገኝላቸው አገሮች ግብፅና ሱዳን ናቸው፡፡ ሱዳን ከግብፅ ጋር በንጽጽር ሲቀርብ በናይል ወንዝ ያላት ተጠቃሚነት በአራት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያነሰ ነው፡፡ ሱዳን የተሻለች ተጠቃሚ ናት የምትባለው አንድ በመቶ የማይበልጥ የናይልን ውኃ ተጠቃሚ ከሆነችው ኢትዮጵያ ጋር ስትነጻጸር ነው፡፡ ሱዳን በናይል ጉዳይ ከሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች የተለየ አቋም ለመያዝ የምትገደደው በግብፅ መንግሥት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የግብፅ ገዢዎች ሱዳንን እንደ አነስተኛ አጋር /Junior partner/ የሚያዩበት ምክንያት ከዚህ ይመነጫል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ትናንት እንዳሉት ሱዳኖች ከፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ጀምሮ ፍትሐዊ ክፍፍል እንዲኖር መጠየቅ ጀምረዋል፡፡
ምንም ተባለ ምን የግድቡ መሠራት በሁለቱ አገሮች ያሉ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ፣ በጐርፍ አደጋ እንዳይመቱ፣ የተስተካከለ የውኃ ፍሰት እንዲኖር፣ የትነት መጠን እንዲቀነስ፣ ብሎም በተመጣጣኝ ዋጋ ኢነርጂ መግዛት የሚያስችላቸው ነበር፡፡ ፖለቲከኞቻቸው ይህን ሳያውቁ ቀርተው አይደለም፡፡ ይህን ለማስረዳት ዲፕሎማት መሆን አያስፈልግም፡፡ የግብፅ ሕዝብ ከኢትዮጵያውያን ጋር ተባብሮና ተከባብሮ ከመሥራት ውጭ ዓላማ እንደሌለው ከማስረዳት ውጭ ምታ ነጋሪት ማለት የትም አያደርስም፡፡ ብዙ ቢቀረንም አሁን ያለንበት ደረጃ የደረስነው አንገታችን ደፍተን በመሥራታችን ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት ሰፊ የማስረዳት ሥራ የሚጠብቀው በግብፅ መንግሥት ሳይሆን፣ ጉዳዩን እየተዛበና እየተጠናገረ በሚነገራቸው አገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ላይ መሆን ይገባዋል፡፡
በናይል ጉዳይ ምን ያህል በጐ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ቢኖርም፣ በግብፅ ፖለቲከኞችና የመገናኛ ብዙኅን ዘንድ ያጠሉ አሉታዊ አመለካከቶች በቀላሉ አይወገዱም፡፡ አልአህራም ኢትዮጵያ የናይልን ወንዝ እንደ ስትራቴጂ በመያዝ በግብፅ ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር እንደመሣሪያ ልትጠቀምበት ትፈልጋች ሲል ዘግቧል፡፡ ይህ ቧልት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ማንንም የመጉዳት ፍላጐት እንደሌላት ሳያውቁ ቀርተው አይደለም፡፡ አልሚሰር አልዩም ጋዜጣ ደግሞ የኢትዮጵያ ዕርምጃ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ግብፃውያንን ሊጐዳ ይችላል ማለትም ጀምሯል፡፡ ከሰሞኑ የግብፅ የመገናኛ ብዙኅን አርእስተ ዜና መግቢያና መውጫ ያው የፈረደበት የዓባይ ዜና ሆኗል፡፡ የዚህ ፕሮፓጋንዳ ዋና ዓላማ እንደተለመደው በውስጥ ያለውን ውጥረት መሸፈኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ግድቡ በኢትዮጵያ መንግሥት ቁጠባና በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ የሚሠራ መሆኑን እያወቁ ድኅረ ሙባረክ ሥልጣን ያለው ወታደራዊ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ የሚያደርግ የልዑካን ቡድን ወደ ቻይና፣ አውሮፓ፣ ጣሊያን፣ ሆላንድ፣ የተባበሩት ኤምራይቶችና ሳዑዲ ሊልክ መሆኑን እየተነገረ ነው፡፡ ይህ የቆሰለ ነብር ዓይነት ድርጊት ይመስላል፡፡ የግብፅ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ ሲጨልምባት እፎይ ብለው የተኙት የጨለመው ሊነጋ ሲል መሆኑን ዘንግተውታል፡፡
