Wednesday, May 22nd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

በሰፋፊ መሬቶች ላይ የሕግ ጥሰት ይስተዋላል ተባለ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

በታደሰ ገብረ ማርያም

ለአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ የወጡት ሕጎችና መመርያዎች በተለያዩ ወቅቶች ሲጣሱ ይስተዋላል፡፡ ጥሰቶቹ የሚስተዋሉትም ትላልቅ ወይም ሰፋፊ መሬቶችን ያለአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ለባለሀብቶች ወይም ለኩባንያዎች በመስጠት መሆኑን አቶ ንጉሡ አክሊሉ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች መድረክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቫይሮመንት ጋዜጠኞች ማኅበር መጋቢት 29 ቀን 2003 ዓ.ም. ባካሔደው የክብ ጠረጴዛ ስብሰባ ላይ ዋና ሥራ አስኪያጁ እንዳመለከቱት፣ አንዳንድ ተቆርቋሪዎች ጥሰቱ ይጣራ የሚል ጥያቄ በሚያቀርቡበት ወቅት ጉዳዩ በይበልጥ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ‹‹ምንም ችግር የለውም፡፡ ኩባንያዎቹም ጠቃሚ ናቸው›› እያሉ የሚሰጡት መልስ ለችግሩ መባባስ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ሳያካሔድባቸው ለኩባንያዎቹ ከተሰጡት ሰፋፊ መሬቶች መካከል ፍሎራ ኢኮ ፓወር ለተባለው ኩባንያ ባቢሌ የሚገኘውን የዝሆን መጠለያን እንዲያለማ ከሁለት ዓመት በፊት መሰጠቱ ይገኝበታል፡፡ ኩባንያው ዝሆኖቹ ያሉበትን ጥብቅ ቦታዎች ውስጥ ገብቶ የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ለማካሔድ መንቀሳቀሱን፣ በመሠረቱ ጥብቅ ቦታዎች ምንም ዓይነት ግምገማ ሊካሔድባቸው የማይገቡ ቦታዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ኩባንያው በጥብቅ ቦታዎች ገብቶ ብዙ ደን ካወደመና ብዙ ጥፋት ከፈጸመ በኋላ ፕሮጀክቱን አቁሞ ለቅቆ እንዲወጣ መደረጉን ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ግሎባል ኢነርጂ ለተባለ ሌላ ኩባንያ የጉሎ ዘይት ፍሬ ለማምረት ከሁለት ዓመት በፊት ወላይታ ውስጥ 10 ሺሕ ሔክታር መሬት እንደተሰጠው፣ ነገር ግን የክልሉን መንግሥት ሳያስፈቅድና ከስምምነቱ ውጭ ገበሬዎች ከማሳቸው ላይ አንድ ሦስተኛውን ለጉሎ ዘይት ፍሬ ልማት እንዲያውሉት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ቦታው ከፍተኛ የሆነ የመሬት ጥበት፣ የሕዝብ ብዛትና የምግብ እህል እጥረት ያለበት መሆኑን ገልጸው፣ እያንዳንዱ አርሶ አደር ላመረተውም የጉሎ ዘይት ገንዘብ ሳይሆን ኩፖን ብቻ እንደሰጣቸው አስረድተዋል፡፡ ኩባንያው ለአርሶ አደሮቹ ገንዘባቸውን እንዲከፍልና ከአካባቢያቸውም እንዲርቅ መደረጉን አመልክተዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል ጉደሬ ወረዳ ልዩ ስሙ ጉማሬ ቀበሌ የሚገኘውና ጥቅጥቅ ደን ያለበትን ቦታ ያለ ተጽእኖ ግምገማ ለሻይ ልማት እንዲያውለው በቅርቡ ለአንድ የውጭ ኩባንያ መሰጠቱ ሌላው የሕግ ጥሰት መሆኑን አቶ ንጉሡ አመልክተው፣ ይህ ቦታ ወደ 15 የሚደርስ ትላልቅ ምንጮችና በርካታ ወንዞች የሚነሡበት ሥፍራ መሆኑንና  ጉዳዩም ውዝግብ ማስነሣቱን ተናግረዋል፡፡

‹‹አንድ የውጭ ኢንቨስትመንት በተለይ የግብርና ኢንቨስትመንት ፍሰት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ አገሪቱን በትክክል መጥቀሙን ማረጋገጥ የሚችልባቸው መንገዶች አሉ›› ያሉት አቶ ንጉሡ፣ ከእነዚህም መካከል አንደኛው መንግሥት አምኖበት ያቋቋመው ድርጅት ኩባንያው የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ሪፖርት እንዲያቀርብ ማድረግ እንዳለበትና ግምገማውም በአግባቡና በጥራት መከናወኑን ማረጋገጥ እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡

የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ መካሔድ ያለበትም ፕሮጀክቱ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ሲሆን፣ ግምገማውም መከናወን ያለበት በገለልተኛ አካል አማካይነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የፌዴራልም ሆነ የክልል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን መሥርያ ቤቶች ግምገማው በአግባቡና በጥራት መካሔዱን መቆጣጠር እንጂ ራሳቸው ግምገማ እንደማያካሒዱና ማካሔድም እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛ የሆነ የልማት ሥራዎች በሚከናወንባቸው የመንግሥት መሥርያ ቤቶች ውስጥ የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ዩኒቶች ማቋቋማቸውን፣ እነዚህም ዩኒቶች በራሳቸው የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ሊያካሒዱ እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቶቹ ከተቋቋሙባቸው መሥርያ ቤቶች መካከል፣ ግብርና፣ ውኃና ኢነርጂ፣ ማዕድን፣ ከተማ ልማት ዘርፎች እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

ኩባንያዎቹ በራሳቸው ወይም ገለልተኛ በሆኑ ባለሙያዎች የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ካካሔዱ በኋላ ለአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ወይም በየሚኒስቴሩ ለተቋቁሙት ዩኒቶች ሪፖርት እንደሚያቀርቡ፣ ባለሥልጣኑና ዩኒቶቹ ሪፖርቱ ትክክል መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ የመፍቀድ በአግባቡ ካልተሠራም ውድቅ የማድረግ ሥልጣን እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የግምገማው ሪፖርት በአግባቡ መሠራቱ ከተረጋገጠ በኋላ በዚህ ፕሮጀክት ሊጎዱ ወይም ሊጠቀሙ ይችላሉ ለተባሉ ወገኖች የግምገማው ሪፖርት ሊደርሳቸው እንደሚገባ ከአቶ ንጉሡ ማብራርያ ለመረዳት ተችሏል፡፡