በናታን ዳዊት
ካሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ አሁንም ድረስ መወያያ የሆነው ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው ‹‹የታላቁ ሚሌኒየም ግድብ›› ጉዳይ ነው፡፡
በተለይ የዚህ ግድብ ሥራ የሚጠይቀው ወጪ 80 ቢሊዮን ብር መሆኑና በኢትዮጵያ ታሪክ ይህንን ያህል ወጪ የተደረገበት ፕሮጀክት ያልነበረ መሆኑ ሲታሰብ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል፡፡
ምንም አልሠራልንም እያልን ለዘመናት ስንዘፍንለት የነበረው ዓባይ በእኛው በኢትዮጵያውያን ጉልበትና ገንዘብ ተገድቦ ለዜጐች ጥቅም እንዲሰጥ የተወሰደውን ዕርምጃ የማይደግፍ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ተገንብቶ እንዲያልቅ የማይመኝ የለም ብቻ ሳይሆን፣ ለግንባታው ማጠናቀቂያ ይፈለጋል የተባለውን ገንዘብ ለማሟላት ሁሉም የአቅሙን የሚያደርግ ስለመሆኑም እየታየ ነው፡፡
የታላቁ ሚሊኒየም ግድብ ሥራ ይፋ ከሆነበት ቀን ጀምሮ በተለይ ‹‹የመሠረት ድንጋይ›› ከተቀመጠበት ዕለት ወዲህ፣ የሕዝቡ ስሜት ለፕሮጀክቱ እውን መሆን ያለው ፍላጐት ምን ያህል እንደነበር መለካት የተቻለበት ነው ሊባልም ይችላል፡፡
ከዚህ መልካም ዜና ጐን ለጐን ሌላው ሰሞነኛ መወያያ አጀንዳ የነበረው ክስተት ደግሞ ከሁለት ዓመታት በላይ ተጥሎ የነበረው የባንኮች የብድር ገደብ መነሳት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹የባንኮች የብድር ገደብ በቅርቡ ይነሳል›› ማለታቸውን ተከትሎ ብሔራዊ ባንክ የብድር ገደቡን ማንሳቱን ሲያስታውቅ፣ በተለይ ባንኮችና ብድር ለማግኘት ላይ ታች ሲል ለቆየ ተበዳሪ ሁሉ መልካም ዜና፣ የምስራች ብለውታል፡፡ ይሁን እንጂ የብድር ገደቡ ቢነሳም ከጐኑ ያስከተለው አንድ መመሪያ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ከዚህ በኋላ ባንኮች በሚሰጡት እያንዳንዱ ብድር ላይ 27 በመቶውን ለቦንድ ግዥ ወይም ለግምጃ ቤት ሰንድ ግዥ እንዲያውሉ የሚያስገድድ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡
የዚህ መመሪያ መውጣት በመንግሥት በኩል እንደተነገረው ባንኮችን የሚጠቅምና፣ አገራዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው ለማስቻል ነው፡፡ አንዳንድ የኢኮኖሚና የባንክ ባለሙያዎች ደግሞ ከብድር ጣሪያው መነሳት ጋር ተሳስሮ የመጣው መመሪያ ወደፊት በኢኮኖሚው ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል የሚል ስጋት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡
መመሪያው በተለይ የባንኮችን የማበደር አቅም የበለጠ የሚገድብ፣ የትርፍ መጠናቸውን የሚቀንስና በአጠቃላይ በባንክና በመድን ኢንዱስትሪው ላይ ትልቅ ፈተና ይጋርጣል በማለት ስጋታቸውን አጠንክረው ይናገራሉ፡፡
ከሁሉም በላይ ግን መመሪያው ሸማቾችን የሚፈታተን ሊሆን የሚችል ነው መባሉ ደግሞ የበለጠ ያሳስባል፡፡ ባንኮች ከሚያበድሩት ገንዘብ 27 በመቶውን ለቦንድ ወይም ለግምጃ ቤት ሰነድ ግዥ አውሉ መባላቸው እንደመንግሥት እምነት ጠቃሚ ነው ቢባልም፣ መመሪያው የባንኮች የማበደር አቅምን በመጫን የብድር ወለድ ክፍያን እንዲያሳድጉ ያስገድዳል፡፡
እስካሁን ባለው የባንኮች አሠራር እንደብድር ሁኔታው ከዘጠኝ በመቶ ጀምሮ እስከ አሥራ አንድና አሥራ ሁለት በመቶ ወለድ እያሰቡ ሲያበድሩ ቆይተዋል፡፡ የዚህ መመሪያ መውጣት ግን ባንኮች የሚያበድሩ መጠን መቀነስን ተከትሎ ሊገጥማቸው የሚችለውን ክፍተት ለመሙላት የብድር ወለድ የክፍያ መጠን የሚያሳድጉ ከሆነ ተፅእኖው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊያርፍ የሚችለው ሸማቹ ላይ ስለሚሆን ለዋጋ ግሽበት እንዲጋለጥ ያደርገዋል የሚለው ስጋት ጐልቶ እየወጣ ነው፡፡
በአገራችን የሚታየውን የግብይት ሥርዓት ስንመለከት ደግሞ አብዛኛው ሸማች የሚጠቀምበት ሸቀጣ ሸቀጥ ከውጭ የሚመጣ፣ ይህንን ለማምጣትም ደግሞ አስመጪው ከባንክ በመበደር የሚሠራ በመሆኑ ለሚበደረው ብድር የሚከፍለው ወለድ የሚጨምር ከሆነ ጫናውን በቀጥታ የሚያሳርፈው ሸማቹ ላይ ነው፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት በተጠና ጥናት ከ1997 እስከ 2001 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ባንኮች ካበደሩት ውስጥ 52 በመቶ የሚሆነውን ከንግድ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለንግድ ሥራ በሚሰጥ ብድር ላይ የባንክ የወለድ መጠን ከፍ ማለቱ በገበያ ውስጥ የሚያሳርፈው ተጽእኖ ቀላል አለመሆኑን ያሳያል፡፡
ይህ ከሆነ ደግሞ ገበያው የባሰ በዋጋ ጭማሪ ግለት ተሟሙቆ ሸማቹን የሚፈታተነው መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ አንድ አስመጪ ዕቃ ለማስመጣት ከባንክ ለሚበደረው ብድር 12 በመቶ ወለድ ሲከፍል ቆይቶ አሁን ደግሞ የብድር ወለዱ ወደ 15 በመቶ እንኳን ቢያድግበት ሸማቹ ላይ ያንን ዋጋ ማሳረፉ አይቀሬ ነው፡፡
በመሆኑም አዲሱ መመሪያ ባንኮች ሊገጥመን ይችላል ከሚሉት ችግር ባለፈ ሸማቹ ላይ ሊያሳርፍ የሚችለው ጫና የበለጠ ይሆናል፡፡ አሁን ደግሞ ብዙ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ እየጨመረ ባለበት ወቅት የባንኮች የብድር ወለድ መጠን ሊጨምር ይችላል የሚለው ፍራቻ ገበያውን የበለጠ እንዳያጋግለው አሰግቷል፡፡
መንግሥት ይህንን ዕርምጃ ሲወስድ እንዲህ ዓይነት ክስቶችን እንዴት መቆጣጠር እንዳለበት ተዘጋጅቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የገበያ ሒደቱ ወይም ልምዱ እንደሚነግረን ባንኮች አትራፊ ለመሆን የተወሰነ ለውጥ ማድረጋቸው የማይቀር ከሆነ፣ የሚወስዱት ዕርምጃ በገበያ ውስጥ ተጽእኖ መፍጠሩ የማይቀር መሆኑን ነው፡፡
የዚህ መመሪያ መውጣት መንግሥት እንዳሰበው የባንኮችን አገራዊ አስተዋጽኦ ለማጉላት ጭምር ነው ቢባልም፣ ዕርምጃው ሌላ ቀውስ እንዳያመጣ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በመመሪያው ሳቢያ ሊከተሉ የሚችሉ ለውጦችንም ከስር ከስር በመከታተል፣ ቢቻል ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር በመወያየት መፍትሔ ማፈላለጉ የበለጠ ትኩረት ይሰጠው፡፡


