Wednesday, Jun 19th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ዓባይ-ግልብጥ

E-mail Print PDF
User Rating: / 0
PoorBest 

 

የምንሳፈፍበት-ባሎን ሠራሁና

ከጀት ፈጥኜ
ከሚግ ተወርውሬ-
ከሮኬት በልጬ
ከራዳር አምልጬ
ሽቅብ ወጣሁና…


ከቬኑስ አቅራቢያ - አንዲት ትንሽ ጎጆ - አበጀሁኝና
በምፈልገው ልክ - ውስጧን ከፋፍዬ - አጸዳሁኝና
ማጀቱን ሳሎኔ - መኝታውን ጓዳ - ማብሰያውን
ሰርቪስ አደረኩኝና፤
ያችን ትንሽ ጎጆ - ወዲህ ወደዚያ
እንደ ሕፃን ዳዴ - እያልኩ እየቦረኩ
እንደ አምቦሳ ጥጃ - ውስጧ እየፈረጠጥኩ
የቅጽበትን ዕድሜ - የአፍታን ዘመን ታሪክ
ውስጧ አሰፈርኩና
ባሎኔን ገጥሜ - መንሳፈፍ ጀመርኩኝ፡፡
ቆይቼ…
ቁልቁል ተንደርድሬ - ወደታች ስመጣ
ያችን ትንሽ ጎጆ - ብቻዋን ጠፈር ላይ
ከምተዋት ብዬ
‹‹ላፍርሳት? ልተዋት?›› - በሚል መንታ ሐሣብ
ልቦናዬ ታሞ
እያቀሰትኩ ሳለ…
ዓይኔን ተወርውሮ - ተምዘገዘገና
ከውቅያኖስ ይልቅ
ከባሕራት ይልቅ
እንደ እናት መቀነት ከተጠመጠመው ዓባይ ላይ ተሰካ፤
ዓባይን ከእናቱ - ከላዩ ላይ ሆኜ ቁልቁል ሳስተውለው
ሳየው ሳየው ሳየው - ሳየው ቆየሁና
ከተረገዘበት - ከተጸነሰበት - ከተወለደበት
ከእናቱ ሆድ ጣና
አሻፈረኝ ብሎ - ኮተቱን ጠቅልሎ
በጉያው ሸሽጎ - በሆዱ ስር አዝሎ
አብስ የማለቱ - ጭልጥ የማለቱ
ምሥጢሩ ረቆብኝ
መላው ብልሃቱ - ስውር ብሎብኝ
ማሰቢያ አእምሮዬን - ጠይቄ ጠይቄ
ድንገት አንዲት ሐሳብ - ብልጭታዋ ባርቆ
እንደ ሀሌ ብርሃን - ከራዕይ ተደባልቆ
ጸጥታን ደርምሶ - ዝምታን ሰንጥቆ
ከልቤ ልብ ላይ - ተቀበቀበና
ያስቃስተኝ ጀመር - ከአለሁበት ስፍራ
ከመሬት ወደላይ - ከሰማይ ወደታች
እንዲያ ስፍጨረጨር…..
ይሄ ነው ያላልኩት - የሺሕ ፈረስ ጉልበት
የሺሕ ቦንብ ፓወር
የሺሕ ነገር አቅም
በውስጤ አመቀና
እጄን በረጅሙ-ቁልቁል ወደ ምድር
ዘረጋሁኝና
ጣቴን ወደ መሬት - ሰገሰግኩኝና
አንድ እጄን ከአናቱ - አንድ እጄን ከግርጌው
አመቻቸሁና
ከተጣበቀበት - ከአፈሩ ሰቅስቄ
በኃይሌ አላቅቄ
እንደ ጨቅላ ሕፃን - ዓባይን ታቀፍኩት፡፡
በድዱ እየሳቀ - ቀልብ እንደሚነሳ
እንደ ድንቡሼ ልጅ - በክንዴ እንደያዝኩት
ዓባይን ጉንጩ ላይ  - እጅና አንገቱ ስር
ሳም ሳም አረኩት፡፡
ድንቡሼውን ስሜ - ያንገቱን ስር ሽታ
ምጌ እንደጠገብኩኝ
አቅጣጫ ቀይሬ፡-
ሜድትራኒያንን መወለጃ እትብቱ
የሚቀበርበት
ጣና ባሕር ዳርን - ጉዞ ሚያበቃበት
ግብፅና ሱዳንን - መንገዱ ማለፊያው
አፈር ሚያዝልበት
ኢትዮጵያችን ደግሞ - ቁልል ለም አፈሩን
የሚያራግፍበት
አድርጌ አስተኛሁት - ዓባይን በጀርባው
ያስወጣውን ሁሉ - መልሶ እንዲያስገባው!

