በአስፋው ብርሃኑ
የ3ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ነው ኤሌክትሪካልና ኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን መነካካት የጀመረው፡፡ በአንድ ወቅት ሁለት ሽቦዎችን የኤሌክትሪክ ሶኬት ውስጥ ካስገባ በኋላ ማሳ (short) አድርጎ ቤት ውስጥ ችግር ፈጥሮ እንደነበር ያስታውሳል፡፡
እንዲህና እንደዚያ እያደረገ ዛሬ ደግሞ ሔንሪ ሩዶልፍ ሔርዝ ለዓለም የተዋወቀውን የሬዲዮ ሞገድ ማሰራጫ ሠርቶ አየር ላይ አውሏል፡፡ ሞገዱ ኤፍኤም ሲሆን የተለያዩ ፍሪኩዌንሲዎችን ሲቀያይር ቆይቶ በስተመጨረሻ ኤፍኤም 97.5 ላይ የተሻለ ጥራት ያለው ድምፅ ማግኘት እንደቻለ ይናገራል፡፡ የዚህ ፈጠራ ባለቤት ዘንድሮ የፕሪፓራቶሪ ፈተና ወሳጅ ተማሪ ብሩክ ተፈራ ሲሆን፣ ተወልዶ ያደገው ይርጋለም ከተማ ነው፡፡
ተማሪ ብሩክ ገና የ21 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ ከዕድሜው ትንሽነት አንጻር የሠራቸው ውጤቶች የነገው የአገራችን ተስፋ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው፡፡ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መስተዳድር ትምህርት ቢሮ ባዘጋጀው የትምህርት ሲምፖዚየም ላይ ለኤግዚቢሽን የቀረቡ የአንዳንድ ተማሪዎች የፈጠራ ግኝቶች አስደናቂዎች ነበሩ፡፡ በዚያ ኤግዚቢሽን ላይ የፈጠራ ሥራዎቹን ያቀረበው ብሩክ ተፈራ ሲመራመርበት በነበረው የኤፍኤም 97.5 ማሰራጫ ሰርኩዊት ቦርድ ለታዳሚዎች ሙዚቃ ሲያስደምጥ የበርካቶችን ትኩረት ለመሳብ ችሏል፡፡
የይርጋለም ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነው ብሩክበቀጣይ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ ኤሌክትሪካል ምህንድስናን በማጥናት የፈጠራ ዝንባሌውን በጽንሰ ሐሳብ አጣምሮ በምርምር ሥራው አገራችን ከውጭ የምታስገባቸውን ቴክኖሎጂዎች በአገር ውስጥ ተመርተው የማየት ህልም እንዳለው ይናገራል፡፡
በልጅነት ዕድሜው የጀመረው የኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪካል የምርምር ሥራ የቤተሰቦቹ፣ የመምህራኑ፣ የጓደኞቹና የተለያዩ ግለሰቦች እገዛና ማበረታታት ከጐኑ እንዳልተለየው በምስጋና ይገልጻል፡፡ ተማሪ ብሩክ ከኤፍኤም 97.5 ማሰራጫ በተጨማሪ የቡና መቁያና የውኃ ማሞቂያ መሥራቱን፣ የቤት በር ሲከፈት እየበራ የሳይረን ድምፅ የሚያሰማ ደወል እንዲሁም የቡና መፍጫ ሰርኪዩት ዲዛይን እያደረገ መሆኑን ሲናገር፣ አቋርጬው ‹‹አሁን አንተ ኮሌጅ መግቢያ ፈተና ልትወስድ ነው ብዙ ማጥናት ይጠበቅብሃልና በየትኛው ጊዜህ ነው ይህን ሁሉ የምትሠራው?›› ብዬ ለጠየቅሁት ተማሪ ብሩክ፣ ‹‹ይህን ሁሉ የማደርገው በትርፍ ጊዜዬ ነው አንጠቀምም እንጂ ያለን ትርፍ ጊዜኮ ብዙ ነው፤ ጥናቴ ላይም ምንም ተጽእኖ የለውም፤›› በማለት ያብራራል፡፡
