Wednesday, May 22nd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

‹‹ከፍተኛ ችግር ሆኖ ያገኘነው የዕርዳታ ፈላጊው ቁጥር መብዛት ነው›› አቶ ይልማ ወልደ ዮሐንስ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

የተወለዱት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሆሳዕና ከተማ ውስጥ ነው፡፡ የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት ከተማ ሆሳዕና ውስጥ አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግ ይዘዋል፡፡

ለሦስት ዓመታት በተለያዩ የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ከሠሩ በኋላ ለበርካታ ዓመታት መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ሲሠሩ መቆየታቸውንም ይገልጻሉ፡፡ አሁን ጄኔቫ ግሎባል የሚባል ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ የኢትዮጵያ ተወካይ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ አቶ ይልማ ወልደ ዮሐንስ፡፡ ጄኔቫ ግሎባል ዓለም አቀፍ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ ስለሠራቸውና በመሥራት ላይ ስላለው ፕሮግራም ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ጄኔቫ ግሎባል ምንድን ነው?

አቶ ይልማ
፡- ጄኔቫ ግሎባል ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው፡፡ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ብቻ ነው ከማለት ይልቅ ሰዎች ራሳቸውን እንዲችሉ በተለየ መንገድ የገንዘብ ዕርዳታ ስለሚያደርግ በቢዝነስ ሞዴል መልክ እየሠራ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዓላማው ምንድን ነው?

አቶ ይልማ
፡- ዓላማው በሦስተኛው ዓለም ያሉ ምንም ዓይነት ገቢ የሌላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች መርዳትና ከድህነት እንዲላቀቁ ማድረግ ነው፡፡ በአይቮሪኮስት፣ በሩዋንዳና በተለያዩ አገሮች እየሠራም ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ጄኔቫ ግሎባል ፕሮግራሞችን የሚሠራው እንዴት ነው?

አቶ ይልማ
፡- መሠረታዊ ስትራቴጂው የአጋር ድርጅቶችን አቅም ሥልጠና በመስጠት ማጠናከር አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ስትራቴጂ፣ በርካታ ቢሮዎችን ከፍቶ መንቀሳቀስ ሳይሆን ከኅብረተሰቡ ጋር የሚሠሩ አጋር ድርጅቶችን በማጠናከር እነርሱ ደግሞ ሥራውን ራሳቸው እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጄኔቫ ግሎባል ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ የከፈተው መቼ ነው?

አቶ ይልማ
፡- ጄኔቫ ግሎባል ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ ከፍቶ መንቀሳቀስ የጀመረው እ.ኤ.አ በ2007 ነው፡፡ ኤንፒአይ (NPI) የሚባል በዩኤአይዲና በጄኔቫ ግሎባል ፋውንዴሽን በራሱ ፈንድ የሚደገፍ ፕሮግራም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለኢትዮጵያ የተሰጠው ፈንድ ምን ያህል ነው?

አቶ ይልማ
፡- የ12 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፕሮግራም ነው፡፡ ትልቅ ፕሮግራምም ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ2007 ጀምሮ ከ30 አጋር ድርጅቶች ጋር እየሠራን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ ምንድን ነው?

አቶ ይልማ
፡- የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ በአገር ውስጥ ያሉት አጋር ድርጅቶች ትልቅም ይሁን ትንሽ፣ በሕጋዊ መንገድ እንደ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ተመዝግበው በአካባቢያቸው ያሉትን የኅብረተሰብ ክፍሎች መድረስ መቻል አለባቸው፡፡ ይኼንን እኛ የአቅም ማጠናከር (ካፓሲቲ ቢዩልዲንግ) ፕሮግራም እንለዋለን፡፡ የአገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት በኤችአይቪ/ኤድስ ላይ ለመሥራት ሲገቡ እንዴት መሥራት እንዳለባቸው የማያውቁ ከሆነ ዕውቀቱን እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ከትላልቅ ለጋሽ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የመሥራት ልምድ ከሌላቸው ያንን ልምድ እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡ በቀጣይ የአገር ውስጥ አጋር ድርጅቶች ከዓለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ዕርዳታ አግኝተው እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ቴክኒካዊና የድርጅታዊ አቅም ግንባታን በጋራ አጣምሮ የያዘ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮግራሙ ለስንት ዓመት ይቆያል?

አቶ ይልማ
፡- ፕሮግራሙ ለሦስት ዓመት ይቆያል፡፡ በሦስት ዓመት ውስጥ የኤችአይ ቪ/ኤድስን መከላከልና በቫይረሱ የተጠቁትን መርዳት፣ ወላጆቻቸውን በኤችአይቪ ያጡትን ሕፃናት እንደ ማነኛውም ወላጅ እንዳላቸው ልጆች ከማኅበረሰቡ ጋር ሆነው እንዲማሩ መርዳት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮግራሙ የሚሠራው በመላው አገሪቱ ላይ ነው?

አቶ ይልማ
፡- በመላው አገሪቱ አይደለም፡፡ በአዲስ አበባ፣ በአማራና በኦሮሚያ ላይ ብቻ የሚሠራ ፕሮግራም ነው፡፡ ሰላሳዎቹም አጋር ድርጅቶች (ፓርትነርስ) የሚገኙት በሦስቱ ክልሎች ብቻ ነው፡፡ አንዳንዶቹ አጋር ድርጅቶች በኤችአይቪ/ኤድስ ዙርያ ሠርተው አያውቁም፡፡ ለዚህም ነው የአቅም ግንባታ ልምምድ በቅድሚያ እንዲወስዱ የተደረገው፡፡ አሁን የአቅም ምግባታ ሥልጠናውን ከወሰዱ በኋላ በኤችአይቪ ላይ በደንብ እየሠሩ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ከዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶች ፈንድ እያገኙ በደንብ እየሠሩ ነው፡፡ እነዚህ የአገር ውስጥ አጋር ድርጅቶች ደግሞ ከ500 ሺሕ በላይ የሆኑ ሰዎችን እንዲያዳርሱ ማድረግ ነው፡፡ በእነዚህ ዓላማዎች ላይ ነው እየሠራን ያለነው፡፡ በአሁኑ ፕሮግራም የተወሰኑ አጋር ድርጅቶች ራሳቸውን ችለው እንደሚሠሩ አረጋግጠን ሰርቲፋይ ያደረግናቸው ባለድርሻ አካላት አሉ፡፡ በሚቀጥለው ዓመትም በተመሳሳይ መንገድ ሰርቲፋይ የምናደርጋቸው ይኖራሉ፡፡ ይኼ ማለት ደግሞ ማንኛውንም ለጋሽ ጠይቀው ዕርዳታውን ማግኘት ይችላሉ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጄኔቫ ግሎባል በቀጥታ ተረጂዎችን ማግኘት አይችልም?

አቶ ይልማ
፡- የእኛ ሥራ አጋር ድርጅቶችን ሥልጠና መስጠትና ቁጥጥር ማድረግ ነው፡፡ ድርጅቶቹ ከተጠቃሚዎቹ ጋር በትክክል መሥራታቸውን እንቆጣጠራለን፡፡ በጀት እንመድባለን፡፡ በበጀቱ ልክ ሥራውን ውጤታማ ማድረጋቸውን ቁጥጥር እናደርጋለን፡፡ ወላጅ አልባ ልጆችና ቫይረሱ ያለባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በትክክል እየረዱ መሆናቸውን እንቆጣጠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- አጋር ድርጅቶቹ ምንም ገቢ የሌላቸውንና በኤችአይቪ/ኤድስ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ወይም ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች የሚመርጡበት መስፈርት ምንድን ነው?

አቶ ይልማ
፡- ተረጂዎች የሚመረጡበት መስፈርት አለ፡፡ ድርጅቶቹ በሚሠሩበት አካባቢ ካሉ ቀበሌዎች ወይም ወረዳ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የሚረዱ ወገኖችን የሚመርጡበት መስፈርት አለ፡፡ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ካለን በጀት አንፃር ግን የበለጠ ችግር ያለበትን በመምረጥ ነው ዕርዳታው የሚደረገው፡፡ ለምሳሌ በቫይረሱ የተያዙትን ለመርዳት መጀመሪያ መመረጥ ያለባቸው አልጋ ላይ የዋሉ ናቸው፡፡ ወላጅ አልባ የሚባሉትም ረዳት የሌላቸውና የሚያሳድጋቸው የሌላቸው ስለሆኑ እነሱን ማስቀደም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የቀበሌዎች ተመራጮችና በየቀበሌው የሚቋቋም የፕሮጀክቱ ዓብይ ኮሚቴዎች ስለሚኖሩ በጋራ በቀላሉ ቅድሚያ ተረጂዎችን መምረጥ ይቻላል፡፡ ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ፣ እናትና አባታቸውን በኤችአይቪ/ኤድስ ያጡ ሕፃናትና ምንም ገቢም ሆነ ረዳት የሌላቸው የሚመረጡበት መስፈርት አለ፡፡ ትምህርት ቤት መሄድ የማይችሉትን፣ ሕክምና ማግኘት የማይችሉትንና የመሳሰሉት ዋና ዋናዎቹ መስፈርቶች ናቸው፡፡ አጋር ድርጅቶቹ በመከላከል ዙርያም ይሠራሉ፡፡ ማለትም ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ ለኅብረተሰቡ የማንቃት፣ እንዲጠነቀቁ የማድረግና ቫይረሱም ያለባቸውን በአግባቡ መድኃኒት እንዲወስዱና ራሳቸውን እንዲጠብቁ የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ዕርዳታው በምን መልክ ነው የሚሰጠው?

አቶ ይልማ
፡- ዕርዳታው በገንዘብ መልክ አይሰጥም፡፡ የሚሰጠው ወላጅ አልባ ለሆኑት ልጆች ለትምህርት የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁስ በመክፈል፣ ዩኒፎርም በማሰፋት፣ ለትምህርት ቤት በመክፈልና ምግብ ገዝቶ በመስጠት ነው፡፡ በማንኛቸውም ዕርዳታ ድርጅቶችም ቢሆን ዕርዳታ በገንዘብ መልክ አይሰጡም፡፡ ሁሉም አገልግሎት በዓይነት ነው የሚሰጠው፡፡ 12 ሚሊዮን ዶላር በብር ተመንዝሮ ሲታይ በጣም ብዙ ነው፡፡ ዕርዳታ ከሚፈልገው የኅብረተሰብ ክፍል አንፃር ስናየው ግን እጅግ በጣም ትንሽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮግራማችሁ ምን ያህል የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመርዳት ነው? ምን ያህልስ ረድታችኋል?

አቶ ይልማ
፡- እኛ ያሰብነው 600 ሺሕ ያህል ሰዎችን ለመርዳት ነበር፡፡ አሁን ግን ገና የፕሮግራሙ ጊዜ ሳያበቃ 850 ሺሕ ሰዎችን መርዳት ተችሏል፡፡ ይኼንን ፕሮግራም የኅብረተሰቡና የእድሮች አስተዋጽኦና ተሳትፎ የአገልግሎቱን ቁጥር አብዝቶታል፡፡ ይህ የሆነውም ፍላጎቱ በጣም ብዙ በመሆኑ ነው፡፡ ዕርዳታ ሲባል ለይስሙላ ዝም ብሎ ሳይሆን የአገልግሎት ፓኬጅ አለ፡፡ በአገልግሎት ፓኬጁ መሠረት ተረጂዎቹን ሰው ሊያደርግና ሊለውጥ በሚችል መንገድ መሆኑን ተረጂዎችም እየመሰከሩ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ተረጂዎችን ለይስሙላ ሳይሆን ሰው በሚያደርግ መንገድ የተያዘውን ፓኬጅ ተከትለን እንረዳለን ብለዋል፡፡ ሰው በሚያደርግ መንገድ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

አቶ ይልማ
፡- ወላጅ አልባ ስንል ዕርዳታውን ብቻ አይደለም፡፡ ወይም ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩት ምግብ ማደል ብቻ አይደለም፡፡ የተወሰነ መቋቋሚያ በመስጠትና በመከታተል በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲያሻሽሉና እንዲያድጉ እናደርጋለን፡፡ ፕሮግራሙ እንዲቀጥል የምናደርግበት ስትራቴጂያችን አንዱ መንገድ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ በማድረግና መቋቋሚያ መስጠትና መከታተልም ነው፡፡ ብዙ ሰዎችም ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ሌሎችን እየረዱም ነው፡፡ አልጋ ላይ ተኝተው የነበሩ የቫይረሱ ተጠቂዎችም በተደረገላቸው ዕርዳታ ዛሬ ተነስተው ሥራ እየሠሩ ማየት በመቻላችን በጣም ደስተኞችም ሆነናል፡፡ ከዕድሮች፣ ኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከል ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር በመገናኘት ሥራው እንዲሰፋና ወገኖች እንዲረዱ እያደረግንም ነው፡፡ እዚህ ጋ ላመሰግን የምፈልገው አንዳንድ ዕድሮች አባሎቻቸው ወርሃዊ ክፍያ ሲከፍሉ ሃምሳ ሳንቲም ጨምረው በመክፈል እኛ ከምንረዳው ጋር በመጨመር ዕርዳታ እያደረጉ በማየቴ ነው፡፡ አጋር ድርጅቶቻችን እኛ አሠልጥነን አቅም እንዲፈጥሩ ያደረግናቸው ብቻ ሳይሆኑ እነዚህም ጭምር መሆናቸውን መግለጽ እንወዳለን፡፡ በአጠቃላይ በኤችአይቪ/ኤድስ ዙርያ የሚሠራ ፕሮግራም በመሆኑ፣ ገቢ የሌላቸውና ራሳቸውን መርዳት የማይችሉ፣ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩትንና ወላጅ አልባ የሆኑትንና ወደ ትምህርት ቤት መሄድ የማይችሉትን እንረዳለን፡፡ ዓላማው የኤችአይቪ/ኤድስን ተፅዕኖ መቀነስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከጄኔቫ ግሎባል ፕሮግራም ጋር የሚሠራ የመንግሥት አካል አለ?

አቶ ይልማ
፡- ከእኛ ጋር የሚሠሩ አጋር ድርጅቶች አሉ፡፡ እኛ ለአጋር ድርጅቶች እናመቻቻለን፡፡ ኤችአይቪ/ኤድስ ላይ የሚሠራ ማንኛውም ድርጅት ከጤና ጥበቃና ከብሔራዊ የኤችአይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት ጋር ነው፡፡ በወረዳ፣ በዞን ወይም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሠራው ከእነሱ ጋር ነው፡፡ እኛ በምንሠራበት በሦስቱ ክልሎች አጋር ድርጅቶቻችንን ሰብስበን የልምድ ልውውጥ ስናደርግ የሁለቱን መሥርያ ቤቶች አባላት ጠርተን ነው፡፡ ያሠለጠናቸው አጋር ድርጅቶች በተለይ ከጽሕፈት ቤቱ ጋር ይፈራረማሉ፣ ስምምነት ይፈጽማሉ፡፡ ፕሮግራሙ የጤና ፕሮግራም በመሆኑ መሥራትም የሚገባን ከእነሱ ጋር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተመሳሳይ ፕሮግራም ካላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ሆናችሁ በጋራ ትሠራላችሁ?

አቶ ይልማ
፡- እኛ የምንሠራው አገር ውስጥ ካሉ አጋር ድርጅቶች ጋር ነው፡፡ ትልቅ ፕሮግራም ያለን በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ውስጥ ነው፡፡ እኛ በኤችአይቪ ዙርያ ከሚሠሩት ኦሳና መቅድም ጋር አብረን እየሠራን ነው፡፡ ከመካነ ኢየሱስ፣ ከሲአርዲኤና ከሌሎችም ጋር እየሠራን ነው፡፡ ዩኤስአይዲ አጋር ካደረጋቸው አጋር ድርጅቶችም ጋር እየሠራን ነው፡፡ ለብቻችን የምንሠራው ብዙም የለንም፡፡ ጄኔቫ ግሎባል ከመንግሥት ጋር ያለው የሥራ ግንኙነት በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ አብዛኛውን ከአጋር ድርጅቶች ጋር ነው የምንሠራው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ለፕሮግራሙ ከተያዘው 12 ሚሊዮን ዶላር በጀት እስካሁን ምን ያህሉን ተጠቅማችኋል?

