በኃይሌ ሙሉ
የማኀበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ 4.5 ቢሊዮን ብር በሚደርስ ወጪ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ የተሠማራ መሆኑን፣ የኤጀንሲው ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጋሻው ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ከዚህ ቀደም ጥናት ተደርጐባቸው ኪሳራ እንደማያስከትሉ በታወቁ ኢንቨስትመንቶች ላይ ተሰማርቶ የቆየ መሆኑን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በቦንድ፣ በግምጃ ቤት ሰነድ ግዥና በጊዜ ገደብ ተቀማጭ ወ7ለድ በአጠቃላይ 4.5 ቢሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲውል እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
‹‹የጡረታ ፈንድ ኢንቨስት ሲደረግ አደጋው ዜሮ መሆን አለበት፡፡ የሕዝብ ሀብት ስለሆነ አስተማማኝ ባልሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች መሳተፍ የሚቻልበት ሁኔታ የለም፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በአሁኑ ጊዜ ፈንዱ ኢንቨስትመንት እያካሄደባቸው ከሚገኙት ከቦንድ ግዥ፣ ከመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነድ፣ ከአክሲዮንና ከጊዜ ገደብ ተቀማጭ በተጨማሪ፣ የመክሰር አደጋቸው ወደዜሮ በተጠጉ በሌሎች ሰባት የኢንቨስትመንት መስኮች ኢንቨስት ለማድረግ ጥናት ተካሂዶ የተጠናቀቀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና መንግሥት በዘንድሮው ዓመት ለጡረተኞች ክፍያ ባደረገው ጭማሪ በወር ግማሽ ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ እንደሚያወጣ በኤጀንሲው የተሠራው ጥናታዊ ውጤት ያመለከተ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት ለጡረተኞች የተመደበው ተጨማሪ ክፍያ በባንኮች፣ በፖስታ ቤትና በሌሎች ከፋይ ተቋማት እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፣ መንግሥት የክፍያ አገልግሎት ለሚሰጡ ድርጅቶች የሚያወጣውን ክፍያ ጨምሮ በአጠቃላይ በየወሩ 497 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ክፍያ ለጡረተኞች ይከፍላል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡


