Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉይድረስ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ

ይድረስ ለኢትዮጵያውያን በሙሉ

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ   

ኢትዮጵያ ከጌታ ልደት ጀምራ የክርስቶስን ከድንግል ማሪያም መወለድ ካበሰሩትና ልደቱን በደስታ ከተቀበሉት ከመጀመርያዎቹ እንዷ መሆኗን ቅዱስ መጽሐፍ የመሰከረው ታላቅ ማስረጃ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ከመጀመርያዎቹ የጌታን ልደት ከመሰከሩት ቅዱሳን አገሮች አንዷ ሆና የኖረች አገር ለመሆኗ የሚያጠራጥር ነገር ያለ አይመስለኝም። ይህም በመሆኑ የፈጣሪን መንገድ የተከተለች፣ ለንዋይ ሳይሆን ለሃይማኖቷ የቆመች፣ ሌላውንም ተቀብላ በማስተናገድ የተመሠገነችና የታወቀች አገር ለመሆኗ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ታዲያ ምነው ወገኔ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ለመላው ዓለም የነበረውን ሁኔታ ማስረዳትና ወደ ልቦናችን እንድንመለስ መሞከር ታሳነን?

ነባር አባቶችም ኢትዮጵያ ስትነካ ዓናይም ብለው ሕይወታቸውን አሳልፈው የሰጡላት አገር ስትሆን፣ ከየትኛው ጎሣ፣ ከየትኛው ዘር መጣን ሳይሉ ለእናት አገራቸው ሕይወታቸውን አሳልፈ የሰጡበትን ዘመን ለኢትዮጵያውያን ማስረዳት የሚያሻኝ አይመስለኝም፡፡ አገርን በሥልጣኔ፣ በኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ሌሎች የምዕራብ አገሮች ወደ ደረሱበት ለማድረስ ይጥሩ ነበር እንጂ ዛሬ እኔ እንደማደርገው ለግል ጥቅማቸው የሚሯሯጡና ሌላው ወገናቸው ሲራቆትና ሲራብ ለማየት እንኳ እምነት ጊዜ እንደሌላቸው ዛሬ የምንኮራበትንና ልናጥፋው የተዘጋጀንበትን አለኝታነት አኑረውልን ነበር ያለፉት፡፡ ታዲያ ይህንን አዙሮ ማየት ያቃተው የእኔ ትውልድ አጥፍቶ መጥፋትን  እንደ ሙያ በመያዝ እነሆ ለነፃነታቸው ከታገልንላቸው ወንድም እህት አፍሪካ አገሮች እንኳ ዝቅ እያልን በመሄዳችን አዙሮ የማየት አንገትና ጭንቅላት የሌለው ትውልድ እንደ  እንጉዳይ ፈልቶ፣ ለራሱም ሳይሆን ለመጪውም ትውልድ የእሾህ መዝጊያ እየፈጠረ ከማደግ ይልቅ መሽቆልቆልን፣ ከኅብረት ይልቅ መለያየትን፣ ከማወቅ ይልቅ መደንቆርን፣ አብሮ ከመበልፀግ ይልቅ በግል አጋባሽነትን፣ ከአገር ልጅ ይልቅ ለነጭ ባርነትን የመረጠ ትውልድ ኢትዮጵያን ወደ ጥፋት ጎዳና ለመምራት እየተሽቀዳደመ ነው።

- Advertisement -

የአንድ አገር ሕዝብ መጀመርያ መገንዘብ ያለበትና ሊቆምለት የሚገባው ለአገሩ ክብርና ነፃነት ነው፡፡ ለምን? አገር የሌለው ሰው ከሰዎች በታች ነውና፡፡ ምናልባት ሠርቶ በመኖርና እንደ ልብ በመንቀሳቀስ የትስ ቢሆን ሠርቼ ከኖርኩ ምንቸገረኝ የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን አንድ ደረጃ ሲደርሱ ልዩነቱን ለማየት የሚያስገድዳቸው ሁኔታ ሲፈጠር ያኔ ነው የሚታወቀውና ማን እንደ አገር የሚሉት። በእርግጥ አሜሪካ የሁሉም መጤ አገር በመሆኗ ሁሉንም ለማካተት ብትሞክርም፣ ያ የቀለም ጉዳይ ሁሌም ጥያቄ ያስነሳል።

