Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየኢትዮጵያንና የራስ በራስ አስተዳደር አሀዶቿን ሰላምና ልማት ዕውንና ዘላቂ የማድረግ ተልዕኮ

የኢትዮጵያንና የራስ በራስ አስተዳደር አሀዶቿን ሰላምና ልማት ዕውንና ዘላቂ የማድረግ ተልዕኮ

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ዓለም፣ በዓለም አቀፉ ሶሲዮ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት የውጦሽ ጉዞ ውስጥ መሆኗንና ዓለም አቀፋዊ ለውጥ የምትሻ መሆኗን በ19-20ኛ ክፍለ ዘመን ያስተዋለው የሶሻሊስት ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ ተሰባብሮ ቢወድቅም፣ ዓለም የተሳሰረ ዓለም አቀፋዊ ጉዞዋ አልተደናቀፈም፡፡ እንዲያውም በመረጃና በመገናኛ ቴክኖሎጂ ረገድ የማያቋርጥ አብዮትን እየተመገበ የዓለምን መስተጋብር የመንደር ያህል እየሆነ ሊመጣ ችሏል፡፡ የዓለም ጣጣና መዘዞችም ሆኑ መልካም ሥራዎች ከአንዱ ወደ ሌላው እየተሸጋገሩ፣ የእያንዳንዳችንንና የሁላችንንም ዕጣ የመወሰን ፍጥነትና ጉልበታቸውም ጨምሯል፡፡ በዚያው ልክ የሶሻሊስት ዓለም-ገብ እንቅስቃሴ ሲሰናበት ዓለማችን የአዲስ ለውጥ ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ አላጣችም፡፡ ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴን ግድ የሚለው መላ ድምሪቱን ምድረ በዳ ከመሆን የማትረፍ ትግል፣ ‹‹አረንጓዴ ዓለም አቀፋዊ የለውጥ እንቅስቃሴ››ን ፊት ለፊት አምጥቶ የሁላችንም ትርታ እንዲሆን እየጎተጎተ ነው፡፡

የዓለም የደፋ ቀና ጉዞ አካል የሆነው የኢትዮጵያ የለውጥ ልምድ፣ በ1966 ዓ.ም. አብዮት አማካይነት ተራማጅና ዓለም አቀፋዊ አመለካከት ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ቢገባም ‹‹ጠላትና ወዳጅ››፣ ‹‹ጨቋኝና ተጨቋኝ›› በሚል ቀላል አፈራረጅ ተጠላልፎ ከተሰባበረ በኋላ በስብርባሪነት የተረፉትን ብሔርተኛ ትግሎች ለቅሞና እነሱን ይዞ ለውጥ ለማምጣት ተፍጨርጭሯል፡፡ ስብርባሪ ዕይታ ያለው የብሔርተኛ እንቅስቃሴ የመንግሥት ሥልጣንን በ1983 ዓ.ም. ግንቦት ወር ይዞ የኅብረተሰባችንን ኢትዮጵያዊ (አገራዊ) አተያይ በየብሔረሰብና ጎጣ ጎጥ ውስጥ አውርዶ ከእዚህ እስከ እዚህ የእኔ በሚል ክፍፍል ውስጥ ቢበጣጥሰውም፣ አተያያችን ተበጣጥሶ አልቀረም፡፡ የዓለማችን የተሳሰረ ዕጣ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ባለው ፈርጁ፣ እንኳን የኢትዮጵያ የውስጥ አካላት የአፍሪካ ቀንድ ጎረቤታም አገሮችም ሞትና ሽረታቸው አንድ ላይ እንደሆነ እየደጋገመ (አልገባ ሲለን በእሳትና በባሩድ እየቀጣ) ሲያሳየን ኖሯል፡፡ ይህ እየጎተጎቱና እየቀጡ የማስተማር ልምድ በመላ የአፍሪካ ቀጣናዎችም የነበረ ነው፡፡ ዛሬ በአፍሪካ ቀጣናዎችና በአፍሪካ አኅጉር ደረጃ የሚታዩ አንድ ላይ ተጋግዞ የመንቀሳቀስ ጥረቶች ሁሉ የዚያ ትምህርት ውጤቶች ናቸው፡፡

እውነታ ያቀዳጀን ትምህርት ይህ ብቻ አይደለም፡፡ አገሮች በልዩ ልዩ የስብስብ መልክ መተጋገዛቸውን የተሳሰረ ዕጣቸው ግድ እንዳላቸው ሁሉ፣ እያንዳንዱ አገር የውስጥ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሰላሙ ከተዝረከረከበት ከደጅ የሚያጋጥመው አይዞህ ባይ ብቻ ሳይሆን፣ አባባሽና አድብቶ ቦጫቂም እንደሆነ ያስገነዘበ ነው፡፡ የእነ ዛየርና የደቡብ ሱዳን የቀውስ ልምድ ይህንኑ ነው የሚያስተምረው፡፡ የኢትዮጵያ ልማትና ወዳጅነት የሱዳንም ጥቅም መሆኑን በተግባር ያየችው ሱዳን፣ ኢትዮጵያ ትግራይ ላይ ጦዞ  በነበር የውስጥ ቀውሷ በተጠመደች ጊዜ፣ ዘረፋና ማቃጠል የተካሄደበት መሬት የማስፋት ዘመቻ ማካሄዷም የዚሁ ትምህርት ምስክር ነው፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ትምህርት ከዚህም የበለጠ ብርቱ ነው፡፡ ቀጣናው የቋንቋና የባህል አምሳያነትን የሚጋሩ ሕዝቦች ከአንድ በበለጡ ድንበርተኛ አገሮች ውስጥ የሚገኙበትና ድንበር ዘለል እንቅስቃሴያቸውን መቆጣጠር ከባድ የሆነበት፣ በዚያው ልክ ድህነት የተንሰራፋበት፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ቀውስ ያላባራበት፣ ሰላምና መረጋጋት በቀላሉ የሚተረተርበት፣ እንደዚያም ሆኖ ከቀይ ባህር እስከ ህንድ ውቅያኖስ ትልቅ የንግድ እንቅስቃሴ ደጃፍ እንደ መሆኑ ብዙ አፍጣጭ ያለበት (የውጭ ኃይሎች ጣቢያ ያበጁበት) ቀጣና ነው፡፡ ይህ እውነታ የቀጣናውን አገሮችን ሁለገብ ኅብረት እንደሚጠይቃቸው ሁሉ፣ ኅብረታቸውና ትግግዛቸው እንዲፀናም የእያንዳንዱ አገር ጠንካራ ሆኖ መጎልበት ወሳኝና ግድ ሆኗል፡፡ በቀላል አነጋገር በድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና በድንበር-አለፍ ሕዝቦች ከጎረቤቶቿ ጋር የተያያዘችው ኢትዮጵያ፣ ከጎረቤቶቿ የሚመጡ ቀውሶችን መመከት የምትችለው ተከባብሮ በመልማት ነው፡፡ መልማትን በተግባር ማራመድ የምትችለውም፣ የውስጥ ሰላሟንና አንድነቷን በመንከባከብ ጥንካሬ ለሌሎች ምሳሌ መሆን ከቻለች ብቻ ነው፡፡ ይህ ያልገባቸውና ቁራጭ አገር ለመሆን የሚመኙ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም ካሉ ፖለቲከኛ ነን አይበሉ፡፡

