በብሩክ ገብረ መድኅን
ከሠላሳ ሦስት ሺሕ በላይ ወጣትና አንጋፋ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ስካውት ማኅበር፣ የወርቃማው ሕግ መርሕን ለማስፈጸም እስከ 2004 ዓ.ም. ድረስ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ሆኖ ተመረጠ፡፡
‹‹ለአንተ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን ለሌላው አድርግ›› የሚለው የወርቃማው ሕግ መርሕ በዓል ባለፈው ረቡዕ በግዮን ሆቴል በተከበረበት አጋጣሚ፣ የበጎ ፈቃድ አምባሳደርነት ማዕርጉን ለኢትዮጵያ ስካውት ማኅበር ያበረከቱት አምባሳር ሙሴ ኃይሉ የኢንተር ፌዝ ፒስ ቢዩልዲንግ የቦርድ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ በወቅቱም ሊቀመንበሩ ‹‹የወርቃማው ሕግ መርሕ ለሰው ልጆች ሰላማዊ ሕይወት መስተጋብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን በመግለጽ፣ ለመርሑ ስኬት ሁሉም የበኩሉን ሊያደርግ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
አምባሳደርነቱን የሚያመለክተው የምስክር ወረቀት የተቀበሉት የማኅበሩ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አያሌው ተስፋዬ፣ ማዕርጉ ለሰው ልጆች ሰላም መስፈን ይበልጥ በቁርጠኛነት ለመሥራት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
የወርቃማው ሕግ መርሕ በዓል በየዓመቱ መጋቢት 27 (ኤፕሪል 5) በመላው ዓለም ታስቦ እንዲውል ሐሳቡን ያፈለቀው የኢትዮጵያ ኢንተር ፌይዝ ፒስ ቢዩልዲንግ ሲሆን፣ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ መታሰብ መጀመሩ በወቅቱ ተገልጿል፡፡


