Thursday, Jun 20th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

‹‹በዓባይ ላይ የባለቤትነት መብት ይከበር የሚለው የተፋሰሱ የራስጌ አገሮች ጥያቄ ነው››

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

 

አምባሳደር ዶክተር ተውፊቅ አብዱላሂ

ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ከሱዳን ጠረፍ 40 ኪሎ ሜትር ላይ በምትገኘውና ቡምባዲ በምትባለው አካባቢ የሚገነባውን ታላቁ የሚሌኒም ግድብ የመሠረት ግንባታን መርቀዋል፡፡

ታላቁ ግድብ ከ78 ቢሊዮን ብር በላይ ይፈጃል ተብሎ ሲገመት፣ ሙሉ ወጪውም በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ይሸፈናል ተብሏል፡፡

ግድቡም የጣናን ሐይቅ እጥፍ የሚያክል ሰው ሠራሽ ሐይቅ የሚፈጥር ሲሆን፣ 5250 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል፡፡ ኢትዮጵያም ፕሮጀክቱን ለዓለም ይፋ ካደረገች በኋላ በተለይ ከግብፅ ከፍተኛ የሆነ ጫና እየተደረገባት ይገኛል፡፡ በዚህ መሠረትም ግብፅ የጦር ሠራዊቷ በተጠንቀቅ እንዲቆም እስከማለት መድረሷ ይነገራል፡፡ አምባሳደር ዶክተር ተውፊቅ አብዱላሂ አህመድ የቀድሞ በየመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ በ1992 ዓ.ም. በተደረገው ብሔራዊ ምርጫ ተመርጠው እስከ 1997 ዓ.ም. ድረስ የፓርላማ አባል ነበሩ፡፡ ከ1998 እስከ ጥር 1 ቀን 2003 ዓ.ም. ድረስ በየመን የኢትዮጵያ ባለሙሉሥልጣን አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡ አምባሳደር ዶክተር ተውፊቅ በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት በጠቅላላ ሕክምና ዶክትሬታቸውን ያገኙ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በአጥንት ጥገና ስፔሻላይዝ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም ከአምስተርዳም ስኩል ኦፍ ሎው በዓለም አቀፍ ሕግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ የሁለተኛ ዲግሪያቸውም የመመረቂያ ጽሑፍ በዓባይ ላይ ያጠነጠነ ነበር፡፡ አምባሳደር ዶክተር ተውፊቅ በዓባይ ወንዝና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሪፖርተር ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የአምስተርዳም የሕግ ትምህርት ቤት ሲማሩ ስፔሻላይዝ ያደረጉት በናይል ላይ እንደሆነ ገልጸውልናል፡፡ ለምንድን ነው በናይል ላይ ያተኮሩት?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- በአምስተርዳም የሕግ ትምህርት ቤት የፓርላማ አባል በነበርንበት ጊዜ እዚህ መጥተው ነበር የሚያስተምሩን፡፡ እናም ይህ የናይል ጉዳይ ብዙ አወዛጋቢ ነገሮች ያሉበትና ብዙ የአገር ጥቅሞች በተለያየ መልኩ የሚንፀባረቁበት ስለሆነ በናይል ላይ የምርቃት ጽሑፌን አደረኩ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በምረቃ ጽሑፍዎ ላይ በናይል ላይ ምን ያህል አተኮሩ? በናይል ተፋሰስ ላይ ምን ምን ነጥቦችን ዳስሰዋል?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- ናይል ቤዝን ኢንሽቲቭ የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ1999 በዳሬ ሰላም ነው፡፡ መሠረቱ (የመጀመያ ዓላማው) በናይል ተፋሰስ አገሮች መካከል ያለውን የመጠራጠርና የመጠላላት ስሜት በማጥፋት ለማቀራረብ ነው፡፡ በናይል ተፋሰስ ዙሪያ ትብብር ለመፍጠር ነው፡፡ ከዚያ በፊት መቀራረብ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡ ስለዚህ በምሑራን የተጀመረው ሐሳብን የማንሸራሸር ስለነበር አገሮቹ በጋራ ቢሠሩ ሁሉም ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ ስለዚህ ወደ ትብብር ሊያመጣቸው የሚችል አማራጭ ስለነበረ ስለሱ ማወቅ ስለፈለግኩ ነው በዚህ ላይ ያተኮርኩት፡፡

ሪፖርተር፡- የትብብር ማዕቀፉ ስምምነት አሁን ወደ ሙሉ ስምምነት ለመድረስ እየተቃረበ ነው፡፡ ምክንያቱም ስድስት አገሮች ፈርመውታል፡፡ አሥር ዓመት ያህልም ፈጅቷል፡፡ ለምንድን ነው አሥር ዓመት ያፈጀው?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- በመጀመሪያ ለማለት የፈለግኩት የተብላላና ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበት፣ ሁሉም የድርሻውን ሊወስድ የሚችልበት አቀራረብ በአገሮቹ መካከል አልነበረም፡፡ ሁለተኛ የግርጌ አገሮች በሌሎቹ የተፋሰስ አገሮች ላይ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ ለምን አሥር ዓመት ፈጀ ሲባል የነበረበት ችግርና የነበረበት አረንቋ ሲታይ አሥር ዓመት ረጅም ጊዜ ነው፡፡ አሁን ግን የደረስንበት ለመድረስ መክፈል የነበረብን መስዋዕትነት ነበር፡፡ ዝርዝር ሁኔታውን ስገልጽ ማየት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ እ.ኤ.አ በ1999 ዳሬ ሰላም ላይ ሲመሠረት አባል አገሮች ዘጠኝ ናቸው፡፡ ማለትም ዴሞክራቲክ ኮንጐ፣ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ ናቸው፡፡ በአገሮች መካከል የጋራ መብትን መሠረት ያደረገ ፍትሐዊ የውኃ ክፍፍልን መሠረት ያደረገ አቀራረብ ስለነበረ ነው አሥር ዓመት የፈጀው፡፡ ይህ ስብሰባ ከመደረጉ በፊት በአገሮች መካከል የቃላት ጦርነት ነበር፡፡ ወደ ትብብር የሚያመጣ ሳይሆን ወደ መናቆር፣ ልዩነትን በጣም እያሰፋ የሚሄድ አቀራረብ ነበር፡፡ ስለዚህ በትብበር መልክ ሁሉንም አዋጭ፣ ሁሉንም አገሮች ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚችል መልኩ ለማስተባበር የተደረገና የተከፈለ መስዋዕትነት ነው፡፡ እንደዛም ሆኖ በጥናቶችና በተለያዩ የማዘግያ ዘዴዎች ይህንን ያክል የሚቆይበት ምክንያት አለ፡፡ እንዳልኩት በናይል ተፋሰስ አገሮች መካከል የነበረው አሰላለፍ አሁን ያለውና በፊት የነበረው አንድ አይደለም፡፡ አገሮች ከጥቅማቸው አኳያ ፍትሐዊ ክፍፍልን አስመልክቶ አንድ አቋም ይዘው መውጣት የተቻለው በጣም አስቸጋሪ፣ ፈታኝና እህል አስጨራሽ ትግል ከተደረገ በኋላ ነው፡፡ እናም ይኼንን መግባባት ወደ አንድ ማዕቀፍ ማምጣት ተችሏል፡፡ በዚህ ብዙ የደከሙና የለፉ ግንባር ቀደም አገሮች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ በዋናነት ኢትዮጵያ ነች ያስተባበረችው፡፡  

ሪፖርተር፡- ግብፅና ሱዳን የማይስማሙበት ምክንያት ምንድን ነው?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- እ.ኤ.አ በ1929 ቅኝ ገዢው እንግሊዝና ግብፅ (ሱዳን በእንግሊዝ ሥር ነበረች) ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ሁለተኛ እ.ኤ.አ በ1959 ግብፅና ሱዳን ሲፈራረሙ ይኼንን ውኃ ሁለቱ ብቻ ነው መከፋፈል የፈለጉት፡፡ የዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ሕግ የተደረጉትን ስምምነቶች ተግባራዊ አላደረጉም፡፡ ይህም ማለት ስምምነቶቹ የተደረጉት የሌላውን አገር ጥቅም ባካተተ መልኩ አይደለም፡፡ አዲስ ስምምነት ማድረግ ደግሞ ድሮ ከሚደርሳቸው ድርሻ እንደሚቀንስባቸው ያውቃሉ፡፡ በሌላ በኩል የዓለም አቀፉ ሕግ አዲስ ስምምነት እንዲደረግ አያስገድድም፡፡ ለምን ስምምነት አለማድረጉ መዘግየቱ እነሱ ይጠቀሙበት የነበረውን ክፍፍል ምንም እንኳን ዕውቅና ባንሰጠውም፣ ሕጋዊ አይደለም ብንልም፣ እነሱ እየተጠቀሙበት ነበር፡፡ ስለዚህ ይኼንን አዲስ ስምምነት አለማድረግ ጥቅሙ የጐላ የሚሆነው ለእነሱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አዲስ ስምምነት እንዲደረግ አይፈልጉም ነበር፡፡

የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ የምንለው እ.ኤ.አ በ2010 እንዲፈረም ወደ መግባባት የተመጣው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ይኼንን ሰብረን ማውጣት የቻልነው ዘጠኙንም አገሮች ያካተተ አዲስ ስምምነት ለማድረግ በመስማማታችን ነው፤ ይኼ አዲስ ግኝት ነው፡፡ ምክንያቱም ዓለም አቀፍ ሕግ ባያስገድድም የተደረጉትን ስምምነቶች ላለመቀበል ከበፊቱ የተለየ የተቀየሰ ዘዴ ነው ማለቴ ነው፤ ለውጡም ይኼው ነው፡፡ ስለዚህ ግብፅና ሱዳን ዋናው የማይፈልጉበት ምክንያት በተቻለ መጠን ገፍቶ የመጣውን የፍትሐዊነት ክፍፍል መቋቋም ስላልቻሉ እሺ ብለዋል፡፡ ግን በስምምነት ደረጃ ሲደረስ ላለመፈረምና ለማዘግየት የተለያዩ ዘዴዎችን ሲጠቀሙ ነበር፡፡ ስለዚህ ለሁሉም ክፍት ተደርጐ አብዛኛው አገር የተቀበለው ስምምነት ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ ከዘጠኙ አገሮች ስድስቱ የተቀበሉት ከሆነ እ.ኤ.አ በሜይ 14 ቀን 2011 ላይ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ የምንለው ፊርማው ይጠናቀቃል፡፡ ከ11 ዓመት አድካሚ ጥረትና ሙግት በኋላ የተገኘ ድል ነው፡፡ ይህንን ለማኮላሸትም የተለያዩ ዘዴዎችን ሲጠቀሙ ነበር፡፡ አንደኛ በአገሮች መካከል የተደረሰውን መግባባትና መስማማት ለማዛነፍ፣ ሁለተኛ ለማጥላላት፣ ሦስተኛ በግብፅና በሱዳን ላይ ያነጣጠረና እነሱን ሊጎዳ የሚችል አድርገው ለሕዝባቸውም፣ ለሌላው ሲያሳውቁና የተፋሰሱ አገሮችንም ለመከፋፈል ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ ስምምነቱ ሲደረግ መጀመሪያ የፈረሙት አራት አገሮች ብቻ ስለነበሩ፣ ‹‹ይኸው አራት አገሮች ብቻ ናቸው የፈረሙት›› ብለዋል፡፡ ለአንድ ዓመት ክፍት ነው የሚሆነው እ.ኤ.አ ሜይ 13 ቀን 2011 ድረስ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ እንዳይፈርሙ የኮንጐን ፕሬዚዳንት፣ የኬንያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ግብፅ በመጥራት ለማግባባት ሞክረዋል፡፡ የእነሱም ታላላቅ ልዑካን ወደነዚህ ወደ ተፋሰሱ አገሮች ሄደው ለማግባባትና ከዚህ ስምምነት እንዲታቀቡ ወይም ራሳቸውን ወደኋላ እንዲመልሱ ጥረት እያደረጉ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለንበት ሁኔታ በተፋሰሱ አገሮች ውስጥ ያሉ ሁለት ቡድኖች እንዳሉ ማየት እንችላለን፡፡ የግርጌውና የራስጌው አገሮች ፍጥጫ ነው ልንለው እንችላለን?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- በእርግጥ በዋነኛነት ለምሳሌ ክፍፍሉም ላይ ቢሆን ዋናው ዓመታዊ የውኃው መጠን 85.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ነው፡፡ ምንም ተቀባይነት ባይኖረውም ሁለቱ አገሮች ያደረጉትን ስምምነት እኛም ሌሎችም አንቀበለውም፡፡ በይፋም ተነግሯል፡፡ እንደዚህም ሆኖ ሁለቱ ድርሻቸው ሦስት ለአንድ ነው፡፡ ሱዳን ከራሷ ድርሻ አሳልፋ የተወሰነውን ትሰጣለች፡፡ እናም ሁለቱን በእኩል ልናያቸው አንችልም፡፡ ግን ሁለት ጐራ እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ የግርጌውና የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የተለያየ አቋም አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ፖለቲከኞች የሚሉት አለ፡፡ ኤክስፐርቶችም የሚሉት አለ፡፡ ከኬንያ፣ ከግብፅ፣ ከሱዳን የተውጣጡ ኢንጂነሮች አሉ፡፡ አንዴ አነጋግሬያቸው ነበር፡፡ ውኃው ለሁሉም ይበቃል፤ ምንም ችግር የለም ይላሉ፡፡ እንዲያውም አንደኛው ግብፃዊ ፖለቲከኞቹ የሚያወሩትን አያውቁም ነው ያለኝ፡፡ እኛ ነን ትክክለኛውን ነገር የምናውቀው ብሎኛል፤ ይህንን ሕዝቡ በምን መልኩ ነው ማወቅ ያለበት?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- ሕዝቡ ማወቅ ያለበት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ሕግ አለ፡፡ ከዓለም አቀፉ ሕግ ደግሞ ያንን ተንተርሶ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ አሁን ለፊርማ የቀረበና በስድስት የላይኛው ተፋሰስ አገሮች የተፈረመው አለ፡፡ ወንዙ የሚያልፍባቸው አገሮች ሁሉ በዚህ ውኃ መጠቀም መብታቸው ነው፡፡ ይኼ አንቀጽ አምስት የዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ሕግ ነው፡፡ በዚህ በትብበር ስምምነቱ አንቀጽ አራት ይሆናል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ሲጠቀሙ ሌላውን አገር በእጅጉ የማይጐዳ መሆን አለበት ይላል፡፡ ይኼ አንቀጽ ሰባት ነው፡፡ የዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ሕግ በትብብር ስምምነቱ ማዕቀፍ አንቀጽ አምስት ነው፡፡ ይኼንን ያጣጣመ አካሄድ ነው መሆን ያለበት፡፡ ሁሉንም ሊጠቅምና ሊያሳትፍ በሚችል መልኩ መሆን አለበት፡፡ በፊት የነበረውን ስምምነት የምንቃወመው (1929 እና 1959) ሌሎቹን አስወጥቶ ለሁለቱ አገሮች ብቻ ነው መብት የሰጠው፡፡ ስለዚህ ይህ በሆነበት ሁኔታ ልንቀበለው አንችልም፡፡ የውኃ አጠቃቀም ድርሻ ለማን ይሁን የሚለው ይኼ በስሌት የሚሆን ነው፡፡ መጀመሪያ ባለመብትነት ሊከበር ይገባል፡፡ ከዛ በኋላ ውኃው ይበቃል አይበቃም ለሚለው የተሰሉ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ውኃው 85.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው አልን፡፡ ከዛ ውስጥ በትነት የሚሄደው እስከ 10 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግድብ ሲሠራለት ትነቱ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ሁለተኛ ሱዳን ላይ መሬት ውስጥ የሚሰርገው ውኃ ከ2-6 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ነው፡፡ ይህንንም ለማስቀረት በ1970ዎቹ ፕሮጀክቶች ተጀምረው ነበር፡፡ ሱዳን ውስጥ በነበረው የእርስ በርስ ግጭት ቁሟል፡፡ ሦስተኛ እነዚህ በግርጌ ያሉት በተለይ ግብፅ ውኃ በጣም የሚጠቀሙ አዝርእቶችንና ተክሎችን ማብቀል የለባትም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ብዙ ውኃ ይፈልጋሉ፤ እነዚህን ከማብቀል ይልቅ ከሌሎች ከተፋሰስ አገሮች ኢምፖርት ቢያደርጉ ይመረጣል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ መሠረታዊ የሆኑ ናቸው፡፡ ከዛ በኋላ ለማ ምን ያህል ይደርሰዋል የሚለው አንደኛ የሕዝብ ብዛት፣ ሁለተኛ አማራጭ (ዝናብ፣ ሌላ ወንዝ)፣ ሦስተኛ በዚህ የሚገለገለው ሕዝብ አስተዋጽኦ፣ እዚህ ወንዝ ላይ ያለው ድርሻ ግምት ውስጥ ይገባል፡፡ እነዚህ ቴክኒካዊ የሆኑ ነገሮች ናቸው፡፡ ግን መጀመሪያ መብትን ማስከበሩ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን ለጋራ ጥቅም ግንኙታቸውን ሊያጠናክር የሚችል ስምምነት አድርጐ መውሰድ ይገባል እንጂ መናቆሪያና የእርስ በእርስ ንትርክ የምንፈጥርበት አይደለም፡፡ ለልማት ሁላችንም በዚህ መጠቀም አለብን፡፡ የቴክኒክ ሰዎች ሲጀመርም ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት በዚህ ላይ ነው፡፡ እነዚህ ዕውቁቱ ያላቸው ሰዎች በሐሳብ የማቀራረብና ረጅም ጊዜ የፈጀውን ይህንን መድረክ ለመፍጠር ነው፡፡ እ.ኤ.አ ከ1999 ጀምሮ ፖለቲከኞች መግባባትና መቀራረብ የጀመሩት በየአገራቸው ባሉት የዚህ ዓይነት የትብብር መድረክ መፈጠር አለበት በሚሉት አማካይነት ነው፡፡ የባለሙያዎች ድርሻ ቀላል አይደለም፡፡   

ሪፖርተር፡- ማን ምን ያህል ይደርሰዋል የሚለውን ለመወሰን ኃላፊነቱ የማን ነው?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- በኋላ የሚወሰን ነው፡፡ ለምሳሌ የትብብር ስምምነቱን አንዱ ይኼንን ሊያስተዳድር ይችላል፡፡ አሁን ለጊዜው ያለው የናይል ተፋሰስ ኢንሼቲቭ ነው፡፡ ያንን ወደ ናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ነው የሚቀይረው፡፡ በስምምነቱ መሠረት ይኼ ተቋም ነው የሚያስተባብረው፡፡ በእሱ ሥር የተለያዩ ባለሙያዎችን ያካተተ አደረጃጀት ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በትብብር ማዕቀፉ ስምምነት ውስጥ አንቀጽ 14 ነው ግብፅንና ሱዳንን ቅር ያሰኛቸው፤ ስለውኃው አጠቃቀም የሚገልጽ ነው እሱ፡፡ እኩል ድርሻ የሚለውን ትንሽ ቢያብራሩልን? አሁን ኢትዮጵያ ልትገነባው ያሰበችው የሚሌኒየም ግድብ እኩል ክፍፍል የሚለውን አያዛበውም?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- ሁለቱን ጐራዎች የሚያጣላው እሱ ነው፡፡ እነሱ የሚፈልጉት ቀደም ሲል የተፈረሙት መብቶቻቸው የማይነኩ፣ የማይለወጡ፣ ታሪካዊ መብቶቻቸው ናቸው፡፡ ጥያቄው እነዚህን ባካተተ መልኩ አዲስ ስምምነት ይፈረም ነው፡፡ ሁለተኛ ፍትሐዊ ሲባል ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በእኩልነት የባለቤትነት መብት ሊኖራቸው ይገባል ማለት ነው፡፡ ማን ምን ያህል ይጠቀም በኋላ የሚመጣ ነገር ነው እንጂ፣ በዓባይ ላይ የባለቤትነት መብት ይከበር የሚለው የተፋሰሱ የራስጌ አገሮች ጥያቄ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ሁሉም መሠረታዊ የሆነ መጠቀም መብቱ ነው፡፡ ግን ሌላውን በማይጐዳና በሚያመች ሁኔታ ነው ሲባል፣ ይኼን መብትና ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ የሚሠሩ ነገሮች አሉ፡፡ ምክንያቱም በጋራ ተጠቃሚ የሚኮንበትም ነው፡፡ ግድቦቹ ሲሠሩ ይዘዋቸው የሚሄዱት ደለሎች ይቀንሳሉ፡፡ የእኛንም ደለል እንዲሞላው አንፈልግም፡፡ ስለዚህ ስምምነቱ ውስጥ እነዚህን ደለሎች የምንቀንስባቸው፣ የደን ማልማት ፕሮጀክቶች ወይም ሌላ ጥፋት ሊያስከትሉ የሚችሉትን በጋራ ወጪን በመጋራት መሠራታቸው ተገቢ ይሆናል፡፡ ግን ዋናው መሠረቱ ሁሉም ባለቤትና እኩል መብት ያለው መሆኑን የማይሽር ነው፡፡ መብት መሆኑን አስረግጠን እንናገራለን፡፡ አፈጻጸሙ ላይ ሕጉ ላይ ነው ወደኋላ የሚሉት፡፡ አሥርና አሥራ አምስት ዓመት መፍጀቱ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ የሄድንባቸው፣ የተራመድንባቸው ሰንካላና የማደናገሪያ፣ የጊዜ ማራዘሚያ ዘዴዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ ግን ለጥረታችን ምስጋና ይግባውና፣ ለአስተዋይና የተጠና የተሰላ አቀራረብ ከምንም በላይ እዚህ ደረጃ ደርሰናል፡፡ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች አንድ አቋም ይዘዋል፡፡ ግብፅና ሱዳንም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር እነሱም በእኩልነት ተጠቃሚ ስለሚሆኑ፣ በባለቤትነት የማታዩበትም ስለሆነ፣ ውኃውም የሚበቃንም ስለሆነ፣ ቢዘገይም እነሱም የስምምነት ማዕቀፉ ፈራሚዎች ይሆናሉ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ልትገነባው ያቀደችው አዲሱ ግድብ መጠኑ የጣናን እጥፍ የሚያክል አርቲፊሻል ሐይቅ ይኖረዋል፡፡ ይህንን ሐይቅ ለመሙላት ደግሞ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፡፡ በተለይ ደግሞ ግብፅ የዓባይን ውኃ ለአንድ ቀን ማጣት አትፈልግም፡፡ አርቲፊሻል ሐይቁ በሚሠራበት ወቅት የግብፅና የሱዳን ተፅዕኖ ምን ይሆናል?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- ወደ 62 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩቢክ ውኃ ነው የሚይዘው፡፡ በአንድና በሁለት ዓመት ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ ውኃ የሚወስድ ነው፡፡ የዓባይን ፍሰትም ሙሉ ለሙሉ የሚዘጋ አይደለም፡፡ ሁለተኛ በእነሱ ላይ ሊያመጣ የሚችለው በተለይ ሱዳንን ጐርፍ በየጊዜው ያጠቃታል፡፡ ስለዚህ ይህንን ይቀንስላታል፡፡ ግብፅ ደግሞ የራሷ የሆነ የተከማቸ ሐይቅ አላት፡፡ እርግጥ ፍሰቱ በተወሰነ ደረጃ ቢቀንስም ውኃው ግን መድረሱ አይቀርም፡፡ ምንም ሊያስከትል የሚችለው የውኃ እጥረት ግን የለም፡፡

ሪፖርተር፡- የግብፅ መንግሥታት ከድሮ ጀምሮ የሚያነሱት ነገር አለ፡፡ የዓባይ ውኃ ተነካ ማለት ግብፅ ተነካች ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ግብፅ የዓባይ ስጦታ ነች እየተባለ የሚነገር ነገር አለ፡፡ በየቀኑ ምንም ውኃ እንዲቀንስ አይፈልጉም፡፡ በተወሰነ ደረጃ እኛ ማቆር ብንጀምር ለእነሱ ሰላም ይሰጣቸዋል ወይ? ውስጣቸውስ ይቀበለዋል ወይ? ወደ ሌላ አዝማሚያ ሊወስዳቸው አይችልም ወይ?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- ስጋቱ ይገባኛል፡፡ የዚህ አሥር አሥራ አንድ ዓመት የፈጀው የናይል ተፋሰስ አገሮች ስምምነት አንዱ ጥረት ይኼ ነው፡፡ ቢያንስ በምሑራኑ ላይ፣ ቀጥሎ በፖለቲከኞቹ ላይ፣ ቀጥሎ በሕዝቡ አካባቢ በጋራ የሚያገኘውን ጥቅም ማስረዳት ተሞክሯል፡፡ ሁለተኛ መብትን ሊያስረዳና ሊገልጽ በሚችል መልኩ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ተደርጓል፡፡  ስለዚህ እኛም እንደ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች እነዚህን በተለያዩ ሁኔታዎችም መግለጽ መቻል አለብን፡፡ በሌላው ዓለም ለግብፃውያን ሌላ አረንቋ ሆኖ ያለው ሁኔታ፣ በተለይ በሚዲያ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ግብፅን እንደመጉዳት ተደርጐ ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ምሑራን በተለያዩ ሚዲያዎች መግለጫዎችን ይሰጣሉ፡፡ የስምምነት ማዕቀፉ ፊርማ በአንድ ዓመት ያልቃልና ይሄን ልናደርግ ይገባል፡፡ ለዓለም አቀፍ በልማት አጋሮቻችንን ማሳወቅ፣ የልማት አጋሮቻችን ላይ ያለውን ተፅዕኖና ወዳጅ አገሮቻችን ላይ ያለውን ግፊት ሰብረን መውጣት አለብን፡፡ በዋነኝነት በዓለም አቀፍ መድረኮች በእኛ ብቻ ሳይሆን፣ የላይኛው ተፋሰስ አገሮችን ባካተተ ሁኔታ ይህን መቆጣጠር የምንችለው ራሳችን ነን፡፡ ምክንያቱም ግብፆች በፌስቡክ ከዓመት በፊት ጀምሮ የናይል የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ መፈረም ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በጣም እየተንቀሳቀሱ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ አገራዊ ጥቅም አመርቂ ራዕይ ነውና ስለዚህ እኛ የምንንቀሳቀሰው የተወሰኑ አገሮችን ለማጥቃት ሳይሆን፣ ሕዝቦችን ለማጣላት ሳይሆን፣ ለመበደል ሳይሆን ለጋራ መብቶች መከበር ነው፡፡ የእኛም ሕዝብ መታየት አለበት፡፡ 360 ሚሊዮን ሰዎች በላይኛው የተፋሰሱ አገሮች በድርቅና በረሃብ እየተቸገሩ እያለ በዚህ ውኃ መጠቀም አትችሉም ማለት አግባብነት የሌለው፣ ፍትሐዊ ያልሆነና ይህን ሊቀበል የሚችል በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊኖር አይችልም፡፡ አይገባምም በሚል ይህንን መልዕክት ማስተላለፍ መቻል አለብን፡፡   

ሪፖርተር፡- ብዙ ጊዜ ዓባይን ለመጠቀምና ፍትሐዊ ክፍፍሉን በተመለከተ ሁሌም የሚሰማው እዚህ አገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደካማ የሕዝብ ግንኙነት ምክንያት እንደዚህ ዓይነት ነገሮች ሲደመጡ አይሰሙም፡፡ ይኼን የፍትሐዊ ክፍፍል ጉዳይ በኢንሽየቲቩ ካልሆነ በቀር ኢትዮጵያ ለብቻዋ 86 በመቶ ውኃ ለዚህ ተፋሰስ እያዋጣች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሲናገሩ የዓለም ጆሮ ያደምጣል፡፡ ከዛ ውጪ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ የለም፡፡ በዚህ ዓይነት እንዴት ነው ኢትዮጵያ መብቴ ነው ብላ የምትከራከረው? ለዓለም ማስረዳት የምትችለው? የኢትዮጵያ የሕዝብ ግንኙነት በጥቃቅን ነገሮች ውስጥ ጊዜውን ከማባከን ውጪ ወጣ ብሎ ሲንቀሳቀስ አይታይም፡፡

አምባሳደር ተውፊቅ፡- ጥረታችንና አካሄዳችን ይኼን ይመስላል፡፡ ሁለተኛ ኢትዮጵያውያን እሴቶቻችን ናቸው፡፡ እነሱ በሚኖሯቸው አጋጣሚዎች ባላቸው ግንኙቶች፣ በተለያዩ ጥረቶች ጭምር በተለያዩ መድረኮች ማስረጽ መቻል አለብን፡፡ በመሆኑም የሁላችንም ተሳትፎ ሊኖር ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ግድቡ ከተወራ በኋላ ግብፅ ቁጡነትን ነው እያሳየች ያለችው፡፡ ሱዳን ስምምነቱ ውስጥ ልትገባ የምትችልበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንዳንዴ የማሳመን ሁኔታዎችም አሉ፡፡ ይኼ ነገር ትክክል ነው ወይ? ማድረግስ እንችላለን?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- ፉክክርና ፍጥጫ ነው የያዝነው እያልን ከእነሱ በበለጠ መሥራት አለብን፡፡ እኛን ሊተባበሩን የሚችሉትን ወገኖች ሁሉ ማሳመንና አቅማችንን በተወሰነ አካባቢ ብቻ ሳይሆን ሰፋ አድርገን ማንቀሳቀስ ይገባናል፡፡ ማንም በጎ አመለካከት ያለው ኢትዮጵያዊ ለዚህ ዓላማ የማይቆም ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ስለዚህ ያንን ጥረት መጠቀም መቻል አለብን፡፡ ሁለተኛው መድረኮች መከፈት መቻል አለባቸው፡፡ ሦስተኛ ይኼ ጥረት የእኛ ብቻ ሳይሆን የላይኛው ተፋሰስ አገሮችም ሊደግፉትና በዚሁ ጥረት ውስጥ ሊገቡ ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌ የሱዳንን ሪፈረንደም አስመልክቶ የነበሩት ስምምነቶች ላይ ለውጥ ያመጣል የሚል ግምት ነበር፡፡ ይኼ ትርጉም አለው፡፡ ይኼ ትርጉም የሚኖረው ይህንን ስምምነት ዕውቅና ሰጥተን ስንቀሳቀስ ነው፡፡ የነበሩትን ስምምነቶት ዕውቅና ባልሰጠንበት ወቅት ሌላ አገር መጣ አልመጣ ለውጥ አያመጣም፡፡ ሁለተኛ የግብፅ አካላት አዲሱን የኃይል ማመንጫ የሚሌኒየም ግድብ አስመልክቶ ጥናትና መረጃዎች እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ይኼ የሚያሳየው በዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ሕግ ይህን ማድረግ የሚቻለው ማለትም መረጃ መስጠትና መለዋወጥ የሚቻለው በአንድ ዓይነት ስምምነት ስትገዛ ነው፡፡ ስምምነቶች ሲኖሩ ይህን ነገር ለማድረግ ያስገድዳሉ፡፡ ይኼ ጥያቄ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን እንዲፈርሙ ከሚገፋፋቸው ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ መብት ሊሆን የሚችለው በዚህ ስምምነት ውስጥ ሲኖሩ ነው፡፡ እናም ይህን መረጃ መስጠትና ማሳመን አለብን፡፡ በ60 ቀናት ውስጥ መልስ ማግኘት መቻል አለብን፡፡ በ60 ቀናት ውስጥ መልሱን የማይነግሩን ከሆነ ግንባታውን እንቀጥላለን፡፡ አካሄዱ ይኼ ነው፡፡ መሠረቱ ስምምነቱ ነው፡፡ ስለዚህ ዞረው መምጣት አለባቸው፡፡ የማይታለፍና ሌላ አማራጭ የሌለው ሒደት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስምምነቱን ኮንጐ አልፈረመችም፡፡ ግብፅ ሰሞኑን የማሳመን ሥራ እየሠራች ነው፡፡ ታላላቅ ሰዎችን ወደ ሱዳንና ኡጋንዳ ልካለች፡፡ ሁለት ሦስተኛው አገሮች ቢፈርሙም የሚቀሩ ቴክኒካዊ ነገሮች አሉ፡፡ ግብፅ ከዚህ በኋላ ይኼን የማፍረስ አቅም አላት? ሊጨናገፍ ይችላል? የሱዳንስ ጉዳይስ? ደቡብ ሱዳን እንደ 10ኛ አገር በምትገባበት ጊዜ ያለው ሁኔታ እንዴት ይሆናል?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- መጀመሪያ ለምን 11 ዓመት ፈጀ ስንል መነሻው ከዜሮ የነበረና ከመቀራረብ፣ ከመነጋገርና ከመደጋገፍ በታች ተነስቶ የተሠራ በመሆኑ ነው፡፡ አሁን የተገነባው የመቀራረቡ፣ የመብት ጉዳይ፣ የመደጋገፍ፣ እኔ ነኝ ባይነት፣ እኔ ባለቤት ነኝ ብለው ሁሉም አገሮች፣ በተለይ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች አንድ አቋም የያዙበትና በጠንካራ መሠረት ላይ የተደረሰ ስምምነት ነው፡፡ በቀላሉ ሊናድ የሚችል አይደለም፡፡ እንደዛም ሆኖ ግብፆች ባለሥልጣናትን ለማማለል የሚያደርጉት ጥረታቸው አይቆምም፡፡ ግን እዚህ ስምምነት ደረጃ ላይ የደረስነው አድካሚ ነገሮችን አልፈን ነው፡፡ የላይኛው አገሮች በአስተማማኝ ለእኛ ሲሉ ሳይሆን ለራሳቸው መብት እየተንቀሳቀሱ ስለሆነ ይናዳል ብዬ ግምትም፣ ጥርጣሬም፣ ስጋትም የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በግብፅ የነበረው ብጥብጥ ባለሥልጣናቱን ናይል ላይ የነበራቸውን ትኩረት እንዲዘነጉ አድርጓቸው ነበር?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- አይ እንዲያውም ያለውን ውጥረት ለማስተንፈስ ምክንያቶች ነበር የሚፈልጉት፡፡ እናም አዘናግቷቸዋል ማለት አንችልም፡፡

ሪፖርተር፡- የግድቡ መሠረት ሲወጣ ግብፅ ብጥብጥ ላይ ነበረች፡፡ ይኼ ብጥብጥ ትኩረታቸውን አለወጠውም ማለት ይቻላል?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ይኼ የጊዜ ስሌት ካልሆነ በስተቀር እ.ኤ.አ 2011 የትብብር ስምምነቱ ማዕቀፍ መጠናቀቂያ ጊዜ ነውና የዘወትር አጀንዳቸው ነው የናይል ጉዳይ፡፡ ምክንያቱም ይኼ ጉዳይ የሚመራው በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ የተዘናጉበት ጉዳይ አይደለም፤ ሊዘናጉበት የሚችሉበትም አይደለም፡፡ ካላቸው አሉታዊ አካሄድ ማለት ነው፡፡ ሆነም እኛ የዓለምን ኅብረተሰብ፣ የግብፅን ሕዝብ፣ የዓረቡን ዓለም የማሳወቅና የማሳመን ተግባር መሥራት አለብን፡፡ ለዚህ ሚዲያ አጠቃቀማችንን፣ ምሑራንን መጠቀምን፣ ዓለም አቀፍ መድረኮችን በዚህ ዙሪያ ማግኘት አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- ታላቁን ግድብ አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲናገሩ ለትንሹ ስጋት ብለን እንቅልፍ አጥተን አናድርም ብለዋል፡፡ ከወደ ግብፅ ደግሞ አንዳንድ የሚደመጡ ነገሮች አሉ ስጋትን የሚያጭሩ፡፡ ሁለቱን እንዴት ማስታረቅ እንችላለን?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- ስጋት አይኖርም ሳይሆን የስጋት መጠኑ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ሁለተኛ ይህንን ጥረት ማሰናከል የግብፅ ባለሥልጣናት ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይህንን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወይም በዓባይ ወንዝ የተጠቃሚነት መብት የሚያነሱትን ለማስበርገግ የሚያደርጉት አንዱ ከፍተኛ የተደራጀ የተጠናከረ የጦር ኃይል መገንባት ነው፡፡ በእነዚህ የሚያደርጓዋቸው እንቅስቃሴዎች አሉባልታዎችና ብዥታዎችን ለመፍጠር ነው፡፡ ስጋቱ በጣም ትንሽ ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግብፅን አሁን እያስተዳደሩ ያሉት ወታደሮች፣ ወታደሮቻቸው በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አዘዋል የሚል ከግብፅ ሚዲያዎች አካባቢ እየተናፈሰ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ስጋቱን አሳንሶ ማየት ይቻላል?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- ነባራዊውን ሁኔታውን ለማሳየት ነው እንጂ አሳንሶ ለማየት አይደለም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ በሠለጠነው ዓለም የዚህ ዓይነት አጉራ ዘለል አካሄድ ማንም ያደርጋል ብዬ አላስብም፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግጋትንና የዓለም አቀፍ ትኩረትን ያገኘ ነገር ነውና ዝም ተብሎ በአንድ አገር ላይ ቀጥታ ወረራ ይደረጋል የሚል እምነት የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- ግብፅና ሱዳን እስከአሁን አልፈረሙም፡፡ አንፈርምም ብለው አቋማቸውን አሳውቀዋል፡፡ ነገር ግን ቅድም እንዳሉት እርስ በርሱ የሚጋጭ ነገር ያደርጋሉ፡፡ ጥናቱ ይሰጠን ይላሉ፤ እንደዚሁ ይቀጥላሉ ብለው ያምናሉ?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- አንድ ማስተካከያ ምንድን ነው፡፡ በትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱ ያልፈረመ አገር አይደለም ያልኩት፡፡ ይኼ የዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በተመለከተ ስምምነት በተደረገባቸው፣ አንድ የተፋሰስ አገር ማንኛውንም ፕሮጀክት ሲሠራ ያገባኛል የሚል አገር ማብራሪያ መጠየቅ፣ ጥናቱን መጠየቅ መብቱ ነው፡፡ ጥናቱን ጠይቆ ወይም የሚሠራው ነገር እንደሚፈጸም ተገልጾለት መልስ ያልሰጠ ከሆነ የፈለግከውን ታደርጋለህ፡፡ ይህንን ሲጠይቁ ስላልፈረሙ ሳይሆን ስምምነት በሌለበት ይኼንን ነገር መጠየቅ የተገላቢጦሽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስምምነቱን ሳይጠይቁ መፈረም ይችላሉ?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- በአንድ በኩል ስምምነቱ በሚሰጣቸውን መብቶች ለመጠቀም ይፈልጋሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ስምምነቱ በሌለበት ሁኔታ ይጠይቃሉ ማለቴ ነው፡፡

 

ሪፖርተር፡- መንግሥት ሰሞኑን በኤርትራ ላይ እያነሳ ያለው ነገር ምናልባት ግብፅ ነገር ብትፈልግ ኤርትራን ትጠቀምባታለች፤ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ነው የሚል ስጋት ኅብረተሰቡ ውስጥ አለ፡፡ ስምምነቱን ያልፈረመችው ሱዳንም እንደዚሁ ለግብፅ መንደርደሪያ ትሆናለች የሚሉ ስጋቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሁለት አገሮች በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ እያሉ ግብፅን በርቀት ላይ ነች ብለን ማሰብ እንችላለን?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ግልፅ አድርገውታል፡፡ በቀጥታ የግብፅ መንግሥት ኢትዮጵያን ይወራል የሚል ስጋቱ በጣም ያነሰ ነው የሚመስለኝ፡፡ ግን በተደራቢነት ትልቁ ስጋታችን የሻዕቢያን መንግሥት በመንደርደሪያነት በእኛ ላይ ሊያዘምት ይችላል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የሻዕቢያው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ በተደጋጋሚ የግብፅና የተለያዩ አገሮችን ሲጐበኝ ነበር፡፡ ዋናው የጉብኝቱ ምክንያቱ እነዚህን ነገሮች ለማደራጀት እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ይህንን ነው ለማሳሰብ የፈለጉት፡፡ ዋናው ሐሳብ የሚመነጨው በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ በነጭ ለባሾቻቸው በሻዕቢያና እነሱን በመሰሉት ነው፡፡ ምክንያቱም አልሸባብና ሌሎቹም የሚያደርጉትና ሊያደርጉት የሚችሉት ይህንን ነው፡፡ በሱዳን በኩል ያለውን ስናይ በተለይ ሪፈረንደሙን በተመለከተ ኢትዮጵያ የወሰደችው ገለልተኛና የጉርብትና አቋም ነው፡፡ የሰሜኑንም የደቡብንም እምነትና ድጋፍ አግኝታለች፡፡ እናም በሱዳን በኩል ባንዴ አጣዳፊ የሆነ ነገር ይደርስብናል ብለን አንሰጋም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያና በኤርትራ በነበረው ግጭት አማካይነት ወደ ጦርነት ሲገባ የተሳሳተ ስሌት ነበር የሚሉ አሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት በደንብ ያልተጠኑ ነገሮች ክፍተት ይፈጥራሉ የሚል ስጋት አለ፡፡

አምባሳደር ተውፊቅ፡- ስጋቱ እንዳለ ይገባኛል፡፡ መንግሥታችን በቂ ትንተና፣ በቂ ዝግጅት፣ በቂ ክትትል እያደረገ ስለመሆኑ አልጠራጠርም፡፡ ኢትዮጵያን የመበጥበጥ ሁኔታ ሊመጣ የሚችለው ዋናው ስጋቱ ከሻዕቢያና ከእሱ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ የሚያደርጉት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል እነፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ናይልን ብትገድብ የዓይናችን ብሌን ነው በሚል ብዙ ነገር አውርተው ነበር፡፡ ያኔ ኢትዮጵያ ምንም አላደረገችም፣ ጥናቶች ብቻ ይጠናሉ፤ አሁን ግን ኢትዮጵያ እንገድባለሁ አለች፡፡ ይኼ ነገር ያኔ የነበረውን ስጋት አያባብስም?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- መንግሥታችን እገድባለሁ ሳይሆን ግድብ እሠራለሁ ነው ያለው፡፡ የኃይል ማመንጫ ግድቦችን እሠራለሁ ነው ያለው፡፡ ይኼ መብታችንም ነው፤ አካሄዱ ጤናማ የሆነ፣ ግጭት የማያስነሳ ፍትሐዊ አካሄድ ነው፡፡ ግን ይኼን ተከትሎ ይህንን ጥረት ለማስለወጥ የማይደረጉ፣ የማይቧጠጡ ነገሮች የሉም፡፡ ከብዙ ድካምና ውጣ ውረድ በኋላ ይኼ ግድብ ሊገነባ ስምምነት የተደረሰበት መሠራቱ የግድ በመሆኑ ነው፡፡ የአንድ አገር ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የአካባቢው አገሮች በናይል ተፋሰስ ያሉ የላይኛው የናይል ተፋሰስ አገሮች ስጋቱ እንዳላቸው ይገባኛል፡፡ የስጋቱን መጠን በተመለከተ ግብፅ ቀጥታ ወረራ ታደርጋለች የሚለው በጣም ትንሽ ነው፡፡ ግን የአካባቢው አገሮች በተለይም ደግሞ ሻዕቢያን ተጠቅማ፣ ምክንያቱም ኢትዮጵያን ሊጎዳ የሚችል ማንኛውንም ነገር ከማድረግ እንደማይቆጠብ በማወቅ ግብፅ እንዳዘጋጀችው፣ በማስፈራሪያም፣ በማስጠንቀቂያም መንቀሳቀሱ እንደነበር በግልጽ ይታወቃል፡፡ መንግሥት ይህን በቅርብ ይከታተለዋል፣ በቂ ዝግጅት አድርጐበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የግብፅ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሥራት ከተንቀሳቀሰች ወዲህ ባለሥልጣኖቻቸውን እየጐተጐቱ ነው፡፡ አንደኛ ከዚህ በስተጀርባ ያለችው እስራኤል ስለሆነች፣ እስራኤል ደግሞ በአሁኑ ወቅት በተፈጠረው ሁኔታ ስጋት ስላላት የተዳከመች ግብፅን ነው ማየት የምትፈልገው ስለዚህ እኛ ከኢራን ጋር ግንኙታችንን ከፍ ማድረግ አለብን፡፡ በአሜሪካኖች ሥር ሆነን ያተረፍነው ነገር የለም፤ ዞሮ ዞሮ ሙባረክም ቢሆኑ ግብፅን ሽባ እንድትሆን አድርገዋታል የሚሉ አሉ፡፡ ከዚህ አንጻር እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን የማየት ነገር በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አለ?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- በዚህ መልኩ ሳይሆን የናይል ተፋሰስ አገሮች አሁን ካለበት የናይል ተፋሰስ ስምምነት ወደ ቋሚ ኮሚሽን ማድረስና የሁሉን አገሮች መብት ባከበረ መልኩ፣ ዘላቂነት ባለው መንገድ ሊያስተባብር የሚችል የትብብርና የስምምነት ማዕቀፍ እንዲፈረም ሲሉ፤ ግብፆች አንዱ ዘዴያቸው ማስፈራራት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ ሆን ብለው የተሳሳተ ግንዛቤ ለሕዝባቸውና ለአካባቢው አገሮች በተለይ ኢትዮጵያ የግብፅን ሕዝብ በረሃብ ለመቅጣት ተዘጋጅታለች ይላሉ፡፡ በሌላ መልኩ ስናየው ግብፅ ከእስራኤል ጋር በጣም የቀረበ ግንኙነት ያላትና ይህንን ውኃ ለመጠቀም ዳር ዳር እያሉ ያሉት ሁለቱ አገሮች እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ እ.ኤ.አ በ1977 የእስራኤል ባለሥልጣናት ሳዳትን ለማስፈቀድ ግብፅን በጐበኙበት ጊዜ፣ በጊዜው ለነበሩት ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን ውኃ እዚህ አድርሰነዋል ብለዋቸዋል፡፡ የናይል ወንዝ ግብፅ ውስጥ የሚጓዝበትን መንገድ ሁሉ አስተው ወደኋላ ወደ መቶ ኪሎ ሜትሮች ወንዙን እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ከዛም አልፎ ወደ ሲናይ አስተላልፈውት ለእስራኤልም ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ እንደነበሩ እናውቃለን፡፡ እናም ለዚህ ዝግጅት ምን አድርገናል ሳይሆን፣ ሊነሳ የሚችለው የእስራኤል ቀረቤታ ለኢትዮጵያ መንግሥት ነው ወይስ ለግብፅ መንግሥት የሚለው ነው፡፡ እናም ኢትዮጵያ በሱዳንና በግብፅ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ እነሱን ሊጐዳ የሚችል በደል በምንም ዓይነት አትፈቅድም፡፡ ስለዚህ ከዓረቡ ዓለምና ከሕዝባቸው ጋር ለማጣላት ለእስራኤል ፍጆታና ጥቅም ስትል ኢትዮጵያ የናይልን ወንዝ ለመገደብ እንደተነሳሳች ግብፆች በዚህ ዓይነት ስም ማጥላላት እንደሚሠሩ እናውቃለን፡፡ እንቅስቃሴያቸው ሁለንተናዊ ነው፡፡ አገሮችን በመጠቀም፣ በማስፈራራት፣ ሽብርተኞችን እኛ ላይ በማዝመት፣ ተቋማትንና የመንግሥት አውታሮችን ዒላማ በማድረግ፣  ብሎም የሰላም ኃይሎችን ዒላማ ያደረገ የሽብር እንቅስቃሴዎች ከማድረግ አይታቀቡም፡፡

ሪፖርተር፡- ሁል ጊዜ ስጋቶች ይኖራሉ፡፡ ስጋቶችን ለመቋቋም የግድ አንድ ነገር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ምናልባት ከግብፅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሊመጣባት የሚችለውን ነገር ለመመከት ምን ያህል ዝግጁ ናት?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- በቀጥታ ስጋት ሊሆን የሚችለው ከኤርትራ በኩል ያለው ነው፡፡ ቀጥሎ ከአልሸባብ ሲሆን፣ ሻዕቢያ የሚያስተባብራቸውም አሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥታችን ንቁና ጠንቃቃ በመሆን እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይህንን ሊያኮላሽና ሊመክት በሚችል መልኩ የፖሊሲ ለውጥ እያደረገ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ከኤርትራ ጋር ባለው ሁኔታ እነሱ እንደፈለጉ ገብተው አተራምሰው ሊወጡበት የሚችሉበት እንደሌለና ጥቃትን በብቃት መመከት ይቻላልም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የኤርትራን ተቃዋሚዎች በመደገፍ በመንግሥታቸው ላይ እንዲነሱ ማድረግ፡፡ መንግሥታቸውን ለመለወጥ ማለቴ በአገራቸው ላይ ይኼ ግትርነት የማይጠቅም መሆኑን በመረዳት ለሚፈልጉት ድጋፍ የኢትዮጵያ መንግሥት ከጐናቸው እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡  

ሪፖርተር፡- የዚህ ግድብ መሠራት ከተበሰረ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ አንድነት ለመፍጠር የሚያስችሉ መሠረቶች እየታዩ ነው፡፡ ይህንን መነሳሳት መንግሥት ለወደፊቱ በሚገባ ለመጠቀም ያለው ዝግጁነት ወይም ቁርጠኝነት ምን ይመስላል?

አምባሳደር ተውፊቅ፡- መንግሥት በአገራችን ውስጥ አንደኛ የመቻቻል አገራዊ ፖሊሲ ነው ያለው፡፡ ሁለተኛ ይኼን የመቻቻል አገራዊ ፖሊሲ እንዲኖር፣ ምንም እንኳ በፖለቲካ አስተሳሰብ የተለያየን ብንሆንም ለአገራችን የጋራ አቋምና አመለካከት እንዲኖረን ብዙ ጥረት እያደረገ ነው ያለው፡፡ ትስስሩ ከሌላው ጊዜ የበለጠ እንዲሆንና ይኼው መቀጠል እንዳለበት የሚያሻማ አይደለም፡፡ የአሁኑ የሚሌኒየም ኤሌክትሪክ ማመንጫ ግንባታን አስመልክቶ የሕዝብ ተነሳሽነት በጣም የሚያደፋፍር ነው፡፡ በዚህም መንግሥት የወጣናቸው እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ሆነው፣ በአገር ውስጥም በውጭም ይህንን መግለጽ የሚችሉ ከተለያዩ ክልሎች የውጣጡና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ያሉበት ቡድን ተንቀሳቅሷል፡፡ ሁለተኛ በአገር ውስጥ ያለው ምላሽ ሲታይ ቦንድ ለመግዛትና የቁጠባ ቦንድ ለመክፈት ያለው መራወጥ በጣም የሚያመረቃ ነው፡፡ ለዚህ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ቦንድ መግዛት ብቻ ሳይሆን በተነሳሽነት ሕዝቡ መዋጮ ማዋጣት አለብን እያለ ነው፡፡ ይኼ የሚያበረታታ ነው፡፡ ሆ ብሎ የተነሳውን ሕዝብ በዚህ ዓላማ ዙሪያ ማሰለፍ  ይገባል፡፡ ሊነሱ የሚችሉ፣ ሊያደናግሩ የሚችሉ ጥያቄዎችን የሚፈታ ተቀራራቢ የሆነ ነገር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ በእስልምና ሃይማኖት ይኼ ቦንድ አትራፊና ወለድ ያለው ስለሆነ በእምነታችን የተከለከለ ነው ይላሉ፡፡ ከወለድ ነፃ የሆነ የሚሌኒየሙ የኃይል ማመንጫ ግድብ ቦንድ መኖሩን፣ ሁለተኛ በእምነት ብቻ ሳይሆን በራስ ተነሳሽነት ወለድ አንፈልግም የሚሉትን ሁሉ ማስተናገድ እንደምንችል ማብራራት ያስፈልጋል፡፡ ከዛ በላይ ደግሞ ማድረግ ያለብን በዚህ ዓላማ ብዙዎቹ ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ ግን ውጭ አገር ያሉ ቤተሰቦቻችን ይህንን ቦንድ እንዲገዙ የራሳችንን ቅስቀሳና ውትወታ ማድረግ እንዳለብን ነው፡፡ ሦስተኛ በዓለም አቀፍ ሚዲያ ይህንን በጎ ፍላጐትና ዓላማ ማስተዋወቅ አለብን፡፡ በምንችላቸው የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ችሎታው ያላቸው የፌስቡክም ሆነ የትዊተር ቡድኖችን እየፈጠሩ መንቀሳቀስ የግድ ይሆናል፡፡ ቅድም እንዳልኩት የትብብር ማዕቀፉ ፊርማ የሚዘጋበትን ጊዜ አስመልክቶ በሁሉም የናይል ተፋሰስ አገሮች የተጠናከረና የተደራጀ ቅስቀሳ መድረክ ቢፈጠር የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከምንም ጊዜ በላይ በአገር ልማት ዜጎቻችንን ማሰባሰብ የተቻለበት አጋጣሚ እየተፈጠረ እንደሆነና ይኼም ኢትዮጵያዊነት የበለጠ ያቀራርባል ብዬ አስባለሁ፡፡