Saturday, May 25th

English Version

Error
  • Error loading feed data.

አሜሪካዊው መሀንዲስ በሚስታቸው የድረ ገፅ አስተያየት ከሀገር እንዲወጡ ተደረገ

E-mail Print PDF
User Rating: / 20
PoorBest 

- ውጭ ጉዳይና የአሜሪካ ኤምባሲ ዲፕሎማሲያዊ ይዘት የሌለው ክስተት ነው ሲሉ ጉዳዩን አጣጥለዋል
(በናምሩድ ብርሃነ)

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲን በመገንባት ላይ የሚገኝ የግል ተቋራጭ ተቀጣሪ የነበሩ አንድ አሜሪካዊ መሀንዲስ ባለቤታቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በሚመለከት በድረ ገፅ ላይ በሰጡት ስሜት ጎጂ አስተያየቶች ምክንያት ከሀገር እንዲወጡ ተደረገ፡፡



ብራንደን ባሪ የተባሉት እኚሁ መሀንዲስ ከሀገር እንዲወጡ የተደረገው የኤምባሲው ባለሥልጣናትና የተቋራጩ የቢ.ኤል ሃርበርት ተወካዮች በጉዳዩ ላይ ከተወያዩበት በኋላ ነው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳዩን "ቦታ የሚሰጠው" ክስተት እንዳልሆነ በሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይም ምንም አይነት ተፅዕኖ እንደማይኖረው ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡

"እኛ ጉዳዩን በሚመለከት መግለጫ የምንሰጠው ሴትየዋ የሰጧቸውን አይነት አስተያየቶች ስለምናወግዝ ጉዳዩ ደግሞ ከእኛ የግንባታ ቦታ ጋር በመያያዙ ብቻ ነው" ሲሉ የኤምባሲው ቃል አቀባይ ማይክል ጎንዛለዝ ተናግረዋል፡፡

የዚህ ጋዜጣ ዘጋቢዎች ሊያገኙት በቻሉት መረጃ ሊአን ኤመርሰን ባሪ የተባሉት እኚሁ ሴት ኢትዮጵያን እንዲሁም ኢትዮጵያውያንን በሚመለከት በተደጋጋሚ ለወራት የዘለቀ ስሜት የሚነኩ አስተያየቶችን በግል ድረ ገጻቸው ሲሰጡ ነበር፡፡ ሁኔታው ከተፈጠረ በኋላ ግን ይኸው ድረ ገፅ እንዳይነበብ ተደርጓል፡፡

በኢትዮጵያ የሚገኙ የቢኤል ሃርበርት ተወካዮች በበኩላቸው ጉዳዩ በኢትዮጵያውያን ሠራተኞች እና በድርጅቱ መካከል ከተፈጠረ የደሞዝ ጭማሪ አለመግባባት ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

"ያም ሆነ ይህ ግን የሴትየዋ አስተያየቶች በምንም አይነት ድርጅታችን የማይደግፋቸው በመሆኑ መሀንዲሱ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል" ሲሉ እነዚሁ ተወካዮች ለሪፖርተር ገልፀዋል፡፡

አስተያየቶቹን ሲሰነዝሩ የነበሩት ሴት ከሦስት ሳምንት በፊት ከኢትዮጵያ መውጣታቸውን ከላይ የተገለፁት ምንጮች ለሪፖርተር አሳውቀዋል፡፡

ደሞዝን በሚመለከት ስላለው አለመግባባት ማብራሪያ የሰጡት እኚሁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የቢ.ኤል ሃርበርት ተወካዬች "ኢትዮጵያውያኑ ሰራተኞች ድርጅቱ አሜሪካ ውስጥ ለሠራተኞቹ በሚከፍለው የደሞዝ መጠን እንዲከፍላቸው እየጠየቁ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የማይታሰብ ነው፡፡ ከ10 እስከ 12 የአሜሪካ ኤምባሲዎች በአፍሪካ ስንገነባ ለሀገሪቱ ተወላጆች በዛ መልኩ ከፍለን አናውቅም" ብለዋል፡፡

ተወካዮቹ አክለውም "የሀገር ውስጥ ዋጋን ስናጣራ እኛ የምንከፍለው ደሞዝ ከ44 እስከ 164 ፐርሰንት ሌሎች የተቋራጭ ድርጅቶች ከሚከፍሉት በላይ ነው በዛ ላይ አሰልጥነናቸው ታታሪ የሆኑትን ኢትዮጵያውያን ወደ ሌሎች ሀገሮች ፕሮጀክቶቻችን ይዘን ነው የምንሄደው" ብለዋል፡፡

ቢ.ኤል ሃርበርት ኢንተርናሽናል በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎችን በመገንባት የሚታወቅ የግል የኮንስትራክሽን ድርጅት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያኑ ሰራተኞች በጉዳዩ ላይ ያላቸው አስተያየት ለማግኘት የተደረገ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ትላንትና ከሰዓት በኋላ መግለጫ ያወጣው ቢ.ኤል ሃርበርት በተፈጠረው ሁኔታ ማዘኑን ሆኖም ግን የድርጅቱን የሥራ ሥነ ምግባርና ገፅታ የማያመላክት መሆኑን አሳውቋል፡፡ "እንደ በኢትዮጵያ የሚሠራ የአሜሪካ ተቋራጭ ድርጅት በተቀጣሪያችንና ባለቤታቸው የግል ድረ ገፅ ኢትዮጵያውያንንና ኢትዮጵያውያን ሠራተኞቻችንን ስም በሚያጎድፍ መልክ ስለተሰጡት አስተያየቶች ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡ አስተያየቶቹ የቢ.ኤል ሃርበርትን የሥራ ስነ ምግባርና ገፅታ ግን አይወክሉም" ሲል ድርጅቱ በአሜሪካ ኤምባሲ በኩል ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አሳውቋል፡፡