በእስከዳር አስማረ
አጭር ቁምጣቸውን እና ከትከሻቸው ላይ ጣል ያደረጉት ‹‹ጎጃም አዘነ›› ነጠላቸው የመጡበትን አካባቢ ይናገርባቸዋል፡፡
የአርሶ አደር ልጆች መሆናቸውን እልፍ ሲልም የሰዎች ማዕድ መነሻ የሆነውን መሬት ሲያገላብጡ ስለመክረማቸው እጃቸው ይመሰክራል፡፡ የነበሩበት ቀዬ ጸጥታ፣ ዕርጋታና ለምለም ውበት ለዘላለም ይኑር በሚል ይመስልም ዛሬም ከመሀል ከተማዋ አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠው ከብርድ የማታስጥላቸውን አጭር ቁምጣቸውን መቀየር አልፈለጉም፡፡
የጎፋ አካባቢ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ናቸው፡፡ የአስፓልቱ ጥጋ ጥግ የቀን መዋያቸው፣ የሥራ ቦታቸው እንዲሁም ማደሪያቸው ነው፡፡ በአካባቢው ከሚያድሩ መኪኖች ሥር ማደርም የተለመደ ነው፡፡ ሥራ ካልተገኘ በስተቀር በብርድም በፀሐይም ሰብሰብ ብለው ባንድ ቦታ መቀመጥን ይመርጣሉ፡፡ ከአንድ አካባቢ መምጣታቸውም ተግባብተው ለመኖር ረድቷቸዋል፡፡
ከየት ነው የመጣችሁት? የሚለውን ጥያቄዬ ተከትሎ ሳቃቸውን ለቀቁት፡፡ በዕድሜ በለጥ የሚል የሚመስለው ልጅ እግርም እየሳቀ ከየት ይሆናል ከገጠር ነዋ! አለኝ፡፡ ለጠቅ አድርጎም፣ ‹‹ሁላችንም ከጎጃም ነው የመጣነ›› አለኝ፡፡ ለምን እንደመጡ፣ እንዴትስ እንደሚኖሩ ስጠይቃቸው፣ ተራ በተራ ያስረዱኝ ጀመር፡፡
‹‹ደሴ ተፈራ እባላለሁ፤ ዕድሜዬ 25 ደርሷል መሰል፤ ኮሰበር ከምትባል የጎጃም ወረዳ ከመጣሁ ሦስት ወር ገደማ ሊሆነኝ ነው፡፡ የመጣሁትም ማዳበሪያ የምገዛበት ገንዘብ ልሸቅል ብዬ ነበር፤ አልሆነልኝም፡፡ እህል እንኳን የምቀምሰው በሁለት ቀን አንዴ ሆኗል፡፡ በዛ ላይ የማድረው እዚሁ ጥግ አስፓልት ላይ ነው፡፡ ቅዝቃዜውም በሽተኛ ሳያደርገኝም አይቀር፡፡ አገሬ የምገባበት ገንዘብ ባገኝ ነገ ዛሬ ሳልል እመለስ ነበር፡፡ እኔ የከተማውን ኑሮ ዱሮም አልወደው፡፡ እንደው ቢቸግረን መጣሁ እንጂ፡፡ አሁን አሁን አውቶብስ ተራ ሔጄ የማይጨክን ወገኔን አስቸግሬ ልመለስ ብዬ አስብና ቀዬዬ የሚጠብቀኝ ከዚህ የከፋ ይሆንብኛል፡፡ የትራንሰፖርት ተበድሮ የላከኝ አባቴ፣ ለከርሞ ለማረስ ለአሠሪዎቼ የምከፍለውና የማዳበሪያው ከየት ሊመጣ እልና ዕድሌን አማርራለሁ፡፡ የራሴ መሬት የለኝም፡፡ የራሴው መሬት ቢኖረኝ እኩሌታ ለመካፈል ምን አንከለከለኝ፤ የማርሰው እኮ የሰው መሬት ነው፤ ዱሮ ዱሮ መሬቱም፣ ሰውም፣ ኑሮውም ደግ ነበር፡፡
ዛሬ ሰው ብቻ መሰለሽ የከፋው መሬቱም ነው፡፡ የመሬት ባለቤቶቹ እኩሌታ ተካፍለን ብቻ በጄ አይሉም፡፡ ተጨማሪ ብር ፈለጉ፡፡ በዛ ላይ ዛሬ መሬቱ ካለማዳበርያ እምቢ ብሏል፡፡ ታዲያ የማዳበርያም የምችለው እራሴው ነኝ፡፡ ዋጋው ደሞ አይቀመስም፡፡ ድሮ ድሮ መንግሥት በቀብድ ይሰጠን ነበር፡፡ ዛሬ ሙሉውን መክፈል አለብን፡፡ ኧረ ጣጣው ብዙ ነው እቴ፤›› አለኝ፡፡ ደሴ የታጨችለት የ8 ዓመት ሚስቱን እናቷ ጥሎ እንደመጣ፣ ጠቅልሎ ለማግባት ግን በቂ ንብረት እንደሌለውና እሷም እንዳልደረሰች፣ እናቲቱም አርጅታ የሚጦራት እንደሌለም ነገረኝ፡፡
