Saturday, May 18th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

‹‹[የኢትዮጵያን] አየር በዕቃ ሞልቶ እንዲማግ ማድረግና መሸጥ ይቻላል››

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

 

አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም መሥራች

አቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪን የመሠረቱ፣ የአሥራ ሦስት ወራት ጸጋን (13 Months of Sunshine) የፈጠሩና በርካታ ሥራዎችን ያከናወኑ የኢትዮጵያ ቱሪዝም አባት ናቸው፡፡

በቅርቡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይህንን ውለታቸውን ቆጥሮ ዕውቅና በመስጠት ምስላቸውን በስጦታ አበርክቶላቸዋል፡፡ አሁንም ድረስ ከመሥራት አልገታም የሚሉት አቶ ሀብተ ሥላሴ የ81 ዓመት አረጋዊ ናቸው፡፡ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አራት የቱሪዝም ፕሮጀክቶችን ያለ ምንም ክፍያ ለመስጠትና ለማገዝ ፍላጎት እንዳላቸው ለሚኒስትር አቶ አሚን አብዱልቃድር ነግረዋቸዋል፡፡ በቱሪዝም ዘርፍና በተያያዥ ጉዳዮች ሔኖክ ያሬድና ብርሃኑ ፈቃደ አነጋግረዋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪዝም ዘርፍና በሌሎች ሥራዎች ኢትዮጵያን ለምን ያህል ጊዜ አገልግለዋል?

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- ከመጀመሪያው እ.ኤ.አ ከ1954 [1946 ዓ.ም.] ጀምሮ አገልግያለሁ፡፡ ያኔ ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣሁ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እሠራ ነበር፡፡ ከዚያ በግድ ቱሪዝምን ላይ እንድሠራ አዘዙኝና ገባሁበት፡፡ ከባድ ሥራ ነው፡፡ ያን ጊዜ ካሜራ ወደ ኢትዮጵያ አይገባም ነበር፡፡ ሲገባም ጉምሩክ ይይዘዋል፡፡ ፈቃድ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ማውጣትም ያስፈልግ ነበር፡፡ በዚህ ሰበብ ሁለት ጊዜ ያህል ታስሬያለሁ፡፡ ፎቶ ግራፍ ለምን ታነሣለህ ብለው አሰሩኝ፡፡ ያን ጊዜ ፎቶ ግራፍ የሚያነሣ ሰው ሰላይ ተደርጎ ይታሰብ ስለነበር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቱሪዝም ሙያዎ ኢትዮጵያን ምን ያህል ያውቋታል?

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- ያልደረስኩበት ቦታ የለም፡፡ በእግር፣ በፈረስ፣ በግመል፣ በሔሊኮፕተር፣ በአውሮፕላን ሁሉ ተዘዋውሬ ከ100 በላይ ሰው ያልረገጣቸው የኤርትራ ደሴቶችን ጭምር አይቻለሁ፡፡ ትልቅ ሀብት ናቸው፡፡ ቢያውቁበት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መሰብሰብ ይችሉ ነበር፡፡ በጋምቤላ በኩል ጂካው ድረስ ሔጃለሁ፡፡ የደቡብ ሱዳን ጠረፍ ነው፡፡ በኤርትራ በኩል ቤኒአሚር ድረስ ወዳለው የጠፈር ቦታ ደርሻለሁ፡፡ ቤንሻንጉልን በሙሉ እስከ ሱዳን ድረስ አዳርሻለሁ፡፡ መሥራት ካስፈለገ ማየት፣ ማወቅ ግድ ይሆናል፡፡ ካየንና ካወቅን በኋላ ማውራት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት እርስዎ ብዙ ሠርተዋል፤ ከሠሯቸው መካከል አሁንም ድረስ ጎልቶ የሚታወቀው ‹‹ኢትዮጵያ የአሥራ ሦስት ወር ጸጋ›› የሚለው መለያ ነው፡፡ አሁን መቀየር አለበት የሚሉ አሉ፡፡ ይቀየር ቢባል ምን ይሰማዎታል?

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- ሁልጊዜ አንድ ነገር ሲፈጠርና የሚበልጠው ሲገኝ ያንን ማየቱ ተገቢ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ምክትል ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ወልድ ሀብተ ወልድ ፎቅ ቤት ሠርተው ነበር፡፡ ያን ጊዜ በንጉሡ ዘመን የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ነበር፡፡ መንግሥቱ ንዋይ ደግሞ ጠንሳሽና የእኛም ዘመድ ነበር፡፡ ሰውዬው ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ሠርተሃል ተብለው ታሰሩ፡፡ ይህ ከሆነማ አፍርሱት ቢሏቸው የለም አንተን ነው የምናፈርሰው ብለው ገደሏቸው፡፡ አሁን ደግሞ በተገላቢጦሽ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ እንዲሠራ ነው የሚፈለገው፡፡

ሪፖርተር፡- የአሥራ ሦስት ወር የፀሐይ ጸጋን እንዴት መረጡት?

