Thursday, Jun 20th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

ይከራያል! የለቅሶ ቤት፣ የሬሳ ሳጥን . . .

E-mail Print PDF
User Rating: / 1
PoorBest 

በብሩክ ገብረ መድኅን እና በቴዎድሮስ ክብካብ

ወይዛዝርቱ በተላበሱት ሙሉ ጥቁር ልብሳቸው ላይ ጥቁር ሻርፕ ደርበዋል፡፡ ጥቁር መነፅርም አድርገዋል፡፡ ወንዶቹም ጥቁር ሱፍ ተላብሰው ነበር፡፡ ተለቅ ተለቅ ያሉ እናቶች በጥቁር ልብሳቸው ላይ ነጠላ ደርበዋል፡፡ ዘመናዊ ከሚባሉ መኪኖች ከሚወርዱት ለቀስተኞች የሚወጣው መልካም መአዛ አካባቢውን አውዶታል፡፡

ከቀብር መልስ ነበርና እጃችንን እየታጠብንና ንፍሮ እየዘገንን ወደግቢው ዘለቅን፡፡ ግቢው ፀዳ ያለ ነበር፡፡ መኖርያ ቤቱም እንዲሁ፡፡ ከመኖርያ ቤቱ አንደኛው ክፍል በመግባት ለለቀስተኛ ከተዘጋጀው ምግብ እያነሣን በሳሎን ቤቱ ከተደረደረው ወንበር ተቀመጥን፡፡ በግቤው ውስጥ ድንኳን አልነበረም፡፡ የሚያስተናግዱትም የአካባቢው የሚመስሉ ነዋሪዎች ሳይሆኑ የቤተሰብ የቅርብ ወዳጆች ነበሩ፡፡

የተዘጋጀውን ምግብ ከበላን በኋላ በጨዋታ ጨዋታ የለቅሶ ቤቱ የኪራይ መሆኑን ሰማሁ፡፡ የለቅሶ ቤት በኪራይ መኖሩ ግን እንግዳ ሆኖብኝ ነበር፡፡ በመሆኑም ክሥተቱ አዲስ ስለሆነብኝ ለቀስተኞቹንና አከራይዋን አነጋገርኩኝ፡፡

ላለፉት 22 ዓመታት ኑሮውን ከእናቱ፣ ከሦስት እህቶቹና ከአንድ ወንድሙ ጋር በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው ተክሌ ሀብተ ወልድ ታላቅ ወንድሙ ኢንጂነር ቴዎድሮስ ሀብተ ወልድ ባለፈው ወር ማገባደጃ ላይ በመኪና አደጋ ሕይወቱ ያለፈው በአዲስ አበባ ነበር፡፡ መርዶውን ካሉበት ሆነው ቢሰሙም እዛው ለመቀመጥ አልወሰኑም፡፡ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ለአንድ ሳምንት አዲስ አበባ በመምጣት ቀብሩን ማስፈጸምና ሠልስቱንና አስራ ሁለቱን ማውጣት እንዳለባቸው ይወስናሉ፡፡

የለቅሶ ሥነ ሥርዓቱን አዲስ አበባ ለማከናወን በአዲስ አበባ ቤት ላልነበራቸው የተክሌ ቤተሰቦች ለችግራቸው መውጫ የሆናቸው አዲስ አበባ ባለ ጓደኛቸው በኩል የተገኘው የኪራይ ለቅሶ ቤት ነው፡፡

ተክሌ ኢትዮጵያ ያሉ ወዳጁ ጋ በመደወል የወንድሙን መሞት ነግሮ የለቅሶ ቤትና ሌሎች አሰፈላጊ ቁሳቁሶችን እንዲከራይለት በመጠየቁ በቀን 1500 ብር የሚከራይ የለቅሶ ቤት መስቀል ፍላወር አካባቢ ይገኝለታል፡፡ ለተክሌና ቤተሰቦቹ እፎይታ ነበር፡፡