(ደመቀ ከበደ፤ አንድ ክንፍ፣ 2003 ዓ.ም.)

*********************

ጦርነት

‹‹ስጋ አማረኝ አለች የቀለቤ እናት
መተማ አትሄድም ወይ ከታረደበት››

ሁላችንም እንደምናውቀው ሕይወት የተለያዩ ለመኖር የሚያስፈልጓትን ሁኔታዎች እያበራከትንላት እንደመጣን ሁሉ በየቀኑ እያደጉ የመጡ ብዙ ችግሮች፣ ውስብስብና ብሎም የተገደበች መሆኗን ነው፡፡

ለሁሉም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃዎች የጦርነት ክስተት ራስን የማጥፋት ጥሩ ምሳሌያዊ ትዕይንት ሊሆን ይችላል፡፡

አልበርት አንስታይን ሲግመንድ ፍሮይድን በጦርነት ውስጥ ስለሚኖሩት ሥነ ልቦናዊ መርሆዎች አስመልክቶ የሚከተለውን ጥያቄ አቀረበለት፡- ጥቂት ገዢዎች ብዙኃኑ በማስገደድ በምላሹ የሚሰቃይበትንና ሕይወቱን የሚያጣበትን ዓላማ ተመልካች ሊያደርጉት እንዴት ይችላሉ? ለምን ብዙኃኑ በዚህ መንገድ በፈቃደኝነት ራሳቸውን በዕብደት አቅጣጫና ራስን አሳልፎ በመስጠት ይለበለባሉ? ጥላቻና ጥፋት በተፈጥሮ የሰውን ልጅ በመምራት የሚያረኩ እነኚህም በማንኛውም ጊዜ ራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩ ሆነው ነገር ግን በቀላሉ ተነሳስተውና ተስፋፍተው ወደ ብዙኃኑ የአእምሮ ሕመምን የሚያመላክቱ ናቸውን?  ለእነኚህ ማንነትን የሚያሳጣ የጥላቻና የጥፋት የአዕምሮ በሽታ ተቃዋሚ በብዛት በመፍጠር የሰውን ልጅ ዕድገት ከሕገ ተፈጥሮ ውጪ ለመቀየር ይቻላልን?

ፍሮይድም ከረጅም ዓመታት የክሊኒካል ግኝቶች በመነሣት አጠቃላይ ምላሹን ከዚህ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡፡ በርግጥ መብት ቀድሞውንም ምናልባት አሁንም ቢሆን ያለ ኃይል ድጋፍ ሊኖር አይችልም፡፡ የጥላቻና የጥፋት ተፈጥሯዊ ስጦታ ለመኖሩ ፍሮይድ በአዎንታዊ አባባል እርግጥ ነው ብሎ መልሷል፡፡ ለመጣላት ፈቃደኛ መሆን በተለያዩ ዓይነት አነሳሾች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለምሳሌ ሞቅ ባለ አቀራረብ፣ በግልፅ በመናገር ወይም ሊጠቀሱ በማይችሉ ሁኔታዎች ጠብ በመጫርና በጥፋት ደስታን ማግኘት በትክክል ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው ነው፡፡ ከእነዚህ የጥፋት አዝማሚያዎች የሚመነጭ ወይም የሚገኝ እርካታ በሌሎች ይቀይራሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሐሳባዊ አነሳሾች ስር በመውደቅ በቀላሉ የተፈጥሮ ውድመቶች የሚታዩበት የእይታ ሰሌዳ ሲስበን በሌላ ጊዜ ደግሞ በጣም የሚታወቁና የጥፋት መሪዎቹ ለራሳቸው ላልታሰቡት ምክንያቶች ዕርዳታ በማድረግ ይሆናል፡፡

(ንጉሡ አጥናፉ፤ ሕይወት ግዛቷ ሲጣስ፣ 2003 ዓ.ም.)

***********

የምናየው እንዴት ነው?

ከጓደኞቻችን ጋር ተቀምጠን ስናወጋ አንዱ የቆዩ ፎቶግራፎች አልበም ሲያወጣ፣ ተቀብለነው እንገልጠዋለን፡፡ በድንገትም የድሮ የትምህርት ቤት ጓደኞቻችንን ፎቶግራፍ ልናገኝ እንችላለን፡፡ ያንን ለብዙ ጊዜ ያላየነውን ልጅ ምስል እንዴት እንዳስተዋልነው አናስበውም፡፡

መጀመርያ ብርሃን ፎቶግራፍ ላይ ማረፍ አለበት፡፡ በዚህም ጊዜ ፎቶግራፍ ብርሃኑን ያንጸበርቅና በተለያየ አቅጣጫ ይበትናል፡፡ ከዚህ ብርሃን ጥቂት ወደ ዓይናችን ይገባል፡፡ ዓይናችንም የፎቶግራፉን ተመሳሳይ ምስል በሬቲናችን ላይ ይፈጥራል፡፡ ምስሉ በአግባቡ ቁልጭ ብሎ እንዲታየን ዓይኖቻችን ተንቀሳቅሰው የልጅ ፊት ምስል ልክ በማኩላው (አጥርቶ የሚያሳየው የሬቲና ክፍል) ላይ ማሳረፍ አለባቸው፡፡ ስለዚህ ለዓይኖቻችን ማንቀሳቀሻ መንገድ መኖር አለበት፡፡

ሳናረጅና ገና ማንበቢያ መነጽር ሳያስፈልገን የዓይኖቻችን ሌንሶች በራሳቸው ውፍረታቸውን በመጨመርና በመቀነስ ምስሉን ማኩላው ላይ ቁጭ ያደርጉታል፡፡

ምስሉ ማኩላው ላይ እንዳረፈ ወደ ነርቭ ንዝረት ተቀይሮ ወደ አንጎል ይሄድና እዚያ ይተረጎማል፡፡

አንድን ፎቶግራፍ በፀሐይ ብርሃን ወይም በቤት ውስጥ መብራት ስንመለከተው ወደ ዓይናችን የሚገባው የብርሃን መጠንና ቀለማት በእጅጉ ይለያሉ፡፡ ይሁን እንጂ አንጎላችን ሁለቱንም ምስሎች ተመሳሳይ አድርጎ ያያቸዋል፡፡ ምክንያቱም ፌቲናችን በረቀቀ መንገድ የሚገባውን ብርሃን ያጣራዋል፡፡ ይህም የተጣራ መረጃ ወደ አንጎል የማያ ክፍሎች ይደርሳል፡፡ እነዚህም የአንጎል የዕይታ ክፍሎች እንደ አቅጣጫ፣ እንቅስቃሴ፣ ቀለም፣ ርቀት፣ የብርሃን ኃይልና የመሳሰሉትን በማገናዘብና በመመርመር አንጎል ውስጥ እንደገና የራሱን ሌላ ምስል ይፈጥራል፡፡ እንዲህ ያለውን ረቂቅ አካሄድ አብዛኞቻችን እንዲያው ልብ አንለው ይሆናል፡፡

(ዶ/ር አበባ ተክለ ጊዮርጊስ እና ሌሎች፤ ግላኮማ፣2002 ዓ.ም.)

**************************

ከበር

‹‹ዓርብ›› የአሜሪካ ባንኮች የሚዘረፉበት ዝነኛው ቀን

በደቡባዊውና በምሥራቃዊው ግዛት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ባንኮች ላይ የተጧጧፈ ዝርፊያ ከሚፈጸምባቸው ዕለታት ባብዛኛው ዓርብ ረፋዱ ላይ በመሆኑ ዕለቱ ‹‹ዝነኛው ዓርብ›› ተብሎ ተሰይሟል፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ በአገሪቷ ከሚገኙ ባንኮች፣ የገንዘብ ተቋሞችና የብድር አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች 43 ሚሊዮን ዶላር ተዘርፏል፡፡ ዘራፊዎቹ ደግሞ በተለያዩ ባንኮች ላይ ጥቃቱን የሰነዘሩ ሲሆን፣ የተደረጉት የዝርፊያዎች መጠንም 5,446 እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ስለተፈጸሙት ዝርፊያዎችና ስለ ዕለተ ዓርብ እንዲህ እያብራራ የሚያስረዳው ኤፍ ቢ አይ ሲሆን፣ ዝርፊያዎቹ የተጧጧፈባቸው የአገሪቷ ግዛቶችም ደቡባዊውና ምዕራባዊው ክፍል እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም በደቡባዊው የአገሪቷ ግዛት ውስጥ ከሚገኙት የገንዘብ ተቋማት ላይ ብቻ 1,790 ዝርፊዎች በመከናወናቸው አካባቢው መሪነቱን ሲቀዳጅ፣ በምዕራባዊው ግዛት ስር የሚገኙት የገንዘብ ተቋማት ላይ ደግሞ 1,691 ዝርፊዎች በመፈጸማቸው ክፍሉ ተከታይ ሆኗል፡፡

