በዳዊት ታዬና በኃይሌ ሙሉ
መንግሥት ያዘጋጀው የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ ረቂቅ አዋጅ ሰሞኑን ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ረቂቅ አዋጁ በፕሮቪደንት ፈንድ ታቅፈው ላልነበረ የግል ድርጅት ሠራተኞች ዋስትና እንደሚሰጥ የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ይገልጻል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የግል ድርጅት ተቀጣሪዎች ረቂቅ አዋጁን በበጐ ጐኑ የተመለከቱት ሲሆን፣ የተወሰኑት ደግሞ በአዋጅ ላይ በተካተቱት አንዳንድ አንቀጾች ደስተኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የግል ድርጅት ሠራተኞች ላይ ብዥታን ፈጥረዋል፡፡
በአዋጁ ላይ እንደተገለጸው፣ ከሰኔ 2002 ዓ.ም. በፊት ፕሮቪደንት ፈንድ ያቋቋሙ የግል ድርጅቶች ከፈለጉ ብቻ ነው በጡረታ ፈንድ እንዲታቀፉ የሚደረጉት፡፡ ጡረታ ፈንድ ውስጥ መግባት ካልፈለጉ ቀደም ሲል ባቋቋሙት ፕሮቪደንድ ፈንድ መቀጠል ይችላሉ፡፡ ከሰኔ 2002 በፊት ተቋቁመው የፕሮቪደንት ፈንድ ያልነበራቸው የግል ድርጅቶች ግን በግዴታ የጡረታ ፈንድ ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ በጡረታ ፈንድ የሚታቀፉ አንድ የግል ድርጅት ሠራተኛ የደመወዙን ሰባት በመቶ ድርጅቱ ደግሞ አሥራ አንድ በመቶ ለጡረታ አበል የማዋጣት ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ በግል ድርጅት ውስጥ ከአሥር ዓመት በታች ያገለገለ አንድ ሠራተኛ ከሥራ ሲለቅ ምንም ዓይነት ክፍያ የማያገኝ መሆኑም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተደንግጓል፡፡
ብሩክ ከበደ የግል ድርጅት ተቀጣሪ ነው፡፡ ለግል ድርጅቶች የጡረታ አበል እንዲያዋጡ የሚያስገድድ ሕግ መውጣቱን ይደግፋል፡፡ ይሁን እንጂ ከአሥር ዓመት ያነሰ ጊዜ ያገለገለ ሠራተኛ ያዋጣው ገንዘብ አይመለስለትም ተብሎ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ መካተቱ ተገቢ ነው ብሎ አያምንም፡፡
‹‹አንድ ሠራተኛ ዘጠኝ ዓመት ሙሉ በአንድ መስሪያ ቤት ውስጥ ሠርቶ ለመልቀቅ ቢፈልግ፣ እርሱም ሆነ መስሪያ ቤቱ ያጠራቀሙለት ገንዘብ ሊቀርበት አይገባም፤›› ይላል፡፡
ብሩክ እንደሚለው አንድ ሠራተኛ በጡረታም ሆነ በፕሮቪደንት ፈንድ ገንዘብ ሲጠራቀምለት ታሳቢ የሚያደርገው ጡረታውን ብቻ አይደለም፡፡ የተጠራቀመለትን ገንዘብ ይዞ በመውጣት አንድ ሥራ ሊሠራበት እንደሚችል አስቦ ሊሆን ስለሚችል ዘጠኝ ዓመት ሠርቶ ሲለቅ ያጠራቀመው ገንዘብ ሊመለስለት ይገባል፡፡
‹‹ሠራተኛው አሥር ዓመት ሳይሞላው መልቀቅ የሚፈልግበት ምክንያት የተሻለ ሥራ ሳያገኝ ሊሆን እንደሚችልም መታሰብ አለበት፤›› የሚለው ብሩክ፣ ደመወዝ ለማግኘት ወይም የግል ሥራ ለመሥራት ያሰበ ሠራተኛ አሥር ዓመት ሳይሞላው ሲለቅ እርሱም ሆነ ሲሠራበት የነበረው መስሪያ ቤት ባዋጡት የጡረታ አበል የተጠራቀመለትን ገንዘብ አለማግኘቱ ሠራተኛውን ተጐጂ የሚያደርገው መሆኑን ያስረዳል፡፡ አያይዞም ‹‹ይህ አንቀጽ ድጋሚ መታየት ይኖርበታል›› የሚል ሐሳብ ሰንዝሯል፡፡
አቶ ብሩክ ሥጋት ያሳደረበት በረቂቅ አዋጁ የተካተተው ሌላው ጉዳይ፣ ‹‹በዲሲፕሊን የተባረረ ሠራተኛ እስከተባረረበት ጊዜ ድረስ ያጠራቀመው ገንዘብ አይከፈለውም፤›› መባሉ ነው፡፡
በግል ድርጅት ውስጥ አሠሪውና ሠራተኛው መካከል አለመግባባት ቢፈጠር አሠሪው ሠራተኛውን ለመጉዳት በዲሲፕሊን ተባሯል ብሎ ቢያመለክት፣ ሠራተኛው ለዓመታት አለ ብሎ የሚያስበውን የጡረታ ክፍያ ሊያጣ እንደሚችል የጠቆመው አቶ ብሩክ፣ ይህ ጉዳይ በቅጡ ሊታይ የሚገባ መሆኑን ይገልጻል፡፡
ዮናስ ተስፋዬ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሠራ የሂሳብ ባለሙያ ነው፡፡ እሱ የሚሠራበት ድርጅት ከአሥር ዓመት በፊት የተቋቋመ ቢሆንም፣ የድርጅቱ ሠራተኞቹ የፕሮቪደንት ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት ያህል ያለማኅበራዊ ዋስትና ሲሠራ የቆየው ዮናስ ሰሞኑን ለተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው አስገዳጅ የግል ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ተደስቷል፡፡
የግሉን ሥራ ለመፍጠር የሚያስችለው የገንዘብ አቅም የሌለው በመሆኑ ተቀጣሪ ሠራተኛ ሆኖ ከመሥራት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለው የሚናገረው ይሄው ወጣት፣ በሚሠራበት ድርጅት ውስጥ ምንም ዓይነት የማኅበራዊ ዋስትና ሳይኖረው ሲያገለግል መቆየቱ ያስጨነቀው እንደነበር ይናገራል፡፡ ተስፋዬ እንደሚለው ከሆነ አስገዳጅ የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ ለተቀጣሪ ሠራተኞች እፎይታን የሚሰጥ ነው፡፡
‹‹ከዚህ ድርጅት ብለቅ የወደፊት ዕጣ ፈንታዬ ምን ይሆናል እያልኩ እጨነቅ ነበር፡፡ አሁን ግን የመንግሥት ሠራተኞች ብቻ ያገኙት የነበረውን ተጠቃሚነት እኔም ማግኘት በመቻሌ እድሜዬ ገፍቶ ከሥራ ስለቅ ምን ልሆን እችላለሁ የሚለው ጉዳይ የሚያስጨንቀኝ አይሆንም፤›› ሲል የጡረታ ፈንድን ጠቀሜታ ያስረዳል፡፡
ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በምህንድስና ተመርቆ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ሥራ ከጀመረ አንድ ዓመት የሆነው ወጣት ቴዎድሮስ በላይነህ በበኩሉ፣ በረቂቅ አዋጅ ላይ ያለው አመለካከት የተለየ ነው፡፡
በግል ድርጅት ውስጥ ለረጅም ጊዜ የመሥራት ዕቅድ እንደሌለው የሚናገረው ወጣት ቴዎድሮስ፣ አሥር ዓመት ሳይሞላው ከድርጅቱ በሚለቅበት ወቅት ከራሱ ደመወዝ የሚቆረጠው ሰባት በመቶ የጡረታ አበልና ድርጅቱ የሚያዋጣለት አሥራ አንድ በመቶ የጡረታ አበል ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን መደረጉ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ይናገራል፡፡
ቴዎድሮስ እንደሚለው፣ ተቀጣሪ ሠራተኛ ከአንድ ድርጅት በሚለቅበት ጊዜ ባገለገለባቸው ዓመታት ድርጅቱና ሠራተኛው ያዋጡት የጡረታ አበል ተመላሽ ሊሆንለት ይገባል፡፡
ባለፈው ሳምንት እትም ያነጋገርናቸው የተቃዋሚ ፓርቲ ብቸኛው የምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሰይፉም ተመሳሳይ አስተያየት ነው ያላቸው፡፡ አንድ ሠራተኛ ከድርጅቱ ሲለቅ ድርጅቱና ሠራተኛው ያዋጣው የጡረታ አበል ከነወለዱ ሊመለስለት እንደሚገባ የሚናገሩት አቶ ግርማ፣ ‹‹መንግሥት ከአሥር ዓመት በታች ያገለገለ የግል ድርጅት ሠራተኛ ምንም ዓይነት ክፍያ አይሰጠውም፤ ከሀያ ዓመት በታች ያገለገለ የግል ሠራተኛ ደግሞ ራሱ ያዋጣው ገንዘብ ብቻ ይመለስለታል የሚል ረቂቅ አዋጅ ማውጣቱ ከመውረስ የማይተናነስ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በአቶ ግርማ እምነት የግል ድርጅት ሠራተኞች ያዋጡት የጡረታ አበል ከሥራ ሲለቁ እንዳይመለስ ማድረግ ሥራ ፈጣሪን እንዳይበረታታ ያደርጋል፡፡
የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጋሻው ግን በአቶ ግርማ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ የግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ ፈንድ መውጣቱ ለግል ሠራተኞች የሥራ ዋስትና ከመስጠቱ በተጨማሪ ለድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹ረቂቅ አዋጁ የመውረስ መንፈስ አለበት›› ተብሎ በአቶ ግርማ የተገለጸውም ስህተት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ከአሥር ዓመት በታች ያገለገሉ ሠራተኞች ከሥራ በሚለቁበት ጊዜ ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳይከፈላቸው የሚደረገው መረዳዳት (Solidarity) የተሰኘውን ዓለም አቀፍ መርህ መሠረት በማድረግ ነው፡፡
አንድ ሰው ይሠራበት የነበረውን ድርጅት ለቅቆ የራሱን ሥራ ከጀመረ የተሻለ ነገር አግኝቷል ተብሎ እንደሚታመን የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፣ ከሥራ ለቅቆ የሄደው ሰው የጡረታ አበል ወደ ጡረታ ፈንድ ገቢ የሚደረገው በተቀጣሪ ሠራተኛነት ለረጅም ጊዜ አገልግለው ጡረታ የሚወጡትን ሰዎች ለመርዳት ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
በረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ባለድርሻ አካላት አልነበሩም
የመንግሥትና የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ረቂቅ አዋጅን ለማውጣት እንቅስቃሴ የተጀመረው ከስድስት ዓመት በፊት ነበር፡፡ የረቂቅ ዝግጅቱንም በሦስትዮሽ እንዲሠራ ለማድረግ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽንና መንግሥት ተሳትፈውበት ሲሠሩ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ሳይታሰብ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽንና የአሠሪዎች ፌዴሬሽን በረቂቅ አዋጁ ዝግጅት ላይ ተሳታፊ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ አሁን የቀረበውም ረቂቅ በመንግሥት የተዘጋጀ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር ኮንፌዴሬሽንና የአሠሪዎች ፌዴሬሽን ኃላፊዎች እንደጠቆሙት፣ ረቂቁን ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ቢሆንም፣ ይህ ተሳትፏቸው ከተቋረጠ ግን አምስት ዓመታት አልፏቸዋል፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅም እስካሁን ድረስ ያልደረሳቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በተለይ ለግል ድርጅቶች ሠራተኞች የጡረታ ፈንድ አዋጅ መውጣቱ ቀደም ብሎም የሚደገፍ ጉዳይ የነበረ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በረቂቅ አዋጁ በተካተቱት ዝርዝር ጉዳዮች ላይ አስተያየት ለመስጠት ረቂቁን መመልከት እንደሚኖርባቸው የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ ‹‹ሆኖም አንድ ሠራተኛ ለጡረታ ያዋጣው ገንዘብ አሥር ዓመት ካልሞላው አይመለስለትም የሚል አንቀጽ ካለው መስተካከል የሚኖርበት ይመስለኛል፤›› ይላሉ፡፡
‹‹አንድ ሠራተኛ ለጡረታ የሚያስቀምጠው ገንዘብ የራሱ ሊሆን ይገባል፡፡ ቢያንስ ያጠራቀመው ገንዘብ ሊመለስለት ይገባል፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ በረቂቅ አዋጁ አነጋጋሪ ነገሮች ካሉበት ኢሠማኮ ረቂቁን አይቶ የራሱን አስተያየት የሚሰጥበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የአሠሪዎች ፌዴሬሽን አንድ ኃላፊ በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡን የሰሙት በሚዲያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የረቂቅ ዝግጅቱ የአሰሪዎችን ፌዴሬሽን ሊያሳትፍ ይገባ እንደነበር የጠቆሙት እኝሁ ኃላፊ፣ ፌዴሬሽናቸው ወደፊት በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የራሱን አቋም የሚያሳውቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባንኮችና የጡረታ አዋጁ
በሁለቱም ረቂቅ አዋጆች ውስጥ አስገዳጅ ሊሆኑ የሚችሉ ሕግጋት ተካተዋል፡፡ በተለይ የጡረታ መዋጮ ሥራዎችን በተመለከተ ኤጀንሲው ተገቢውን የጡረታ መዋጮ ለጡረታ ፈንዱ ገቢ ሳያደርግ ከሦስት ወር በላይ የቆየ የግል ድርጅትን በባንክ ካለው ሂሳቡ ላይ ተቀንሶ ወደ ፈንዱ ገቢ እንዲሆን ሥልጣን ያለው መሆኑን ያመለክታል፡፡
ይህንን ለማስፈፀም ማንኛውም ባንክ በኤጀንሲው ሲጠየቅ አባል ድርጅቱ መሰብሰብ ያለበትን የጡረታ መዋጮ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከግል ድርጅት ሂሳብ ላይ ቀንሶ ለኤጀንሲው ገቢ በማድረግ ግዴታ የሚጣልበት ከመሆኑም በላይ በግል ድርጅቱ የጡረታ እቅድ ለተሳተፉት ሠራተኞች ደመወዝ የሚከፍል አሰሪ ገንዘቡ የሚገኝበትን የባንክ ቅርንጫፍ የሂሳብ ቁጥርን ለኤጀንሲው ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ የሂሳብ ቁጥሩ ሲቀየርም በ15 ቀን ለኤጀንሲው ማሳወቅ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አንድ አሠሪ የጡረታ መዋጮ ሰብስቦ ሳያስገባ የሚወዝፍ ከሆነ ተሰብሳቢ መዋጮውን ለማግኘት በቀጥታ የግል ድርጅቱን በመሸጥ ገቢ የማስደረግ ሥልጣን ለኤጀንሲው ይሰጣል፡፡
የጡረታ አበል መጠን ጭማሪ ተደርጐበታል
በሁለቱም የረቂቅ አዋጆች (በግልና በመንግሥት) አንድ ሠራተኛ ከአሥር ዓመት ያላነሰና 20 ዓመት ያልሞላ አገልግሎት ፈጽሞ በራሱ ፍቃድ ሥራውን ከለቀቀ፣ ወይም ከ20 ዓመት ያላነሰ አገልግሎት ፈጽሞ በአዋጁ እንደ ምክንያት ከተጠቀሰው ውጪ በሆነ ምክንያት ከተሰናበተ የአሠሪውን ድርሻ ሳይጨምር ሠራተኛው ባዋጣው መጠን ብቻ መዋጮው እንደሚመለስለት ይጠቅሳል፡፡
በመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ረቂቅ ውስጥ የአገልግሎት የጡረታ አበልን መጠን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እስካሁን ሲሠራበት በነበረው የአገልግሎት ጡረታ አበል የሚታሰበው ሠራተኛው ባገለገለባቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ ይከፈለው የነበረው አማካይ ደመወዝ 30 በመቶ ሆኖ ከአስር ዓመት በላይ ለፈጸመው ለእያንዳንዱ ዓመት የመከላከያ ሠራዊት ወይም የፖሊስ አባል ላልሆነ የመንግሥት ሠራተኛ 1.12 በመቶ ተጨምሮ ይታሰብለታል ይላል፡፡ በአዲሱ ረቂቅ ላይ ግን የተወሰነ ጭማሪ ተደርጐ ወደ 1.25 በመቶ አድጓል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት ወይም የፖሊስ አባል ለሆነ ደግሞ ከአስር ዓመት በላይ ለፈጸመው አገልግሎት ለእያንዳንዱ ዓመት 1.5 በመቶ ተጨምሮ እንደሚታሰብለት፣ እስካሁን አገልግሎት ላይ ያለው የመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ያመለክታል፡፡
በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ደግሞ ለመከላከያ ሠራዊትነት ወይም ለፖሊስ አባል የሚታሰበው ወደ 1.65 በመቶ ማደጉን ያሳያል፡፡