‹‹ከአሜሪካ ስንመጣ ሦስት ቀን አስበንና ሰልስቱንም አውጥተን ለመመለስ ቢሆንም 12 ቀን ማውጣት የሚል የለቅሶ ባህል ስላለ ለ12 ቀን ከፍዬ ተከራየሁ›› ሲልም ተክሌ አወጋኝ፡፡

እነተክሌ ለቅሶ ቤቱን ያለምንም ቁሳቁስ ቢከራዩም ለለቅሶ ቤቱ አስፈላጊ የሚባሉ የምግብና ሌሎች ቁሳቁሶች በማቅረብ ስትሠራ ያገኘናት ወ/ት መሠረት አክሊሉ  ስለሁኔታው አስረዳችኝ፡፡

ለምግብ እና መስተንግዶ ለመስጠት በሰው ለአንድ ጊዜ 60 ብር እንደምታስከፍል የምትገልጸው መሠረት ምግብ አዘጋጅቶ ከማቅረብ ባሻገር ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ ለስላሳ መጠጦች ናብኪንና አልፎ አልፎም ቢራም እንደምታቀርብ አጫወተችኝ፡፡

የለቅሶ ቤት ኪራይ በተመለከተ ላነሣሁላት ጥያቄ ‹‹በፊት በፊት  ድንኳን መከራየት፣ እንጀራ መግዛትና ለሐዘንተኛው ወጥን ሠርቶ ማቅረብ የተለመደ አልነበረም፡፡ ሁሉም ነገር በዕድር በኩል ይከናወናል፡፡ አሁን ዘመኑ እየተለወጠ ነው፡፡ ወደፊት ቤት ተከራይቶ ለቅሶን በጥቂት ቀናት ማከናወን መለመዱ አይቀርም፤›› ብላለች፡፡

በለቅሶው ቤት ውስጥ ሲያስተዛዝኑ ያገኘናቸው ወ/ሮ አልማዝ በረዳ ለቅሶን በኪራይ ቤት ማከናወኑ ከዚህ በፊት ያጋጠማቸው ክሥተት መሆኑን፣ አንድ በጀርመን ይኖሩ የነበሩት ወዳጃቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የሟች ባለቤት በቤቷ ለቅሶዋን ስትቀመጥ ከጀርመን የመጡት የእንጀራ ልጆቿ ለብቻቸው ለቅሶ መቀመጥ በመፈለጋቸው ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ ለለቅሶ የሚሆን ቤት ለ12 ቀን ያህል በመከራየት ለቅሶዋቸውን እንደተወጡ አስረድተውኛል፡፡

ይህንን የለቅሶ ቤት ኪራይ ሁኔታ በወቅቱ ስንወያይ የሰሙና ሁኔታው እጅግ አግራሞት የፈጠረባቸው አቶ ዓለሙ አረጋ የተባሉ አዛውንት፣ ‹‹ቤትን ለለቅሶ ቤት ማከራየት እጅግ ለህሊና ይከብዳል›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በወቅቱ ውይይታችንን በጥሞና ሲከታተል የነበረ ሲራክ ሞገስ የተባለ ጎልማሳ   ከአሰርት ዓመታት በፊት የፍሥሐ በላይ ይማምን ‹‹አልቃሽና ዘፋኝ›› የሚለውን ቴአትር አስታውሶ፣ ‹‹መቼም ለሠርግ ቤት ሙሽሮች እንደሚከራዩ ሁሉ፣ ለለቅሶም ቤትም መከራየቱ ምን ችግር ይፈጥራል?›› ሲል ይጠይቃል፡፡

