ቀና ይበል ጥቁር ፊታችሁ
አበሾች ይብራ ገፃችሁ
የሳባ ኩሩ ዘር ናችሁ
ይልቃል መሠረታችሁ
ከፍታው የተራራችሁ
የጀግና መጠለያችሁ
ጥላነው ኩሩ ልባችሁ
በቋሚ ጀግንነት እውነት
በእናንተ መስዋዕትነት
መላው ጥቁር ዘር ይኰራል
ይገዝፋል ዓይኑ ይበራል
የሳባ ዘሯ ይጣራል
አፍሪካን ተነሱ! ይላል
የእማማ የኢትዮጵያ አፈር
ነፃ ነው የአበሻ ምድር
አፍሪኮች ተነሱ! ጽኑ!
ነፃ ሰው . . . ነፃ ሰው ሁኑ!
የጥቁር ዜጐች በሙሉ
ተነሱ ነፃነት በሉ!
(ላንግስቶን ሁግሄስ፤ ዘ ኮል ኦፍ ኢትዮጵያ - ትርጉም - ዓለም ፀሐይ ወዳጆ፤ የማታ እንጀራ፣2002 )
* * *
‹‹ኧረ ቁጭ ብያለሁ!››
ሰውየው ያጣ የነጣ ድሃ ቢሆንም አንዲት ዶሮ ግን ነበረችው፡፡ ለዶሮይቱ አውራ ባያዘጋጅላቸው ከጎረቤት አውራ ዶሮ ጋር በምታደርገው ግንኙነት በየቀኑ አንደ አንድ እንቁላል ትጥልለታለች፡፡ እርሱ ደግሞ ያቺን ከሥሯ እያነሳ ለሰፈሩ ባለሱቅ ይሸጥና ዳቦ ገዝቶ እየገመጠ ወደ ቤቱ ይገባል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ሲኖር አንደ ምሽት ከቀን ሥራው ሲመለስ ራቱን የምትመግበውን ዶሮ ከቆጧ ላይ ያጣታል፡፡ ምናልባት ጎረቤት ካለው አውራ ዘንድ ሔዳ እንደሆነ ብሎ ቢጠይቅም የለችም፡፡
በጣም አዝኖ ጉዳዩን ለአካባቢያቸው መሪ ይነግራቸዋል፡፡ እሳቸውም ብልህ ነበሩና ሐሳቡን ከሌሎች ጉዳይ ጋር በማያያዝ ስብሰባ ይጠራሉ፡፡ ከስብሰባው አጀንዳዎች አንዱ የጠፋችው ዶሮ ጉዳይ ነበርና መሪው ስለስርቆት አስከፊነት የተወሰነ መልዕክት አስተላለፉ፡፡ ቀጠሉናም ስለጠፋችው የድሃው ዶሮ ገለጻ ካደረጉ በኋላ የተቀመጠውን ሕዝብ፣ ‹‹በሉ ቁጭ በሉ›› ይላሉ፡፡ ሕዝቡ፤ ‹‹አንድም የቆመ ሰው በሌለበት፣ ‹‹ተቀመጡ›› ማለታቸው ምንድን ነው?›› ብሎ ሲያጉረመርም፣ ሰብሳቢው ጠረጴዛውን መታ መታ አደረጉና፣ ‹‹ያጉረመረማችሁበት ምክንያት ገብቶኛል፡፡ እኔ ‹‹ቁጭ በሉ›› ያልኩት የዶሮዋ ሌባ አለመቀመጡን ስላየሁ ነው፤›› አሉ፡፡ ይኼኔ፣ ድንገት አንድ ወጣት ከተቀመጠበት ተነሥቶ፣ ‹‹ኧረ ቁጭ ብያለሁ!›› ብሎ ራሱን አጋለጠ፡፡
(ዘመን፤2001)
* * *
‹‹አንድ ጠርሙስ አረቄ . . . !››
በጠጪነቱ የታወቀ የአንድ መሥሪያ ቤት ሠራተኛ ጧት ሥራ ከመግባቱ በፊት ከቤቱ ጀምሮ ባሉ አንድ አራት መጠጥ ቤቶች ጎራ እያለ ፉት ይላል፡፡ ማታም እንዲሁ አትለፍ የተባለ ይመስል የደንቡን ሳያደርስ ቤቱ አይገባም፡፡ ይህ ልምዱ እንደማያዋጣው በብዙ ሰዎች ከተነገረው በኋላ አንድ ጧት ለራሱ ቃል ገባ፣ ሳይጠጣ ቢሮው ገብቶ ሳይጠጣ ቤቱ ለመመለስ፡፡ እናም፣ ምሎ እና ተገዝቶ እኒያን መጠጥ ቤቶች ጧት ላይ እየገላመጠ እና እየረገማቸው አልፎ መሥሪያ ቤቱ ደረሰ፡፡ በውሳኔው ተደስቶ በሰላም ሲሠራ ከዋለ በኋላ ማታም ወደ ቤቱ ሲመለስ የጧቱኑ ዕርምጃ ወሰደ፡፡ ሳይቀምስ ውሎ ሳይቀምስ በመግባቱ ተደስቶ፣ ‹‹ጀግና ነኝ! ቆራጥ! ለዚህ ጀግንነቴ አንድ ጠርሙስ አረቄ ይገባኛል በማለት ወደ አረቄ ቤት በረረና አረፈዋ!
(ዘመን፤2001)
* * *
ፉዞ! ፉዞ!
በሀያ አምስት ዓመት
ዕድሜው ሽበት ወሮታል፡፡ ወጣት እንጂ አዛውንት አለመሆኑ ግን ከፊቱ ወዝ ይታወቃል፡፡
አይናገርም፤ አይጋገርም፡፡ ብቻውን መንገድ ለመንገድ ሲንከራተት ይውላል፡፡ ሲደክመው ካገኘው ሻይ ቤት ገብቶ ሻይ ያዛል፡፡ እስመጣለት ድረስ ፊቱን በመዳፉ ያሻሸዋል፡፡ ዓይኖቹን በጣቶቹ ጫፍ ጫን ጫን ይላቸዋል፤ እንቅልፉ መጥቶ ለመንቃት እንደፈለገ ሁሉ፡፡ በእውነቱ ከሆነ ሁልጊዜም ቢሆን በእንቅልፍ መሰል ሰመመን ውስጥ የሚኖር ይመስላል፡፡ ዓይቹ ውጫዊ ነገር የሚያዩ ቢመስሉም ውጫዊ ነገር አያዩም፡፡ ዘወትር የሚመለከቱት ወደ ውስጥ ነው፤ ወደ አእምሮው ውስጥ፤ ወደ ሕሊናው ውስጥ፤ በአጠቃላይ ወደ ሕይወቱ ውስጥ፡፡
በሰው መሐል ቢሆንም እንኳ ዘወትር ብቸኛ ነው፡፡ ሻይ ቤት በሚገባበት ጊዜ አሳላፊው ወይም አሳላፊዋ ሲመጡ ‹‹ሻይ›› ከማለት በስተቀር ሌላ ቃል አይተነፍስም፤ በውስጣዊ ሕይወቱ ሰምጦ ስለሚቀር፡፡
ሻይ ቤት ውስጥ ያገኙትና ከሱ ራቅ ብለው የተቀመጡት ሁለት ሰዎች ስለሱ ያወሩ ጀመር፤ አንድ ቀን፤
‹‹ታውቀው የለም?››
‹‹ማንን?››
‹‹ያን ወጣት አዛውንት…. ወይንስ አዛውንቱ ወጣት ልበለው? ለወሬ የማያመች አሳዛኝ ሰው! አሁን ማን ይሙት በሀያ አምስት ዓመት ዕድው ሽበት ያበቀለ ሌላ ሰው ታውቃለህ?››
‹‹ኦ! እሱን ማለትህ ነው! ለመሆኑ ስለሱ የሚወራው እውነት ነው እንዴ?››
‹‹ስለሱኮ ብዙ ነገር ይወራል፡፡ የትኛውን ማለትህ ነው?››
‹‹ከዚህ ያደረሰው የሴት ፍቅር ነው የሚባለው፡፡››
‹‹እውነት ነው እንጂ! እኔኮ ደህና አድርጌ አውቀዋለሁ፡፡ መምህር ነበር፡፡ እንዴት ያለ ደስተኛ ሰው ነበር መሰለህ ሳቂታ… ተጫዋች! በዚያ ላይ ለሴት የማይንበረከክ ኩሩ ወጣት ነበር፡፡ በኋላ ጣለበትና አንዷን ተማሪ ወድዶ ቁጭ! እሷ ደሞ የሰጥጣን ቁራጭ ነች…. ክልፍልፍ፡፡ አልፈልግህም አለችው፡፡ የወንድ ልጅ ኩራቱን ሰበረችበት፡፡ ከዚያ ወዲያ ሰው ለመሆን አልቻለም፡፡ እምቢ አልፈልግህም ስትለው የዓለም ፍጻሜ የደረሰ መሰለውው፡››
‹‹ደካማ ሰው መሆን አለበት!››
‹‹እንዴት?››
‹‹አንዲት ሴት ልጅ አልፈልግህም ብትለው ሌላ ሴት ልጅ አይፈልግም ኖሯል? እንዴት የዓለም ፍጻሜ የደረሰ ይመስለዋል? በጣም ደካማ ሰው መሆን አለበት፡፡››
‹‹ኧረ አይጣል በል! ከጣለኮ ይኸው ነው! ፉዞ ሆኖ መቅረት!››
‹‹ፉዞ! ፉዞ!››
(ሳህለሥላሴ ብርሃነማርያም፤ ሽኩቻ፣ 1987)
* * *
ገራገር
በሐውልቷ ጡት የተበሳጩት የፈረንሳዩ ከንቲባ
በፈረንሳይ የምትገኘውና የ10 ሺሕ ሰዎች መኖርያ የሆነችው የኑቬሊኤን ፊሬዬን ከንቲባ የሆኑት ጀራርድ ኮርዶን፣ ማሪየን ለምትባል ፈረንሳዊት የተሠራላት የጠረጴዛ ሐውልት ጡቷ ተልቋል በሚል እሳቤ በብስጭት ከከንቲባው ጽሕፈት ቤት ወርውረውታል፡፡
ማሪየን በፈረንሳይ የሪፐብሊክ ፓርቲ ቀንደኛ ተሳታፊ የነበረች ሲሆን፣ ሐውልቷ የተሠራው ለሴት አርበኞች መታወሻነት ነው፡፡ የሐውልቷ ጡት ተልቋል ብለው ሐውልቱን ያስወገዱት ከንቲባ በምትኩ ከተማዋ ካላት በጀት 1 ሺሕ 280 ዶላር ወጥቶ ሌላ ሐውልት እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡
ሐውልቱን የሠራችው አርቲስት ካትሪን እንደተናገረችው ከሆነ፣ የሐውልቷን ጡት ያተለቀችው ሆን ብላ ሲሆን፣ እንዲያስተላልፍ የፈለገችውም መልዕክት የሪፐብሊክ ፓርቲ እጅ ለጋሽ፣ ደግና ሁሉንም ነገር በስፋትና በብዛት የሚያደርግ እንደሆነ ለመጠቆም ነው ብላለች፡፡ አያይዛም፣ ‹‹ከንቲባው ካቀረብኩላቸው አማራጭ ዲዛይኖች ውስጥ መርጠው የሠራሁትንና ለአራት ዓመታት ያህል አፍንጫቸው ስር አድርገው ሲመለከቱ ኖረው ካበቁ በኋላ ወርውረውታል›› በማለት በከንቲባው ድርጊት ደስተኛ እንዳልሆነችና ሐውልቱን ግን ጨርሰው እንደማይሰባብሩት ምኞቷ እንደሆነም ገልጻለች፡፡
ከንቲባው ውሳኔውን የወሰኑት ብቻቸውን እንደሆነና ለዚህ ደግሞ ምክንያቱን መግለጽ አለመፈለጋቸው ተገልጿል፡፡ ይሁንና አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የከንቲባው ጽሕፈት ቤት ሠራተኛ፣ ሐውልቱ ጥሩ እንደነበርና ሐውልቱ የተሠራላት ማሪየን የእናትነት ምልክትም እንደነበረችም ገልጿል፡፡
* * *
ባንኩን ከባንክ ዘራፊዋ የታደጉት የ66 ዓመት አዛውንት
አንዲት ሴት እጇን ቦርሳዋ ውስጥ በመክተት ሽጉጥ እንደያዘችና ሁሉም ሰው መሬት ላይ እንዲተኛ በጩኸት በማዘዟ ባንኩ ውስጥ ያሉት ሰዎች ከመሬት ተገናኝተው ነበር፡፡ ይሁንና ብሞትም አይቆጨኝም ያሉት ሴት ለመዝረፍ የተጣጣረችውን ሴት በጠረባ በመጣል ፖሊሶች በቦታው እስከሚገኙ ድረስ በቁጥጥር ስር አውለዋታል፡፡
ለመዝረፍ አቅዳ የነበረችው ብሪን፣ ሙከራዋ ፈረንጆች የአፕሪል ወራቸውን ሲጀምሩ በተለያዩ ቀልዶች የሚዝናኑበትን ቀን ‹‹አፕሪል ዘ ፉልን›› አስመልክቶ እንደነበረ ብትናገርም፣ ወደ ጊዜያዊ የእስር ክፍል እየወሰዷት የነበሩት ፖሊሶችና በባንኩ የነበሩ ሰዎች ግን አስቂኝ ሆኖ አላገኙትም፡፡ ይብሱንም ወደጊዜያዊ ማሰሪያ ክፍል በመወሰዷ 10 ሺሕ ዶላር ሊከፈላት እንደሚገባም ጠይቃለች፡፡
‹‹ደረጃው አራት ላይ የደረሰ የካንሰር በሽተኛ ነኝ፡፡ የምሞተው በፈጣሪ ፈቃድ ነው፡፡ ይሁንና ዘራፊዋ በተኮሰችው ጥይት እኔ አልሞትም›› ያሉት አዛውንቷ ሕይወታቸውን ስለታደጉላቸው የባንኩ ሠራተኞችና ደንበኞች ታላቅ ምስጋናና አድናቆትን ለግሰዋቸዋል፡፡


