ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገችው ያለችውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት የኮሪያ ሪፐብሊክ ትብብር እንድታደርግላት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን በጽሕፈት ቤታቸው በኮሪያ የውጭ ጉዳይና ንግድ ሚኒስትር ኪም ሱንግ ሁዋን የተመራውን ቡድን ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ የምታካሂደውን መጠነ ሰፊ ዕቅድ ከግብ ለማድረስ የአገሪቱን ሁለገብ ድጋፍ ትሻለች፡፡ ኮሪያ ለአምስት ዓመታት የተያዘውን ዕቅድ በመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታ በተለይም በመንገድና በባቡር መስመሮች ግንባታ፣ በግብርና፣ በማዕድንና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስኮች ያላትን የካበተ ልምድ በማካፈልና በመሳተፍ ኢትዮጵያን እንድትረዳ መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲን ዋቢ በማድረግ ዘገባው ገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ የተሳተፈችበትን የኮሪያ ጦርነት የተጠናቀቀበት 60ኛ ዓመት ክብረ በዓልን በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ በልዩ ዝግጅት ለማክበር መታቀዱን በዘገባው ተመልክቷል፡፡
* * *
የዓለም ባንክ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 8.1 ሚሊዮን ብር ሰጠ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ለዳያስፖራ ተሳትፎ ፖሊሲ ዝግጅት ማስፈጸሚያ የሚውል 8.1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አገኘ፡፡ በሚኒስቴሩ የዳያስፖራ መረጃና ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወልዴ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገር ልማት ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል ተቋማዊ አሠራር ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከዓለም ባንክ በድጋፍ መልክ የተገኘው ይኼው ገንዘብ ሚኒስቴሩ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ፖሊሲ ዝግጅት ማስፈጸሚያና የመረጃ ቋት ለማደራጀት የሚውል ነው፡፡
* * *
በኢትዮጵያውያን አያያዝ ላይ ከሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ተደረገ
በሳዑዲ ዓረቢያ ጄዳ ቆንስላ ጄኔራል አምባሳደር መርዋን በድሪ የኢትዮጵያውያንን አያያዝ በተመለከተ ከሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ለኢዜአ እንዳስታወቀው፣ አምባሳደር መርዋን በጂዳ የጄዛን ግዛት አገረ ገዥን ልዑል መሐመድ ቢን ናስር አብዱል አዚዝን ጄዛን በሚገኘው ቤተ መንግሥት በመገኘት አነጋግረዋቸዋል፡፡ አምባሳደሩ በጄዛን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አያያዝና ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በተመለከተ ከአገረ ገዢው ጋር መወያየተቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡ ከውይይታቸው በኋላም የኢትዮጵያውያንን ተጨባጭ ሁኔታ በማጥናት የመፍትሔ አማራጭ ሐሳቦችን የሚያቀርብ ኮሚቴ በከተማዋ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብና ከጄዛን አገረ ገዥ መሥርያ ቤት መሰየሙ ተጠቁሟል፡፡
* * *
ፓርላማው የፋይናንስ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አፀደቀ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሐሙስ ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ስብሰባ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል የተደረገውን የፋይናንስ ስምምነት ረቂቅ አዋጅ መርምሮ አፀደቀ፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው፣ የተፈረመው ስምምነት ለመሠረታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ ድጋፍ ለምዕራፍ ሁለት መርሐ ግብር ማስፈጸሚያ የሚውል ነው፡፡ በመርሐ ግብሩ የመጀመሪያው ምዕራፍ ከአገሪቷ የልማት አጋሮች በተገኘ የፋይናንስ እገዛ የፌዴራል መንግሥት ለብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት የሚመድበውን የበጀት ድጋፍ ከፍ እንዲል የረዳ መሆኑን ምክር ቤቱ መግለጹን ዘገባው አስረድቷል፡፡ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ድጋፍ መርሐ ግብር ቀደም ሲል የልማት አጋሮች ይሰጡት የነበረው የቀጥታ በጀት ድጋፍ ሲቋረጥ መንግሥት የዘረጋው የልማት አጀንዳ እንዳይደናቀፍ የተዘጋጀ የፋይናንሲንግ መርሐ ግብር መሆኑ ተገልጿል፡፡