የኢትዮጵያና የራስ በራስ አስተዳደር አሀዶቿ ሰላምና ልማት የሚጨበጠው አንድ ላይ ሆኖ ጠንካራ ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን በመገንባት ውስጥ መሆኑ የማያጠያይቅ እውነታና ተግባር ከሆነ፣ ተከታዩ ጉዳይ ፌዴራላዊነቱንና የራስ በራስ አስተዳደር አሀዶችን አገነባብ አግባብቶ የማራመዱ ነገር ነው፡፡ ይህ ተግባር የሥልጣን ድርሻዎችንና መዋቅራዊ ግንኙነቶችን አጥርቶ ሥርዓቱ የሚሻቸውን ተቋማት የማደርጀት ጉዳይ ብቻ አይደለም፣ እገጭ እገው የሚፈጥሩ የአተያይ መፈናካሮችን የማራቅና የማስታረቅም ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ በፊት ባቀረብኩት ጽሑፌ ውስጥ ሕዝብ የቂምና የጥላቻ ፖለቲካን ለመሸሽ ከጎጆ ፖለቲካ ይልቅ፣ ኅብረ ብሔራዊ ፖለቲካዎችን (ፓርቲዎችን) ወደ ማማረጥ እንዲያጋድል ሐሳብ ሰንዝሬ ነበር፡፡ ይህ ጥቅል ሐሳብ ግን ካልተቃና ያሳስታል፡፡ ኅብረ ብሔራዊ ነኝ ወዳለ ሁሉ ማጋደል ጥላቻን ወደ መራቅ አያደርስም፣ የጥላቻ ችግር በሁለቱም መልኮች ውስጥ ሊገኝ ይችላል፡፡ ኅብረ ብሔራዊ ነኝ ያለ ቡድንም በአመለካከትና በጥንቅር ይዘቱ ጎጇዊ ሆኖ ሊገኝ ይችላል፡፡ ከዚህም ያለፉ የአተያይና የዓላማ መፈናገጥ ፈለጎች በሁለቱም የፖለቲካ አደረጃጀቶች ውስጥ አሉ፡፡ እነዚያን ሁሉ መሻገር የሚቻለው ኅብረ ብሔራዊ ነኝ ያሉ ቡድኖች ከብሔርተኛ ቡድኖች ሥጋቶችና ፍላጎቶች ጋር ለመነካካት ሲጥሩ፣ ብሔርተኞችም ኅብረ ብሔራዊ ነን ከሚሉት ጋር ለመነካካት ሲጥሩና በጥረታቸውም የጋራ ድልድይ ሲፈጥሩ ነው፡፡ የእዚህ ጽሑፍ ትኩረት የአተያይና የመርህ ድልድል ፈልጎ ማሳየት ነው፡፡ የድልድዩ የንጣፍ ሥራ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የጋራ መግባባት አማካይነት ተማሪዎችን ብዙ ቋንቋዎች በማስተማር መርሐ ግብር ተጀምሯልና ትንታኔዬ የሚጀምረው እሰየው በሚል አድናቆትና ምሥጋና ነው፡፡ የሁለቱን ክልሎች ፈለግ ሌሎች አካባቢዎችና ከተሞችም ይከተሉታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ከ1983 ዓ.ም. አንስቶ የብሔርተኞች ትግል በኢትዮጵያ ውስጥ አሸንፎ የመንግሥት ሥልጣን ከያዘና ብሔር/ብሔረሰብነትን የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት፣ የሕገ መንግሥትና የመንበረ መንግሥት አገነባብ ትርታው ያደረገበት ልምድ ስኬታማ ውጤት አልሰጠም፡፡ የአገረ መንግሥትና የአካባቢ (ክልላዊ) መንግሥታትን ግንባታ አመጋግቦ ለማዋጣት አልተቻለውም፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ብሔርተኞቹ ‹‹የብሔር ጭቆናን ማስወገድ… የብሔር እኩልነት…›› የሚል ጩኸትና አነብናቢነት ይኑራቸው እንጂ፣ ሁሉንም ብሔረሰቦች በእኩልነት የማየትና መብቶቻቸውን የማክበር ይዘት በአመለካከታቸውም በተግባራቸውም ውስጥ አልነበረም፡፡ ትኩረታቸው ሁሉ የራሴ የሚሉት ብሔር/ብሔረሰብ ላይ የተሳካ በመሆኑ ዕይታቸውና የፓርቲ አደረጃጀታቸው ሌላውን ያገላል፡፡ በግንባር ደረጃ ቢሰባሰቡ እንኳ አግላይነታቸው አይቀየርም፡፡ በአደረጃጀት ተዋህደናል ቢሉ እንኳ አመለካከታቸው ያልተዋሀደ፣ በየፊናቸው የእኔ ለሚሉት ብሔረሰብ በማብለጥና በመታመን ላይ የተጣበበ በመሆኑ በሽኩቻ ከመታመስ አያመልጡም፡፡ የ‹‹ደኢሕዴን›› ልምድ ሽፍንፍኑ ሲገለጥ ያሳየን ይህንን ሀቅ ነው፡፡