እዛው የለቅሶው ታዳሚ የነበሩ የአዲስ አበባ ነዋሪ የለቅሶ ቤት መከራየት ከውጭ ለመጡ ብቻ  ሳይሆን፣ እዚያው አዲስ አበባ የሚኖሩም የሚያደርጉት መሆኑን ነግረውኛል፡፡ በመሥርያ ቤት ውሏቸው ከፍተኛ ኃላፊነት ሆነው እዚህ ግባ የማይባል ቤት ያላቸውና ማንነታቸውን የሚደብቁ ሰዎች ሐዘናቸውንም ሆነ ደስታቸውን የራሳቸው ባልሆኑ ሥፍራዎች ማከናወን እንደሚፈልጉ ገልጸውልኛል፡፡

‹‹የቅርብ ጓደኛዬ የሆነ ሰው አባቱ ሲሞቱ ቤቱን የመሥርያ ቤት ሰዎች እንዲያዩበት ስላልፈለገ በሚስቱ ቤተሰቦች ቤት መቀመጡን አስታውሳለሁ፡፡ ስንወጣ የምንሸፍነውን የእኛነታችንን ገመና የሚያወጣውኮ ለቅሶ ነው፤›› ሲሉም አክለውልኛል፡፡

የሥነ ማኅበራዊ ጥናት የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት አቶ ገዛኸኝ አዳሙ ቤትን ለለቅሶ ቤትነት ማከራየትን ከዚህ በፊት ሰምተው የማያውቁ ቢሆንም፣ ማኅበራዊ ተጋብሮ በየጊዜው እየተለወጠ የሚኖር በመሆኑ ክሥተቱ ሰዎች ለገቢ ማግኘት ሲሉ ቤታቸውን ማከራየቱ ከዚህ በፊት እንደነበሩ ለውጦች ኅብረተሰቡ ተቀብሎት ሊሔድ እንደሚችል ያላቸውን ሙያዊ ግምት ያስረዳሉ፡፡ 

‹‹በዚሀ ዘመን ሰው ገንዘብ ለማግኘት በርካታ ሥራዎችን የሚሠራ ቢሆንም  ቤትን ለለቅሶ ቤትነት ማከራየት ግን አሁን ላለው ማኅበረሰብ ለመቀበል የሚከብድ ቢሆንም›› የምትለው መሠረት፣ ‹‹የኪራዩ ገንዘቡ ፈጥኖ የሚመጣ በመሆኑና አከራዩም በወቅቱ ለሚፈልገው ጉዳይ ስለሚያውለው ጥቅሙ ከፍተኛ ነው፤›› በማለትም ሐሳቧን ትቋጫለች፡፡

የሬሳ ሳጥን በኪራይ
አያቱ ሲሞቱ የሬሳ ሳጥን የመግዛት ኃላፊነት የተሰጠው ለርሱ ነበር፡፡ ከጓደኛው ጋር በመሆን ሳጥኑን ለመግዛት ያቀናውም ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ ከሚገኙ የሬሳ ሳጥን መሸጫዎች ነው፡፡ አያቱ ደብረ ሊባኖስ እንደሚቀበሩ፣ በሳጥን ሳይሆን በሰሌን ተጠቅልለው የሚቀበሩ በመሆኑ፣ ውድ ዋጋ የሚያወጣና ለማጓጓዣ ብቻ የሚጠቀምበት የሬሳ ሳጥን እንዲሸጥለት ካወያየው የሬሳ ሳጥን ሻጭ የሰማው መልስ ግን አስገርሞታል፤ አስደንግጦታልም፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም ሰምቼው የማላውቀው አስተያየት ስለሰጠኝ ደነገጥኩ፤ ለማመንም አልቻልኩም ነበር፡፡ የሬሳ ሳጥን ሲከራይ ሰምቼ አላውቅም ነበርና በ200 ብር ሳጥኑን ተከራይተህ አስከሬኑን አድርስና ከቀብር በኋላ በጥንቃቄ ጭነህ መመለስ ትችላለህ፤›› አለኝ፡፡ ከጓደኛዬ ጋር መከርኩበትና በኪራዩ ተስማምቼ ሳጥኑን ይዘን ሔድን፡፡ ከቀብር በኋላም ለአከራዩ ሳጥኑን መለስኩ፡፡››

