Skip to main content
x

በአዳማ ከፕላስቲክ የውኃ ጠርሙሶች ቪላ ቤት ተገነባ

ሲምኮን ቴክኖሎጂስ የተባለ አገር በቀል ኩባንያ፣ አገልግሎታቸውን የጨረሱ  የውኃ ማሸጊያ ፕላስቲክ ጠርሙሶችን በመጠቀም ያስገነባውን ዘመናዊ ቪላ ቤት ለአገልግሎት አበቃ፡፡ ኩባንያው ለአገሪቱ እንግዳ የሆነውንና ለአካባቢ ጥበቃ ፋይዳ ያለውን አሠራር በመጠቀም፣ ከተጣሉ የውኃ መያዣ ፕላስቲክ ጠርሙሶች የተሠራው ሞዴል ቪላ ቤት የተገነባው በአዳማ ከተማ ነው፡፡ የፕላስቲክ ጠርሙስ ቪላ ቤቱ ሐሙስ፣ የካቲት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሕዝብ ዕይታ ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፣ በመቶ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ቪላ ቤት፣ ለግንባታው ከ53 ሺሕ በላይ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ጠይቋል፡፡ የቪላ ቤቱን ግንባታ ለማጠናቀቅ የጠየቀው አጠቃላይ ወጪ 345 ሺሕ ብር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ግንባታውን ለማጠናቀቅም ሦስት ሳምንታት ብቻ እንደፈጀ ኩባንያው አስታውቋል፡፡

የእንግሊዝ ኩባንያ ለማዳበሪያና ባዮጋዝ ማምረቻ የሚውሉት የፕላስቲክ ምርቶችን ይፋ አደረገ

ቢዩታል ፕሮዳክስት ግሩፕ የተሰኘው የእንግሊዝ ኩባንያ፣ ከእንስሳትና ከሰው ብሎም ከሚጣሉ ቆሻሻዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያና ባዮጋዝ ማምረት የሚያስችል ምርትን ጨምሮ እስከ 1.6 ሚሊዮን ሊትር ውኃ ማጠራቀም የሚችሉ የፕላስቲክ ታንከሮችን ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ እንደ አኳታብስ ያሉትን የውኃ ማጣሪያ ምርቶች በማስመጣት ለአገር ውስጥ የሚያቀርበው ሲትረስ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ኩባንያ ጋር በመሆን ምርቶቹን ለኢትዮጵያ ገበያ ማቅረብ የጀመረው ቢዩታል ግሩፕ፣ ‹‹ፍሌክሲጄስተር ቪ80›› የሚል መጠሪያ የሰጠውን ምርት በማምረት ለገበያ ማቅረቡን ጥር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ወቅት ያስታወቁት የኩባንያው የሽያጭ ዳይሬክተር ክሬግ ቦል ናቸው፡፡