ባለፈው ሐሙስ ብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ በሚገኝ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ የታጠቀ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ 12 ተማሪዎችን ገደለ፡፡
ተማሪው 12 ተማሪዎችን ከገደለ በኋላ የራሱን ሕይወት ማጥፋቱን ፖሊስ ተናግሯል፡፡ የብራዚል ባለሥልጣናት በብራዚል ታሪክ እንደዚህ ዓይነት አሰቃቂ የትምህርት ቤት ግጭት ደርሶ አያወቅም ሲሉ ድርጊቱን ገልጸውታል፡፡ የብራዚል ፕሬዚዳንት ዳይልማ ሮሴፍ እንባቸውን አቅርረው እንዳሉት፣ እንደዚህ ዓይነት ወንጀል የዚህች አገር መገለጫ አይደለም፡፡ ዌልንግተን ሜንሰስ ዴ ኦሊቬራ የ23 ዓመት ወጣት ሲሆን፣ በከፈተው ተኩስ 10 ሴትና 2 ወንድ ተማሪዎችን ገድሏል፡፡
*******************
ኔቶ በስህተት ተቃዋሚዎችን ደበደበ
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) በሊቢያ በስህተት ተቃዋሚዎች ላይ የአየር ጥቃት አድርሷል፡፡ ተቃዋሚዎችም በስህተት የተፈጸመው የኔቶ ጥቃት ለጋዳፊ ወታደራዊ ኃይሎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሳያደርግ አልቀረም ብለዋል፡፡ ባለፈው ሐሙስ በደረሰው ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች ሲሞቱ፣ ከ20 በላይ ተቃዋሚዎች ቆስለዋል ተብሏል፡፡ በጥቃቱም የተቃዋሚዎቹ ታንኮች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡ የኔቶ በሊቢያ ያለው ዘመቻ ምክትል ኮማንደር፣ የጥምረቱ ኃይሎች በስህተት አጅዳቢያ ጠረፍ ላይ ጥቃት እንዳደረሱ አምነዋል፡፡ ሆኖም ተቃዋሚዎቹ የጋዳፊን ታንኮች ይጠቀሙ እንደነበር ምንም ዓይነት መረጃ እንዳልነበራቸው ገልጸዋል፡፡
*******************
እስራኤል ከስምምነቱ በኋላ ሁለት የሀማስ ሚሊሻዎችን ገደለች
እስራኤል ከተኩስ ማቆም ስምምነቱ በኋላ ባለፈው ዓርብ በጋዛ ላይ ባደረገችው የአየር ጥቃት ሁለት የሀማስ ሚሊሻዎችን ገደለች፡፡ እስራኤል ጥቃቱን የሰነዘረችው ሐሙስ የሀማስ ሚሊሻዎች በትምህርት ቤት አውቶቡስ ላይ የተኮሱት ሚሳኤል አንድ ሕፃንን ክፉኛ አቁስሎ ሾፌሩ ላይ መጠነኛ ጥቃት ካደረሰ በኋላ ነው፡፡ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትኒያሁ እንዳሉት፣ ሁኔታው በዚሁ ይቀጥላል፡፡ ማንኛውም አስፈላጊ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አንልም፡፡ ዜጎቻችንንም ለመጠበቅ ራሳችንን ከመከላከል አንስቶ ጥቃት እስከመፈጸም ድረስ እንጓዛለን ብለዋል፡፡
*****************
አሜሪካ ለየመን የምትሰጠውን ዕርዳታ አቋረጠች
አሜሪካ በየመን ከተከሰተው ሕዝባዊ አመጽ በፊት በመጠኑ ከፍተኛ የሆነውና ለአገሪቱ ሊሰጥ ታስቦ የነበረውን ዕርዳታን መቋረጧ ታወቀ፡፡ አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የአሜሪካ ባለሥልጣን እንዳሉት፣ አዲሱ ዕርዳታ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን፣ እርዳታው በአሜሪካና በየመን መካከል ሽብርተኝነትን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ ነበር፡፡ አሜሪካም የዕርዳታውን የመጀመርያ ኮታ የካቲት ላይ ትለቃለች ተብሎ የተጠበቀ ሲሆን፣ ይህ አልቃይዳን ለመዋጋት ለፕሬዚዳንት አሊ አብዱላህ ሳላህ መንግሥት የሚሰጥ ትልቁ ዕርዳታ ነበር፡፡


