Monday, May 20th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

‹‹ትውልደ ኢትዮጵያዊው የሚሌኒየም ግድቡን በተመለከተ ዓለማቀፉን ማኅበረሰብ መወትወት አለበት››

E-mail Print PDF
User Rating: / 5
PoorBest 

 

አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ

በምሕረት ሞገስ

ኢትዮጵያ ዓባይን ተከትላ በምታደርገው የሐይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ግንባታም ሆነ ተያያዥ የሆኑ ልማቶች ዓለማቀፍ ዕርዳታ እንዳይገኝ በግብፅም ሆነ ከግብፅ ውጭ የሚኖሩ ግብፃውያን ዓለማቀፉን ማኅበረሰብ ለማሳመን በሚያደርጉት ውትወታ የታወቁና ባብዛኛወም የሚሳካላቸው ናቸው፡፡

አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የኧርነስት ኤንድ ያንግ ማኔጂንግ ፓርትነር፣ በውጭ በተለይም በአሜሪካና እንግሊዝ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ  በግብፃውያኑ በኩል የሚፈጠረውን ጫና ለማርገብ፣ ምላሽ ለመስጠትና በበኩላቸው ዓለማቀፉን ማኅበረሰብ ለመወትወት የተሻለ አቅም አላቸው ይላሉ፡፡

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለመገንባት የመሠረት ቁፋሮው መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. የተከናወነው የሚሌኒየም ግድብን አስመልክቶ ዲያስፖራው ሊያበረክተው በሚችለው አስተዋጽኦ ዙርያ አስተያየታቸውን የሰጡን አቶ ዘመዴነህ፤ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ  በውጭ ምንዛሪ ቦንድ እንዲገዛ በመንግሥት በኩል ከተጀመረው እንቅስቃሴ በተጨማሪ ዲያስፖራው በያለበት ሆኖ ራሱን በማደራጀት ስለሚሌኒየም ግድብ ፕሮጀክት አዎንታዊነት፣ ዓለማቀፉን ማኅበረሰብ የማሳመን ሥራ መጀመር አለበት ብለዋል፡፡

‹‹ትውልደ ኢትዮጵያዊው የሚሌኒየም ግድብ ግንባታውን በተመለከተ ለዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ስለግድቡ አዎንታዊ ገጽታ ማሳመንና መወትወት ይችላል፤›› የሚሉት አቶ ዘመዴነህ፣ በተለይ አሜሪካ የዓለም ባንክን ከፍተኛ በጀት ሸፋኝ በመሆኗ በአሜሪካ በየግዛቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለየግዛቱም ሆነ ለአሜሪካ ኮንግረሶችና ሴናተሮች ውትወታ በማቅረብና ፊርማ በማሰባሰብ ግብፃውያን ለሚፈጥሩት ተቃውሞ ምላሽ መስጠት ይችላሉ፡፡

ኢትዮጵያ በምትሠራቸው ግድቦች ዙርያ በአብዛኛው የሚታየውና የሚሰማው ከግብፅ በኩል የአንድ ወገን ተቃውሞ ብቻ በመሆኑ፣ አሜሪካውያን ባለሥልጣናት የነርሱን ተቃውሞ በመስማት ድጋፍ ለመስጠት ግዴለሽ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ግብፃውያን በዓለም ባንክ ላይ የሚፈጠሩት ጫናም ባብዛኛው ውጤታማና ተሰሚነት የሚያገኝ ሆኗል፡፡ ይህንን ለማምከን ወይም ምላሽ ለመስጠት ውጭ ያለው ዲያስፖራ ተቀናጅቶ እንደ ኢትዮጵያዊነቱ ማገዝ፣ ለተቃውሞውም ምላሽ በመስጠት ውሳኔ ሰጪዎቹ ግራ ቀኙንም እንዲያዩ ለማድረግ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡

እንደ አቶ ዘመዴነህ፣ ከውትወታ ሥራው ጎን ለጎንም የሚሠራው ግድብ ትልቅ ስለሆነ ኤክስፐርቶች ያስፈልጋሉ፤ አንዱም ወጭ ለዓለማቀፉ ኤክስፐርቶች የሚከፈለው በመሆኑ፣ ሙያው ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን መጥተው እንዲሠሩ ማድረግንም ማሰብ ይገባል፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የአገራቸው ጉዳይ ስለሆነ ለውጭ ዜጋው ከሚከፈለው ቀንሰው ሊሠሩ፣ በውጭ ምንዛሬ ሳይሆን በኢትዮጵያ ብር እንዲከፈላቸው ሊስማሙ፣ እንዲሁም የተወሰነ ጊዜ ወስደው በነፃ ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ በዚህ ተሳታፊ መሆን የሚችሉ መሐንዲሶችና ምሁራንም ይኖራሉ፡፡  የግድቡ ሥራ ዘርፈ ብዙ ዕውቀትን ያቀፈ በመሆኑም በመንግሥት በኩል በሚዘረዘሩ የሙያ ዘርፎች ዕውቀቱ ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ መጥተው ሥልጠና ሰጥተው መሔድ የሚችሉበትንም ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡

‹‹የዚህ መንግሥት ደጋፊ ሆኜ አላውቅም፡፡ ሆኖም መንግሥት ለሚሠራቸው ልማቶች ዋጋ መስጠት እፈልጋለሁ፤›› የሚሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ልማት ላይ መሳተፍ የሚፈልጉትና በአሜሪካ የሚኖሩት አቶ ዳንኤል ናቸው፡፡ መንግሥት የመሠረተ ልማት ዕድገትን በተመለከተ የሚሠራቸው ልማቶች ሐይድሮ ኤሌክትሪክን ጨምሮ ሊበረታቱ የሚገባቸው ናቸው ይላሉ፡፡

‹‹የሚሌኒየም ግድብ ፕሮጀክትም በጣም የምስማማበትና ለመደገፍም የምጓጓለት ፕሮጀክት ነው፤›› የሚሉት አቶ ዳንኤል፣ ሆኖም ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ አደጋ ቢያጋጥም ለመቋቋም ምን ያህል ተዘጋጅተናል? እንወጣዋለን? የተጠናከረና ቀጣይነት ያለው ገንዘብ ለማግኘት ምን ያህል ጠንካራ አካሔድ አለ? ግብፅ ጦርነት ብታስነሣ ኢትዮጵያ ግድቡን ለመከላከል፣ ለመጠበቅና ጠብቆም ለማቆየት አቅም አላት?  ለመመከትስ?  የሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይፈልጋሉ ሲሉም ይናገራሉ፡፡

አቶ ዳንኤል፣ ከባድ ኃላፊነትና ከፍተኛ ድጋፍ፣ ፍላጎትም በሚጠይቀው የሚሌኒየም ግድብ ፕሮጀክት መንግሥት ‹‹በኮሚኒስት አቋሙ›› ላይ ለውጥ ለማምጣት እንደ ዓይን መግለጫ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ መንግሥት የቴሌኮምና የባንክ ዘርፍን ለዲያስፖራው ክፍት በማድረግ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት አለበት ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡

‹‹ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ በሚሌኒየም ግድብ ፕሮጀክት ደስተኛ የሚሆን ይመስለኛል፤ የኢትዮጵያውያንን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ጥሩ የመሸጋገርያ መንገድ ነውና›› ያሉን ደግሞ በአሜሪካ የሚኖሩትና በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማገዝ በተለያየ ጊዜ በመምጣት የሚሳተፉት  አቶ ካሕሣይ አብርሃ ናቸው፡፡

‹‹ይህን ፕሮጀክት ለማስፈጸም ኢትዮጵያውያንን የፖለቲካ ልዩነት ሊገድባቸው ይገባል ብዬ አላምንም፡፡ ቦንድ መግዛትም በራሱ በቂ አይደለም፡፡ ልማቱን ለማስፈጸም የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያለውም ቢሆን፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እጅ ለእጅ ተያይዞ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተሳታፊ መሆን አለበትም፤›› ይላሉ፡፡

በውጭው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በኤምባሲዎችና በኮሚዩኒቲ በኩል የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ማዘጋጀት እንደሚቻል የሚጠቁሙት አቶ ካሕሣይ ሆኖም መድረኩ ሲታሰብ ጥንቃቄ የተሞላበትና ከሙስና የጸዳ ማድረግ፣ እንዲሁም ሁሉም በሚሌኒየም ግድብ ስም የሚገኘው ገቢ ለግድቡ ግንባታ ብቻ የሚውል መሆኑን ማሳየትና ማሳወቅ ይገባል ብለዋል፡፡ ‹‹ዲያስፖራው ከመጀመርያው ገንዘቡ ለግድቡ ሥራ መዋሉን ከተማመነ ቀጣዩን ትብብር ያለቀስቃሽ በራሱ ፍላጎት የሚያደርገው ይሆናል፤›› ይላሉ፡፡

ከሚሌኒየም ግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቦንዱን በመግዛት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲችሉ የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ባገባደድነው ሳምንት መጀመርያ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከዚህ ቀደም ዲያስፖራው በቦንድ ሽያጭ እንዲሳተፍ ባደረገው ጥሪ መሠረት፣ የሚሌኒየም ቦንድ በዶላር፣ በዩሮና በፓውንድ ስተርሊንግ መግዛት ይችላሉ፡፡ አገር ቤት ከመጡ በኋላም ቦንዱን በማስያዝ ብድር የሚያገኙበት ሁኔታም ተመቻችቷል፡፡ የቦንዱም ወለድ በዶላር የሚከፈል ይሆናል፡፡ ገንዘቡን ከፈለጉት በየስድስት ወሩ ወደሚኖሩበት አካባቢ ማስተላለፍ ይቻላል፤ ካልሆነም በወለዱ ተጨማሪ ቦንዱን መግዛት ወይም ለሌላ ጉዳይ ማዋል ይችላሉ፡፡

በሌላ በኩል አሁን እየተሰራጨ ባለው የመንግሥት ቁጠባ ቦንድም መሳተፍ ይችላሉ፡፡