ኢትዮጵያ ታማኝና እንግዳ ተቀባይነቷን ነቢዩ መሐመድ መስክረውላታል፡፡ ቃላቸውም ይህ ነበር፡፡ ባለቤታቸውን፣ ልጃቸውንና ተከታዮቻቸውን በተቸገሩበት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሂዱ እንግዳ ተቀባይዋና ፍትሕ የነገሠባት አገር ነችና፡፡ ወደ እዚያች አገር ስትሄዱ ፍትሕንም መስተንግዶውንም ታገኛላችሁ ብለው የላኳቸው 70ዎቹም ስደተኞች፣ እንደተባለው የተጠየቁትን በትክክል መልሰው ያለ ምንም ችግርና መከራ ኖሩ፡፡ የፈለገ አገሩ ሲመለስ መቅረትን የመረጠም በመቅረቱ፣ እነሆ ተዋልዶና ተባዝቶ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይባባል የሚጋባውም ተጋብቶ ተዋልዶ ኢትዮጵያ እዚህ ደርሳለች፡፡ ዛሬ  ግን ወገንን ከወገን ሃይማኖትን ከሃይማኖት ጋር በማለያየት የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም፣ ይህንን በፍቅር የኖረን ሕዝብ ለማጋጨትና ለማለያየት የሚሠራው ሴራ መሠረት የሌለው ነው ብለን ብንገምትም፣ ‹‹ያልጠረጠረ ተመነጠረ እንዳይሆን›› ነቅተንና ተዘጋጅተን መከላከል የእያንዳንዳችን ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝበን የድርሻችንን የምንከፍልበትን መንገድ እንቀይስ፡፡ ጥንት በአያት ቅድመ አያቶቻችን ዘመን ንጉሥ ቢቆጣና ፍትሕ ቢያጎድል የተፈረደበትና አቅም ያጣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ተጠልሎ፣ ደወል ተደውሎ በቤተ ክርስቲያን አማላጅነት ንጉሡም የዚያ ተገዥ በመሆኑ ይቅር ለእግዚአብሔር ብሎ ዕርቀ ሰላም ይወርድ ነበር፡፡ ጳጳሳቱም ለአገራቸውና ለወገናቸው ክብርና ነፃነት ሲሉ የማንም ወገን ሳይሆኑ፣ በግንባራቸው አፈሙዝ ተደቅኖባቸው ለሕይወታቸው ሳይሳሱ ያለፉበትን ዘመን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የትናትናውን የጣሊያን ወረራና የአገርን ክብር ሊያዋርድ የመጣውን ጣሊያን እንቢ አሻፈረኝ በማለት ግንባራቸውን ለጥይት የሰጡትን የኢሉአባቦር ጎሬ አቡነ ሚካኤልንና በአዲስ አበባ የተሰውትን አቡነ ጴጥሮስን እንደ ምሳሌነት ማቅረብ ይቻላል፡፡

ታዲያ ዛሬ ምነው በኢትዮጵያ የእነ አቡነ ሚካኤልና አቡነ ጴጥሮስን ፈለግ የሚከተል ጠፋ? መነኮሳቱም ባህታዊያኑም ወደ ወገንተኝነት ጎራ ገብተው ይሆን? መቼም ሰዎች ናቸውና ፍፁም ሊሆኑ ስለማይችሉ ቢሳሳቱም ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱና የገቡትን ቃል ኪዳን እንዲፈጽሙ በፀሎት እንርዳቸው፡፡ ብለን በአንድነት ወደ ልቦናቸው እንዲመለሱና ለአገራቸው ለወገናቸውና ሞተናል ለተቀበሉት ታላቅ ኃላፊነት ቆመው፣ የአስታራቂነትንና የሰላምን መንገድ እንዲያስተምሩና የሰላም ተምሳሌት እንዲሆኑ እንፀልይላቸው፡፡