ሌላው ታሪኩን ያጫወተኝ በላይነህ አያና ነው፡፡ 12 ዓመቱ ሲሆን፣ የመጣውም ከጎጃም ከሰላ ወረዳ ነው፡፡ ‹‹እዚህ የመጣሁት ልጆች ተከትዬ ነው፡፡ ብር የሰጠኝ አባቴ ነው፡፡ እሱ እኔ ወዲህ ከመምጣቴ በፊት ሁመራ የሚባል አገር ሥራ አለ ተብሎ ሔዶ ነበር፡፡ ግን ብዙም ሳይቆይ ታሞ መጣ፡፡ ያን ጊዜ ሃብታም ቤት ተቀጥሬ ብሠራም የሚችሉኝ ሆዴን ብቻ ነው፡፡ በሆዱ ቢጠግብም ልቤ አይጠግብም፡፡ ቤተሰቤ እየተራበ እኔ ሆዴ ቢሞላም ሞላሁ ይል መስሎሽ? ወዲህ የመጣሁት እኮ እናቴን፣ አባቴንና ታናናሽ እህት ወንድሞቼን እረዳ ብዬ ነው፡፡ ዱሮ አባቴ የሰው መሬት እያረሰ የሚያገኛትን ቀምሰን እናድር ነበር፡፡ አሁን የሰው መሬት ለማረስም ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እኔም አዲስ አበባ በሽታ የለም፡፡ ጥሩና ንጹሕ ከተማ ነች፤ ብር ይገኝባታል ሲባል ወዲህ መጣሁ፡፡ እዚህ መጥቼ ግን እንደሚባለው አይደለም፡፡ ለሆድም ይቸግራል፡፡ ሰዉ አንዳንዴ የሠራሁበትን አይሰጠኝም፡፡ ሌቦች የምንመስላቸውም አሉ፡፡››
አብዛኞቹ ከአንድ ወረዳ የመጡ በመሆናቸው እርስ በእርስ ይደጋፈፋሉ፤ ይዋደዳሉ፤ ሥራ ከሌላቸው በስተቀር የሚውሉት በአንድ ላይ ነው፡፡ ምንም ሳያገኝ የዋለ ሠርቶ ከዋለው የሻይ እና የዳቦ ይበደራል፡፡
ከመሃላቸው በዕድሜ የሚበልጠውና አዲስ አበባን ለ10 ዓመት የሚያውቃት ቀለሙ የመጣው፤ ከፍጋታ ሎኮማ ወረዳ ነው፡፡ ‹‹እየተመላለስኩ እኖራለሁ፡፡ ሚስቴንና ሦስት ልጆቼን ትቼ ነው ካገር ቤት የመጣሁት፡፡ የሰው መሬት ነበር የማርስ፡፡ እንደነገሩሽ የሚደርሰኝ ለዓመት ቀለቤ ሊሆነኝ ቀርቶ የማዳበሪያ እና ለባለንብረቱ የምከፍለውን ገንዘብ እንኳን አይሸፍንልኝም፡፡ ከተማን ተወዳጅቼው የቀረሁት ለዚሁ ነው፡፡ ሆኖም ዛሬ የራሴ ሻይ ቤት አለችኝ፡፡ ለቤተሰቤ የምልካት ገንዘብ እና የምጎርሰው አላጣም፡፡ የወገኔን ስቃይ ሳይ ግን በጣም አዝናለሁ፡፡
ሀገሬው ቀዬው መንደሩ ተራቁቶ የሰው ያለህ፣ የጎበዝ ያለህ የሚል ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በላይ የወንዜ ልጆች እዚህ ሲጉላሉ ሳይ ከማዘን በላይ የማመጣው የለማ! አባቶቻችን ‹እምነ ረሀብ ይኄይስ ኲናት› ይላሉ፤ ከረሀብ ጦር ይሻላል ማለት ነው፡፡ እና በረሃብ የሚሰቃይ ወገኔን እያየሁ ሰላም የለኝም፡፡›› ሌላኛው ወጣት ዋሲሁን ዳኘው ደግሞ ‹‹አዲስ አበባ ከመጣሁ ብሰነብትም›› በቁምጣዬ ምክንያት የወጣልኝ ‹ቆምጬው› የሚለው የከተማ ስም ግን አልተቀየረም›› ብሎኛል፡፡ አያይዞም እንዳለው፣
‹‹አገር ቤት ጎበዙ ወጣቱ የለም፡፡ ይልማም ይበጅ ወዲህ ወደ ከተማ ነው፡፡ እቤት የቀሩት አቅመ ደካማ አባት እና እናት ናቸው፡፡ እነሱም ቢሆኑ ቤታቸውን ዘግተው ሳይወጡ አይቀሩም ብዬ እፈራለሁ፡፡››
አንዳንዶቹ ትምህርት ቤት ገብተው ሁለተኛና ሦስተኛ ክፍል ሲደርሱ እንዳቋረጡ፤ አብዛኞቹ ደግሞ እንዳልጀመሩ፣ ብዙዎቹ ከከተማው ኑሮ አብልጠው የገጠሩን ኑሮ እንደሚወዱት፣ ችግር ባይዛቸው እንጂ ወዲህ የሚመጡት እዛው ቀያቸው ቢቀመጡ እንደሚወዱምና ከከተማው እራፊ ጨርቅም የእነሱ ጎጃም አዘነ ቅዝቃዜ እንደሚከላከልላቸው ‹‹የኛ ይበልጣል›› በሚል መንፈስ! አጫወቱኝ፡፡