ይህ በደቡብና በምዕራብ የተከፋፈለው ዝርፊያ ካሊፎርኒያ ከምዕራብ፣ ቴክሳስ ደግሞ ከደቡብ ግዛት በርከት ያለ ዝርፊያ እንደሚፈጸምባቸው ተገልጾ፣ የዝርፍያዎቹ መጠንም 805 እና 464 ናቸው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ከአገሪቷ በሰሜናዊው ክፍል የምትገኘው ሰሜን ዳኮታ ላይ ደግሞ እጅግ ዝቅተኛ ዝርፊያ እንደተመዘገበም ተገልጻEል፡፡

እንደ ኤፍ ቢ አይ መረጃ በአገሪቷ አጠቃላይ 5,628 የባንክ ዝርፊያዎች እንደተፈጸሙና ከዚያም ውስጥ 74 የሚሆኑት ዝርፊያዎች በሌቦች የተከናወኑ ሲሆን 13 የሚሆኑት ደግሞ በገንዘብ ተቋሞች ውስጥ የሚገኙ አካላት ሥልጣናቸውን በመጠቀም የተከናወኑ ዝርፊያዎች እንደሆኑም ታውቋል፡፡

ይሁንና በፈረንጆች አቆጣጠር በ2009 የተደረጉት አጠቃላይ ዝርፊያዎች 6,065 የነበሩ ሲሆን፣ ባሁኑ ሰዓት ያለው የዝርፊያ መጠን ቀንሶ ቢታይም ምክንያቱ ግን ምን እንደሆነ በግምት መናገር እንደማይቻል የኤፍ ቢ አይ ቃል አቀባይ ዳኒስ ገልጸዋል፡፡

************


የኒውዮርክ አይጦች የአገሪቱን ቱሪዝም እያበላሹ ነው

በኒውዮርክ የምትገኘውና ከፍተኛ የንግድ፣ ፋሽንና የተለያዩ ሞቅ ደመቅ ያሉ እንቅስቃሴዎች በሚካሄዱባት ማንሃታን የሚተራመሱት አይጦች፣ የከተማዋን የቱሪዝም ገቢ በማቀዝቀዛቸው፣ እነርሱን ለማጥፋት 1.5 ሚሊዮን ዶላር በከተማዋ በጀት ስር እንደገና ሊመደብ እንደሚገባ የአንድ ወረዳ ፕሬዝዳንት የሆኑት ስካት እንደገለጹ ሮይተርስ አስነብቧል፡፡

እነዚህ በየጎዳናውና በየባቡር መንገዱ የሚሯሯጡትና ለተመለከታቸውም የሚዘገንኑት አይጦች፣ ከተማዋን ለመጎብኘት የመጡትን ቱሪስቶች እንዲሸማቀቁና መጥፎ ስሜት እንዲፈጠርባቸው ስለሚያደርግ የከተማዋ የቱሪስት ፍሰት እንዲቀንስ ምክንያት እንደሆነ ስካት ገልጸዋል፡፡ በሁኔታው ያዘኑት ስካት፣ ‹‹ጎብኚዎች ወደ እዚህች ከተማ መጥተው የዕረፍት ጊዜያቸውን ከኒውዮርክ አይጦች ጋር እየተጋፉ ማሳለፍ አይፈልጉም፤›› ብለዋል፡፡

አይጦችን የመቆጣጠሩ ሒደት ለከተማዋ የጤና ክፍል በጀት ውስጥ ተካትቶ ተመድቦ ነበር፡፡ ይሁንና የነበረው በጀት በመቀናነሱ የጉዳዩ ተሳታፊ መሆን የሚገባቸው 57 የተባይ ማጥፋትና መቆጣጠር ሥራን የሚያከናውኑ አካላት እንዳይሳተፉ ምክንያት በመሆኑ፣ በከተማዋ የነበረው የአይጥ ብዛት በ1.5 በመቶ እንዲያድግ ሆኗል፡፡ በመሆኑም አይጦቹ ለሰዎች ጤና አደገኛ ከመሆናቸው ባሻገር፣ በልጆች ጤና ላይም ከፍተኛ አደጋን እንደሚፈጥሩም ተገልጿል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አክለውም2 የከተማዋ የተባይ መቆጣጠርና መከላከል ፕሮግራም ክፍል፣ ከሕንፃ ባለቤቶች በየዓመቱ ለተባይና ተባይ ነክ ለሆኑ ችግሮች ለመከታተያና ማጥፊያነት እንዲውል በሚል፣ ስድስት ሚሊዮን ዶላር የሚሰበስብ ቢሆንም ከተማዋ አሁን ላለችበት ችግር ግን በተቆራረጠ በጀት መፍትሔ መስጠት መፈለጉ ስሜት የማይሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