ወገኖቼ ማንም ሊሳሳት ከመንገዱ ሊወጣ ይችላል፡፡ ያንን የተሳሳተ ግለሰብ መክሮ የመመለስ፣ የማስገንዘብና ወደ ልቦናው እንዲመለስ የማድረግ አቅሙም ሆነ ኃይሉ ያላቸው አባቶች ምነው ጠፉ? ወጣት አዲስ ነገርን የመፍጠር፣ ሩጦ የማምለጥ፣ ጠላት ሲመጣ አገሩን ላለማስነካት ታጥቆ ወገንንና አገርን የማስከበር አቅም ቢኖረውም፣ ሽምግልና እስከ ስሙ ሽማግሌ ስለሚባል ያለፈን በማስታወስ፣ የዛሬን ተመልክቶ ከትናት በማወዳደርና መጪው ምን ይሆን ብሎ በመመልከት ከወጣቱ ይልቅ ሽማግሌ መሆን አይሻል ይሆን? እንደ አጋጣሚ ሆኖ የዘመኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ወጣት በመሆናቸውና ያሰባሰቧቸው ሚኒስትሮቻቸውም የዕድሜ ተመሳሳይ በመሆናቸው፣ ነባሩ ታሪክ ተረስቶ ከአርባ ዓመታት ባልበለጡ ወጣቶች መሪነትና አማካሪነት በመካሄዱ ፈርወደ መልቀቅ እየተቃረብን ነው፡፡ በእርግጥ መሪዎች ወጣት መሆን ይችላሉ፡፡ ግን ከጀርባቸው ልምድን የተጎናፀፉ፣ ይህ ቢሆን ምን ያስከትል ይሆን? የሚሉ ጉልበት ስለሌላቸው ብቻ ወደ ጦር ሜዳ ልዝመት ሳይሆን ጦርነቱ ምን ያስከትል ይሆን? የሚሉ መካሪዎች ከጀርባ ሆነው ሲመሩ ነበር አስተዳደር በትክክል ሲካሄድ የነበረው።

ራስ ተፈሪ መኮንን የሰላሌ አውራጃ ገዥነቱን ለስም ቢቀበሉም መካሪዎቻቸው ነበር እንጂ፣ አውራጃውን ይመሩ የነበሩት ራስ ተፈሪ መኮንን አልነበሩም፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ለእናንተው እተወዋለሁ። እንደገና ራስ ተፈሪ ትንሽ ትምህርትም ልምዱንም ካገኙ በኋላ ወደ ሲዳሞ ሲዛወሩ፣ እሁንም በታላላቅ አማካሪዎች ድጋፍና ዕርዳታ ለታላቅ መሪነት ደርሰው የሰማነውና ያየነው ጉዳይ ነው። የመጀመሪያው ወጣት የአሜሪካ መሪ ጆን ኤፍ ኬኔዲ በ42 ዓመት ዕድሜው ያንን ታላቅና ግዙፍ አገር እመራለሁ ብሎ ሲመረጥ፣ ከጀርባው የነበሩት ታላላቅ በዕውቀት የዳበሩ ሰዎች አማካሪነት ነው የአጭር ጊዜ አመራሩን ተረክቦ የመራው።

መሪዎች የተለየ ስጦታና ዕውቀት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ግን ጊዜ ከሰጠን እንደፈለገን ሹመንና ሸልመን አገር እናስተዳድራለን የሚል ቅዥት ካላቸው፣ አወዳደቃቸውም አያምርምና አዋቂን ከማራቅ ይልቅ አቅርበው ማማከሩ ሳይበጃጅቸው አይቀርምና በአንክሮ ቢታሰብበት የተሻለ ይሆናል። አገር ኗሪ ሰው አላፊ መሆኑን እንዴት መገንዘብ ያቅተናል? ሰላም ሊመጣ የሚችለው በኅብረትና በቀናነት ሲዘከር ብቻ ነው፡፡ ጊዜ ከሰጠን ብሎ አይቶ እንዳላዩ ማልፍ ውጤቱ ለልጅ ልጅ የሚደርስ መከራ ነውና ይህንንም መመልከትና አዙሮ የማየት ጭንቅላት እንዲኖር ያሻል።

ዛሬ የዓለም የተፈጥሮ ሀብት ተመናምኖ የዓለም ታላላቅ ነን ባዮች ሁሌም እንዳልተኙልን ሁሉ፣ ዛሬ ብሶባቸው ሊያለያዩንና ሊበታትኑን በትክክል አቅደው ስለተነሱ የመለያየትን እንቢልታ የሚነፉ ወገኖቻችን ይህንን ሸር በሚገባ ተመልከተውት ይሆን? ኢትዮጵያ ለዘመናት ዳር ድንበሯን ስትጠብቅና ከጠላት ስትከላከል የኖረችው ከእንዲህ ዓይነት አደጋ የሕዝቧን ነፃነት ለማስከበር ስትል መሆኑን፣ ጤነኛ ኢትዮጵያዊ ይስተዋል ብዬ ለአንዲት ደቂቃ እንኳ አላስብም፡፡