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- እኔ ያደግሁት ውጭ አገር ነው፡፡ የትም ዓለም ላይ 13 ወር የለም፡፡ ፒራሚድ ሲታይ ግብፅ ነው፡፡ ኤፍል ታወር ሲታይ ፈረንሳይ ነው፡፡ የነፃነት ሐውልት ሲታይ አሜሪካ አለ፡፡ እኛ የምንታወቅበት የለንም ነበር፡፡ ሁሉ ነገር ከዘር፣ ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ሳላውቀው አንድ ወቅት ላይ የ13 ወር ደመወዝ ይሰጠን ብዬ ጠየቅኩ፡፡ ወዲያው ይህንን ሐሳብ ለቱሪስት መሳቢያነት መቀየር እንደሚቻል አሰብኩ፡፡ ሌላው ሁሉ ከዘር ከሃይማኖት ጋር የሚያያዝ ነበር፡፡ ላሊበላን ባደርግ ኢትዮጵያ በሙሉ ክርስቲያን ባለመሆኑ ችግር ነበረበት፡፡ የአሥራ ሦስት ወር ፀሐይ ግን ከምንም ነገር ጋር አይገናኝም፡፡ ምንም የፖለቲካና የሃይማኖት ንክኪ የለውም፡፡ አሁን ከዚያ የበለጠ ከተገኘ ቶሎ መተካት ነው፡፡ ምንም ችግር የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ዛሬም ድረስ መሥራት የሚፈልጓቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ?

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- ለመርዳት ነው የምፈልገው፡፡ መሥራት ያለባቸው የተመደቡት ሰዎች ናቸው፡፡ እነርሱን ለመርዳት ዝግጁ ነኝ፡፡ አምስት ያህል ፕሮጀክቶች አሉኝ፡፡ ፍልውሃን በአግባቡ አልተጠቀምንበትም፡፡ ወንዶገነትና ሶደሬ አካባቢ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ነገር ግን ከ3000 በላይ ፍልውኃ በየቦታው አለን፡፡ ያ የማያልቅ፣ ከወርቅና ከከበረ ድንጋይ ሁሉ የበለጠ ሀብት ነው፡፡ ነገር ግን አልተሠራበትም፡፡ እኔጋ ጥናቱ አለ፡፡ ዩኔስኮ ውኃውን መርምሮ ያገኘው ጉዳይ አለ፡፡ ጥናቱ በእጄ ስላለ ለመንግሥት እሰጣለሁ፡፡ ይሠሩበታል ብዬም አስባለሁ፡፡ አሁን ቱሪስቶች ያሉት እዚሁ ከጎናችን ነው፡፡ ዱባይ፣ ኢምሬቶች አሉ፡፡ ዱሮ ዓረብ ድሀ ነበር፡፡ አሁን ግን ዓለምን የያዙት እነርሱ ናቸው፡፡ ፍልውኃ፣ አረንጓዴያማ መስክ ይወዳሉና አቅሙ ላላቸው ባለሀብቶች መስጠት ከተቻለ ሰው ይመጣል፡፡ ከዱባይ አዲስ አበባ የሚያስፈልገው፡፡ የሦስት ሰዓት በረራ ብቻ ነው  ከአውሮፓና ከአሜሪካ ሰው ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከባድ እየሆነ ነው፡፡ ቀውስ ላይ ናቸው፡፡ ጃፓን ከባድ አደጋ ደርሶባታል፡፡ የቅርብ አገሮች ግን መምጣት የሚችሉበት አቅም አላቸው፡፡ በግብፅ ለሁለት ዓመት ቆይቻለሁ፡፡ አባቴ አምባሳደር ነበሩና በዚያ ኖረናል፡፡ በጣም ቃጠሎ ነው፤ ሲበዛ ሞቃት ነው፡፡ በክረምት ብቻ ወደ እስክንድርያ እንሔድ ነበር፡፡ አሁንም በጣም ሞቃት ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- እርስዎ የአሥራ ሦስት ወር ጸጋ ብለው ነበር ብዙ ጸጋ አለ. . ?

