Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየበዳይና የተበዳይ ሚዛናዊ ሆኖ የማሰብ ግዴታ

የበዳይና የተበዳይ ሚዛናዊ ሆኖ የማሰብ ግዴታ

ቀን:

በያሬድ ነጋሽ

በደል ካልን በዳይና ተበዳይ የሚል ሁለት ጎራ እናገኛለን። በዳይ አልበደልኩም የሚል የእምነት ክህደት ቃሉን መስጠቱ እንዳለ ሆኖ፣ በደሉን የፈጸመበትን ምክንያት አስገዳጅ የሆነና ተገቢነት እንዳለው በማስገንዘብ መከራከሪያ ሊያደርገው ይችላል። ሆኖም በየትኛውም መመዘኛ “በዳይ ከአስገዳጅ ምክንያቱ አንፃር ልክ ነበር” የምንልበት አካሄድ ግን  ተቀባይነት ያለው መደምደሚያ በጭራሽ ሊሆነን አይችልም። በዚህ ርዕስ ዋና ጉዳያችን ተበዳይ ነው።

ተበዳይ እንደ ነገሩ ክብደት በይቅርታ አልፎ ከበዳይ ጋር የቀደመ ወዳጅነቱን ሊቀጥል የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ሁሉ፣ ይቅርታ ማድረግ ይቅርና ፍርድና ካሳ ቢያገኝ እንኳን ለቁስሌ መጠገኛ የሚሆን አይደለም በሚል ጥርስ ነክሶና ለበቀል ማፈላለጉን ለመቶ ዓመታት ሊያስቀጥል መቻሉ ሌላው ገጽታው ነው። ተበዳይ መራራ ቁርሾውን ይዞ ዘመናት ከተሻገረ በኋላ፣ ስለደረሰበት በደል ምልከታውን ከፅንፍ አውጥቶ በሚዛን እንዲሰፍር የሚያስገድዱ ሁኔታዎችን መመልከት ይጀምራል።

በመካከለኛይቱ ምሥራቅ እስራኤል በናዚ ጭፍጨፋ በስድስት ሚሊዮን አይሁዳውያን ላይ ያደረሰውን በደል ለመካስ ዓለም አቀፍ ካሳ፣ ገላጋይነትና አሸማጋይነት ቁስሏን የሚጠግን ከመሆን ይልቅ እንዲያመረቅዝ የሚዳዳው ነው በማለት፣ በተቻላት አቅም አነሰም በዛም በየትኛውም መልኩ በበደሉ ተሳትፏል ያለችውን አካል ከተደበቀበት የዓለም ጥግ ድረስ በማነፍነፍ ስትገል ብቻ ፍትሐዊ እንደሚሆን በማመን ከተጓዘች በኋላ፣ ነገሩን በሌላ አቅጣጫ እንድትመለከት የሚያስገድዳት መረጃዎች መውጣት ጀመሩ።

ይኸውም ከበዳዮቻቸው ወገን ሆነው ነገር ግን ጥቅም ሳይፈልጉ በርህራሔ በመነሳሳት አይሁዶችን ለሞት ሲሳደዱ፣ ወይም ወደ ማጎሪያ ካምፖች፣ ወይም ወደ ግድያ ማዕከላት ሳይደርሱ የታደጉ፣ አይሁዶችን ለማዳን በሚያደርጉት ሙከራ የራሳቸውን ሕይወት ወይም ነፃነት አደጋ ላይ የጣሉ፣ አይሁዶችን ወደ ክርስትና ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት የመከላከል ጥበቃ ያደረጉ፣ አይሁዳዊ ልጅን በጉዲፈቻ ለመውሰድ ያላንገራገሩ እንደነበሩ መረጃው በስፋት ተሠራጨ።