ወገኖቼ ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት ከየት እንደመጣሁና የምንና የማን ዝሪያ መሆኔ ሳላውቅ ነበር የቆየሁት፡፡ ታዲያ በ2007 ዓ.ም. ለብዙ ዓመታት ከቆየሁበት አገር ወደ ትውልድ አገሬ ብቅ ስል የማን ወገን ነህ? የማን ዘር ነህ? በሚል ባልተለመደና በማላውቀው  አዲስ  ነገር ቢያጣድፉኝ እኔ ኢትዮጵያዊ እንጂ ሌላማ ምን ልሆን እችላለሁ በሚል ንትርክ ለአቤቱታ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሄዴ ትዝ ይለኛል። ይህንን ለምን አነሳህ ብትሉኝ፡፡ ዛሬ የማየው ውጥንቅጥ፣ መላ የጠፋውና ግራ የሚያጋባ አካሄድ ስላስጨነቀኝ ነው፡፡ 360 ሚሊዮን የሚጠጋ ዜጋ ያላት ቅልቅል አገረ አሜሪካ ጥቁሩን፣ ቢጫውንና ነጩን አጠቃላ ይዛ ሁሉም እኔ አሜሪካዊ ነኝ ለማለት ሲሽቀዳደሙና የሌላውንም ነጥቀው ወደ ራሳቸው ለማዞር በሚሹበት ዘመን፣ ሌላው ዓለም ለቴክኖሎጂና ለኢንዱስትሪ በሚሯሯጥበት ጊዜ፣ ባልተለመደ መንገድ የኢትዮጵያ ልጆች ለልዩነት መሯሯጣቸው እጅግ ከማስደነቁ በላይ ሌላ ምን ይባላል?

ወገኖቼ ቀልጠፍ ብለን ለሥራና ለልማት ብንነሳ እንጂ ለመለያየት የትኛው ሥልጣኔና ዕውቀት ኖሮን? አንዱ ከአንዱ የተሻልን ሆነን ነው ለዚህ ሁሉ መከራ ደጉን ሕዝባችን የምንዳርገው? ሰከን ብሎ ማሰብ ይጠቅማልና ሰክን ብላችሁ አስቡ፡፡ ከጠላት መንጋጋ እንዴት አድርገው ነው አባቶቻችን ተከላክለው ለዚህ ነፃነት ያበቁን? እኛስ ምን ሠርተንና በልጠን እንገኝ? ለአጉል ዘመቻ ጊዜን ሰጥተን በወገናችን ላይ ከመቀለድ ይልቅ፣ ለአንድነትና እንነሳ ነው መሆን ያለበት፡፡ ከህልም ሩጫ ለመታቀብ እንነሳሳ፡፡ ባልሠራነውና ባላለማነው የአባቶቻችንን ታሪክ ብቻ እያወራን ጊዜ ከማጥፋት፣ የተሻለ ለመሥራትና ሌሎች ወደ ደረሱበት ለመድረስ እንሽቀዳደም፡፡ ቀጥለን ለሥልጣን ኮርቻ መወዳደሩን ብናስከትል ይሻላል፡፡ ለፌዝ ከሆነ እንደርሳለንና ቆርጠን መወሰን ያለበን ጊዜው አሁን ነው፡፡ ሳናመነታ በኅብረት ለመነሳሳት ተዘጋጅተን ለናቁንና ሊያለያዩን ለሚፈልጉት የዓድዋን ጀግንነት ለመድገም እንሞክር፡፡ የማይጨውንም ወረራ በዓለም ሸንጎ ፍትሕን ለማሳየት እንደሞከርነው ሁሉ፣ አሁንም አገራችንን ለማስቀደም እንጣር፣ ቀደምት ነበርንና አሁንም ለቀደምትነት እንዘጋጅ፣ ሁሌ ተመፅዋች ከመሆን ለመፅዋችነት እንንደርደር፡፡ ምን ጎድሎን ነው ስንዴ የምንለምነው? መሬት ጠቦን? ውኃ አጥተን? ወይስ የተማረና የሚሠራ ጉልበት ያለው ኢትዮጵያዊ እጥረት? ወይስ አለማወቅ? እናንተው መልሱት፡፡ ወገን ሲራብ የዕለት ጉርሱን አጥቶ ሲለምን ማየት ካላሳፈረን ምን ይሆን የሚያሳፍረን? ወገኖቼ ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንምና እስካሁን ያልኩት ይብቃንና ለአብነሮነት፣ ለጋራ ጥቅምና ለአገር ኩራት ተባብረን እንነሳ ነው መልዕክቴ፡፡ እንነሳ!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...