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- (አቋርጠው) ደመወዝ የለውማ፡፡ (ሳቅ…) የአሥራ ሦስት ወር ደመወዝ አይከፈልም፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ኬንያ ያሉት አገሮች ግን የዱር እንስሳት ሀብት ብቻ እያላቸው ነገር ግን ብዙ የተጠቀሙበት ሁኔታ አለ፡፡

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- እነሱ ስለሠሩ ነዋ፡፡ እኛ አንሠራም፡፡ አንዱ ሲሠራ አሥሩ ወደ ኋላ ይጎትታል፡፡ ምቀኝነት አለ፡፡ የአበሻ ጠባይ አብሮ መሥራት ስለሌለው መድረስ ያለብን ቦታ አልደረስንም፡፡

ሪፖርተር፡- አየር በዕቃ ሞልተው ለመሸጥ የሞከሩበት ጊዜ እንደነበር ይነገራልና ስለ እርሱ ቢነግሩን፤

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- የኢትዮጵያ አየር በየትም ዓለም ላይ አይገኝም፡፡ አንድ ጊዜ ከንጉሡ ጋ ገባሁና አየር ይሸጣል አልኳቸው፡፡ ገንዘብ ሚኒስትሩ መጡና ምን ይለፈልፋል ብለው አጣጣሉኝ፡፡ አጋጣሚ ሆኖ እ.ኤ.አ በ1970 [በ1962 ዓ.ም.] በኦሳካ ኤግዚቢሽን ነበርና ወደ ቶኪዮ ዞር ዞር ብዬ ለማየት ሔድኩ፡፡ አንድ ቦታ ላይ የፊጂ ተራሮች የሚል ጽሑፍ ያለበት ቆርቆሮ አየሁ፡፡ ሳነሣው ባዶ ነው፡፡ ውስጡ ያለው የፊጂ አየር ብቻ ነው፡፡ ሰዉ ገዝቶ በአፍንጫው መማግ ብቻ ነው፡፡ ያንን ገዛሁና ወደ ንጉሡ አመጣሁ፡፡ ስጦታ አምጥቼልዎታለሁ አልኩና ሰጠኋቸው፡፡ አንሥተው ሲያዩ ምንም የሌለው መስሏቸው ምን ትቀልዳለህ አሉኝ፡፡ አየር ይሸጣል ያልኩዎት ይኼ ነው፤ ገዝቼ መጣሁ አልኳቸው፡፡ ገንዘብ ሚኒስትሩን ጠሩና ታስታውሳለህ ያልከውን ይኸውልህ አየር ይሸጣል አሏቸው፡፡ ይኼንን አሁንም ማድረግ ይቻላል፡፡ አየር በዕቃ ሞልቶ እንዲማግ ማድረግና መሸጥ ይቻላል፡፡ ውኃ በፕላስቲክ እየተሸጠ እኮ ነው፤ ሰው ግን አያምንም፡፡ አይቀበልም፡፡ አገሪቱን ያጠቃት በምቀኝነት፣ በዘር፣ በሃይማኖት መከፋፈላችን ነው፡፡ አንድ ሆነን ካልሠራን ከባድ ነው፡፡ አሁን ብዙ ለውጥ መጥቷል፡፡ ከሞት የተመለስኩ ያህል የሚሰማኝ ጊዜ አለ፡፡ ሴቱ ሁሉ እንደ ልቡ ነው፡፡ ወደ ዱባይና ወደመሳሰሉት አገሮች ሲሔዱ፣ ሲሠሩ የሚታዩ ቆነጃጅቶች ብዙ አሉ፡፡ በእኛ ጊዜ እንዲህ አይታሰብም፡፡ ብዙ ለውጥ አለ፡፡ የሰው አስተሳሰብ ተቀይሯል፡፡  

ሪፖርተር፡- አንድ ኒውዚላንዳዊ ቢሊየነር ኢትዮጵያን በሔሊኮፕተር ጎብኝቶ መደነቁን ሲናገሩ ነበርና እለ እርሱ ቢገልጹልን፤

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- ፓይለቱ የሰውዬው ልጅ ባል ነው፡፡ ሰውዬው ደግሞ ባለሔሊኮፕተር ነው፡፡ የእርሱ አስጎብኚ ከእኔ ጋር የሚሠራ ነውና ተዟዙሮ አይቶ እኔን ማየት ፈለገና ራት ጋበዘኝ፡፡ ተኝታችኋል አለኝ፡፡ በሔሊኮፕተር ከ125 በላይ አገሮች እየተዘዋወርን አይተናል፤ እንደ ኢትዮጵያ ግን የሚሆን አላየንም አለኝ፡፡ ሰውዬው የምንም ፍላጎት የለውም፡፡ ለጥቅም ብለው ነው እንዳይባል፣ አገራቸው እዚህ እንኳ ኤምባሲ የላትም፡፡ ሰውዬው ደግሞ እጅግ ባለጸጋ ናቸው፡፡ ቢሊየነር በመሆናቸው ለጉብኝት ብቻ ነው የመጡት፡፡ ያዩትን አይተው ተኝታችኋል አሉኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሽልማት ሲሰጥዎ፣ በሕይወቴ ለመጀመርያ ጊዜ ለሽልማት ተጠራሁ ብለዋል፡፡ ለምንድ ነው ከዚህ በፊት ይህንን ሁሉ ሠርተው ያልተሸለሙት?

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- ምቀኞች ስለሆንን፡፡ ሁሌም ሲጠሩኝ ለአንድ ወቀሳ ነው፡፡ ቤተ ክህነት ተጠርቼ በቴሌቪዥን ለምን እንዲህ ተናገርክ እባላለሁ፡፡ ያን ጊዜ ከቀረጥ ነፃ ዕቃዎች መሸጫ ሱቅ (ዲውቲ ፍሪ ሾፕ) ከፍተን ነበር፡፡ የእኛ ቢሮ ከመንግሥት ቢሮዎች ሁሉ ሀብታም የሚባለው ነበር፡፡ ያን ጊዜ የቱሪዝም በጀት 220 ሺሕ ብር ስለነበር በዚህ በጀት እንዴት አገርን ማሳደግ ይቻላል እያልኩ ከጃንሆይ ጋር እጨቃጨቅ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ቁልፉን ይዤ ሔድኩና ጃንሆይ ይኼንን መሥርያ ቤት ለሒሳብ ሹም ይስጡት፤ ደመወዝ ከመክፈል ውጭ ሌላ ሥራ መሥራት አልቻልኩም አልኳቸው፡፡ የዲውቲ ፍሪ ሾፕ ፈቃድ ስጡኝ ብዬ ጃንሆይን ጠየቅኩ፡፡ ኋላ ላይ ገንዘብ ሚኒስትሩ መጡና እኛ ኮንትሮባንድ መቆጣጠር አቅቶናል፤ ሀብተ ሥላሴ ደግሞ አናታችን ላይ ኮንትሮባንድ ለመፍጠር ይፈልጋል አሉኝ፡፡ ንጉሡም፣ ሥራህ መቆጣጠር ነው እንጂ ሥራ አይሠራ ነው የምትለው፤ ወይስ መቆጣጠር አልችልም ማለትህ ነው ብለው ጠየቋቸውና ተፈቀደልኝ፡፡ ሥራ ሊጀመር ሲል ደግሞ ገንዘብ ስለጠፋ የአባቴን ካርታ ወስጄ ለአንድ ሕንድ ሰጠሁና 5000 ዶላር ተበደርኩ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ማግኘት ተቻለን፡፡ በአንድ ወቅት ከመላው ኢትዮጵያ ሀብታም የነበረው የእኛ መሥርያ ቤት ነበር፡፡ አንድ ሚኒስቴር በጊዜው እንዲነግድ አይፈቀድለትም ነበር፡፡ ለእኛ ተፈቅዶ ነበርና ብዙ ገንዘብ አስገብተናል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሕንፃ ተሠርቶ ሥራ ሲጀምር የሚያገለግሉት የእኛ መኪኖች ነበሩ፡፡ 46 ያህል ነበሩን፡፡ እኔ እንደ ሾፌር፣ እንደ አስጎብኚ፣ እንደ ፎቶግራፍ አንሺ እየሆንኩ ሠርቻለሁ፡፡ በኋላ ምቀኛ በዛና ከቀረጥ ነፃ የተሰበሰበ ገንዘብ ወደ መንግሥት ግምጃ ይግባ አሉ፡፡ ያ አሠራር ዛሬ ቆይቶ ቢሆን ኖሮ አሥር ሚሊዮን ሰዎች በተሰማሩበት ነበር፡፡ 

ሪፖርተር፡- በጊዜው ሴቶችን ፎቶግራፍ ያነሡ ነበርና ከንጉሡ ዘንድ የገጠመዎት ጉዳይ አለ ይባላል፤

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- አዎ፡፡ አንዲት የጋምቤላ ሴት ፎቶግራፍ አንሥቼ ነበር፡፡ ሴትየዋ ጡቷ ቆንጆ ነበርና አንሥቼ ፖስተሩ ከመታተሙ በፊት ናሙናውን ለንጉሡ አስገብቼ ጠረጴዛ ላይ እደረድር ነበር፡፡ ንጉሡ መጥተው ሲያዩ ይኼ ምንድነው አሉና ጠየቁኝ፡፡ አይ ቱሪስቶች እንዲህ ማየት ይወዳሉ ስላቸው፣ አንተም ትወዳለህ ይባላል አሉኝ፡፡ ታትሞ ሲወጣም ሳንሱር ይደረግ ነበር፡፡ ራቁት እያሳየ ነው ብለው ከንጉሡ ዘንድ መልሰው ይዘው መጡ፡፡ ንጉሡም አይተናል አሉና መለሷቸው፡፡ ከዚያ በኋላ የቱንም ነገር ከመሥራቴ በፊት ቀድሜ ለንጉሡ ስለማሳይ አይተናል እያሉ ሚኒስትሮችን ይመልሷቸው ነበር፡፡ ብዙ መሥራት አንወድም፡፡ ስንሠራ ደግሞ ምቀኛው ወደ ኋላ የሚጎትት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እሰጣለሁ ካሏቸው ፕሮጀክቶች አንዱ፣ አንድ ብር ቢያንስ በአንድ ዶላር መመንዘር የሚያስችል ነው ብለዋል፤ ይኼ አስማት አይደለም ሲሉም ሰምተናልና እንዴት ነው የሚሆነው?

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- አንድ ብር በአንድ ዶላር መመንዘር አስማት አይደለም፡፡ እንዴት እንደሆነ የምነግራቸው ግን ለሚኒስትሩ ነው፡፡ እሳቸው ከተስማሙ በኋላ የእሳቸው ፕሮጀክት ይሁን፡፡ አሁን መናገሩ ጊዜው አይደለም፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ የቡና ፌስቲቫል በየዓመቱ መካሔድ የሚችል ነው፡፡ በቀላሉ ከ10 ሺሕ ሰው በላይ ከውጭ ማሳተፍ ይቻላል፡፡ የተሳትፎ አስከፍሎ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ይቻላል፡፡ የመስቀል ፌስቲቫልም አለ፡፡ ብዙ ሰዎች እንዲመጡ ማድረግና ብዙ ገንዘብ ማግኘት ያስችላል፡፡ ፍልውኃውና ሌሎችም ሥራዎችን በደንብ መሥራት ከተቻለ ትልቅ ዕድገት ያመጣል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ሰዓት ‹‹ወላይታ›› የሚል ባህላዊ ክራቫት ሠርተዋል፡፡ ይኼንን ለመሥራት እንዴት ተነሣሱ?

አቶ ሀብተ ሥላሴ፡- አንድ ሰው ቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ ከገባ አይወጣም፡፡ በቃ እንደ ልክፍት በሽታ ሰውነት ውስጥ የሚገባ ነው፡፡ ጡረታ ብወጣም በተፈጥሮዬ ቁጭ ማለት ስለማልወድ ክራቫት ለመሥራት ሰዎችን አማከርኩ፡፡ አያዋጣም፤ አትሥራ አሉኝ፡፡ ካፒታል የለም እንጂ በብዛት ይሸጥ ነበር፡፡ ብዙ አምባሳደሮች ይገዛሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች ክራቫት ሲገዙ የምርቱን ዓይነትና መለያ እንጂ በላዩ ላይ ያለውን ሥዕል አይጠይቁም፡፡ ሰዎች የእኛን ከጥበብ የተሠራ ክራቫት ስንሰጣቸው ይኼ ምንድን ነው? ይላሉ፡፡ እኔም መንገድ አድርጌ እንጂ ለገንዘቡ ብዬ አይደለም፡፡ ከ25 ዓይነት በላይ ክራቫቶች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በእጅ ብቻ የተሠራ ክራቫት አለን፡፡ የወላይታ ሸማኔዎች ንድፉን ሰጥቻቸው ጥሩ ሠርተውታል፡፡ ግን ገና ጅምርና ጥናት ላይ ነኝ፡፡ አሁን ሁለት ፍሬ በእጅ የተሠራ አለ፡፡ አንዱን ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እሰጣለሁ፡፡ አውሮፓውያን ይኼንን ክራቫት በእጃቸው ብቻ መሥራት አይችሉም፡፡ እኛ በራሳችን ጥሬ ዕቃ እዚሁ በእጃችን መሥራት ችለናል፡፡