ችግሩ የዕይታና የፓርቲ አደረጃጀት መጎነዳደሽ ብቻ አይደለም፡፡ ሌላውን ማግለልና ‹‹የእኔ አይደለም›› ማለት በራሱ በእኩልነት የማየትንና የማስተናገድን አቅም አሳጥቶ ወደ ጨቋኝነትና ተጨቋኝነት ግንኙነት ይወስዳል፡፡ ከእዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ፣ አመለካከትና ትኩረት በየሠፈር ውስጥ መትረክረኩ፣ ኢትዮጵያዊ መሆን ደግሞ የዘፈቀደ ጉዳይ (ቢሹ የሚይዙት ባይሹ ጥለውት የሚሄዱት) ተደርጎ መታየቱ ሁለት እውነታዎችን አስቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ኢትዮጵያ የምትባል አገር አካልነታቸው ሜካኒካዊ (የብዙ ብሔረሰቦች “አገር” የሚባል በረት ውስጥ መታጎር) ዓይነት አለመሆኑን፣ በዘመናት የሕዝብ እንቅስቃሴና መዘማመት የተገነባ ከአፈርና ከዛፍ ያለፈ የሕዝብ፣ የባህሎች፣ የቋንቋዎችና የታሪክ ዝምድምዶሽ የተፈጠረበት የኅብረተሰብ አገርነት መሆኑን አልጨበጠም፡፡ ከዚህ የባሰው ስህተት ደግሞ በዛሬው የዓለም ሁኔታና በአፍሪካ ቀንድ እውነታ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ልብ ሆኖ የጠነከረ አገር የመገንባት ጉዳይ ለየትኞቹም በኢትዮጵያ ለሚገኙ ብሔረሰባት የቢሻኝ ጉዳይ ሳይሆን፣ የዕልቂት/የትርምስ እራት ሳይሆኑ ከድህነት ማምለጫቸው መሆኑ ያለ ማወላወል አለመጤኑ ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ለ27 ዓመታት ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ በመሠረተ ልማትና በኢኮኖሚ ምንም አልተሠራም ብሎ የመሸምጠጥ ነገር አይደለም፡፡ ማሳየት የተፈለገው የሕወሓት/ኢሕዴግ የብሔር ፖለቲካ ኢትዮጵያን በአስተሳሰብና በአተያይ ጎነዳድሾ፣ የማይግባቡ ሹክቻዎች በፈሉባቸው ትንንሽ ሩጫዎች እንደ ቦረቦራት ነው፡፡ ‹‹27/30 ዓመት ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ተሰበከ፣ ኢትዮጵያዊነት ተዳከመ፤›› የሚባለው በሌላ አባባል ይኸው ነው፡፡

በአጭሩ በየጎጥና በብሔረሰብ ላይ የተሳካ ጉንድሽድሽ አመለካከት ኅብረተሰቡን በእኩልነትና በመተማመን አስማምቶ ጠንካራ አገር ለመገንባት አላስቻለም፡፡ የሚያስችልም አቅም የለውም፡፡ እንኳን በአገር ደረጃ በክልሎች ደረጃም የተግባባ የኅብረተሰብና የመንግሥት ግንባታ ማካሄድ አልተቻለም፡፡ የዚህም ምክንያት ዞሮ ዞሮ አግላይና አድሎኛ አመለካከቱ ነው፡፡ ‹‹የእኔ››፣ ‹‹የአካባቢዬ ባለቤት›› ከሚላቸው ውጪ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እንደ ‹‹ዕዳ›› ነው የሚያያቸው፡፡ እነዚያን “ዕዳዎች” ለመገላገልም ሁለት መንገዶች ሲወስድ ታይቷል፡፡ አንዱ በጥላቻ ጠምዶና አስጠምዶ በማብረርም ሆነ የጥቃት ዕርምጃ በመውሰድ እንዲመናመኑ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ሻል ያለው መንገድ ደግሞ፣ በክልልም ሆነ በዞንና በወረዳ ደረጃ “ዋና” ከሆነው ብሔረሰብ ውጪ የሆኑ ወይም ዲቃላ የሆኑ “ዕዳዎችን” ቢወዱም ባይወዱም በዋናው ብሔረሰብ ባህልና ቋንቋ ማወራረድ ነው፡፡ በእዚህ ዓይነቱ አሮጌ የድፍጠጣ መንገድ ወጥ ብሔር የመገንባት ሙከራ ቅራኔዎችን፣ እንቢታና ውዝግቦችን፣ ግጭቶችን አራብቷል፡፡ በዚህ መንገድ “መጤ”ን ጨርሶ ለመገላገል ማሰብም ቅዠት ነው፡፡ በየክልሉ የግንብ አጥር ቢታጠር እንኳ፣ የብዙ ዓይነት ሰውና ባህል እንቅስቃሴ ባለበት በዛሬው ጊዜ መጤነትን መግታትና ማድረቅ አይቻለም፡፡ ስለዚህ ድፍጠጣና የኃይል ጥቃት እየፈጸሙ ማፈናቀል ቀውስን ከማባዛት በቀር ትርፍ የለውም፡፡ ከዚህ አላዋቂነትና አቃዋሽነት የፀዳ አንድም ክልል በኢትዮጵያ የለም፡፡ የሰብዓዊ መብቶችና የዜግነት መብቶች መከበር ጉዳይም ውልቅልቁ ከወጣ ከራርሟል፡፡

በየክልሎቹና በየዞኖች በተዋረድ ሲገዙ የቆዩት ብሔርተኞች፣ ባይተዋር አድርገው ‹‹ነፍጠኛ/መጤ›› የሚሏቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች አስደንብሮና አጥቅቶ በማብረር ለማመናመን፣ እንዲሁም በስልቀጣ የባለቤት ብሔር ማዳበሪያ ለማድረግ ሲሠሩ የቆዩት የነፍጠኛ ታሪክ ቅሪትንና መጤነትን በማፅዳት ወይም ወጥ ብሔሮች በመገንባት ፍላጎት ብቻ አይደለም፡፡ እንዲያውም ዋናው ፍላጎት ገዥነታቸውን እንደ ዘር ሐረግ (ዳይናስቲ) ቀጣይ አድርጎ ማስተማመን ነው፡፡ ለእነዚህ የሶሲዮ ኢኮኖሚ ሐሳብ ይዞ የመወዳደር ጎዳና በተከታታይ የመግዛት ዋስትና አይሰጥም፡፡ ዋስትና የሚሰጣቸው በብሔር ማንነት ተደራጅቶ ሌላ ‹‹ባዕድ›› እንዳይገባ እየመከቱ በብሔር ዝምድና ‹‹መመረጥ›› ነው፡፡ በእነሱ የሥልጣን ‹‹ጉልተ ርስት›› ውስጥ ያሉ ሌሎች ማኅበረሰቦችና ብሔረሰብ-ዘለሉን አማርኛን የሚናገሩ ቅይጦች ዕዳና ጠላት የሚሆኑት እዚህ ላይ ነው፡፡ በከተሞችና በአንዳንድ የገጠር ኪሶች ተከማችተው ‹‹የዜግነት እኩልነት››፣ ‹‹የዜግነት ፖለቲካ›› ‹‹ሰብዓዊ መብት›› እያሉ ‹‹ይቀባጥራሉ››፡፡ ለአካባቢው ‹‹ባለቤት›› የሚባለውን የብሔር ቡድን ትተው ‹‹ባዕድ›› ፓርቲ በመምረጥ ‹‹ሊያስጠቁ/ሊያስደፍሩ›› የሚችሉ ናቸው፡፡ መመናመን፣ መፈናቀል፣ መወገድ ወይም መሰልቀጥ ያለባቸው ለዚህ ነው፡፡ ‹‹ባለቤት›› እኛ ነን የሚሉ ቡድኖች ‹‹መጤዎች›› እነሱን ባለመምረጣቸው ይናደዳሉ፣ መደፈርና መጠቃት ይሰማቸዋል፡፡ ‹‹ባጎረስን/በተሸከምን ስለውለታችን›› እንዴት አያጎነብሱልንም ነው ነገሩ፡፡ የእኔ ናችሁ ሳይሏቸው እነሱን አግልለው ‹‹አራቋች!››፣ ‹‹የበደል ቅሪቶች!›› ብለው እየተፀየፏቸውና በተለያየ መልክ ከጥቅምና ከእኩል መስተንግዶ እየገፏቸው እንዲመርጧቸው መጠበቅ የሚገርም የፖለቲካ ደነዝነት ነው፡፡

ብሔርተኞች በአተያያቸው በአገራችን ውስጥ ዛፍ ዛፉን በማየት ላይ ያተኩራሉ በሚል ምሥል ሊገለጹ እንደሚችሉ ሁሉ፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮሩ ፖለቲከኞች ደግሞ ዛፉን ትተው፣ የዛፎቹ ኅብር በሠራው አጠቃላይ የደኅንነት እውነታ ላይ ያተኩራሉ ቢባል ስህተት አይደለም፡፡ ብዙዎቹ “አገራዊ/ኅብረ ብሔራዊ” ነን የሚሉ ፓርቲዎች ጥንቅራቸውን እንተወውና ደኑን ብቻ ማየት የሚሹ ናቸው፡፡ ብዙ ንቃታቸውና ንግግራቸው መፈክር መሳይ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በአባቶቻችን ተጋድሎና ደም የተገነባች፣ አባቶቻችን አጥንትና ደማቸውን ከስክሰው ያወረሱን ነች፡፡ ልንከባከባት፣ ልንጠብቃትና ለመጪው ትውልድ ልናስረክባት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደ ሃይማኖታችን ልንወዳት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ትናንትም ነበረች፣ ዛሬም አለች፣ ነገም ትኖራለች፡፡ መሪዎች፣ ፓርቲዎች፣ መንግሥታት ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ግን አታልፍም፡፡ ኢትዮጵያ ከሁላችን በላይ ነች! ኢትዮጵያ እናት ነች! አባቶቻችን ተጋድለው እንዳቆዩዋት እኛም እንሞትላታለን…›› ከማለት ያለፈና የጠለቀ ነገር ሲናገሩ ዓይታዩም፡፡ ይህንን በእዚህ ደረጃ እየተባለ ያለውን ለማለት ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች አስፈላጊ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ይህንን ሁሉ ተራው ሰው ዘንድ (ከትንሽ እስከ ትልቅ ድረስ) እናገኘዋለን፡፡ በየሰው ዘንድ የምናገኘው ይህ የአገር ፍቅር ስሜት የይስሙላም ሳይሆን እውነተኛ ነው፡፡ አገር እንደ ዋዛ የማይገኝና የማይገነባ፣ አገሬ ወገኔ ቤቴ ብሎ የመኖር ጉዳይ ለሁላችንም የ‹ደመነፍስ› ንቃት ያህል ስለሆነ ነው፡፡ እርስ በርስ ዘመዳም መሆናችን፣ አንዳችን ለአንዳችን አስፈላጊ መሆናችን ለሁሉም ተሬ ይገባዋል፡፡ ‹‹ብሔረሰብ ከብሔረሰብ ጋር (ሶማሊ ከአማራ ጋር፣ ኦሮሞ ከትግሬ ጋር፣ አኙዋኩ ከአፋር ጋር፣ ወዘተ.) በምን ይዛመዳል? ለምን አንዳቸው ለሌላቸው ያስፈልጋሉ? አንድ ሁለት ብለህ ዘርዝርልኝ…›› ቢባል ተሬው ሰው ሊቸግረው ይችላል፡፡ ቢቸግረውም ግን ስህተት እንዳልሆነ ይታወቀዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተመራማሪዎችና ተንታኞች የሚያስፈልጉት በሌጣ ምልከታ የማይጤኑ ነገሮችን ለማሳየትም ነው፡፡

