Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

በዚህ ጊዜ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የማያቸው አስከፊ አዝማሚያዎች እንደ ዜጋ ይህንን አጽፈውኛል፡፡ ከልጅነቴ ጀምሬ በአካባቢዬ በቅርበት የማውቃቸው ሰዎች ለእኔ የዘመድ ያህል ይሰሙኝ ነበር፡፡ ሠፈራችን ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመጡ ሰዎች ስለተሞላ በተለይ ጎረቤቶቻችን የቤተሰብ ያህል ቅርቦቼ ነበሩ፡፡ አብሮ አደግ ጓደኞቼም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው በጣም በጣም ጥሩዎች ነበሩ፡፡ በልጅነቴ በአካባቢያችን ከሚነገሩ ቋንቋዎች መካከል አማርኛ፣ ጉራጊኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ትግርኛና ወላይትኛ በጣም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ይኼም ሆኖ ግን የጋራ መግባቢያ የሆነው አማርኛ ሁላችንንም በማዕከልነት ስለሚያገናኘን ማንም ከየት መጣ የማንም ጉዳይ አልነበረም፡፡ ዋናው ሰብዓዊ ፍጡር መሆኑ ብቻ በቂ ነው፡፡ የአካባቢያችን ሕዝብ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኝ ስለነበርም ድህነቱ ራሱ እንዲደጋገፍ እንጂ፣ እንዲተናኮስ አያደርገውም ነበር፡፡ ሰው ሆኖ መገኘት በቂ ነበር፡፡

ዓመታት እየነጎዱ እኔና ቢጤዎቼም ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስንገባ፣ የቀዝቃዛው ጦርነት ውጤት የሆነው የዓለም በሁለት ጎራ መከፈል አንዱን እንድንመርጥ አስገደደን፡፡ በወቅቱ ደግሞ ሶሻሊዝም የዓለም ወጣቶችን ቀልብ የሳበ በመሆኑና እንደ ወረርሽኝ በማዳረሱኧ የእኔና የመላው ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ልብ ሸፈተ፡፡ የሶሻሊዝም ፍልስፍናን እያነበብን ‘ዓለም የወዛደሮች ትሆናለች’ የሚለውን ንድፈ ሐሳብ ስንኮመኩም፣ ለአገራችን ደሃ ሕዝብ ሶሻሊዝም የመጨረሻ መፍትሔ ይሆን ዘንድ ተመኘን፡፡ ቃልም ገባን፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሶሻሊዝም ዕውን መሆን የሚያልሙ ወጣቶች እንደ አሸን ፈሉ፡፡ የተማሪዎች የትግል እንቅስቃሴ የመጨረሻ ግቡ ሶሻሊዝም ሆነ፡፡ የንጉሡ ሥርዓትም ለሶሻሊዝም ሥርዓት መስፈን በቆረጡ የሕዝብ ልጆች ተጋድሎ ተገረሠሠ፡፡ የሰብዓዊ መብትና የማኅበራዊ ፍትሕ መረጋገጥ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ሰረፀ፡፡ ያ በጎ ዓላማና አጀንዳ በአቋራጭ በወታደራዊ አምባገነኖች ተጨፍልቆ መከራና ሰቆቃ ነገሠ፡፡ ስደት፣ ሞት፣ እስራትና ጥራኝ ዱሩ ተከተሉ፡፡ የሕዝብ ልጆች የተዋደቁለት ዓላማ መከነ፡፡