ከዚህ ለዘብ ያሉት ግብፅ በውጭ ጉዳይ መስክ ከአካባቢው የተፋሰሱ አገሮች ጋር አዲስ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከሪያ ዕርምጃ እንድትወስድ ይጠይቃሉ፡፡ አጠቃላይ ስትራቴጂው እንዲቀየር ቶሎ ባይጠበቅም ይህ ጥሩ ፍንጭ ነው፡፡ በግብፅ ታዋቂ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አመድ አባሳ ለአገሪቱ የሽግግር መንግሥት የናይል ተፋሰስን ጉዳይ ለመፍታት ያስችላል ያሏቸውን አምስት ሐሳቦች አቅርቧል፡፡ በዚህም መሠረት የመጀመሪያው ከተለያዩ የግብፅ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ምሁራን ወደ ተፋሰሱ አገሮች መላክ፡፡ ይህ ግብፅ ቀደም ሲል የተለያዩ የነፃ ትምህርት ዕድሎችን በመስጠት ተፅዕኖ ለማሳደር የምታደርገው ጥረት አካል እንደሆነ ይታመናል፡፡ የናይል ሳተላይት ቴሌቪዥን በማቋቋም በተፋሰሱ አገሮች ቋንቋዎች በማሠራጨት የግብፅን አቋም ማንፀበረቅ ሌላው አማራጭ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የግብፅ መንግሥታት ጤናማ ያልሆነ አካሄድ ከቋንቋ ይልቅ ተግባር ይገልጸዋል፡፡ በሦስተኛ የግብፅ የኢንቨስትመንትና የንግድ ኩባንያ መመሥረትና ማጠናከር የሚሉ ናቸው፡፡
የልማት ጄኔራሎች
የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጦር ሜዳ ጀግኖቹን ያወድሳቸዋል፣ ያሞግሳቸዋል፡፡ የልማት ጀግኖቹንስ? ይህ ትውልድ የራሱን ታሪካዊ ቅርስ ለማኖር ርብርብ እንዲያደርግ ብሔራዊ ጥሪ ቀርቦለታል፡፡ መንግሥት በዲፕሎማሲው መስክ የሚያደርገው ጥረት እንዳለ ሆኖ ያለው በገንዘቡ የሌለው በጉልበቱና በእውቀቱ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ይጠበቃል፡፡ ሁሉም ዜጋ ለዚህ አገራዊ ጥሪ መልስ የመስጠት የሞራል ግዴታ አለበት፡፡ ሕዝቡ ቦንድ በመግዛት ራሱንም አገሩንም መጥቀም እንደሚችል ተናግሯል፡፡ እንደሚጠበቀው ቦንዱን ሁሉም ዜጋ ሊገዛው አይችልም፡፡ በቦንድ ሽያጭ ምንነት እንዲሁም አፈጻጸም ላይ ያለው ብዥታ ማብራሪያ መስጠት የሚያስፈልገው ሆኖ ሌሎች የአስተዋጽኦ ማድረጊያ አማራጮችም መታየት አለባቸው፡፡ ቴሌቶን ይዘጋጅ? በመሥሪያ ቤት መዋጮ ይሁን? ከሚመለከተው አካል አስቸኳይ መልስ ይጠበቃል፡፡ አንድ ብርም ሆነ አንድ ሺሕ የሚያዋጣ ሰው ፕሮጀክቱ የራሴ ነው እንዲል የሚያስችለው ሁኔታ ዕውን እንዲሆን የተለያዩ አማራጮች መፈተሽ አለባቸው፡፡ እንደዚህ በማድረግ በፕሮጀክቱ ሥራ በቀጥታ የሚሳተፉ ወገኖቻችን አለን እንበላቸው፡፡
ኢትዮጵያ 45 ሺሕ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላት ሲሆን፣ የሚሊኒየሙ ግድብ ግን የመጀመሪያው ወሳኝ ምዕራፍ ነው፡፡ ይህን ስናሳካ ብቻ ቀሪውን የማሳካት ሰፊ ዕድል እንዳለን የመስኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በመጪዎች ሦስት ዓመት የምናመርተው 700 ሜጋ ዋት (1 ዩኒት 350 ሜጋ ዋት) የሚይዝ ሲሆን ከ57 ወራት በኋላ ይደርሳል ለሚባለው የ5250 ሜጋ ዋት (ከ15 ዩኒቶች መሆኑ ነው) እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ነው፡፡ በአጠቃላይ የምናደርገው እንቅስቃሴው ይህን ከግምት ያስገባ ነው፡፡
እዚህ ላይ የልማት ጄኔራሎቻችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ የታላቁ የሚሊኒየም ግድብ የሚፈጥረውን ኃይል ለማስተላለፍ የሚካሄደውን ፕሮጀክት ጥናትና ዲዛይን የሠሩት ኢትዮጵያውያን ዜጐች በመሆናቸው እንኮራለን፡፡ ኢትዮጵያ ባፉት ጥቂት ዓመታት ባደረገችው የግድቦች ግንባታ ሰፊ የእውቀት ሽግግር ተፈጥሮ የአሁኑን ግድብ በራሳችን ኃይል የምንመራበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ የፕሮጀክቱ መሪዎች ናቸው፡፡ አቶ ስመኘው በቀለ (ሲቪል ምህንድስናውን)፣ አቶ ክፍሌ ቦሮ (ኤሌክትሮና ኃይድሮ ሜካኒካል) ቀደም ሲል በነበሩ ፕሮጀክቶች የነበራቸውን ልምድ በመውሰድ፣ በሺዎች ከሚቆጠሩ ወገኖቻቸው ጋር ዕቅዱን ከወረቀት ወደ መሬት ያወረዱ በ40ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ያሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ እነዚህ የልማት አርበኞች ናቸው፡፡ ሁለቱ ኢንጂነሮች በጊቤ ሁለትና በጣና በለስ ፕሮጀክት መሪ ተዋናዮች ነበሩ፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን ዛሬ ብቻቸውን አይደሉም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ስለ ዓባይ እያዜምን ጨለማ ውስጥ መቀመጥ ሌላው አማራጭ ነው፡፡ የዓባይን ግድብ የመገንባትና ያለመገንባት የምርጫ ጉዳይ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አሻራቸውን ለማኖር ከመምረጥ ሌላ አቋም አይኖራቸውም፡፡ ኢንጂነሩ ዮሐንሰ አበበም ሆነ የመቱው ቴዎድሮስ ታደሰ አቋም ሁሉንም ዜጋ ይወክላል፡፡
ሰላም!!
This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it