ሰፊ አገር፣ ትልቅ ሥልጣኔ፣ ዓይነተ ብዙ ሕዝብ በሆንን ቁጥር ሀብታምነታችን ይጨምራል፡፡ አንዳችን ጋ የሌለ ነገር ሌላችን ጋ ይገኛል፡፡ የሀብት ብዝኃነት የሚባለው በጥሬው ይህ ነው፡፡ የሀብት ብዝኃነት ፈርጁ እያሌ ነው፡፡ የአየር ንብረት ዝንጉርጉነት ሀብት ነው፡፡ የአየር ንብረት ዝንጉርጉርነት በብዝኃ ሕይወትና በግብርና የሚያስገኘው ሀብተ ብዙነት በራሱ ግዙፍ ነው፡፡ የከርሰ ምድር ጥንቅር ዝንጉርጉርነት በራሱ ሀብት ነው፡፡ ዓይነተ ብዙ ባህል (ወግ ልማድ፣ የቃል ቅርስ፣ የመድኃኒትና የሕክምና ቅርስ፣ የሙዚቃና የሥነ ጥበብ ዝንጉርጉር ሀብት) እርስ በርስ መጠቃቀሚያ ነው፡፡ የሕዝብ ጥንቅርና የቁጥር ብዛታችን በዕውቀት፣ በፈጠራ፣ በሐሳብና በዘዴ አመንጭነት መስተጋብር አንዳችን ለሌሎቻችን የምንኳኳንበት ብዝኃ ሀብት ነው፡፡ የአስተዳደጋችን ዝንጉርጉርነት ከአየር ንብረትና ከኑሮ ባህል ጋር ሁሉ ተያይዞ ለልዩ ልዩ ጥንካሬዎችና ዝንባሌዎች የሚሰጠን አቅም ሁሉ አንዳችን ለሌላችን የምንተርፍበት ነው፡፡ ብዛታችን ከአገር ልጅነት “ደመ ነፍሳችን” ጋር የሁላችን ደኅንነት ዋስትናም ነው፡፡

የአገር ልጅነት ‹‹ደመ ነፍስ›› እያልሁ የምገልጸው በግብታዊነት የምናውቀውን/የሚታወቀንን፣ ግን አትቱ ስንባል ልናትተው የሚቸግረንን የጋራ ዝምድናችንን ለመጠቆም ነው፡፡ ይህንን ዝምድና ‹‹ኢትዮጵያን አባቶቻችንና እናቶቻችን አወረሱን›› የሚል አባባል አይገልጸውም፡፡ የምንረግጠው፣ የምናርሰውና የምናደንቀው ምድራችን ራሱ የዘመናት ታሪካችን ነው፡፡ ታሪካችንን የያዘው ከርሰ ምድር የሚገኘው በአፋር፣ በትግራይ፣ በኦሞ፣ በሐረር ወይም በተመረጡ የኦሮሚያና የደቡብ ሥፍራዎች ውስጥ ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉም ከርሰ ምድራችን የስደት፣ የጦርነትና የቅልቅል ታሪካችንን ሁሉ ንጣፍ በንጣፍ ይዟል፡፡ እኛ ራሳችን የዘመናት መስተጋብሮች፣ (ፍልሰት፣ ጦርነት፣ መፈናቀል፣ መቀላቀል፣ ወዘተ.) የቀመሙት የሕዝብ መለዋወስ ሥሪት (የታሪክ ሰነድ) ነን፣ ያ ሁሉ ታሪክ እኛ ውስጥ አለ፡፡ የእዚያ ሁሉ ቅርስ ቅንብር አንዱ በአንዱ ላይ እየተገነባ በእኛ ውስጥ አለ፡፡ ማለትም የዘመናት የኢትዮጵያ ግንባታ መልክዓ ምድሩ፣ የሚዳሰስና የማይዳሰስ ቅርሳ ቅርስና ባህሉ ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ እኛ  በሕይወት ያለነው ሰዎችም ላይ ታዝሎ አለ፡፡ መቶ ሚሊዮን ብለን የምንቆጥረው የሰው ብዛት ራሱ የኢትዮጵያ መገለጫ ነው፡፡ ይህንን በሁለት ፈርጅ ላስቀምጠው፡፡ ዛሬ ‹‹የተለያየ ባህልና ቋንቋ ያለን፣ ብሔረሰባዊ ጎጣዊ ማንነት ያለን›› እያልን ባይ እንሁን እንጂ፣ በታሪክ ውስጥ በአራቱም ማዕዘን እየተፋሰስን እርስ  በርስ ከመቧካትም በላይ፣ ከሌላው አፍሪካና ከዓረብ/እስያ ጋር ሁሉ ተቧክተናል፡፡ የእዚያ ሁሉ ቡኮ ዝርዝር ታሪክና ቅንብር በያንዳንዳችን ዘረመል ውስጥ ተቀናብሮ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ የቀለም ድምቀትና መፍዘዝ፣ የፀጉር ዞማነትና መንቆርጨጭ፣ የአፍንጫ መሰልከክና መደፍጠጥ፣ የከንፈር መሳሳትና መወፈር ሁሉም ብሔረሰቦች ውስጥ መገኘት የመላላሳችን የፊት ለፊት ማስረጃም ነው፡፡

በሌላ በኩል ልዩ ልዩ ቋንቋ፣ ባህልና ሥነ ልቡና፣ ልዩ ልዩ ሙዚቃ፣ ውዝዋዜና ዘፈን ያለን የምንመስለውን ያህል፣ ዘመዳምነታችንን ከዝንጉርጉርነት ጋር ተፋቅረው የሚያሳዩ አሻራዎችም አብረውን አሉ፡፡ ሴም ቋንቋዎች ውስጥ የኩሽና የኦሞ ቋንቋዎች ባህሪ እናገኛለን፣ ኩሽ ቋንቋዎች ውስጥ እንደዚያው፡፡ “በዓይነተኛ” ባህሎቻችን ውስጥ አያሌ የጋራ ባህሎቻችንን እናገኛለን፡፡ የገዳ ልዩ ልዩ ፈርጆች ከኦሮሞ ውጪ በሌሎች ማኅበረሰቦች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ውዝዋዜያችን በአያሌው የረገጣ፣ የትከሻና የአንገት ጨዋታ የደራበት ሊሆን የቻለው በአጋጣሚ አይደለም፡፡ በማኅበረሰባዊ-ባህላዊ ጥንቅር መቧካታችንን ለማጤን፣ የእኔን ቃል ልመነው አልመነው ብሎ ከህሊና መሟገት አያሻም፡፡ እነ ራያ፣ ወልቃይት፣ ሰላሌና የመሳሰሉ የማኅበረሰቦች መቀላቀያዎችን ማስተዋል ነው፡፡ በእነ ራያ ውስጥ የነባር ነዋሪዎችን ከኦሮሞ፣ ከትግሬ፣ ከአፋር ከአማራ ጋር መላላስን ዓይተን፣ የእዚህ ዓይነት አያሌ ዲቃላ ሰነዶች በመላላስ ሒደት እየጠፉ ወጥ የሆኑበትን ሒደት ደግሞ በረዥም የታሪክ አዝግሞት ውስጥ መገመት ነው፡፡

የመላላሳችን ጥልቀት በሥነ ልቦና ደረጃ (በዓይን አፋርነት፣ በይሉኝታ፣ በሚስጥራዊነት፣ ወዘተ.) ኢትዮጵያውያን እንዲህ ናቸው ብሎ በአገር ደረጃም ለመናገር ያስችላል፡፡ ይህንን ለመረዳት እኛን በደንብ ያስተዋሉ የውጭ ዜጎችን ብንጠይቅ፣ እኛ ስለራሳችን ከምንናገረው በላይ ስለማንነታችንና ስለፀባያችን ይነግሩናል፡፡ እኛ ከተለያየ አካባቢ ተውጣጥተን ለሆነ ጊዜ የተለየ ባህልና ሰዎች ባሉበት ባዕድ አገር ውስጥ ብንቀመጥም፣ ምን ያህል ተመሳሳይ ናፍቆትና አምሮት እንዳለን ማጤን እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያችን ኢትዮጵያዊነት ስንል ማየት ያለብን ወደኋላ ሳይሆን ራሳችንን ነው፡፡ ስለኢትዮጵያ ማንበብ ስንፈልግም ማሰብ ያለብን ወደ ቤተ መጻሕፍት መሄድን ብቻ አይደለም፡፡ ጽሑፍ/መዛግብቱ ኑሯችን ውስጥ አለ፡፡ ትናንትናና ዛሬም የነገ ተስፋም በእኛ ውስጥ አለ፡፡ መደናበሩንም፣ የብሶትና የበቀል ቃሩንም፣ ደጉንም ክፉውንም ልምድ የጎተትነው፣ ያቀመስነውና የቀመስነው እኛው ነን፡፡ በዛሬው እኛነታችን ውስጥ የ1960ዎቹ ትውልድ፣ የእነ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ የእነ ምኒልክም ሆነ ከዚያ በፊት የነበሩ ባለታሪኮችና ትውልዶች ደግና ክፉ ልምድ ሁሉ አለ፡፡ የዛሬ ነባራዊና ህሊናዊ ግንኙነታችንና ልምዳችንም በእኛ ውስጥ አሉ፡፡ ከትናንትናና ከዛሬ፣ ጋር አብሮ የነገ ዕድልና ተስፋም በእኛ ውስጥ አለ፡፡

በእኛ ውስጥ ያለውን ትናንት፣ ዛሬና ነገን አቀናብረን ከትናንትና በተሻለ አስተዋይነት ኑሯችንን ማቃናትና ወደፊት ማስኬድ የእኛ እንጂ የማንም ኃላፊነት አይደለም፡፡ የኤርትራ ታጋዮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር 30 ዓመት ተዋግተው ለተከናወነው መለያየት፣ ከዚያም በኋላ ጦርነትን ለወለደ አኗኗራቸው፣ ያንን ተከትሎ ለገቡበት በኩርፊያና በመተነኳኮል ራስን የማሰቃየት ኑሮ፣ ዛሬም ከጥፋት ቁርጠኛ ትምህርት መውሰድ ለተሳነው የሽኩርምሚት ወዳጅነታቸው ምኒልክንና አፄ ኃይለ ሥላሴን ጥቅል ተጠያቂ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከመሀል እስከ ዳር ድረስ ለተከሰቱት የናጠጡ ቀውሶችና ከ1960ዎቹ ጀምሮ ‹‹ነፍጠኛ ትምክህተኛ/ጠባብ›› እየተባባልን ቁርሾ ከምረን ዛሬ ለደረስንበት በቀለኛ ዕብደት ጣታችን ወደ ራሳችን እንጂ፣ ወደ እነ ምኒልክ ሊያመለክት አይችልም፡፡ ዛሬ ለተፈጸመው ጭካኔ፣ ለፈሰሰው ደምና እንባ ሁሉ ሳፊ ተጠያቂዎቹ እኛው ነን፡፡ በፍዝነትም ሆነ በንቁነት፣ ትናንትናችንን ከዛሬ ጋር ማግባባት የተሳነን እኛው ነን፡፡ በእኛ ውስጥ ካለው ደጉንም ክፉውንም ልምድ የጎተትነው ቁርሾና ብሶቱን ወደ በቀል ያጦዝነው፣ ሕዝባችንን በጥላቻና በነውረኛ ጭካኔ የገረፍነው እኛው ነን፡፡ የዛሬ ኢትዮጵያም እኛው ነን (ገራፊም፣ ተገራፊም፣ በሕዝብ ታጋሽነት ላይ የቂምና የበቀል ዳንኪራ የጨፈርነውም፣ ጭንቅላት አሸዋ ውስጥ የቀበረነውም) ሁሉ በአንድ ላይ፡፡ ከዚህች ከአሁኗ አሳረኛ ኢትዮጵያ የተሻለች ኢትዮጵያ የምትመጣውም በእኛው ልብ መግዛት፣ መታረምና ተባብሮ መሥራት ነው፡፡