ከጊዜ በኋላ ለአንዲት አገር ኅብረ ብሔራዊ ተልዕኮ የተደረገው ትግል ከስሞ በብሔር መደራጀትና መታገል ተጀመረ፡፡ ከዓመታት በኋላም ደርግ ወድቆ አሸናፊዎች ሥልጣን ተረከቡ፡፡ ከአሀዳዊ ወደ ፌዴራላዊ ሥርዓት ሽግግር ተደረገ፡፡ ሁሉም ብሔሮች ተፈቃቅደው በሰላምና በእኩልነት የሚኖሩባት አገር ብትፈጠር ከሚደሰቱ ሰዎች መካከል አንደኛው ነኝ፡፡ ምክንያቱም በልጅነቴ በዚያ በደሃ ሠፈሬ በእኩልነት በሰላም የኖሩ ወገኖቼን አውቃለሁና፡፡ አሁንም በቅርበት ሁላችንም አለንና፡፡ ነገር ግን አጋጣሚን በመጠቀም እኩልነትን ሳይሆን አንዱን በሌላው ላይ ማስነሳትን፣ ማስጠላትንና ቂም ማስቋጠርን ዓላማ ያደረጉ እኩዮች በዚህች አገር ላይ በደል ፈጽመዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጨቋኞቹ እኩል ተረግጦ ያልተገዛ ይመስል፣ አንዱን የጨቋኙ ጭፍራ ሌሎችን ተጨቋኝ የሚያደርጉ አፍራሽ ተግባራት በመከናወናቸው፣ በአግባቡ ከተያዘ መድኅን ሊሆን የሚገባው የፌዴራሊዝም ትርጉም ተዛባ፡፡

አንዳንዶች ከዚያም አልፈው ተርፈው እነሱ ብቻ በዚህች አገር የተሰቃዩ ፍጡራን ይመስሉ አገሪቱን ለማፈራረስ ቀን ከሌሊት ይባዝናሉ፡፡ ትናንት የተፈጸሙ ስህተቶችን በዛሬው ዘመን መሥፈሪያ እየለኩ ሌሎችን ዕዳ ከፋይ ለማድረግ መከራ ያያሉ፡፡ ካለፉት ስህተቶች ተምሮ በመከባበርና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተች አገር እንድትኖር ከማድረግ ይልቅ፣ የፌዴራል ሥርዓቱ በአገሪቱ ላይ ገሃነም ይዞ የመጣ እያስመሰሉት ነው፡፡ ይኼ በፍፁም ስህተት ነው፡፡ በእዚህች አገር ላይ መኖር ያለብን በእውነተኛ እኩልነትና በመከባበር ላይ ተመሥርተን መሆን ሲገባው፣ የሌሎችን መብት የሚጋፉ እኩይ ተግባር ውስጥ የሚገቡ ኋላቀሮችም አሉ፡፡ አሁን ደግሞ ማንነታቸውን በጭምብል የጋረዱ እኩዮች በማኅበራዊ ድረ ገጾች የአገሪቱን ሕዝብ ለማጫረስ የብሔር ቅስቀሳ ጀምረዋል፡፡ ለዘመናት በኅብረታችን ምክንያት ሊደፍሩን ያልቻሉት ጠላቶቻችን ከጉያችን ውስጥ በወጡ ተላላኪዎች አማካይነት በቀላሉ ሊያጠፉን የሚችሉበት መንገድ እየተመቻቸ ነው፡፡

በእዚህ ጊዜ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በፖለቲካ አመለካከት ወይም በተለያዩ ጉዳዮች በኢትዮጵያዊያን መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የሚሞክሩትን ማሳፈር መቻል አለብን፡፡ ከምንም ነገር በላይ የሚያስተሳስረንን ኢትዮጵያዊነት በማስከበር ከፋፋዮችን ማቆም አለብን፡፡ ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ያቃታቸው እኩዮች የዘር ካርድ እየመዘዙ ሊያባሉን ሲሞክሩ፣ ኢትዮጵያዊነት ከምንም ነገር በላይ እንደሚበልጥ ማሳየት ያዋጣናል፡፡ ከአብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች ከተውጣጡ ወገኖቹ ጋር ላደገና በሶሻሊዝም አስተሳሰብ ለተቀረፀ ለእኔ ሰብዕና ዘረኝነት የወረደ አስተሳሰብ ነው፡፡ አገሪቱ ሽማግሌ የሌላት ወይም የሃይማኖት መሪዎች የሌሉባት ይመስል፣ ምድረ ጠባብና ዘረኛ ሕዝብ ሊያፋጅ ሲነሳ ዝም ብሎ መቀመጥ በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ክፋት የተጠናወታቸውን ማውገዝ ተገቢ ነው እላለሁ፡፡

እንዲህ ዓይነቱን አሳሳቢ ጉዳይ አንስተን ከቢጤዎቼ ጋር ስናወጋ አንዱ በፌስቡክ ላይ አንድ የተባረከ ዜጋ ከዓመታት በፊት የጻፈውን ነገረኝ፡፡ ጸሐፊው ወጣት ነው፡፡ ይህ ወጣት ለአገሩ ባለው ተቆርቋሪነት በጣም እወደዋለሁ፡፡ እሱ፣ ‹‹ወቅታዊ የአቋም መግለጫ›› በማለት በጻፈው ጽሑፍ፣ ‹‹በተለየ የምደግፈውም ሆነ የምነቅፈውም ብሔር የተባለ የትንሽ ኮሮጆ አባል አይደለሁም፡፡ እኔ ዜጋ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ ስል ለአንድም ሰከንድ አልጠራጠርም፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን እመኛለሁ፡፡ ፍቅር ለሁላችንም ይወርድ ዘንድ አልማለሁ፡፡ ኢትዮጵያ አንድ እንደሆነች አምናለሁ፡፡ የአንድነቷ ማኅተም ማረጋገጫም የልጆችዋ ፍቅር ብቻ መሆን እንደሚገባውም እረዳለሁ፡፡ ስለኢትዮጵያ ሰላም ብለው ምዕመኖቻቸውን ወደ ቤተ እምነቶቻቸው ለፀሎት የማይጠሩ መንፈሳዊ አባቶች ስላሉን አዝናለሁ፡፡ ዜጎቹን በአግባቡ መያዝ የተሳነው መንግሥት ስላለንም አዝናለሁ፡፡ ምን ማድረግ እንደሚገባው ማወቅ የተሳነው የዋህ ሕዝብ ስላለን አዝናለሁ፡፡ እናት ለልጆቿ አሁንም የምታለቅስባት አገር ስላለችን አዝናለሁ፡፡ ነገር ግን ተስፋ አለኝ፣ ቸር አምላክ ሁሉን ወደ ቦታው ለመመለስ እንደሚችል አውቃለሁ፡፡ የሃይማኖት አባቶቻችን ምዕመኖቻቸውን ለፀሎት አሰባስበው ምድራዊ ቁጭትና እልህ የወጠረውን ልባችንን ወደ መንፈሳዊነት እንዲመልሱልን ተግሳጽ፣ ምክርና ውግዘት በመንፈሳዊያኑ ብቻ እንዲሆን ተስፋ አለኝ…›› በማለት ነበር ወጣቱ ሐሳቡን የቋጨው፡፡

አገሩን የሚወድ ዜጋ ከወገኑ ጋር እየተደጋገፈ በፍቅር ይኖራል እንጂ፣ ጠላት በቀደደለት ቦይ ውስጥ ገብቶ አገሩን አያፈርስም፡፡ የገዛ ወገኑን ድክመት እየተጠቀመ ለጥቃት አያደባም፡፡ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ቢሳሳቱ ወይም በሴረኞች ደባ ነውር እንደፈጸሙ ዘመቻ ቢከፈትባቸው፣ የዘመቻው አካል በመሆን መፈጠራቸውን እስኪጠሉ ድረስ አንገት ማስደፋት ተገቢ አይደለም፡፡ ሰሞኑን በአንዲት የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ላይ እየደረሰ ያለው ውርጅብኝ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ከእምነትም ሆነ ከሞራል አኳያ ራስን ብፁዕ አድርጎ ሌላውን መወንጀል የህሊና ሙግት ማስከተሉ አይቀርም፡፡ የተሳሳተን ማረም እንጂ መኮነን ያለፍኩበት የሕይወት ተሞክሮ ስላልሆነ፣ ወገኖቼ እባካችሁ የገዛ ወገናችንን እየወነጀልን አናሳቅ በማለት እማፀናለሁ፡፡ የመረረው ተስፋ ቆርጦ ሕይወቱን ቢያጠፋ ምን እንጠቀማለን? ስለዚህ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ (ዮናታን አበበ፣ ከፈረንሣይ ለጋሲዮን) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...