እ.ኤ.አ. በ1953 ነገሩን ያጤነው የእስራኤል ፓርላማ፣ ከጠላቶቻቸው ወገን ሆነው አይሁዳውያኑን የታደጉትን አካላት የሚያከብርበትን ሕግን ‹‹በአሕዛብ መካከል የተገኙ ፃድቃን›› በሚል አፀደቀ። የማዕረጉ ስያሜ የተወሰደው ከአይሁድ ወግ (የሊቃውንት ጽሑፎች) ውስጥ ከአይሁዳውያን ወገን ሳይሆኑ፣ የአይሁድን ሕዝብ በችግር ጊዜ የረዱ ግለሰቦችን ከሚያወሳ ታሪክ በመነሳት ነበር። እ.ኤ.አ. በ1963 አይሁዳውያንን ለረዱ  ፃድቃን ክብር የሚሰጡበትን መሥፈርት የሚሰይም የ‹‹ሆሎኮስት›› ባለሙያዎች ኮሚሽን ተቋቁሞ፣ ሞሼ ላንዳው የኮሚሽኑ የመጀመርያ ሰብሳቢ ሆነው ተመረጡ።

መሥፈርቶቹም ግለሰቡ ከግል ጥቅሙ ይልቅ አይሁዳውያንን ለመርዳት ያነሳሳው ከሆነ፣ አይሁዶችን በቤቱ ወይም በመጋዘን ውስጥ በመደበቅና በሚደበቁበት ጊዜ ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን በማቅረብ ከረዳ፣ ለአይሁዳውያኑ ጠቃሚ የሆነ የውሸት የምስክር ወረቀትና መታወቂያ እንዲያገኙ ካደረገ፣ አይሁዶች በናዚ ቁጥጥር ሥር ከነበሩበት ግዛት እንዲያመልጡ የረዳቸው ወይም ብዙም አደጋ ወደ ሌላቸው አካባቢዎች እንዲያሸሹ ካደረገ፣ በመጨረሻም በማጎሪያ ካምፑ ወላጆቻቸው ተወስደው የተገደሉባቸውን ልጆች ካዳነ ወይም በአደራ ከተረከበ የሚሉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ‹‹ግለሰቡ አደረገ ለተባለው ዕርዳታ አንደኛ ደረጃ ምስክር ወይም የማይካድ ሰነድ ሊኖረው ይገባል፤›› በሚል አስቀምጦታል።

ግለሰቡ ይህንን አሟልቶ ከተገኘ በሕዝብ መካከል ፃድቅ በሚል፣ በስሙ የተሠራውን ሜዳሊያና የክብር የምስክር ወረቀት ያገኛል፣ ስሙ በያድ ቫሼም በፃድቅ መታሰቢያ ውስጥ በክብር ግድግዳ ላይ ይጻፋል፣ በያድ ቫሼም ሕግ መሠረት የክብር ዜግነት ይሰጠዋል፣  ሽልማቱን  በሚኖርበት አገር በእስራኤል ዲፕሎማሲያዊ ተወካዮች በኩል ይደርሰዋል፣ ግለሰቡ ከሞትም በኋላ ቢሆን ሽልማቱ ለዘመዶቹ  ይሰጣል። በዚህ መሠረት ከበዳዮቻቸው ዘርና ከሁሉም ቤተ እምነቶች የተውጣጡ ክርስቲያኖች፣ እንዲሁም ሙስሊሞችና ኢአማኒዎችን ጨምሮ እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 1 ቀን 2016 ያድ ቫሼም፣ ከ44 አገሮች ለመጡ 26,120 ግለሰቦችና ቡድኖች ሽልማቱን አበርክቷል።

ከላይ የተመለከትነው ተበዳይ ከበዳዮቼ ወገን ሆነው ነገር ግን ከእኔ ጋር ያበሩ ፃድቃን ይኖራሉ በሚል ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት የተስተዋለበትን ሒደት ሲሆን፣ የበርካታ ተበዳዮች ችግር የሆነው ጉዳይ ግን በእስራኤላውያኑ ዘንድም ተስተውሏል። ይኼውም ‹‹ስንበደል ከራሳችን ወገን የነበሩ አባሪዎች፣ የነገሩ ጠንሳሾችና ጎንጓኞች እነማን ነበሩ የሚለው›› ነው። ይህንን ለመመልከት ወደ ቀጣዩ ክፍል እንለፍ።

በአፍሪካ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በነበረው የባሪያ ንግድ ዙሪያ ዓለም አቀፍ ክርክር ሲካሄድ፣ በሰው ልጅ ንግድ ሀብታቸውን ያካበቱ አንዳንድ አውሮፓውያንና አሜሪካውያን ስማቸው ሲጠለሽ፣ ሐውልታቸው ሲፈርስና ስማቸው ከሕዝብ ሕንፃዎች ላይ ሲወገድ የጥቃቱ ፈጻሚዎች ነጮች ብቻ እንደሆኑ መደምደሚያ ላይ ተደርሶ ነው።