የእዚህ ዓይነት ዕይታ ውስጥ ስንገባ ከእኔ ብሔር ውጪ የሆነ ማኅበረሰብ ‹‹ባይተዋር›› የሚል፣ ከ‹‹ደኑ›› ውስጥ የየራሱን ‹‹ዛፍ›› ብቻ የሚያስተውል ዕይታ ያለበትን ጉድለት እናስተውላለን፡፡ የያንዳንዱን “ዛፍ” ጉዳትና ምቾትን ዘልቆ ለማየት የማይጥረው የ‹‹ደኑ›› ጣሪያ ላይ ብቻ የሚያተኩረውም አተያይ ያለበትን ግልብነት ያጤናል፡፡ ደኑን ከእነ ዓይነተኛ ዛፎቹ የሚያስተውለውንና የሚንከባከበውን ዕይታ ጠጋ ጠጋ የምንለው፣ ለፖለቲካ ጥበበኛነት ወይም በታክቲክነት ይበጀናል በሚል ጥቅመኝነት አይደለም፡፡ ከላይ ለማሳየት እንደ ተሞከረው አገራዊ እኔነታችን ሁሉንም ብሔረሰቦች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎችና ትውልዶች (ያለፉና ያሉትን) ሁሉ ያካተተ (ኢትዮጵያዊነታችን ከደንነትም ከዓይነተኛ ዛፍነትም የተሠራ) ስለሆነ ነው፡፡ እዚህ አተያይ ውስጥ የገባ ሰው መንግሥት ፖሊሲ እስኪያወጣ ድረስ ሳይጠብቅ በማኅበራዊ ተራክቦው ውስጥ የሚያገኛቸውን ባህሎች የእኔ ብሎ ለመተዋወቅ አይሰንፍም፡፡ አገርኛ ቋንቋዎችን በማኅበራዊ መስተጋብር ለመልመድና ለመጠቀምም አይሰንፍም፡፡ ፖለቲከኛም ይህ አተያይ የጠለቀው ከሆነ አተያዩን ከማናኘት ጋር የብዙ ቋንቋ ተናጋሪነት፣ የብዙ አገራዊ ሙዚቃና ውዝዋዜ ከዋኝነት፣ የብዙ አመጋገብ ተቋዳሽነት፣ ወዘተ. ሀብታም የሆነ ሰብዕና እንዲበራከት ይሠራል፡፡ ዛሬ በዋናነት የጎደለን ይህ አተያይ ነው፡፡ ብሔርተኞችና በድፍኑ ‹‹ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ›› የሚሉ ወገኖቻችን ያለባቸው ውሱንነትና የእርስ በርስ አለመተማን የሚቃለለውም በእዚህ አቅጣጫ ነው፡፡ በአግባቡ ኅብረ ብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅት ለመሆን መብቃትም፣ ‹‹አገራዊ/ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ ነኝ›› ከማለትና ከብዙ ብሔረሰቦች የተገኙ በርካታ አባላት ከማካተት ባሻገር፣ በብሔር ፖለቲካና በአፍቃሪ ኢትዮጵያ ፖለቲካ መሀል ያለውን መንፈራከክና የትኩረት ግጭት የሚፈታ (ሁሉንም ማኅበረሰቦች አጣጥሞ የሚያስተማምን መፍትሔ) ለማምጣት መቻል ነው፡፡

ከእዚህ ግብ አኳያ፣ ‹‹ኢትዮጵያ እኛ የተለየ ህልውና የላትም! የኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቡናዊና ትውልዳዊ  ታሪክ ሁሉ በዛሬዎቹ ትውልዶች ውስጥ ታዝሎ ይገኛል! ኢትዮጵያ እኛ ነን! ሁሉም የአገር ልጅ ለእያንዳንዳችን ሥጋ ዘመዳችን ነው! ሁሉም የኢትዮጵያ ቋንቋና ባህል የእያንዳንዳችን ማንነትና ሀብት ነው! በተግባር ከራሴ ጋር ላዋህደው የምችለውን ሁሉ ቀስሜ እዋብበታለሁ!›› የሚለው አመለካት ምን ያህል መፍትሔ እንደሚሆን ለመረዳት አይከብድም፡፡

ባይከብድም በደንብ እንዲሰርፀን የብሔርተኞቹን ልምድና ‹‹በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሁሉም ቋንቋና የሁሉም ማኅበረሰብ የራስ በራስ አስተዳደር ይከበር ከተባለ፣ ያለ ልዩነት ይከበር!›› የሚል መከራከሪያ ይዞ ፈራ ተባ የሚል የፖለቲካ ፍላጎትን በአጭሩ ቁልጭ አድርጌ ላስቀምጥ፡፡ ይህ የፖለቲካ ፍላጎት ከአናት ጠቆም እንዳደረግኩት መንደርደሪያው ‹‹መብቱ ለሁሉም ይሥራ›› ባይ ነው፡፡ ትልቅ ብሔረሰብ ወይም ለአካባቢው ‹‹ባለቤት›› የተባለ ብሔረሰብ ማንነቱንና ገዥነቱን በሌላው ላይ አይጫን፣ ትልቅ ብሔረሰብ ባለበት ክልል ውስጥ ያሉ ንዑስ ብሔረሰቦች (ማኅበረሰቦች) በራሳቸው ቋንቋ ራሳቸውን ያስተዳድሩ፣ ንዑስ ማኅበረሰብ ‹‹ባለቤት ነው›› በተባለበት ሥፍራ ያሉ በቁጥር የሚበልጡ የአካባቢው ነዋሪዎች በሚሹት ቋንቋ መተዳደር መቻል ይኖርባቸዋል (ለነባሩ ንዑስ ሕዝብ ታሪካዊ አስተዋጽኦ ልዩ ዕውቅናና አክብሮት ከሚሰጥ ውክልና ጋር) ይላል፡፡ ይህንኑ የመብት ማዕዘን ተጠልሎም፣ በቅይጥነት የተሞሉ ከተሞችም (በየትም ክልል ይገኙ) በመረጡት ከንቲባና የሥራ ቋንቋ እንዲተዳደሩ ይፈልጋል፡፡ ይህ ፍላጎት ላዩ ሲታይ የፍትሕ ጥያቄን ‹‹ያነገበ›› ይመስላል፡፡ የፍትሕ ፍሬያማነት የሚለካው በሎጂክ ትባቱ ሳይሆን በተጨባጭ ሁኔታዎች ላይ እየተጠበበ በተግባር በሚያስገኘው የሚጎለምስ የጋራ መተሳሰብና መልካም ኑሮ ነው፡፡

የጠቀስነው ፍላጎት ራቁቱን ተግባራዊ ሊደረግ ቢሞከር፣ መድረሻው ለብሔርተኛ ፖለቲከኞች ‹‹ነፍጠኞች/መጤዎች መሬታችንን ተቆጣጠሩት! በገዛ መሬታችን ውስጥ ማንነታችን ከመጤዎች በታች ዋለ!!›› የሚል አጀንዳ ሰጥቶ ያለፍንበትን ዓይነት ደም አፋሳሽ በቀል የሚጠራ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ቀውስ እየጠሩ ለኢትዮጵያ አንድነት አሳቢ ነኝ ባይነት ራስን በራስ መቃረን ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሁሉም በየከተማና በየገጠር ጎሬው በመረጠው ቋንቋና የባህል ዓውድ ውስጥ ተወሽቄ እኖራለሁ ባይነትን ከነፃነት ቢቆጥረው፣ ከጋራ ገጽታው ጋር ተጋጭቶ መናቆርን ማሸነፍ አይችልምና ‹‹ነፃነቱ›› ነፃነት አይደለም፡፡ አልፎ ተርፎም ዘመኑ በዓለምና በአኅጉርም በክፍለ አኅጉርም ደረጃ፣ በራሷ በኢትዮጵያም ውስጥ መረጋጋት፣ የሥራ ዕድል ዕድገት ወዳለበት አካባቢ ሰዎች የሚፈሱበት ነው፡፡ ይህ የሰዎች እንቅስቃሴ በምንም የሚታገድ አይመስልም፡፡ ከሰዎች ጎርፍ ጋር አብሮ የባህሎችና የቋንቋዎች መሠረጫጨትና መለዋወስም መሰስ ማለቱ አይቀርም፡፡ በሌላ አነጋገር የምንገኘው በብዝኃነት ዘመን ውስጥ ነውና በየጎጆዬ ሆኜ ራሴን አስተዳድራለሁ ባይነት እንደነበረ የሚቀጥል አይደለም፡፡ በዚያው ልክ ወጥ የአካባቢ ብሔርነትን በልማት መዶሻና ፍም ሰዎችን ከሰዎች እየቀላቀልኩ አንፃለሁ የሚል ፍላጎትም፣ በውጥንቅጥ ባህሎችና ቋንቋዎች መጋማሸር እየተቀደመ ፈተና ማየቱ አይቀርም፡፡

ለእዚህ ሁሉ ፈተና “የኢትዮጵያ የሆነ ሁሉ እኔነቴና የእኔ ማለት ነው” የሚል አመለካከት ምን ያህል መፍተሔ እንደሚሆን አስቡት፡፡ ያለው የክልል አወቃቀር እንዳለ ቢቀጥል እንኳ የክልሉን የሥራ ቋንቋ ከሌሎች የተጎራባች ማኅበረሰቦች ቋንቋዎች ጋር የእኔ ብሎ በኑሮና በትምህርት ቤት ለመማርና በተግባር መግባቢያ ለማድረግ የፈቀደ ልቦና፣ የማንነት መጥፋት ሥጋትን ሁሉ እንደሚያሟሟ የተማመነ ሰላማዊ ግንኙነት ለማዳበር መሠረት እንደሚሆን፣ እናም ከጥላቻና ከበቀል ተጠቂነት ሁላችንንም ነፃ የሚያወጣ ጎዳና እንደሆነ መገንዘብ አይከብድም፡፡ ንዑስ ማኅበረሰቦች የንዑስ አካባቢያቸውንም ሆነ የሰፊውን አካቢያቸውንና የአገሪቱን የፌዴራል ቋንቋዎች የአፍ መፍቻ ያህል ቀስሞ ቋንቋዎቼ ለማለት አይቸገሩም፣ ከተሞችም እንደዚያው፡፡ ማለትም ፌዴራላዊት ኢትዮጵያ የኅብረ ብሔራዊነት መናኸሪያ፣ የአካባቢ አስተዳደሮችም (ከእነ ኅብረተሰባቸው) የኅብረ ብሔራዊነት መፍኪያ ሆኑ ማለት ነው፡፡ ኅብረ ብሔራዊነት (ልሳኑ ብዙነት፣ ባህለ ብዙነት) የፓርቲና የመንግሥት ፖሊሲ ጉዳይ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦችና ዜጎች ገጽታ ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ ሆነ ማለት የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት፣ የማንነቶች መከባበርና እኩልነት ጠባቂ የማይሻ፣ ተጣሰ የሚል ከሳሽና ተከሳሽ የማይኖርበት የአገር ልጆች ጌጥና ሀብት ሆነ ማለት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...