አቶ ይልማ
፡- እስካሁን ድረስ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ተጠቅመናል፡፡ 80 በመቶ የሚሆነውን ለአጋር ድርጅቶች ነው የምንሰጠው፡፡ የአጋር ድርጅቶችን አቅም ለማጠናከር የምንሰጠው ሥልጠናና ለተለያዩ ኦፕሬሽኖች የምንጠቀመው 20 በመቶውን ብቻ ነው፡፡ በመጨረሻ ላይ በኦዲተሮችና በፕሮግራም አስተባባሪዎች ቁጥጥርና ግምገማም እናደርጋለን፡፡ በዚህ መንገድ ገንዘቡ ለትክክለኛ ሥራ መዋሉን እንቆጣጠራለን፡፡ ቀሪውን ሦስት ሚሊዮን እ.ኤ.አ. እስከ ዲሴምበር 2011 መጨረሻ ድረስ የምንጠቀመው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በምትሠሩት ሥራ ግባችሁን መታችኋል?

አቶ ይልማ
፡- በጣም፤ ከዋናው ዕቅዳችን 60 በመቶ ሆኗል፡፡ ገና የተመደበው በጀት ሳይጠናቀቅ ከጠበቅነው በላይ ግቡን መትቶልናል፡፡ ፕሮግራሙ ቀጣይነት እንዲኖረው ከማድረግ አንፃር የአገር ውስጥ አጋሮቻችን እኛም ባንኖርና ገንዘብም ባይኖር አንዳንዶቹ የኤችአይቪ/ኤድስ ፕሮግራም ኤክስፐርቶች ሆነው መሥራት እየቻሉ ነው፡፡ ከእነሱ ጋር የሚሠሩ የኤችአይቪ/ኤድስ ክለቦች ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ እየተሳተፉ ነው፡፡ መጀመርያ ስንጀምር ከነበረው ጋር ስናነፃፅረው አሁን በጣም ብዙ ተሳታፊ አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ግባችንን መትተናል ብለን እናስባለን፡፡ በተለይ በእኛ ሥልጠና አግኝተውና አቅማቸውን አሳድገው አጋር ድርጅቶች ያደረግናቸው፣ ራሳቸውን ችለውና አቅማቸውን አጎልብተው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመወዳደር ራሳቸው ፈንድ በማግኘት እየሠሩ ስለሆነ፣ በዚህና በዚያ በኩል ግባችንን መትተናል ብለን በሙሉ አፋችን ለመናገር ያስችለናል፡፡ አንድ ፕሮግራም ወይም ፕሮጀክት ውጤታማ ነው ወይም አይደለም የሚባለው በመጀመርያ ሥራ ሲጀምር ያስቀመጠውን ዓላማ ማሳካት መቻሉና አለመቻሉ ላይ ነው፡፡ ጄኔቫ ግሎባልም በመጀመርያ ሲነሳ ሦስት ዓላማዎችን አስቀምጦ ነው፡፡ አንደኛው አገር በቀል አጋር ድርጅቶችን አቅማቸውን በማሳደግ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኤችአይቪ/ኤድስ ተፅዕኖ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማብቃት ነው፡፡ ሁለተኛው ኤችአይቪ/ኤድስን በመከላከል ረገድ ለቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የተጋለጡ ወገኖችን ማዳን ነው፡፡ ሦስተኛው በኤችአይቪ/ኤድስ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ፣ በቫይረሱ ተይዘው በአልጋ ላይ የዋሉና ረዳት የሌላቸውን ወገኖች እንክብካቤና ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ፕሮጀክቱ ግቡን መትቷል፡፡ የበጀት ዓመቱ ፈንድ ከማለቁ በፊት ቢጠናቀቅም አሠራራችን መልካምና ለውጥ የታየበት በመሆኑ ለጋሾቹ ‹‹ለአንድ ዓመት ቀጥሉ›› ብለው ሦስት ሚሊዮን ዶላሩን ለቀውልናል፡፡ ይኼም አንዱ የስኬት ማሳያ መንገድ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት አልጋ ላይ የነበረ ሰው ዛሬ ሲነግድ በማየታችን ይኼ ራሱ አንዱ የሥራው ውጤት በመሆኑ የሚያስደስትም ሆኖ አግኝተነዋል፡፡   

ሪፖርተር፡- ፕሮግራሙ ቀጣይነት ይኖረዋል?