የናይጄሪያዊቷ ጋዜጠኛና ደራሲ አዳኦቢ ትሪሺያ ንዋባኒ፣ ከቅድመ አያቶቿ መካከል ከኢግቦ ጎሳ ወገን አንዱ የሆነው ንዋባኒ ኦጎጎ ኦሪአኩ በደቡብ ምሥራቅ ናይጄሪያ የትምባሆና የዘንባባ ምርቶችን ጨምሮ በርካታ ዕቃዎችን ከማከፋፈል በተጨማሪ፣ የሰው ልጆችንም መሸቀጡን ትናገራለች። ለእዚህ ሰው ባሪያ ከየጎሳው እየፈነገለ የሚያመጡ ከተፈንጋዩ ጎሳ ወገን የሆኑ የተለያዩ ወኪሎች ነበሩት። በመጨረሻም ዛሬ ናይጄሪያ እየተባለ ከሚጠራው ሥፍራ በስተደቡብ በሚገኙት በካላባርና ቦኒ ወደቦች እንዲሸጡ ያደርጋል። ከእዚህ በተጨማሪ ኢፊክና ኢጃው በሚባሉ የባህር ዳርቻዎች ከተለያዩ ጎሳዎች የተውጣጡ ሰዎችን ለሽያጭ በማመቻቸት ኮሚሽን የሚሰበስቡ የተለያዩ አፍሪካውያን ወኪል አቅራቢዎች ሲኖሩ ነጭ ባሪያ ነጋዴዎች ሽጉጥ፣ መስታወት፣ ጂንና ሌሎች ልዩ ልዩ ዕቃዎችን እንደ ክፍያ ያቀርባሉ።

የንግዱ ልውውጥ ሒደት የሚከናወነው የአውሮፓ ገዥዎች በባህር ዳርቻ ላይ በመቆየት፣ አፍሪካውያን ነጋዴዎች እንደተለመደው ቁርጭምጭሚታቸውን በሰንሰለት የታሰሩ፣ አንገታቸው ላይ ገመድ ያጠለቁ ባሪያዎችን እስከ 485 ኪሎ ሜትር (300 ማይል) በእግር አስጉዘው፣ ከአሥር እስከ አሥራ አምስት በመቶ የሚሆኑ ባሪያዎች በመንገድ ላይ ሞተው የቀራት ያመጡላቸው ነበር። በአፍሪካ ሕዝቦች ላይ የተደረገው  ይህንን መሰል የንግድ ልውውጥ እ.ኤ.አ. እስከ 1888 ድረስ ሲቀጥል ይህንን ንግድ ያቆመችው የመጨረሻዋ አገር ብራዚል ነበረች።

ሌላው ደግሞ በኢግቦ ጎሳዎች መካከል የሰው ልጅ መግዛትና መሸጥ አውሮፓውያን ከመምጣታቸው በፊት የነበረ ልምድ ሲሆን ወንጀል የሠራ፣ ዕዳ መክፈል ያልቻለ ወይም የጦርነት ምርኮኛ ባሪያ ይሆኑ ነበር። አንዳንድ ጊዜ በሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ተሰውተው ከሟች ጌቶቻቸው ጋር በሕይወታቸው ይቀበሩ የነበረ ሲሆን፣ ‹‹ባሪያ የሌለው ማንኛውም ሰው ራሱ ባሪያ ይሆናል›› የሚል አባባል በሥነ ቃላቸው ውስጥም ነበር።

‹‹ይህ የእኛ የቃል ኪዳንና የሃይማኖት መሪዎቻችን ፍርድ በመሆኑ፣ የባሪያው ንግድ መቀጠል አለበት ብለን እናስባለን፤›› የኢግቦ ንጉሥ ከተናገሩት (L’univers Illustre በ1868 ፓሪስ)፡፡

ከላይ እንዳየነው በባሪያ ንግድ ወቅት ነጮች ላይ ብቻ ይጠቆሙ የነበሩ ጣቶች እንዲታጠፉና የጥቁር ሕዝብ “እኛም ነበርንበት” በሚል ወደ ራሱ እንዲመለከት የሚያስገድድ ነው። ከዚኛው ታሪክ ተነስተን፣ ተበዳይ ከበዳዮቼ ወገን ፃድቃን አሉ ከሚለው ምልከታው በተጨማሪ፣ በዳይ ጋ ከመድረሱ በፊት “በበደሉ የእኛ ሰዎች ነበሩበት? ወይስ አልነበሩም?” ብሎ መገምገም እንደሚገባው እንገነዘባለን። 

በእኛ አገር በተበድያለሁ የማጣት መቀሳሰር ውስጥ አማራ፣ ጉራጌ፣ ኦሮሞ፣ ወዘተ ተበድያለሁ ለሚል ወቀሳው በመደበኛነት ጣት ወደ ውጭ መቀሰሩ የተለመደ ሲሆን፣ ስንበደል ከበዳዮቻችን ወገን በርካታ ሚሊዮን ንፁኃን ነበሩ፣ ከእኛም ወገን የበደሉ ጠንሳሽና ዋና ተዋናይ የነበሩ፡፡ እንዲያውም ከባዳው ይልቅ በእጅጉ የከፋ በደል ያደረሱ የራሱ ጎሳ አባላትን መፈረጅ በኢትዮጵያ የታሪክ ጸሐፍት ዘንድ የተዘነጋ ይመስላል። የውጭ ሰዎች ግን ዝም ብለው አልታዘቡትም። በኢትዮጵያ ስለነበረው የባሪያ ንግድ ጁሊያ ቦናቺ (Revisiting Slavery and the Slave Trade in Ethiopia, Center for Ethiopian Studies, University of Hamburg) በተሰኘ ትንታኔው ይህንን ይለናል።

‹‹በባሪያ ንግድ ውስጥ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ ገጽታ ከታሪክ በማጣቀስ በግልጽ መቀመጥ አለበት። ከስዋሂሊ የባህር ዳርቻ፣ ከመካከለኛው አፍሪካ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከኬፕ ቅኝ ግዛትና ከህንድ ውቅያኖስ ደሴቶች (ማዳጋስካር፣ ማስኬሬይንስ፣ ሲሼልስ) የተገኙ ባሮች መውጫ በሮች በምሥራቅ አፍሪካ የባህር ዳርቾች ነበሩ። ኢንሳይክሎፔዲያ አቲዮፒካ በኢትዮጵያ ስለነበረው የባሪያ ንግድ ሁኔታ በተለያዩ ንዑሳን ክፍሎች በመክፈል አንደኛ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን፣ ሁለተኛ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የቀይ ባህር የባሪያ ንግድ፣ ሦስተኛ የቤት ውስጥና በፍርድ ቤት ውሳኔ የሚፀና ባርነት በሚል ያስቀምጠዋል። በዚህ አስከፊናና ውስብስብ በሆነው የኢትዮጵያ የባሪያ ንግድ ተቋማት ላይ በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በአገሪቱ የነበረውን የባሪያ ንግድ ጥንታዊነት በጉልህ ያስገነዝባሉ። ፕሊኒ በአክሱምና በአዱሊስ ወደብ ወደ ውጭ ስለሚላኩ ባሪያዎችን ጠቅሷል፡፡ ፔሪፕለስ ኦቭ በኤርትራ የኤደን ባህረ ሰላጤ ወደቦች ስለነበረው ንግድ ጽፏል። በስድስተኛው መቶ ዘመን መጀመርያ ላይ ኮስማስ ኢንዲኮፕሊስተስ የተባለው ግብፃዊ ተጓዥ እንደገለጸው፣ አብዛኞቹ ባሮች ከጥቁር ዓባይ ደቡባዊ ክፍል ተነስተው ወደ ውጭ ይላኩ እንደነበር ጠቅሷል።

ሃውቃልና አል-መቅሪዚ የየመን ንጉሥ ከኢትዮጵያ የተሸጡ ባሮችን ይቀበል እንደነበር ዘግበዋል። ባሪያዎቹ ከኤደን ከሚነሱ ዋና ዋና ዕቃዎች መካከል እንደ አንዱ ይቆጠሩ ነበር። ኢትዮጵያ የዓባይን ሸለቆን ከቀይ ባህር፣ ከህንድ ውቅያኖስና ከኦቶማን የምታገናኝ የባሪያ ንግድ ማዕከል ነበረች። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ዋና ዋና የባሮች መሸጫ ጣቢያዎች መካከል መተማ በሱዳን ድንበር ላይ፣ ምፅዋ በምሥራቅ ይገኙ ነበር።

በንግዱ ሒደት ውስጥ በዋነኝነት ሙስሊም ነጋዴዎች ከጀርባው እንዳሉ ቢወሳም፣ የብሪታኒያ ዲፕሎማት ዋልተር ፕሎውደን ክርስቲያኖችም በባሪያ ንግዱ ውስጥ ይሳተፉ እንደነበር በጽሑፎቹ ያወሳል። ስለዚህ የባሪያ ንግዱ የአገሩ ዜጎች የሆኑ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች በተፎካካሪም ሆነ በጋራ ጥቅም የተሳተፉበት ሥርዓት እንደነበር ሊገነዘቡት ይገባል ይላል፡፡

‹‹ቦናቺ የውጭ ሰው ነው፣ ስለዚህ ዋሽቶናል›› ያልን እንደሆን ቀጣዩን እንመልከት። በኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ባርነትን ለመቆጣጠር ከዋሉ ከመጀመርያዎቹ የጽሑፍ ሕጎች መካከል አንዱ የሆነውና በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበሩት የኮፕቲክ ግብፃዊ ጸሐፊ አቡል ፋዳኢል ኢብን የአረብኛ ጽሑፎች የተተረጎመው ፍትሐ ነገሥት፣ ወይም የነገሥታት ሕግ በሕጋዊ መንገድ በባርነት ሊያዙ ከሚችሉት ሰዎች መካከል የጦር ምርኮኞችን፣ የማያምኑትን፣ የባሪያ ልጆችን፣ ከባሪያ ጋር አብራ የኖረች ወይም ያገባች ሴት፣ ዕዳውን ያልከፈለ፣ ልዩ ወንጀሎችን የፈጸመ ባሪያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይነግረናል። እንደ ንብረት ከመቆጠራቸው የተነሳም  ባሮች  ይሸጣሉ፣ ይከራያሉ፣ ንብረት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ከሁለት በላይ ወንድማማቾችን በአንዴ ሊሸጡ ወይም ሴት ከባሏ ተለይታ ልትሸጥ፣ ወይም ሴት ከልጇ ተለይታ ልትሸጥ ይችላል (ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው 1990 ዓ.ም.  አንቀጽ 31 ገጽ 261-262)።

በተጨማሪ ፍትሐ ነገሥቱ ባሪያዎች ነፃ የሚወጡበትን ሁኔታዎች ያስቀምጣል። ለምሳሌ ባሪያው የአንድ ቤተሰብ ሁለት ትውልዶችን ካገለገለ (የጡረታ ዓይነት)፣ የጌታው ቤተሰብ አባል ለባሪያው አባት ወይም እናት ከሆነ፣ ካህን ወይም መነኩሴ ከሆነ (ይህንን ለማግኘት ባሪያው የጌታውን ፈቃድ ማግኘት ያስገባዋል)፣ ወታደር ከሆነ፣ የጌታውን ሕይወት ካዳነ፣ ነፃ ከወጣች ባሪያ የተወለደች ልጅ፣ በጦርነት ጊዜ ተማርኮ ወደ ጌታው ከተመለሰና ባለቤቱ ሞቶ ወራሽ ካጣ ነፃ ይወጣል (ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው 1990 ዓ.ም. አንቀጽ 31 ገጽ 263)። ‹‹ይሁን እንጂ የነፃ መውጫ ሕጉ ተግባራዊ የሆነባቸው አጋጣሚዎች ውስን ነበሩ፤›› ይላል ነገሩን በጥልቅ የተመለከተው ኤፍ ኤም  ጎድቢ  (The Law of Slavery in Abyssinia,1933)፡፡

ነፃ የወጣ ባሪያ የቀድሞ ጌታውን ከረገመ፣ ከሰደበ፣ ከደበደበ፣ ልጁን ቢመታበት፣ ፍርድ ቤት ቢመሰክርበት ወደ ባርነቱ ሊመለስ ይገባዋል ይላል (ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው 1990 ዓ.ም. አንቀጽ 31 ገጽ 264)። ይህ የሆነው በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ነው ካልን ደግሞ ከ150 ዓመት ያላለፈ ሌላ ማመሳከሪያ እናቅርብ። በአገራችን ባርነት እንዲወገድ በፅኑ ደክመዋል የሚባሉት እንደ ዳግማዊ አፄ ምኒልክና ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሳይቀሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ባሪያዎች እንደነበሩዋቸው ሪቻርድ ፓንክረስት ይናገራሉ (Economic History of Ethiopia, Hail Seaside I University Press, 1968)።

በሰሜን አካባቢ ንጉሦች ነው እንዳንል ደግሞ በ1916 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ለመንግሥታቱ ማኅበር (League of Nations) አባል ለመሆን ባመለከተችበት ወቅት በእንግሊዝ መንግሥት ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦባት ነበር። የኢትዮጵያን መንግሥት የአባልነት ማመልከቻ ለመንግሥታቱ ማኅበር ለማስገባት ወደ ጀኔቫ የተላከው ቡድን መሪ የነበሩት ራስ ናደው አባ ወሎ በፈረስ ስማቸው ‹‹አባ መብረቅ››፣ እንግሊዝ ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ማኅበር አባል እንዳትሆን የተቃወመችበትን ምክንያት ለንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በላኩት የቴሌግራም መልዕክት፣ እንግሊዞች ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የዘገቡትንና በሱዳን፣ በኬንያ፣ በኤደንና በግብፅ ባሉት የቅኝ ግዛት መንግሥቱ በኩል የተሰበሰበውን ማስረጃ በማያያዝ በደቡብ ኢትዮጵያ እየተካሄደ ስለነበረው የባርያ ንግድ ሁኔታ፣ በተለይም የጂማው አባጅፋር እያካሄዱት ያለው መጠነ ሰፊ የባሪያ ንግድ ለማኅበሩ የፖለቲካ ኮሚሲዮንና ለጠቅላላ ጉባዔ በማቅረብ አባል እንዳንሆን ከፍተኛ ተቃውሞ አቅርቦብናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ዳግማዊ ምኒልክና ዳግማዊ አባ ጅፋር በጅማ አቻም የለህ ታምሩ (First Ethiopianism ድኅረ ገጽ 2010 ዓ.ም.)፡፡

የሕግ አግባብና የአስተዳደር ድጋፍ ያለው የባርነት ሥርዓት ሩቅ ሳንሄድ በአገራችን ስናይ ‹‹ያጠቃኝ ያኛው ነው፣ ያጠቃኝ ፈረንጅ ነው፣ ያጠቃኝ  አማራው ነው፣ ያጠቃኝ ትግሬው ነው…›› የምንልበት ወይም ጣት የምንቀስርቀት አጋጣሚ ዝግ ይመስላል። ወይም አሁንም ኦሮሞው አማራና ደቡቡን፣ ደቡቡ አማራና ኦሮሞውን፣ አማራው ኦሮሞውንና ደቡቡን ሸጠ ልንል እንችላለን። ሸጦም ይሆናል። ለገዥ የሚያቀርቡት ግን የየራሱ የጎሳው አባል ባሪያ ፈንጋዮች እንደነበሩ ግን አንጠራጠርም። ድንገት ከምንኖርበት ጎጆ የበለጠ የባርነት ሥፍራ፣ ከአባታችንም የበለጠ በባርነት የገዛን ላይኖር ይችላል።

በዚህ ጽሑፍ ዝግጅት ከመጀመርያ ክፍል እስከ መጨረሻ በደረስንበት የታሪኩ መደምደሚያ መነሻነት፣ ያልተገባ ድርጊት አንደኛው በሌላኛው ላይ የመፈጸሙ አዝማሚያ ከአንድ የማኅበረሰብ፣ የዘር ወይም ከሃይማኖት ተቋም ተፈጥሮአዊ ባህሪ የተቀዳ ተደርጎ የሚታይ ሳይሆን፣ ከየትኛውም የማኅበረሰብ  ክፍል ወይም የሰው ልጅ በሞላ የሚጋራው ድክመቱ መሆኑን ልብ ብለን፣ ተበዳይ አንድም ከበዳዮቼ ወገን ንፁኃን አሉ፣ ሲቀጥልም ከወገኖቼም መሀከል በዳዮቼ አሉ በሚል በሚዛን የማሰብ ግዴታ እንደሚወድቅበት እንገነዘባለን።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...