በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የአገሪቱን የጐማ ዛፍ ምርት ከሦስት ሺሕ ቶን በላይ ለማሳደግ የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የጐማ ዛፍ ልማት ናሽናል ኒኩለስ ፕሮጀክት ማስታወቁን ዋልታ ዘገበ፡፡ የኢትዮጵያ የጐማ ዛፍ ልማት ናሽናል ኒኩለስ ፕሮጀክት በ2009 ዓ.ም. 3,275 ቶን የጐማ ዛፍ ምርት ለገበያ ያቀርባል፡፡
በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ለገበያ የሚቀርበው የጐማ ምርት በአሁኑ ወቅት እየቀረበ ያለውን የምርት መጠን 90 በመቶ የሚያሳድገው ሲሆን፣ የገቢውን መጠን ደግሞ አሁን ካለው የሽያጭ ዋጋ ወደ 300 ሚሊዮን ብር ያደርሰዋል፡፡ ምርቱ የሚገኘው አሁን በጐማ ዛፍ ከለማው 1,438 ሔክታር መሬት ላይና በዚህ ዓመት ከሚለማው 562 ሔክታር መሬት ላይ ነው፡፡ አገሪቱ አላት ተብሎ ከሚገመተው 500,000 ሔክታር መሬት ለጎማ ዛፍ ከሚውለው ውስጥ በአሁኑ ጊዜ እየለማ ያለው እጅግ ጥቂቱ መሆኑ ተገልጾ፣ ዘርፉን ለማሳደግም ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ እስካሁን ድረስ በገበሬዎችና በኢንቨስተሮች እየለማ ያለው መሬት 21 ሔክታር ብቻ እንደሆነ ዘገባው አክሎ አመልክቷል፡፡
* * * *
በብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ላይ ውሳኔ ተላለፈ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባው በብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት ረቂቂ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ ምክር ቤቱ እንደገለጸው በዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ውስጥ ክፍያዎች የሚፈጸሙት የተሻለ ደኅንነትና አስተማማኝነት ባላቸው ጥሬ ገንዘብ ባልሆኑ የክፍያ መሣሪያዎች ነው፡፡ መንግሥት አገሪቱ አሁን የተያያዘችውን ዕድገት ለማፋጠን የሚያግዝ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህ ጥረት እንዲሳካ የሚታሰበውን ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ የሚያደርግ አዋጅ ማውጣትና ተፈጻሚ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ በብሔራዊ ባንክ በኩል ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ መቅረቡ ታውቋል፡፡ ምክር ቤቱ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ እንዲፀድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
* * * *
የኮንዶሚኒየም ዕድለኞች ብድር የሚያገኙበት አዲስ አሠራር ተዘጋጀ
ኅብረተሰቡ የኮንዶሚኒየም ቤት ዕድል እንዳያመልጠው የቅድሚያ ክፍያውን 30 በመቶ በመቆጠብ ቀሪውን ከተቋሙ መበደር እንደሚችል የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋምን ጠቅሶ አዲስ ልሳን ዘግቧል፡፡ አዲሱ አሠራር የተዘጋጀው የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ወጥቶላቸው የቅድሚያ ክፍያ ባለመክፈል ዕድሉ የሚያመልጣቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ችግር ለመፍታት ነው፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤት ዕድለኛ ለመሆን የሚቆጥቡ የኅብረተሰብ ክፍሎች አነስተኛ መሆናቸውን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል፡፡
* * * *
የመንገድ ጥገና ፍላጐት ጥናት ተጀመረ
የመንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት የመንገድ ጥገና ፍላጐት ጥናት ማስጀመሩን አዲስ መዘን ዘገበ፡፡ ጽሕፈት ቤቱ የመንገዶች ደኅንነት እንዲጠበቅና ጥራት ያለው ተከታታይ ጥገና እንዲያገኙ በጀት ከመመደብ በተጨማሪ የመንገድ ጥናት ፍላጐት አስጀምሯል፡፡ የመንገድ ጥገና ወጪ እየናረ መምጣቱ ተጠቅሶ፣ ከጥናቱ ጋር ተያይዞ አግባብነት ያላቸው ወጪ ቆጣቢ የጥገና ስልቶች እንዳስፈላጊነቱ በመጠቀም የመንገድ ጥገና ዋጋን ለማረጋጋት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡


