- እያንዳንዳቸው በአሥር ሺሕ ብር ዋስ ተለቀቁ
በታምሩ ፅጌ
የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ ለይኩን ብርሃኑን ጨምሮ አሥሩም ተጠርጣሪዎች ከመጋቢት 28 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ከአገር እንዳይወጡ በፍርድ ቤት እግድ ተጣለባቸው፡፡
በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸው መጋቢት 28 ቀን 2003 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ስድስተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የነበሩት የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማኅበር ሠራተኞች የነበሩት ተጠርጣሪዎች ከአገር እንዳይወጡ እግድ የተጣለባቸው፣ ዓቃቤ ሕግ ከአገር ሊወጡ ስለሚችሉ ለብሔራዊ መረጃ፣ ደኅንነትና ኢሚግሬሽን ዋና መምርያ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው ማመልከቻ መሠረት ነው፡፡
ተከሳሾቹ ችሎት ቀርበው የክስ ቻርጁ ከተነበበላቸው በኋላ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀው፣ ‹‹ክሱን አንቃወምም፤ ድርጊቱን ግን አልፈጸምንም፤›› ብለዋል››
ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎቹን የእምነት ክህደት ቃል ከተቀበለ በኋላ የዓቃቤ ሕግን የምስክሮች ቃል ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱን አጠቃሏል፡፡
ዓቃቤ ሕግ 6,196,760.88 የአሜሪካን ዶላር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እንዲፈቅድ አዘዋል በሚል ክስ የመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች አቶ ለይኩን ብርሃኑ፣ አቶ ምትኩ አብሹ፣ አቶ ታደሰ አሻግሬ፣ ወይዘሮ ወንጌላዊት ብርሃነ ሥላሴ፣ አቶ ጌታሁን አለማር፣ አቶ እንዳለ ቱኒ፣ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ አባተ፣ አቶ ደረጀ አበበ፣ አቶ ቸርነት ዋቅጋሪና ወይዘሮ ፍቅርተ ሽመልስ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡


