በሔኖክ ያሬድ
‹‹መዳኒት ናት ድሬ
እውነት እንደ ስሟ
ላፈቀራትማ ስትሰጥ እንዳቅሟ››
እያለ ‹‹ድሬ ድሬ›› በሚለው ነጠላ ዜማው ስለድሬዳዋ ከተማ ያቀነቀነው ድምፃዊ ሚኪያስ ቸርነት ነው፡፡ ከኅብረተሰቡ ዘንድ በቅርበት ያስተዋወቀውን ይህንኑ ነጠላ ዜማ ያካተተ አዲሱን አልበም ‹‹ሰላም አላት››ን በዚህ ሳምንት ለአደባባይ አውሎታል፡፡
በተክለ ሰውነቱ ግዝፈት ጎልቶ ከሚታየው ሚኪያስ ጋር ባደረግነው ያፍታ ቆይታ እንደተረዳነው፣ ‹‹ሰላም አላት›› አልበም 13 ዘፈኖችን ሲያካትት፣ ዜማዎቹ በሙሉ የድምፃዊው ናቸው፡፡
‹‹በሬዱ ኢንተሎ ኦሮሞ
ምሽቱ ሰላም ነው
አሸወይና ነው›› የሚለውን የአማርኛና ኦሮምኛ ቅልቅል የኾነው ‹‹አሸወይና ነው›› ግጥሙን ከቴዎድሮስ ሞሲሳ ጋር ደርሶታል፡፡ የአልበሙን አብዛኞቹ ግጥሞች ግሩም ታምራት፣ አንዱን ደግሞ ኤልያስ አሰፋ እንደደረሱትም ድምፃዊው ገልጾልናል፡፡
‹‹ሚኪ የኔ ደሀ›› በሚል ተቀጽላ እንዲታወቅ ያደረገውም ‹‹የኔ ደሀ›› በሚል ከድሬ ድሬ ጋር ባንድነት በለቀቀው ነጠላ ዜማው ነው፡፡
ለ‹‹የኔ ድሀ›› ዜማው መነሻ የኾነለት የጓደኛው የሕይወት ገጠመኝ ነው፡፡ ጓደኛው ፍቅረኛው ወደ ውጭ ሀገር ስትሔድ ቦሌ ተገኝቶ አሸኛኘት ባደረገላት ጊዜ ያስተዋለውን ገጽታና የተከተለውንም እንባ ጓደኛው ከፍቅር ድህነት ውስጥ እንደጠለቀ አስገንዝቦታል፡፡
‹‹የወሰዳት ስደት
ከሰው አገር ቤት
የኔ ድሀ›› ብዬ ሠራሁና ዜማውን አቀነቀንሁት የሚለው ሚኪያስ፣ ‹‹ዜማውም ሐሳቡም የኔ ሆኖ›› ግጥሙ ግን ግሩም ታምራት እንዳዘጋጀለት አመልክቷል፡፡
በናዝሬት (አዳማ) ተወልዶ ያደገውና የተማረው ሚኪያስ ወደ ሙዚቃ ያዘነበለው በዚያው ከተማ በተቋቋመው ‹‹ትውልድህን አድን የፀረ ኤድስ ክለብ›› ውስጥ በነበረበት ጊዜ ሲሆን በቢጂ አይ (የቅዱስ ጊዮርጊስና ባቲ ቢራዎች አምራች) የናዝሬት ቅርንጫፍ ባቋቋመው ባንድም፣ በወር 350 ብር እየተከፈለው ሙዚቃውን ያቀነቅን ነበር፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላም በአዩ የምሽት ክበብ ሲጫወት ቆይቷል፡፡
ድሬዳዋ በጎርፍ የተጠቃችበትን አጋጣሚ በማሰብ ‹‹መከራው እንዳይበዛባት ፈጣሪን አደራ ለማለት›› ድሬ ድሬን ማቀንቀኑን ከመግለጽ አልተቆጠበም፡፡
‹‹ድሬ ያኔ መከራው ሲደርስባት እንደማንኛውም ሰው አዝኜ ነበር፡፡›› እንዳለው ሚኪያስ አገላለጽ፣ ከተማዋን ለመጀመርያ ጊዜ ያያት ወደ ቁልቢ ባመራበት አጋጣሚ ነው፡፡ ድሬን ሲያያት እንደሚወራላት ፍቅር የኾነች ከተማ ሆና ያገኛታል፡፡ በሕይወት የሌሉት እናቱም ወ/ሮ እታለም ይልማ የድሬ ልጅ ናቸውና ለርሳቸውም መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ዜማውን እያንጎራጎረ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳል፡፡ ግጥሙንም መላኩ ጥላሁን አበጅቶለት ለማቀንቀን ይበቃል፡፡
ሚኪያስ ከአቀንቃኝነቱ ሌላ የሙዚቃ መሣርያዎችንም ይጫወታል፡፡ ከዘመናዊው ኪቦርድ፣ ከባህላዊ ክራርና ማሲንቆን እንደሚጫወት አውግቶናል፡፡ በቮካል ሪከርድስ አሳታሚነትና አከፋፋይነት ብቅ ካለው አልበሙ ባሻገር፣ ድምፃዊው ከሕዝቡ ጋር በተለይም ከሙዚቃው ማኅበረሰብ ጋር የሚያገናኘውን ኮንሰርት ለማዘጋጀት ሐሳብ አለው፡፡