ቻይና ዛሬ ላይ ለደረሰችበት የቴክኖሎጂ ደረጃ የበቃችው የሌሎች አገሮች ፈጠራዎችን እየኮረጀች፣ በምርምር እያሻሻለችና ወጣት ተማሪዎቿ የሚሰለጥኑበት ዩኒቨርሲቲዎችን በማመቻቸት ነው፡፡ ልክ እንደ ሔንሪች ሩዶልፍ ሔርዝ ሁሉ፣ ኢትዮጵያዊ የሬዲዮ ቴክኖሎጂስት አይኖርም ያለው ማን ነው? የሚለው ብሩክ፣ አገራችን ከውጭ የምታስገባውን ቴክኖሎጂ ማስቀረት ብቻ ሳይሆን፣ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን ለሌሎች አገሮች የምትልክበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም እያለ በዓይነ ህሊና በቴክኖሎጂ ያደገች ኢትዮጵያን ፈገግታን በተላበሰ አንደበት ይናገራል፡፡
የሬዲዮ ፍሪኩዌንሲ የአገር ትልቅ ሀብት ነው፡፡ የሕግና የአዋጅ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል፤ ዝም ብሎ አየር ላይ መልቀቅ አይቻልምና፡፡ እነዚህን ነገሮች ስለማወቁ ለጠየቅሁት ተማሪ ብሩክ ሲመልስ፣ ‹‹በእርግጥ እኔ ለአገሬና ለሕዝቤ ይጠቅማል የሚል እምነት ነው የነበረኝ፡፡ ነገር ግን ከሌሎች ሰዎች ስሰማ ለትምህርታዊ ጉዳይ ከሆነ ምንም ችግር እንደሌለው ተገንዝቤአለሁኝ፡፡ እኔም ምርምሬን እቤት ውስጥ መዝሙር፣ ሙዚቃና ሌሎች ነገሮችን ባሰራጭም፣ በትምህርት ቤት ውስጥ ግን ትምህርታዊ መረጃዎች ብቻ እናሰራጭበት ነበር፤›› በማለት ገልጿል፡፡
የትምህርት ቤት ጓደኞቹ በአንዳንድ ቴክኒካዊ ድጋፍ እንደሚያበረታቱትና እነሱም በትርፍ ጊዜያቸው የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እንደሚያደርጉ የሚገልጸው ተማሪ ብሩክ፣ ከነዚህም አንዱ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ምሕረቱ ነው፡፡ ልክ እንደ ብሩክ አዕምሮው በምርምር የለመለመ ሲሆን፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠራ ሞዴል መኪና እና የሊድ ማስለቀቂያና ኃይል መቆጠቢያ ኤሌክትሪካል መሣርያዎችን ሠርቶ በኤግዚቢሽኑ ለዕይታ አቅርቧል፡፡ በእርግጥ የይርጋለም ወጣት ተማሪዎች በፈጠራ ሥራዎች የተካኑ መሆናቸውን ከመምራህሮቻቸው አንደበት ለመረዳት ተችሏል፡፡
‹‹ይህ የብሩክ ኤፍኤም 97.5 የሬዲዮ ድምፅ ነው›› እያለ ለጐረቤቶቹ ለሁለት ወራት ያህል፣ በትምህርት ቤት ደግሞ ለሦስት ወራት ማስደመጡን የገለጸው ብሩክ፣ የይርጋለም 2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ለአንዳንድ ቁሳቁሶች መግዣ 400 ብር የገንዘብ እገዛ ማድረጉን፣ በአንዳንድ ጽንሰ ሐሳቦች ዙርያ ሳይሰለቹ ዕውቀታቸውን ያካፈሉት የፊዚክስ መምህሩ አቶ መላኩና መምህር ጥላሁን ቸርነት መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
ለዕድሜ አቻዎቹና በአጠቃላይ ለወጣቱ ትርፍ ጊዜያቸውን በፍላጐታቸውና በዝንባሌያቸው ዙርያ አትኩረው በመሥራት ራሳቸውን ከሱስና ከአልባሌ ቦታዎች ውሎ እንዲቆጥቡ በማለት አገራችን ከወጣቱ ዜጋ ብዙ እንደምትጠብቅ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡


