Thursday, May 23rd

English Version

Error
  • Error loading feed data.

‹‹የሴቶች ጉዳይ››

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

 

በምሕረት አስቻለው

‹‹የኦሮሚያ ሴቶች ጉዳይ ቢሮን በ1984 ወይም 1985 ዓ.ም. በምናደራጅበት ወቅት ወ/ሮ አልማዝ መኮ ወደ ውጭ አገር ሔደው ስለነበር እሳቸውን ወክዬ በአንድ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ፡፡

ከፊት ለፊቴ ከጠረጴዛ ላይ ወ/ሮ አልማዝ መኮ የሚል ጽሑፍ በወረቀት ላይ ይነበብ ነበር፡፡ የዚያ ስብሰባ ዘገባ በቴሌቪዥን ተላልፎ ስለነበር ከዚያ ወዲያ ወ/ሮ አልማዝ ወ/ሮ አሕመድ የሚለው ፍተላ አላስቀምጥ ብሎኝ ነበር፡፡›› ይህንን የሚሉት አቶ አሕመድ መሐመድ ተወልደው ያደጉት በአንድ የአገሪቱ ገጠር ነው፡፡ አባታቸው በእናታቸው ላይ ያደርሱ የነበረውን ጫና፣ በተመሳሳይ በአካባቢያችው በሚገኙ እናቶችና ሴት ልጆች ላይ ይደርስ የነበረውን ተጽዕኖ በመመልከት እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ የልብ ትርታቸው ሆነ፡፡

የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ማኅበረሰብ (ሶሽዮሎጂ)፤ ሁለተኛውን ደግሞ በሥነ ጾታ ጥናቶች አግኝተዋል፡፡ በኦሮሚያ ባህልና ስፖርት፣ በሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም በሌሎች ተመሳሳይ መሥርያ ቤቶች በኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ በፌዴራል የሕዝብ እንባ ጠባቂ የሴቶች፣ የሕፃናትና የአካል ጉዳተኞች ዴስክ ኃላፊ ሆነው በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ የኦሮሚያ የሴቶች ጉዳይ ቢሮን በማደራጀት ረገድ ሚናቸው ከፍተኛም ነበር፡፡

ቀዳሚውን ዲግሪያቸውን እንደሠሩ ወዲያው ‹‹አቻ የሌለው ፍቅር›› የተሰኘ በሴቶች ላይ የሚደርስን ተጽዕኖ የሚያሳይ መጽሐፍ አሳትመው አበርክተዋል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ የሚስተዋለው ስለሴቶች እኩልነት፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን ስለማስቀረት የሚነገረውና ቅስቀሳ የሚደረገው በሴቶች መሆኑ ነው፡፡ ጥቂቶች በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትና ሌሎች ተጽዕኖዎች የማኅበረሰቡ ችግር በመሆናቸው ለችግሮቹ መቀረፍም ሴቶችም ወንዶችም በእኩልነት ሊሠሩ እንደሚገባ ቢያምኑም ለሴቶች እኩልነት፣ በሴቶች ላይ የሚደርስን ተጽዕኖ ለማስቀረት የሚንቀሳቀሱ ወንዶችን (ወንድ የሥርዓተ ጾታ ባለሙያዎችን) እምነትና ትጋት በጥርጣሬ የሚመለከቱ ጥቂት አይደሉም፡፡

‹‹በመንገድ ላይ ወይም በታክሲ ውስጥ ወንድ ልጅ ሴትን ሲደበድብ ተመልክቼ የተጣላሁበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ የትምህርት ወይም የሙያ ጉዳይ ሳይሆን ውስጤ ከልጅነት ጀምሮ የተያዘበት ነገር በመሆኑ የትም ብሔድ በማንኛውም ሁኔታ ስለሴቶች ድምፄን አሰማለሁ፡፡››

እንደ አቶ አሕመድ ገለጻ፣ በሴቶች ላይ ጫና አሳዳሪዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችም ወንዶች በመሆናቸው መቀየር ያለባቸው ወንዶች ናቸው፡፡ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምህዳሩን በበላይነት የያዙት ወንዶች በመሆናቸው ለጾታ እኩልነትም ወሳኝነት አላቸውና ሁኔታውን ለመቀየር ወንዶችም አብረው ከሴቶች ጋር መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡

አብዛኛው ወንድ የሥርዓተ ጾታ አቀንቃኝ (gender activist) በጉዳዩ የሚንቀሳቀሰው በእውነትና በትክክል አምኖበት ነው ማለት ይቻላል? ስንል ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ ‹‹የሰው አመለካከቱ የተለያየ ነው፡፡ አንዳንዱ የተሻለ እንጀራ ያመጣልኛል በማለት ትምህርቱን ሊከታተል በዘርፉም ሊሰማራ ይችላል፡፡ በጣም ጥቂቱ ደግሞ ችግሩን ለመቅረፍ ይሠራል፡፡ ምን አልባት ብዙዎች ገቢ ላይ አተኩረዋል፡፡ ብዙውን ሰው ስንመለከት የመኖር ጥያቄ የገበያ ነገር ነው፡፡ በጣም ጥቂቶች ግን ሕመሙ ቀደም ሲል ጀምሮ ሲሰማቸው የነበሩ አሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሕመሙ በእኩል ደረጃ ይሰማው ለማለት ይከብዳል፡፡››

ሴት የሥርዓተ ጾታ አቀንቃኞች ከቤት ውጭ ስለ ሴት ልጅ መብትና እኩልነት እየሰበኩና ሌሎችን እያስተማሩ በቤታቸው ውስጥ ተመሳሳይ ጫናን ተቀብለው ይኖራሉ የሚል አስተያየት በብዙዎች በተደጋጋሚ ይሰነዘራል፡፡ አቶ አሕመድም ይህን በማስመልከት ‹‹ስለ ሴቶች መብትና እኩልነት የሚያስተምሩና የሚቀሰቅሱ ሴቶችን ተግባር እንዲሁም ኑሮ ስንመለከት ክፍተቶች ይገኛሉ፡፡ በውጭ ግን ሌሎችን ያስተምራሉ፡፡ ይህን ምሥጢር ከራሳቸው በቀር የሚያውቅ የለም፤›› ብለዋል፡፡

ጥቂት የማይባሉም በማኅበረሰብ ውስጥ ሴቶች ላይ የተለየ ጫና፣ የእኩልነት ጥያቄም ስለመኖሩ ይጠራጠራሉ፡፡ ወንዶች ብቻም ሳይሆኑ ሴቶችም ጭምር፡፡ የሴቶች ጉዳይ መነገር ያለበት በሴቶች ብቻ እንደሆነ የሚሰማቸውም አሉ፡፡ በተመሳሳይ የሥርዓተ ጾታ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን መሥራት በጀመሩበት ወቅት እሳቸውን ጨምሮ የሌሎች ወንድ ተማሪዎች በዚያ ክፍል መገኘት ብዙዎቹን የክፍሉን ሴት ተማሪዎች እንዴት? አስብሎ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎች ቢታዩም የወንዶች የሴቶች ጉዳይ መምርያ ኃላፊ ሆኖ መቀመጥ በበጎ የማይታይበት ሁኔታ መኖሩን፣ በአሁኑ ወቅትም እንደዚህ ያሉ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ የሚገኙት ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ ሴቶች መሆናቸውን ከአቶ አሕመድ ንግግር ተደርተናል፡፡

የሥርዓተ ጾታ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ቀድሞ ቢሯቸው በመግባታቸው ከቅጥር ጋር በተያያዘ እሳቸውን የገጠመ ምንም ችግር እንዳልነበር ቢገልጹልንም፣ የሴቶች ጉዳይ በሴቶች መነገር ነው ያለበት፤ በዚህ ረገድ በሚሠሩ ሥራዎችም ተቀባይነት የሚኖራቸው ሴት ባለሙያዎች ናቸው በሚል እሳቤ በቅጥር ላይ ችግር የገጠማቸው ወንድ የሥርዓተ ጾታ ባለሙያዎች እንደነበሩ ካነጋገርናቸው የተወሰኑ የሥርዓተ ጾታ ባለሙያዎች ለማወቅ ችለናል፡፡

‹‹የሥርዓተ ጾታ ጉዳይ የሴቶች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የሴቶችም የወንዶችም ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከአገራችን ዕድገትና ገጽታ ጋርም ግንኙነት አለው፡፡ ሴቶች እናቶች፣ እህቶች፣ ልጆችና ጓደኞቻችን ናቸው፡፡ ስለዚህ ችግሩን ለመቅረፍ ሁላችንም አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን፡፡››

ወ/ሮ ገነት አሸብር የሥርዓተ ጾታ ባለሙያ፣ ጋዜጠኛም ናቸው፡፡ ከሥርዓተ ጾታ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሥልጠናዎች ላይ አሠልጣኝ ሆነውም ይሠራሉ፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርስን ጫናና ተጽዕኖ ለማስወገድ በሚደረግ ጥረት የወንዶችን ተሳትፎ አስፈላጊነት ያምኑበታል፡፡ ጉዳዩ በሴቶችም በወንዶችም ቢነገር አስፈላጊውን ውጤት በቀላሉ ማምጣት እንደሚቻልም ይሰማቸዋል፡፡

‹‹የሴቶች እኩልነት፣ የሴቶች መብት ይጠበቅ፤ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጫና ይቁም፤ ሲባል ጉዳዩ ከወንዶች ጋር ፀብ መሆን የለበትም፡፡ ሴቶችም ወንዶችም ተወያይተውና ተማምነው በመተባበር የሚከተሉት አካሔድ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን ውጭ ስለ ሴት ልጅ መብት እየሰበከ ቤት ውስጥ ሚስቱን የሚረግጥ ስንቱ ነው? ወንዶችም ብቻ ሳይሆን ሴት የሥርዓተ ጾታ አቀንቃኞችን ስንመለከት ስንቱ ምክንያቱን ስለሚያምንበት፣ ስንቱስ ለገንዘብ? የሚለው ዛሬም ጥያቄ ነው፡፡››

እንደ እሳቸው እምነት፣ የወንዶች ተሳትፎ ከሥርዓተ ጾታ ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ረገድ የመንቀሳቀስና አስተዋጽኦ የማድረግ ከሆነ መልካምና የተቀደሰ ሐሳብ ነው፡፡ ነገር ግን አጠቃላይ እንቅስቃሴውን የመምራትና በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በሌሎችም ዘርፎች የበላይ እንደሆኑት ተመሳሳይ አመራርና የበላይነት  የመፍጠር አካሔድ ከሆነ ችግር ይሆናል፡፡ ስለዚህም በጉዳዩ ግንባር ቀደምና መሪ መሆን ያለባቸው ሴቶች ናቸው፡፡