ይህን ያለን አቶ ታሪኩ (ስሙ ተቀይሯል) ከዚህ ቀደም የሬሳ ሳጥን በኪራይ እንደሚገኝ ምንም መረጃው ያልነበረው በመሆኑ ያስደምመው እንጂ፣ በተለይ 600 እና 700 ብር አውጥቶ መግዛት ለማይችሉ በሌላም በኩል በሳጥን ለማይቀበሩ ነገር ግን አስከሬናቸው ሩቅ ቦታ ሔዶ ለሚቀበሩ ሙታን የኪራይ የሬሳ ሳጥን መኖሩ ጥሩ እንደሆነ አጫውቶናል፡፡

በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኘው ሰላም አበረ ተንከባክበው ያሳደጓት አያቷ ወ/ሮ ስንቅነሽ ሲሞቱ፣ በማዕርግና በክብር ይቀበሩ ዘንድ ዘመድ አዝማድ ተፍተፍ ማለቱ አልቀረም፡፡ በዚህ መሀል ውጭ አገር የነበሩ ልጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ቀብሩ በቪዲዮ ተቀርፆ እንዲላክላቸውና እዚያው ባሉበት አገር እርማቸውን እንዲያወጡ ይጠይቃሉ፡፡

ቪዲዮ ሲቀረጽ ግን ‹‹የተሻለ የሚባለውን የሬሳ ሳጥን ተጠቀሙና በምትቀበርበት ወቅት በሌላ ቀይሩት›› የሚል ሐሳብ ከአንዱ ዘመዳቸው ይመጣል፡፡ በዚህ መሠረት ጥሩ የሬሳ ሳጥን ለመከራየት የሬሳ ሳጥን መሸጫ ሱቆች ጎራ ይላሉ፡፡ ከላዩ በመስታወት የተሸፈነና አስክሬኑን የሚያሳይ ሳጥንም ይመርጣሉ፡፡ ባለመስታወቱ ሳጥን የተመረጠውም በቪዲዮ ሲቀረጽ የአያታቸው ግርማ ሞገስ (ሙሉ አካል) መታየት ስለነበረበት እንደሆነ ሰላም ታብራራለች፡፡

የሰላም ቤተሰቦች የተመለሱት ይህን የሬሳ ሳጥን በአንድ ሺሕ ብር፣ የመቀበርያቸውን ደግሞ 450 ብር ገዝተው ነበር፡፡ የሬሳ ሳጥን መከራየት አዲስ አበባ ውስጥ እየተለመደ መምጣቱን ያነጋገርናቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት አስፈጻሚዎች ገልጸውልናል፡፡

ካነጋገርናቸው የቀብር ሥርዓት አስፈጻሚ መካከል ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ፣ ‹‹የሬሳ ሳጥን ኪራይ በጣም የተለመደ ሲሆን፣ የሟች ቤተሰቦች ሬሳውን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመውሰድ ይጠቀሙበታል፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ደብረ ሊባኖስ ገዳም፣ እንዲሁም ሌሎች ክፍላተ ሀገር ለቀብር ሲኬድ ተከራይተው ይሔዳሉ፤›› ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡ ይህ ለምን እንደሚሆንና ገዝተው መሔድና መከራየትስ የሚያስፈልግበትን የተለየ ምክንያት ጠይቀናቸው ነበር፡፡ ‹‹ልዩነቱ አንዳንድ ሰዎች ሲሞቱ በሰሌን እንዲቀበሩ ይናዘዛሉ፡፡ በዚህ መሠረት በሰሌን ከቦታ ቦታ አስከሬኑን ማጓጓዝ ከባድ ስለሚሆን የግድ ሳጥን መከራየት ይኖርባቸዋል፤›› በማለት መልሰውልናል፡፡ ያነጋገርናቸው ቀብር አስፈጻሚ ኪራዩ የሚከናወነው ብር በማስያዣነት በማስቀመጥ ወይም መታወቂያ በማስያዝ እንደሚሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ ግን ሰው በሙሉው ዋጋ ስለሚከራይ ሟች ዘመዱን ከቀበረ በኋላ እዚያው የቀብሩ ቦታ ጥሎት ይመለሳል፡፡

ሁሉም ዓይነት የሬሳ ሳጥኖች የሚከራዩ ሲሆን ከ500 ብር እስከ 1000 ብር ድረስ የሚያወጡም አሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለኪራይ የሚውሉት ከላሜራ የተሠሩ ሳጥኖች በመሆናቸው ብዙም ከሰው ጋር ተሰበረ አልተሰበረ ብለው ግጭት ውስጥ እንደማይገቡም ገልጸውልናል፡፡

አቶ ንጋቱ በረደድ (ስሙ ተቀይሯል) ‹‹እኔ ይህን ሥራን ለ10 ዓመት ሠርቻለሁ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገር የተጀመረው በቅርብ ጊዜ ሲሆን፣ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ በስፋት ይታያል፤›› ብሏል፡፡

ለምን ያህል ጊዜ ነው የምታከራዩት? ስንል ጠይቀነው ነበር፡፡ ‹‹ለአንድ ለሁለት ቀንም እንደ ቀብር ቦታው ርቀት እንስማማለን፤ በቀን ስለማናከራይ ብዙም ችግር የለውም፤›› ብሎናል፡፡ ከ1000 ብር እስከ 2000 ብር ከተማው ውስጥ ያለው ወጭ ሊባል የሚያስችል ዋጋ ነው፡፡ ለምሳሌ 1000 ብር ለምን ዓይነት ሳጥን ታስከፍላላችሁ? ለሚለው ጥያቄያችንም ሲመልስ ‹‹እኛ ብዙውን ጊዜ በዚህ ዋጋ የምናከራየው በቪዲዮ እየቀረጸ ለሚሸጥ ለቀስተኛ ነው፤ ምክንያቱም አሁን አገር ውስጥ ከተለመዱት ሳጥኖች ለየት ባለ መስታወት ስለሆነ ነው፤›› ብሏል፡፡

አቶ ንጋቱ አክሎም፣ ይህንኑ ሥራ አንዳንዴ በሆስፒታል ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር የሚሠሩበት አጋጣሚ እንዳለም ጠቁሟል፡፡ በየሆስፒታሉ የሬሳ በር አቅራቢያ በሚገኙ ቤቶች ውስጥ በማስቀመጥ በተለይም በክፍሉ የሚሠሩት ሠራተኞች በ300 ብር የሚያከራዩትን በኮሚሽን ወደነርሱ የሚያስመጡበት አጋጣሚ መኖሩንም አቶ ንጋቱ ጠቁሟል፡፡ ይህም የሚሆነው አስክሬኑ ከአንዱ ሆስፒታል ወደ ሌላ ሆስፒታል በሚላክበት ጊዜ መሆኑንም ከመጥቀስ አልተቆጠበም፡፡ የሆስፒታል ሠራተኞች ይህንኑ ሥራ አብረው እንደሚሠሩ ያነጋገርናቸው የቀብር አስፈጻሚዎች፣ ‹‹አንዳንዴ እዚያው የሬሳ ክፍል የሚሠሩት የራሳቸውን ሳጥን እዚያ በማስቀመጥ ያከራያሉ፤›› በማለት አውግተውናል፡፡

ያነጋገርናቸውን ቀብር አስፈጻሚዎች ምን ያህል እንደሚያገኙበት ለጠየቅናቸውም ሲመልሱ፣ አንዳንዱ ከሽያጩ የተሻለ ገንዘብ እንደሚገኝበት ሁለት ሦስቴና ከዚያም በላይ ስለሚከራይ የገንዘብ መጠኑን መገመት ቢያስቸግርም፣ ከሚሸጠው የሚከራየው የ30 በመቶ የተሻለ ገቢ እንደሚያስገኝ አመልክተዋል፡፡