አቶ ይልማ
፡- አሁን ባለው ፈንድ እስከ ዲሴምበር 2011 ይቀጥላል፡፡ ይኼንን ፕሮግራም እንዳለ ለማስቀጠል አንዳንድ ጥረቶችን እያደረግን ነው፡፡ ከዛም ባሻገር የሚቻልባቸው መንገዶች ካሉ በሚል ከዩኤስአይዲ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- ላለፉት ሦስት ዓመታት ስትሠሩ ያጋጠሟችሁ ችግሮች ነበሩ?

አቶ ይልማ
፡- አዎ፤ አንዱና ከፍተኛ ችግር ሆኖ ያገኘነው የዕርዳታ ፈላጊው ቁጥር መብዛት ነው፡፡ አገር በቀል አጋር ድርጅቶቹም ሁልጊዜ በሪፖርታቸው የሚገልጹልን የዕርዳታ ፈላጊው ቁጥር መብዛትን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ800 ሺሕ በላይ ዕርዳታ ፈላጊ ልጆች አሉ፡፡ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ የሆኑ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አሉ፡፡ ይኼ ምን ያህል ተሸፍኗል ብንል በጣም ትንሽ ነው፡፡  ወደ ገጠሩ አካባቢ በተለይ በድህነት በጣም ወደተጠቁ አካባቢዎች ሲኬድ ዕርዳታ ፈላጊው ካሰብነው በላይ ነው፡፡ ሁለተኛው ችግር በአቅም ግንባታ ላይ የገጠመን ችግር ነው፡፡ ምክንያቱም አገር በቀል ድርጅቶች ብዙውን ጊዜ ከኤችአይቪ ፕሮግራም ጋር አይሠሩም፡፡ ለጋሾቹ የሚፈልጉትን ጥብቅ ደረጃ ማሟላት የሚችል የለም፡፡ ይኼንን ነገር ለማስቀረትና አቅም እንዲያገኙ ለማድረግ ከፍተኛ ችግር ገጥሞን ነበር፡፡ በተለይ የአጋር ድርጅቶቹ የአቅም ሁኔታ ከፍና ዝቅ ማለትም ሌላው ችግር ነበር፡፡ አምና ጥሩ የነበረው ዘንድሮ ዝቅ ብሎ ይገኛል፡፡ የሠለጠነ የሰው ኃይል ሥራውን ትቶ መሄድም ሌላው ችግር ነበር፡፡ የጎዳና ላይ ተዳዳሪዎችና ሴተኛ አዳሪዎች ሥልጠና ጀምረው ሳይጨርሱ ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወር ሌላው የፕሮግራሙ እንቅፋት ነበር፡፡ በዛም በዚህም ተብሎ በሦስቱም ክልሎች በመከላከሉ አንፃር 860 ሺሕ አካባቢ ሰዎች ዘንድ ለመድረስ ተሞክሯል፡፡ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩት ደግሞ 44,480 ያህል ሰዎች ተረድተዋል፡፡ ወላጅ የሌላቸው ሕፃናት ደግሞ 13 ሺሕ አካባቢ ይሆናሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ የጀመራችሁት ፕሮግራም ምንድን ነው?

አቶ ይልማ
፡- አዲሱ ፕሮግራም የትምህርት ፕሮግራም ነው፡፡ በግንቦት 2003 ዓ.ም. ወይም በመስከረም 2004 ዓ.ም. እንጀምራለን፡፡ ለኤችአይቪ/ኤድስ ፕሮግራም ፈንድ ካደረገው ከአንዱ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው ፈንዱ የተገኘው፡፡ የሦስት ዓመት ፕሮግራም ሲሆን የአምስት ሚሊዮን ዶላር ፕሮግራም ነው፡፡ የምንጀምረው በደቡብ ክልል ነው፡፡ እንደ ኤችአይቪ ፕሮግራም ሁሉ ይኼኛውም ፕሮግራም ወላጆቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች በማጣት መማር ያልቻሉ ልጆችን፣ ምንም ገቢ የሌላቸውንና ድሃ የሆኑ ወገኖችን ለመርዳት የሚያገለግል ፕሮግራም ነው፡፡ ልጆቹን ለአንድ ዓመት በማስተማር ወደ መንግሥት ትምህርት ቤቶች እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